Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጤናው ዘርፍ በሩብ ዓመቱ

የጤናው ዘርፍ በሩብ ዓመቱ

ቀን:

ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ውስጥ አልፋለች፡፡ በተለይም ዓለምን ጭንቅ ውስጥ ያስገባው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ማስከተሉ አልቀረም፡፡ የጤና ዘርፍ ከወረርሽኙ መከሰት በተጨማሪ በሰሜኑ ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነትና በሌሎች አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ተፈትኗል፡፡

ጤና ሚኒስቴር ችግሮችን ተቋቁሞ ለማለፍ የተለያየ የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ ልዩ ልዩ ተግባራትን ማከናወኑን አስታውቋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር የሩብ ዓመት ሪፖርቱን ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጤና ሚኒስቴር የሩብ ዓመት ሪፖርቱን ባለፈው ሳምንት ያቀረበ ሲሆን፣ ሪፖርቱን ያቀረቡ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) የቤተሰብ ዕቅድ ሽፋን፣ የእናቶ ጤና፣ የጨቅላ ሕፃናት፣ ክትባት፣ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር፣ መድኃኒት አቅርቦትና ተያያዥ ሥራዎቻቸው ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡

የእናቶችን ጤና ማሻሻል

ከእናቶች ጤና ማሻሻል አንዱ ሥራ የሆነው የልደት ኩነት ምዝገባ ሲሆን፣ አሁን ባለው አፈጻጸም 71 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለያየ ምክንያት ፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት ያስፈለጋቸው 105,000 ዜጎች፣ በሕጉ ማዕቀፍና አፈጻጸም መሠረት ፅንስ ተቋርጦላቸዋል፡፡

ከጤና ሚኒስቴር የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን መጠን መቀነስ አንዱ ሲሆን በሩብ ዓመቱ ብቻ በ1,000 ሕፃናት 14 የጨቅላ ሕፃናት ሞት ለማድረስ የታቀደውን 14.5 ላይ ማድረስ መቻሉና  በእርግዝናና በወሊድ ወቅት የኤችአይቪ ምርመራ ተደርጎ ውጤታችን እንዲያዩ የተደረጉት 81 በመቶ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡

በበቂ ሁኔታ አገልግሎት ሳይሰጡ የዘገዩ የአፋርና ሶማሌ ክልሎች የጤና ተቋማትንና 150 ጤና ኬላዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ድጋፍና ክትትል መደረጉን አክለዋል፡፡

የሕፃናት ክትባት

የፀረ አምስት ክትባት መቶ በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 87 በመቶ መድረሱን፣ የኩፍኝ ክትባትን 80 በመቶ ላይ እንደሚገኝ፣ ሁሉም ዓይነት ክትባቶችን ያጠናቀቁ 96 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 87 በመቶ ላይ እንደሚገኝ በሪፖርቱ ተዘርዝሯል፡፡ እነዚህ ዕቅዶች ከዓምና ጋር ሲነፃፀሩ ያልተሻሻሉ ቢሆንም፣ ከግብ አኳያ ገና ሒደት ላይ የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ ክትባትና ሌሎች ግብዓቶች በአብዛኛው በድጋፍ የሚገኙ ቢሆንም በመንግሥት ለመግዛት መቻሉን፣ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለሕፃናት ክትባት ለመስጠት 430 ፍሪጆችና 59 ፍሪዘሮች በተለያዩ አራት ክልሎችና በመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ መተከላቸው ተገልጿል፡፡

በሩብ ዓመቱ ትልቁ ችግር ያልተከተቡ ሕፃናት መኖራቸው ነው፡፡ በተለያየ ምክንያት ምንም ክትባት ያላገኙ ወይም ጥቂት ብቻ የወሰዱ ሕፃናትም አንድ ሚሊዮን መሆናቸው፣ እነዚህም በአርሶ አደሮችና ከተሞች የሚገኙ ሕፃናት መሆናቸው በጥናት መረጋገጡ በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡

በተያዘው ዓመት ከክትባት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚሰጡ የባይታሚንና የአልቤዳዞን እደላ ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

በሽታ መቆጣጠርና መከላከል

 በበጀት ዓመቱ አንድ ሚሊዮን ዜጎች ምርመራ አድርገው 1.14 በመቶ (15,496) ኤችአይቪ በደማቸው መገኘቱን፣ ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡  

የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና የሚወስዱት 95 በመቶ መሆናቸውን፣ በሩብ ዓመቱ 98 በመቶዎቹ ከ1,000 በታች ቫይራል ሎድ እንዳላቸው

ኤችአይቪ በደማቸው ተገኝቶ ራሳቸውን ያላወቁ ዜጎች ቁጥር አሁንም ገና በመሆኑ የራስ መመርመርያ ኪት እየተሠራጨም ነው፡፡  

በተያዘው ሩብ ዓመትም 25,214 የኤችአይቪ መመርመርያ ኪት ተሠራጭቷል፡፡ በዚህም ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን እንዲያውቁ እየተደረገ እንደሚገኝ በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡

የሔፒታይተስ ሥርጭት

‹‹ሔፒታይተስ›› ልየታውንና ሕክምናውን ማስፋፋት ላይ ከአጋሮች ጋር እየተሠራ መሆኑን፣ የሥርጭት መጠኑ ሔፒታይተስ ‹‹ቢ›› ዘጠኝ በመቶ ‹‹ሲ›› ደግሞ ሦስት በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ተጠቋሟል፡፡

‹‹ቲቢ በሽታ››

የቲቢ በሽታ አገልግሎት አሰጣጥ ዓምና ከነበረው 72 በመቶ ወደ 87 በመቶ ማደጉን በዚህ ሩብ ዓመት ደግሞ 78 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ሕክምናውን በተሳካ ሁኔታ የሚያጠናቅቁትን 97 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 95 በመቶ ተሳክቷል፡፡

የወባ በሽታ

በተያዘው ዓመት ለጤና ዘርፍ ፈተና የሆነው የወባ በሽታ መሆኑ፣ በበጀት ዓመቱ 19.7 ሚሊዮን አጎበር ታዞ በግዥ ሒደት ላይ እንደሚገኝና ከዚህም ውስጥ 800,000 ወደብ ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ቤቶች በኬሚካል መረጨታቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ቤቶች የኬሚካል ርጭት ለማድረግ ዕቅድ የተያዘና በሽታው በተስፋፋባቸው 565 ወረዳዎች ውስጥ ከፍተኛ ሥራዎችን ለመሥራት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡  

በሩብ ዓመቱ ከተመረመሩት 1.9 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ 25 በመቶዎቹ ወባ እንደተገኘባቸው ጠቁመዋል፡፡

የከተማ ፅዳት

በ2015 ዓ.ም. ሩብ ዓመት 408 ወረዳዎች ላይ የግብይት ማዕከላት የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ አካባቢን ከሜዳ ላይ መፀዳዳት ነፃ ለማድረግ በተሠሩት ሥራዎች መሠረት፣ 7,371 ቀበሌዎች ወይም 41 በመቶ ነፃ ማድረግ መቻሉም በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡

በጤና ጣቢያ የሚሰጥ ቀዶ ሕክምና

በአገር አቀፍ ደረጃ 400 የሚሆኑ ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ በዕቅድ ቢያዝም፣ 76 የሚሆኑት ጤና ጣቢያዎች ብቻ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ እየሰጡ  እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ በቀጣይ ቢያንስ 100 የሚሆኑ ጤና ጣቢያዎች ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንዲጀምሩ ለማድረግ እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡

የመድኃኒት አቅርቦት

የመድኃኒት አቅርቦት በተመለከተ መሠረታዊ፣ ድንገተኛ፣ ሕይወት የሚያድኑና ሌሎችም መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

መሠረታዊ መድኃኒት በአብዛኛው ማቅረብ የሚቻለው በአገር ውስጥ አምራቾች መሆኑን፣ በየጤና ተቋሙ ሲፈተሽ አንዳንዶች ጋር እንደማይኖር ተጠቁሟል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መስከረም 2015 ዓ.ም. መረጃ ሲታይ 74 በመቶዎቹ መድኃኒት እንዳላቸው፣ ከአንዱ ሆስፒታል ወደ አንዱ መቀያየር ደግሞ 83 በመቶ ላይ መድረሱ ተጠቁሟል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት መቶ ጤና ተቋማት ላይ በተካሄደ ጥናት በጤና ጣቢያ መገኘት ያለባቸው 25 የመድኃኒቶች ዓይነቶች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ 90 በመቶ ተገኝተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ቤተልሔም ላቀው (ዶ/ር) የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ከፍተኛ በመሆኑ የአገር ውስጥ አምራች ባለሀብቶችን በማበረታታት  መሥራት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡

በቀረበው ሪፖርት ዓላማውና አፈጻጸሙን መቀመጥ እንዳለበት ጠቁመው፣ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ሥራዎችን በመሥራት ለችግሮች መፍትሔ መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስቴሩ፣ በጦርነት የተጎዱ ተቋማትን መልሶ ማቋቋም፣ ለተፈናቃይ ዜጎች የሚደረጉ ድጋፎች ለኅብረተሰቡ መድረሱን ማረጋገጥና የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን መቅረፍ፣ በማኅበራዊ ጤና መድኅን የመንግሥት ሠራተኛውንና ጡረተኞችን በማካተት ፈጥኖ ወደ ሥራ መግባት እንዳለበትም  አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው በሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የአገልግሎት አሰጣጥና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የምግብና የመጠጥ አቅራቢ ደርጅቶች ቁጥጥር መጠናከር እንዳለበት አንስተዋል፡፡

ከወባ፣ ወረርሽኝንና (ኤችአይቪ) መከላከልና መቆጣጠር ጋር በተያያዘ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ጤናማ ኅብረተሰብ ለመገንባት የእናቶችንና ሕፃናት ሞት ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አብዱርቃድር ገልገሎ (ዶ/ር) ተቋማት መድኃኒት ለመግዛት እንደሚቸገሩ፣ ከፍተኛ የሆነ የመድኃኒት ፍላጎት በመኖሩ ከአቅርቦቱ ጋር እንዳልተጣጣመ፣ በአገር ውስጥ ያሉትም አቅራቢዎች በብቃት ማቅረብ ባለመቻላቸው ችግሩ መከሰቱን ሊያ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

40 በመቶው የአገር ውስጥ የመድኃኒት አቅራቢዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን፣ ግልጽ የሆነ የዲጂታል አቅርቦት ሥርዓትን መዘርጋት የውጭ አቅራቢዎችን በማስፋፋት በኢትዮጵያ እንዲመዘገቡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

የመድኃኒት አቅርቦት ረዥም ሰንሰለትና ተዋንያን ያሉበት በመሆኑ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት የኅብረተሰቡ ትብብር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...