ከኢትዮጵያ ዘመናዊ ሠዓልያን መካከል በፈር ቀዳጅነት ከሚጠቀሱት መካከል በኩሮቹ አፈወርቅ ተክሌ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ስኩንደር ቦጎስያንን በተለየ አገባብ የሚጠቅሱ አሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱ ስለአፍሪካ ባህል መገለጫዎች ፊልም፣ ቴአትር፣ ዳንስ፣ ሙዚቃና ሥነ ጥበብ በሚያትተው አፍሪካንስ አርት ጆርናል ላይ ከገብረ ክርስቶስ ጋር ያወጋው ሲድኒ ደብሊው ሄድ ይገኝበታል፡፡
እንደ ሲድኒ ሄድ አገላለጽ ሦስቱም ሥነ ጠቢባን በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች ለንደን፣ ኮሎኝና ፓሪስ የተማሩ ብሂልን ከባህል ያዛመዱ፣ በአገራቸው ውስጥም የየአጥቢያዎቻቸውን ቀለሞች ያንፀባረቁ ናቸው፡፡ ሦስቱም ከ1950ዎቹ መገባደጃ ጀምሮ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅትን ሽልማት ተቀዳጅተዋል፡፡
በ1925 ዓ.ም. ጥቅምት 5 ቀን በሐረር ከተማ የተወለደውና በአሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት በ1973 ዓ.ም. መጋቢት 21 ቀን ያረፈው ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ በኮሎኝ አርት አካዴሚ (ጀርመን) እያለ በልዩ ልዩ አገሮች እየተዘዋወረ የጥበበ አብስትራክትና የጥበበ ገላጭ ሠዓሊዎችን ሥራ ማጥናቱን ‹‹መንገድ ስጡኝ ሰፊ›› በተሰኘው የግጥም መድበሉ ቀዳሚ ቃል የጻፉት ኄራን ሠረቀ ብርሃን ጠቅሰዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ከ1955 ዓ.ም. ጀምሮ ለዓመታት ያስተማረው ገብረ ክርስቶስ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመመረቂያ ድርሳኑን በእሱ የሕይወት ታሪክ ላይ ባደረገው ብርሃነ መስቀል ደጀኔ አገላለጽ፣ ድንቅ ሥዕሎቹን በአገርና በውጭ አገር በግልና በቡድን በተደጋጋሚ ያሳየ፣ በሕዝቦች የባህል ልውውጥም በየጊዜው የኢትዮጵያ የሥነ ጥበባት ቡድን መሪ ልዑክ በመሆንም በልዩ ልዩ ዓለም አቀፋዊ አደባባዮች ላይ አገሩን የወከለ የጥበብ ሰው ነበር፡፡ በዘመናዊ አሣሣል የጥበብ ሥልቱ በአገሩ ብኩርናን ከማግኘት አልፎ ለዓለም የሥነ ጥበባት ባህልም አንድ የግሉና ልዩ የሆነ መለዮውን ያበረከተ፣ አገሩንና አኅጉሪቱን ጭምር ያስጠራ ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ነበር፡፡
ከሠዓሊነቱ ባሻገር በገጣሚነቱ በባለቅኔነቱ የሚታወቀው በሥነ ግጥም ምሁሩ ብርሃኑ ገበየሁ አገላለጽም፣ ‹‹አዝማሪ›› የተባለውን ገብረ ክርስቶስ ደስታን የሚዘክር ለአንድ ወር የሚቆይ መሰናዶ በስሙ የተቋቋመው ዘመናዊ ሥነ ጥበብ ሙዚየም ባለፈው ሳምንት አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው ዘመናዊ ሥነ ጥበብ ሙዚየም ገብረ ክርስቶስ ማዕከል እንዳስታወቀው፣ ወርኃ ገብረ ክርስቶስ የሚከናወነው በመጪው የካቲት ወር ነው፡፡
‹‹በወሩ አራቱም ሳምንታት ሠዓሊው፣ ገጣሚውና ሰውየው ገብረ ክርስቶስ ደስታ ከዚህ ቀደም ባልታዩና ባልተነገሩ ታሪኮቹ ጭምር በስሙ በተቋቋመው ሙዚየም፣ በስሙ በተቋቋመው ሙዚየም፣ በየመስኩ ባለሙያዎችና ውስጥ አዋቂዎች ይዘከራል፡፡ ይተነተናል››፡፡
ማዕከሉ ሥዕሎቹ የሚታዩበት፣ ሥነ ግጥሞቹ የሚነበቡበት፣ ሰውየውም የሚወሳበት የአራት ሳምንት ሰፊ መርሐ ግብር እንዲሳካ ለማድረግ ለታሪክና ለሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ጥሪ አቅርቧል፡፡ ለዝግጅቱ አቅራቢ ባለሙያዎች፣ ሙሉ ዝግጅቱን በኅትመት፣ በምሥልና በድምፅ ቀርፆ ለማስቀረት፣ በመክፈቻና መዝጊያ መሰናዶዎች ወጪ የሚፈልግ መሆኑን ያስታወቀው ማዕከሉ በዓይነትም ሆነ በገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግለትም ጠይቋል፡፡
ስለገብረ ክርስቶስ ደስታ በዝግጅት አቅራቢነት የመሳተፍ ዕውቀት ወይም የተለየ መረጃ ያላቸው ዝግጅቱን እንዲደግፉም ተጋብዘዋል፡፡
ከገብረ ክርስቶስ ግጥም አንዱ አንጓ
እንደ ሥዕሎቹም በግጥሞቹም ልዕልና ያገኘው ገብረ ክርስቶስ (ቅርቦቹ እንደሚጠሩት ጂኬ) አንደኛው ግጥሙ የጠፈር ባይተዋር ነው፡፡ እሱ ካለፈ ከሩብ ምዕት ዓመት በኋላ የኅትመት ብርሃን ባየው ‹‹መንገድ ስጡኝ ሰፊ›› መድበል ላይ ሐቲት ያቀረቡት ዮናስ አድማሱ ናቸው፡፡ እንዲህም ከተቡ፡- ‹‹እኔ እጅ ባለው የግጥሞቹ ስብስብ በተከታታይ ተጽፈው ያገኘኋቸው ‹ለቡጊ› እና ‹የጠፈር ባይተዋር› የነፍስን ከሥጋ ቁራኛ የመላቀቅ ሰብዓዊ ግፊት (The Human Urge to Free itself from Carnal Bondage) ከዓለመ ዓለማቱ ጋር አንድ የመሆን አምሮት (The Desire to be one with the Universe) ሊጨበጥ ቀርቶ ሊታይም እንኳን የማይችለውን ሕልም ማለም (To dream the Impossible Dream) ይህንንና የበለጠም ያሳያሉ፡፡ የምናየው ገብረ ክርስቶስን ሳይሆን ሰው መሆንን (ሰብዓዊነትን) ነው፡፡ መሆን ‹የማይቻለውን› ይናፍቃል፡፡››
ገብረ ክርስቶስ በ1961 ዓ.ም. ከገጠመው የጠፈር ባይተዋር ግጥሙ የሚከተሉት አንጓዎች ይገኙበታል፡፡
‹‹ግማሽ ቀልድ አላውቅም!
ሞት እንደሁ ልሙት በሴኮንድ መቶኛ
ዕንቅልፍ እንደ ሬሳ ዘላለም ልተኛ፡፡
መንገድ ስጡኝ ሰፊ
ስሔድ እኖራለሁ —
ሰማየ ሰማያት እመዘብራለሁ፡፡
የተዘጋውን በር እበረግዳለሁ፡፡
የሌለ እስቲፈጠር፤ የሞተ እስኪነቃ፤
በትልቅ ዕርምጃ ከመሬት ጨረቃ
ከጨረቃ ኮከብ፤
ካንዱ ዓለም ወዳንዱ፤
ስጓዝ እፈጥናለሁ—
በፀሐይ ላይ ቤቴን ጐጆ እቀልሳለሁ፡፡
ግማሽ ቀልድ አላውቀም!
ከሲዖል ሚሊዮን ቢሊዮን ልቃጠል፡፡
ከገሀነመ እሳት ሚሊዮን ነበልባል፡፡
መንገድ ስጡኝ ሰፊ —