የጥራጥሬና የእህል ላኪዎች ምርቶችን በጥራት በማዘጋጀት፣ ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር በመፍጠርና አዳዲስ መዳረሻዎችን በማስፋት መሥራት እንደሚኖርባቸው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አስታወቁ፡፡
ፕሬዘዳንቷ ይህንን የተናገሩት፣ ‹‹ዓለም አቀፋዊ አጋርነትን ማዳበር›› በሚል መሪ ቃል በሸራተን አዲስ ሆቴል እየተካሄደ በሚገኘው 11ኛው የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ለማምረት የተመቸ የአየር ንብረት ያላት አገር ስለሆነች የጥራጥሬና የቅባት እህል ላኪዎች ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር በመፍጠር ከወጪ ንግድ የሚገኝ ገቢን ለማሳደግ መሥራት እንዳለባቸው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አሳስበዋል፡፡
የግሉ ዘርፍ የቅባት እህሎችን በማምረት፣ በማቀነባበርና በመላክ ላይ እንዲሰማራ ዕድል የሚፈጥር የንግድ ፖሊሲ ለውጦችን በተመለከተ መንግሥት አቅጣጫ ማስቀመጡን ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል።
‹‹ይህ ኮንፈረንስ የሚካሄደው በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በመሆኑ በንግድ ሥራ፣ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በተለይም ግብርናውን ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች በማምረት የማሳደግ ዕድል ተሰጥቷታል። ይህንን ዓላማ ለማሳካት መንግሥት የማበረታቻ ፖሊሲዎችን ነድፏል። በተጨማሪም የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሲባል ከፍተኛ በጀት ተመድቦ የመካከለኛና ትልልቅ የንግድ ሥራዎችን በመደገፍ ላይ ይገኛል። መንግሥት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በአገር ውስጥ ኢንቨስተሮቹ የግብርና ፋይናንስ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ባለሀብቶች ጭምር ነው፤›› ሲሉ ፕሬዚዳንቷ ጠቁመዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲካሄድ በቆየው አገራዊ ሪፎርም መሠረት በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ውጤት በማሳየቱ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ የምግብና የአትክልት ሰብሎች ምርት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
በ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከጥራጥሬና ከቅባት እህሎች የወጪ ንግድ 408 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፣ በተያዘው በጀት ዓመትም የምርት መጠንን በማሳደግ ከዘርፉ ከፍተኛ ገቢ እንደሚገኝ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
ጉባዔው በኢትዮጵያ የሚመረቱ ምርቶችን፣ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች በዓለም አቀፍ ገበያ ተገቢውን ዋጋ ለማግኘት የሚያስችል የገበያ ትስስርን ለመፍጠር አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
በጉባዔው ላኪዎች፣ የግብርና ግብዓትና ማሽን አቅራቢዎች፣ የጉምሩክ አስተላላፊዎች፣ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ዓለም አቀፍ ላኪዎች፣ አምባሳደሮች፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል። በተጨማሪም የዘርፉን ንግድ ለማሳደግ አስተዋጽኦ የሚኖራቸው የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ላኪዎች ማኅበር ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ጉባዔ እስከ ዛሬ ኅዳር 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ይቆያል፡፡ የዘርፉን ማነቆዎች ለማቃለልና ምርታማነትን በማሳደግ የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን የአገር ውስጥ ፍላጎት ለማሟላት፣ እንዲሁም የወጪ ንግድ ግኝቱን ለማሳደግ የሚያስችል ምክክር እንደሚካሄድ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሲሳይ አስማረ ተናግረዋል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑ ላኪዎች፣ የእርሻ ግብዓትና ማሽን አቅራቢዎች፣ የጉምሩክ አስተላላፊዎች፣ በርካታ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ዓለም አቀፍ ላኪዎችና የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች ተሳትፈዋል፡፡