እንደ አለመታደል ሆኖ የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ለሁለት ዓመታት ከተከረመ በኋላ የሰላም መንገድ ተጀምሯል፡፡ በአገር በቀል ሽምግልና ማለቅ የነበረበት ከአገር ውጪ አስጉዞ፣ በባዕዳን ሸምጋይነት የሰላም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ባዕዳኑ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምሥጋና ከማቅረብ ጎን ለጎን፣ የሰላም ስምምነቱ አስተማማኝ እንዲሆን ሁሉም ወገኖች ለገቡት ቃል ታማኝ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ወደ ጦርነት ያስገቡ አይረቤ ትርክቶችና ዕሳቤዎች ቆመው፣ ከአስከፊው ጦርነት ውስጥ በፍጥነት ለመውጣት የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ይተኮር፡፡ ጦርነት ይሰለቻል፣ ያስመርራል፡፡ ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ መሆን የሚችለው የጦረኝነት አባዜ እንዲወገድ የጋራ ጥረት ሲደረግ ነው፡፡ ጦርነት በየአሥርና በየሃያ ዓመት የሚጎበኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተንፈስ ይበል፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ስምምነት ላይ ሲደረስ የተለመደው ሸፍጥና ሴራ ውስጥ መግባት አስነዋሪ ነው፡፡ ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት እንደማይፀና በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ሰላም በመስፈኑ ድሉ የአገርና የሕዝብ ነው ብሎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ሰላምን ለማደፍረስ እንቅልፍ አጥቶ ማደርና በሕዝብ ደም መነገድ መቆም አለበት፡፡
በደቡብ አፍሪካ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት ልዑካን መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት፣ በኬንያ የሁለቱ አካላት ወታደራዊ ኃላፊዎች የትጥቅ ማስፈታቱንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከስምምነት ደርሰው ፊርማቸውን ማኖራቸው ይታወሳል፡፡ ስምምነቱ ከተፈረመና ጋዜጣዊ መግለጫ ከተሰጠ በኋላ፣ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ዓይነት ባህሪዎች እየተንፀባረቁ ነው፡፡ የሰላም ንግግሩ ተካሂዶ ችግሮች እንዲፈቱ የሚያስችል ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ፣ ስምምነቱን ሊያደፈርሱ የሚችሉ አላስፈላጊ ድምፆች ሲሰሙ ሰላም ፈላጊዎች በጋራ መቃወም አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሰላም ሰፍኖ ያ ሁሉ መከራና ሰቆቃ ሊቆም ሲገባ፣ በሕዝብ ስም እየቆመሩ ሰላም ማደፍረስ መፈቀድ የለበትም፡፡ የሰላም ስምምነቱን ከአሸናፊነትና ከተሸናፊነት ጋር ብቻ በማያያዝ የሕዝብን ተስፋ ማጨፍገግ ተገቢ አይደለም፡፡ ሰላም በመስፈኑ የሚከፋቸው ከጦርነቱ የሚያተርፉ የግጭት ነጋዴዎች ብቻ ናቸው፡፡ እንጀራቸውን ከጦርነቱ መቀጠል ጋር ያቆራኙ ወገኖች በሕዝብ ሥቃይና ደም ሊቀልዱ አይገባም፡፡ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የተገባው ቃል ይከበር፡፡
ኢትዮጵያዊያን ከአገር መሪ ጀምሮ እስከ እያንዳንዱ ዜጋ ድረስ ከአገር በፊት የሚቀድም ምንም ነገር እንደሌለ ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የለባቸውም፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች መኖራቸው ጤናማ ነው፡፡ ልዩነቶች ግን በሠለጠነ መንገድ መስተናገድ አለባቸው፡፡ ልዩነቶችን ተቀብሎ በሰጥቶ መቀበል መርህ ለብሔራዊ የጋራ ጉዳዮች በአንድነት መሠለፍ ብርቅ በሆነበት አገር ውስጥ፣ የውይይትና የድርድር ባህል እንዲያብብ ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ችግር ሲያጋጥም ቀውስ በመፍጠር የአገር ህልውናን መገዳደር ድረስ በመሄድ ለታሪካዊ ጠላቶች ክፍተት የሚፈጠረው፣ ይህ ዓይነቱ ባህል አሁንም ድረስ እንግዳ በመሆኑ ነው፡፡ እርስ በርስ በፖለቲካ ልዩነት ጦር በመማዘዝ መገዳደል፣ በቂም በቀል የታጨቀ የጥላቻ ውርስ ይዞ ዓይንህን ለአፈር መባባልና ከዚያ አሳዛኝ አዙሪት ውስጥ ለመውጣት የሚያስችል መፍትሔ በጋራ አለመፈለግ ሰላም ከማደፍረስ የዘለለ ውጤት የለውም፡፡ አሳዛኙን የታሪክ ምዕራፍ በጋራ ከመዝጋት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡
ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ ተረጂነት፣ ኋላቀርነት፣ ማይምነትና የመሳሰሉት የዘመናት ልክፍቶች አሁንም የአገር መጠሪያና መዋረጃ ሆነው ሳለ፣ ነጋ ጠባ የማይረቡ አጀንዳዎች እየፈለጉ መነታረክና መታኮስ ከኪሳራ በስተቀር ትርፍ አላስገኘም፡፡ ኢትዮጵያ የነፃነትና የፍትሕ አገር መሆን የምትችለው፣ መጀመርያ ለዘመናት ከተዘፈቀችበት የውርደት አረንቋ ውስጥ ስትወጣ ነው፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት የምትገመት ትልቅ አገር ውስጥ፣ ኢኮኖሚው በፍጥነት አገግሞ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ መፍጠር ካልተቻለ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ሰላምና መረጋጋት በአስቸኳይ ሰፍኖ ኢኮኖሚው ካለበት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ሥራ አጥ በበዛበት አገር ውስጥ ሥርዓተ አልበኝነት እንጂ፣ የሕግ የበላይነት ሊሰፍን አይችልም፡፡ በተለይ የሰላም ስምምነቱን ፈተና ውስጥ የሚከቱ አይረቤ አጀንዳዎችን መፈብረክ የገዛ ሕዝብ ጠላት መሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከፊቷ በርካታ ጉዳዮች የሚጠብቋት አገር መሆኗ እየታወቀ፣ በየሥርቻው በሚፈበረኩ ግጭቶች ስትታመስ የሚጎዳው በስሙ የሚነገድበት ሕዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትገነባ የሚመኝ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ የግልና የቡድን ጥቅም ከአገር በላይ እንዳይሆን መታገል አለበት፡፡
በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምዷት አጀንዳዎች ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እርስ በርስ መጋጨት፣ መሰዳደብ፣ ቂም መያያዝ፣ ለግድያ መፈላለግና አፍራሽ ጉዳዮች ይብቃቸው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች የታቀፈች አገር ናት፡፡ ችግሮቿን በማራገፍ የተሻለች አገር ማድረግ ሲገባ፣ በማያስፈልጉ ጥቃቅን ጉዳዮች ሳይቀር መተናነቅ ፋይዳ የለውም፡፡ እስካሁን የባከኑ በርካታ ዓመታት ያተረፉት ድህነትን፣ ኋላቀርነትንና ተመፅዋችነትን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አንገት የሚያስደፋ ውርደት ውስጥ ሆኖ ይዋጣልን እያሉ መፎከር አጉል ጀብደኝነት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አጉል ባህሪ ያስንቃል እንጂ አያኮራም፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ሳይቀር በጣም አስከፊ የሚባል የድህነት አረንቋ ውስጥ የሚኖር ሕዝብን እርስ በርሱ ማጋጨት፣ ደም ማፋሰስና በገዛ አገሩ አፈናቅሎ ሜዳ ላይ መጣል አስነዋሪ ነው፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ገዥ መሆን የሚችለው ፖለቲካ በጥበብ ሲመራ ብቻ ነው፡፡ በጥበብ የሚመራ ፖለቲካ ሁሌም ታሳቢ የሚያደርገው በሕዝብ ድምፅ ብቻ የሚገኝን ሥልጣን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በነፃነትና በእኩልነት የሚኖርበት ሥርዓት እንዲፈጠር ሰላማዊ ምክክር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ንትርክም ሆነ ትንቅንቅ አምባገነንነትን ለማስፈን ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ ቢስ ነው፡፡
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚስተዋለው አደገኛ የትጥቅ እንቅስቃሴ እንደ ዋዛ መታየት የለበትም፡፡ በተለይ ኦነግ ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በንፁኃን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የጅምላ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ዘረፋና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡ ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውሮ መሥራት፣ መነገድ፣ መኖር፣ ንብረት ማፍራትና ሌሎች እንቅስቃሴዎች በመገታታቸው ምክንያት ለሥጋት መንሰራፋት ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ተገቢ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት ማድረግ ነው፡፡ ጥያቄ አለኝ የሚለው አካልም ራሱን ለሰላም ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡ ሰላምን ረግጦ ዓላማን በጉልበት ለማስፈጸም የሚፈልግ ካለ ደግሞ ሕጋዊ ዕርምጃ የግድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ዜጎች፣ የእምነት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ሰላም ለማስፈን ይነሱ፡፡ ኃላፊነታቸውንም በሚገባ ለመወጣት ይችሉ ዘንድ ቃል ይግቡ፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ምድር ዘላቂ ሰላም መስፈን አለበት፡፡ ሰላም ዘላቂ የሚሆነው ግን ቃል ሲከበር ብቻ ነው!