Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጅማዋን ጌዴዶ ያለመለመው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ

የጅማዋን ጌዴዶ ያለመለመው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ

ቀን:

በጅማ ዞን ከሚገኙ የገጠር ወረዳዎች ውስጥ ጌዴዶ አንዷ ነች፡፡ በውስጧም 32 ቀበሌዎች አሏት፡፡ ከ300 ሺሕ በላይ ሕዝብ እንደሚኖርባትም ይገመታል፡፡ አንድ አባወራም ቢያንስ ስድስት ከሚደርሱ የቤተሰብ አባላቱ ጋር በ0.5 ሔክታር መሬት ላይ እያረሰ ኑሮውን ይገፋል፡፡ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ፍልሰትና ስደት ከሚታይባቸው አካባቢዎች አንዷ መሆኗም ይነገራል፡፡

አቶ አህመድ መሐመድ በኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብ የጤናና የአካባቢ ጥበቃ ቅንጅት ኮንሰርትየም የሥነ ሕዝብና የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም አስተባባሪ ናቸው፡፡ ከ17 ዓመታት በፊት ሕጋዊ ዕውቅናን አግኝቶ መንቀሳቀስ የጀመረው ድርጅቱ፣ የዛሬ አምስት ዓመት ነበር ወደ ጌዴዶ ወረዳ በመምጣት በኢላላና ሶላ ቀበሌዎች ሥራ የጀመረው፡፡

ከጅማ ከተማ በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ጌዴዶ ወረዳ የሚያስገባው የጠጠር መንገድ አቧራማ ነው፡፡ በመንገዱ ላይ በብዛት እናቶች፣ ልጆች፣ ወጣቶች ለገበያ የሚሆን ጎመን በኮባ ጠቅልለውና በበቅሎዎች ጭነው ወደ ገበያ ያቀናሉ፡፡

ግራና ቀኝ ያሉ የመኖሪያ ቤቶችን የከበቡ የተክል አጥሮች በአቧራ ተሸፍነዋል፡፡ ወደ ገጠር ቀበሌዎች ሲገባ አብዛኛው መሬቱ በገብስና በአረንጓዴ ተክሎች የተሸፈነ ነው፡፡ አካባቢው ተራራና ቁልቁለት የሚበዛበት ቢሆንም፣ በሰብል ያልተሸፈነ መሬት አይገኝም፡፡

ደጋማ የአየር ፀባይ ያለው ይህ አካባቢ ቀድሞ በጉም ተሸፍኖ ለመተያየት ከባድ እንደነበር፣ አሁን ደግሞ ሞቃታማ የአየር ፀባይ እያሳየ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

በአረንጓዴ የተሸፈነው ማሳ እስከ ኢላላ ቀበሌ የሚደርስ ሲሆን፣ በመሀል የቀበሌው ጽሕፈት ቤት ይገኛል፡፡ ከዚህ የቀበሌ ግቢ ፊት ለፊት ተራራ ይታያል፡፡ ተራራውም በዕርከን በተሠራ ማሳ ተሸፍኗል፡፡ ከአናቱ ላይ የጋረደው ሰማይ ተራራ በእጅ የታረሰውን ሥዕል አስመስሎታል፡፡

ወ/ሮ ሳይዳ መሐመድ በኢላላ ቀበሌ ገዳዳ በሚባለው አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ ውልደታቸውና ዕድገታቸውም በዚሁ ነው፡፡ ባለትዳርና የስድስት ልጆች እናት ናቸው፡፡ በልጅነታቸው የሚያውቁት ለምለም መሬት የሰጡትን እጥፍ አድርጎ የሚመልስ ከቤታቸው ቅርብ ከነበረው ምንጭ በመውረድ ራሳቸውንና ጓደኞቻቸውም ታጥበው ለመጠጥ የሚሆነውን ቀድተው የሚመለሱበት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ወ/ሮ ሳይዳ በሃይማኖታቸውና በባህላቸው የቤተሰብ ምጣኔ አጠቃቀም የሚባለው ነገር የተወገዘና የተከለከለ ስለነበር እሳቸውን ጨምሮ ልጆችን በተከታታይ በመውለዳቸው ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው እንደነበረም ይገልጻሉ፡፡

ቀስ በቀስ መሬቱ እየጠበበ፣ የሚሰጠውም ምርት እየቀነሰና ምንጮቹም እየራቁ ሲሄዱ የተወለዱ ልጆች ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሱትም ያልደረሱትም ሥራ ፍለጋ መንደራቸውን በመልቀቅ ለስደት እየተዳረጉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

እሳቸውን ጨምሮ በርካታ የቀበሌው ነዋሪዎችም በደረቀና መሬቱ ተሸርሽሮ አልቆ ምርት ከማይሰጠው መሬት የሚያገኙትን ከቤተሰብና ጎረቤት ጋር በመቃመስ ዓመታትን በችግር ለማሳለፍ መገደዳቸውን ዕንባ ባዘለው ዓይናቸው ይገልጻሉ፡፡

በግቢው ውስጥ ወ/ሮ ሳይዳን ጨምሮ በርካታ አሠልጣኞች በቡድን ሆነው ይታያሉ፡፡ ቡድኖቹ በጤና፣ በሥነ ተዋልዶ እንዲሁም ከአካባቢው በሚገኝ ምርት እንዴት የተመጣጠነ ምግብ ለልጆችና ለቤተሰቦቻቸው ማዘጋጀት እንደሚቻል፣ ገቢያቸውን እንዴት መጨመር እንደሚችሉ ኅብረተሰቡን የሚያሠለጥኑ ናቸው፡፡

በኮንሰርትየም ኢትዮጵያ የተሰጣቸው ሥልጠና ኅብረተሰቡን ለመለወጥ እንደቻለና በተለይም ከባድ ችግር ሆኖ የነበረው የሥነ ተዋልዶ ትምህርት የትኛዋም ሴት ከባሏ ጋር በግልጽ በመወያየት የቤተሰባቸውን መጠን መወሰን የሚችሉበት ደረጃ ላይ ማድረሱን ይናገራሉ፡፡

የተሻሻሉ የጓሮ አትክልቶችንም በቀረበላቸው መሠረት እያመረቱ ከቤተሰብ አልፈው ለጅማ ከተማ ማቅረብ እንደቻሉ ሠልጣኞች ይገልጻሉ፡፡

ስሟ እንዳይገለጽ የፈለገችው ወጣት ከሠልጣኞቹ አንዷ ስትሆን፣ በችግር ምክንያት መንደሯን ከለቀቀች መቆየቷን፣ ቤተሰቦቿን ጥየቃ መጥታ በአንድ     የሥልጠና ቀን ከእናቷ ጋር በመሄድ የተሳተፈችበትን ሥልጠና በሌላ ቀን ራሷ በመቀጠልና ቤተሰቦቿ ጋር በመመለስ ባላቸው መሬት ላይ የተሻሻለ የድንች ዘር አምራች በመሆን ቤተሰቦቿን ማስተዳደር መጀመሯን አንገቷን ካቀረቀረችበት ቀና ሳትል አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

ከቀበሌው ከቅርብ ርቀት ላይ የአቶ ረሂስ ሼህ ጀማል መኖሪያ ቤት ይገኛል፡፡ ‹‹የግዥ ማዳበሪያ ካቆምኩ ከሁለት ዓመታት በላይ ሆኖኛል፤›› ይላሉ፡፡ በሠለጠኑት መሠረት ኮንሰርቲየሙ ከጅማ ግብርና ኮሌጅ እየገዛ በሰጣቸው ቀያይ ትሎች፣ ከከብቶች እዳሪ፣ ከብስባሽ ተክሎች የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት በግቢያቸው የባቄላ፣ የድንች ምርጥ ዘር፣ ገብስ፣ አተርና ሐበሻ ጎመን እያለሙ እንደሆነ በዚህ ሥራ ያመጡትን ውጤት በሥፍራው ለተገኘ ታዳሚ አስጎብኝተዋል፡፡

አቶ ረሂስ እንደገለጹት፣ ይህንን ማዳበሪያ ለሌሎች በመሸጥ ብቻ በወር ብዙ ገቢ ያገኛሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የድንች ምርጥ ዘር ቶሎ ካልተጠቀሙበት ይበሰብስ የነበረ ሲሆን፣ በተሰጣቸው ሥልጠና መሠረት ለእሱ ብቻ የሚሆን መደርደሪያ በማዘጋጀት እስከ አንድ ዓመት ሊቆይ እንደሚችልና በቆየ ቁጥር ደግሞ ዋጋውም ከፍ እያለ እንደሚመጣ መገንዘብ ችለዋል፡፡

ከቤታቸው ጀርባ ባለው የገብስ እርሻ የመሀል መንገድ እየመሩን፣ ከዚህ በፊት በአካባቢው ታዋቂ የነበረው የቀርከሃ ተክል እንደነበር፣ ከረዥም ጊዜ በኋላ በማሳቸው ላይ ዳግም እንዲሞከር በማድረግ ጥራቱን የጠበቀና እስከ 15 ሜትር የሚደርስ ቀርከሃ እያመረቱና ዋጋም ተቆርጦለት ለገበያ ሊቀርብ እንደደረሰ ገልጸዋል፡፡

የገቢያቸውንና የኑሯቸውን ሁኔታ የሚቀይረውን የአፕል ምርት በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን፣ ኮንሰርትየሙ ከግል ንፅህና ጀምሮ የሚሰጠው ሥልጠና ተራቁቶ ለእነሱም ለመኖሪያ አስቸጋሪ የነበረውን አካባቢ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ጫካ ለመመለስ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

አቶ ፀጋዬ ጉታ በኮንሰርትየሙ የጅማ ዞን አስተዳደር የፕሮጀክት አስተባባሪ ሲሆኑ፣ ወደ አካባቢ በ2010 ዓ.ም. መግባታቸውን፣ ሲመጡ አካባቢው በጣም ተራቁቶና ተደጋጋሚ ድርቅ ያጠቃው፣ በተለይም በጌዴዶና በሶላ ቀበሌዎች ችግሩ የከፋ እንደነበር ተናግረዋል፡፡፡

በእነዚህ ቀበሌዎች 1,090 የሚሆኑ አባዎራዎችን በቤተሰብ ዕቅድና በአካባቢ ጥበቃ ገቢያቸውን በማሻሻል በአጠቃላይ በተቀናጀ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ አካባቢው ወደ ቀድሞ ይዞታው መመለስ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ከፍተኛ የደን ምርት የነበራቸውን ዘራቸው እስከ መጥፋት ደርሰው የነበሩትን የቀርከሃ፣ የኮሶና የግራቪሊያ ዛፎች እንደ አዲስ እንዲተከሉ በማድረግ በቀርከሃ 6.5 ሔክታር፣ በኮሶና በግራቪሊያ ደግሞ 11.25 ሔክታር መሸፈኑን ጠቁመዋል፡፡

አካባቢው ደጋ እንደመሆኑ ለገበሬዎቹ ከ7,720 በላይ የተሻሻሉ የአፕል ችግኞችን በመስጠት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መፍጠር መቻሉን ተናግረው፣ የተሻሻሉ የጓሮ አትክልቶች እንዲተከሉ በማድረግ ለቤተሰብ የተመጣጠነ ምግብ እንዴት ማዘጋጀት እንደሚችሉ የተለያዩ ሥልጣዎችንና ድጋፎችን በመስጠት ፕሮጀክቱ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...