Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ የሆቴልና ቅይጥ አገልግሎቶች የሚሰጥ ፕሮጀክት ግንባታ ተጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዲኤምሲ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በቸርችል ጎዳና አካባቢ በሰባት ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ባለአምስት ኮከብ ሆቴልን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ የግንባታ ፕሮጀክት አስጀመረ፡፡

ቻይና ሲቭል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (CCECC) የተባለው የቻይና ተቋራጭና ዲኤምሲ ትሬዲንግ ፒኤልሲ 14.2 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ የሚያስገነባው ፕሮጀክት አራት ሕንፃዎች ያሉት ሲሆን፣ በውስጡም ዓለም አቀፍ ሆቴል፣ ዘመናዊ የገበያ ማዕከልና የመኖሪያ አፓርትመንቶችን የሚያካትት መሆኑን የግንባታ ስምምነት በተደረገበት ወቅት ተገልጿል፡፡

የቻይናው ሁለገብ የኮንስትራክሽን ኩባንያ በሦስት ዓመት ተኩል ገንብቶ እንደሚያጠናቅቀው የተገለጸው የባለ30 ወለል የግንባታ ፕሮጀክት፣ ዳር ኮንሰልቲንግ የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት የአማካሪና የተቆጣጣሪነት ሥራውን እንደሚያከናውን ታውቋል፡፡

‹‹ዲሎይት በሚባል የእንግሊዝ አገር ኩባንያ ለስድስት ወራት የፈጀ የፕሮጀክት ጥናት ተደርጎበታል›› የተባለው ይህ ፕሮጀክት፣ ለከተማ አስተዳደሩ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቀርቦ አዎንታዊ ምላሽ በማግኘቱ፣ የከተማ አስተዳደሩ መሬቱን በሊዝ እንዳቀረበላቸው የዲኤምሲ ትሬዲንግ ፒኤልሲና የሰንሴት ፋርማሲዩቲካል አስመጪ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ሀብታሙ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በግንባታ ሒደትና በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር፣ ለአገሪቱ ገጽታና የቱሪዝም መዳረሻ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል፡፡ ባለሀብቱ በአሜሪካ በአገልግሎት ዘርፉ ላይ ተሰማርተው መቆየታቸውን አስታውሰው፣ ሆቴል፣ ቱሪዝምና ሪል ስቴት ተሳትፎ ያደረጉባቸው ዘርፎች መሆናቸውን አክለዋል፡፡

የተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ ወደ ታላቁ ቤተ መንግሥት የሚያመራ አቅጣጫ ላይ ያረፈው ይህ ፕሮጀክት፣ ሌሎች የግል አገልግሎት አቅራቢ ተቋማት በሚገኙበት ሥፍራ እንደመገኘቱ ልዩ የከተማው መስህብ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን የግንባታ ስምምነት በተደረገበት መርሐ ግብር ላይ ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በአሜሪካ ተገኝተው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች አገር ውስጥ ገብተው እንዲያለሙ ያቀረቡትን ጥሪ መሠረት አድርገው ከ15 ዓመት በኋላ ወደ አገር ቤት መምጣታቸውን ባለሀብቱ አስረድተዋል፡፡

የአገር ውስጥ ባላሀብቶች ወደ አገር ቤት መጥተው በእንዲህ ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክት ግንባታ መሳተፋቸው የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር በመፍጠር ረገድ የሚጫወተው ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዜጎች በሰው አገር ያገኙት የውጭ ምንዛሪ በአገር ውስጥ ልማት ላይ እንዲውል ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

የቻይናው ኩባንያ ሲሲኢሲሲ እ.ኤ.አ. ከ2012 ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማከወናን ይታወቃል፡፡ የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመር፣ ባህር ዳርና ድሬዳዋን ጨምሮ አምስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶች ከገነባቸው ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ጉኦ ቾንግፌንግ በስምምነት መርሐ ግብሩ ላይ፣ በርካታ የቢዝነስ ጉዞዎች፣ ቁጥራቸው የጎላ የውጭ ተቋማትና የንግድ ማኅበረሰብ የላቀ አገልግሎት ፈልገው የሚመጡባት አዲስ አበባ፣ የአፍሪካ የፖለቲካ መዲናነቷን የሚያመላክቱ ሥራዎች እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል፡፡

የቻይናው ኩባንያ ከዚህ በተጨማሪ ቋራ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል ያለውንና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ባለ48 እና ባለ30 ፎቆች ያሉት መንታ ሕንፃ ግንባታ ለማካሄድ ባለፈው ሰኔ ወር ስምምነት ማሰሩ የሚታወስ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች