የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሐኑ ጁላ እና የህወሓት ጦር አዛዥ ጀኔራል ታደሰ ወረደ በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን ስምምነት መሠረት ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ ተስማሙ።
ስምምነቱ በዋናነት ትኩረት ያደረገው በትግራይ ክልል እንዲሁም በአማራና አፋር ክልሎች ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ማድረግ ላይ ሲሆን፣ በዚህም ሁለቱ ወገኖች ለሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ኃላፊነታቸውን ያለገደብ እንዲወጡ ማድረግን ጨምሮ የደህንነት ዋስትና ለመስጠት ተስማምተዋል።
በተጨማሪም የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ ለማስፈታትና መልሶ በማቋቋም ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን ስምምነት ለመተግበር የሚያስችል ዝርዝር መርሐግብር ለመንደፍ የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማምተዋል።