በአዲሱ ዓመትም ጆሮ ዳባ ልበስ የተባለው የወላይታ ሕፃናትና ወጣቶች ሰቆቃ በኢትዮጵያ ጎዳናዎች
በጋዳዋ መንግሥቱ ወልዴ
በወላይታ የዘመን መለወጫ ወደ ትውልድ ከተማዬ ወላይታ ሶዶ ገብቻለሁ። ባለፈው ዓመት በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው የፖለቲካ ሽኩቻ ወደ ጓዳ እንዲገባ ተደርጎ የነበረው የጊፋታ በዓል ዘንድሮ ወደ ቀድሞ ክብሩ፣ ድምቀቱና የአደባባይ ካርኒቫል ቅርፁ ተመልሶ በጉታራ፣ በካዎ ጦና ስታዲየምና በየአሙዋ አባላት ዘንድ በድምቀት መከበሩን ማየት አስደሳች ነው። ጊፋታ ወላይቱማን በሚመጥን ቁመና መመለሱ አንድ የሚያስደስት ዜና ሲሆን፣ ቀጣዩ ትውልድ ይህን ባህል አጠናክሮ መቀጠል የሚያስችል ቁርጠኝነት የሚነበብበት መሆኑ ተስፋ ሰጪ ሆኖ አግኝቻለሁ። ይህን የሕዝብ ክብረ በዓል ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ወጥቶ ሙሉ በሙሉ የሕዝብ እንዲሆን መሥራት ቀጣይ የቤት ሥራ ይሆናል። በጊፋታ አከባበር ሀሴት ሲያደርግ የነበረው ቀልቤ አንድ አንኳር ጉዳይ አንስቶ ማሰላሰል ከጀመረ ውሎ አድሯል። በዚህ ጉዞዬ የወላይታ ሕፃናትና አፍላ ወጣቶች ለሰቆቃ በሚዳርግ አኳኋን የሚያደርጉት የስደትና የፍልሰት ሕይወት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ነፍሴን ሰቅዞ ያስጨንቅ ይዟል። የዚህን ሁኔታ ደርዝ በሁለንተናዊ ይዘቱ ለመረዳት ጥልቅ ጥናት አስፈላጊ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት የተነሳ በዓይን የሚታየው ሀቅ ብቻ ችግሩን በበቂ ሁኔታ ለመረዳት ብዙ ፍንጭ የሚሰጥ ሆኖ ይገኛል። በዚህ የጉዞ ማስታወሻ ያሰላሰልኳቸውን ጉዳዮች እንደሚከተለው ከትብያለውና ከጥሞና ጋር መልካም ንባብ እንዲሆን እመኛለሁ።
በአዲሱም ዓመት ጆሮ ዳባ ልበስ የተባለው የወላይታ ሕፃናትና ወጣቶች ሰቆቃ በኢትዮጵያ ጎዳናዎች፣ በሰው ልጆች የሺሕ ዓመታት ኑባሬ ውስጥ የሰው ልጅ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ተዘዋውሮ የመኖር የሕይወት ዘዬ የመከተል ጉዳይ የነበረና ከሰው ልጆች የአኗኗር ዕድገት ሀዲዲን ተከትሎ በተለያዩ ምክንያቶችና ሁናቴዎች መነሻነት እስካሁኑ የሰው ልጅ ትውልድ ድረስ መልኩንና ባህሪውን እየለዋወጠ የመጣ የማኅበረሰባዊ የዕድገት ምህዋር ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሁነት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የዚህን አንኳር የማኅበረሰብ ዕድገትና ለውጥ መሥተጋብር ጉዳይ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ዕድገት፣ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎችን የሚያጠና ራሱን የቻለ የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ እስከመፈጠርና በጉዳዩ ዙሪያ መሥራት ይገባቸዋል የተባሉና ያገባኛል የሚሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ድርጅቶችና ድንበር ተሻጋሪና አገር አቀፍ መዋቅሮች ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ ያስቻለ ከዓለማችን አንገብጋቢ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንዱ ለመሆን የበቃ ጉዳይ ነው፡፡
ለሰው ልጆች ፍልሰት እንደ ሥርወ ምክንያት የሚወሰዱ መነሻ መንስዔዎች በርካታ መሆናቸውን የዘርፉ ምሁራን የሚስማሙበት ቢሆንም በዋናነት ለሁሉም ዓይነት ፍልሰቶች አስከፊ ድህነት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝ መንስዔ ምክንያት መሆኑን ሁሉም ይስማሙበታል፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ የዘርፉ ምሁራን እንደሚስማሙበት ለሰው ልጆች ፍልሰት እንደ መነሻ ተደረገው ሊወሰዱ የሚችሉት መንስዔ ምክንያቶች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ፡፡ የመጀመሪያው ወደ ፍልሰት ገፊ መንስዔ ምክንያቶች የሚደረግ ፍልሰት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ወደ ፍልሰት ሳቢ ምክንያቶች የሚደረግ ፍልሰት በመባል ይታወቃል፡፡ ከአንድ አካባቢ የተሻለ የኑሮና ሕይወት ስኬት፣ የሥራ፣ ትምህርትና ሌሎች የሕይወት አማራጮች ዕድል ፍለጋን እንደ መነሻ ምክንያት በማድረግ የሚደረገው የወጣቶችና የአፍላ ወጣቶች ፍልሰት በዋናነት የጉዞውን የመዳረሻውን ጫፍ አካባቢ ከመነሻው አንጻር ተሽለው የሚታዩ በመሆናቸው የመዳረሻው አካባቢ ሳቢ ምክንያቶች በማወዳደር የሚደረግ ፍልሰት ሲሆን አስከፊ ድህነትን፣ ጦርነትን፣ ግጭትን፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች፣ ረሀብና ድርቅን ወዘተ ለማምለጥ የሚደረጉ ፍልሰቶች ደግሞ በአብዛኛው የፍልሰቱ አካባቢ መነሻና ገፊ ምክንያቶች ተደርገው የሚወሰዱ ምክንያቶች ናቸው፡፡
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተመራመሩ ሊቃውንት እንደሚስማሙበትና የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት እ.ኤ.አ በ2020 ይፋ ባደረገው ሪፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎች በፍልሰት ላይ የሚገኙ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በዚህ አኃዝ ግምት መሠረት በዓለም ላይ ከሚገኙ ሰባት ሰዎች አንዱ ባንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ሕይወቱን ከፍልሰት ጋር በተያያዘ ሁኔታ ይመራል፡፡ ይኼው መረጃ አክሎ እንደሚጠቁመው ከ700 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ፍልሰት የሚከናወነው ውስጣዊ (ድንበር ዘለል ያልሆነ) ሲሆን 300 ሚሊዮን ዜጎች የሚያደርጉት ፍልሰት ግን ዓለም አቀፋዊ ባህሪይ ያለው፣ ከአንድ አገር ድንበር አሊያም አኅጉራዊ ድንበርን አልፎ የሚደረግ ፍልሰት እንደሆነ የሚጠቁም ሲሆን፣ ሰባ በመቶ የሚሆነው ፍልሰት ማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች በሚገኙ ዜጎች የሚከናወን መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጠው የሰው ልጆች የፍልሰት ጉዳይ በአኅጉረ አፍሪካ ከፍተኛ ፈተና እየሆነ የመጣ መሆኑን ጥናቶች ይስማሙበታል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2020 ይፋ የተደረገው የተባበሩት መንግሥታት የፍልሰት ድርጅት መረጃ በአፍሪካ አኅጉር በፍልሰት ምክንያት በመፈጠር ላይ ያለው ቀውስ በከፍተኛ ደረጃ እያደገና እየተወሳሰበ እንደመጣ ይጠቁማል፡፡ በአኅጉሩ ከሚደረገው ፍልሰት ሃያ አራት በመቶውን የሚሸፍነው ከ20 ዓመት በታች ባሉ ወጣቶች፣ አፍላ ወጣቶችና ሕፃናት የሚደረግ መሆኑ ደግሞ በድህነት አለንጋ በምትገረፈው አፍሪካ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ዓይነት ዕጣ ፈንታን የጋረጠባት ጉዳይ ነው፡፡ በመላው ዓለም በ2021 ብቻ ከ28 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችና አፍላ ወጣቶችና ሕፃናት በዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በፍልሰት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ይህ አኃዝ ከ30 የአፍሪካ አገሮች አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ጋር የሚስተካከል መሆኑ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምን ያህል ሥር እየሰደደና እየተባባሰ መምጣቱን አመላካች ነው፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያዊ ችግሩ ሰፊና ትክክለኛ የመፍትሔ አቅጣጫ ሳይሰጥበት በዝምታ እየታየ ጉዳይ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። በዚህ ጉዳይ የዶክትሬት ጥናቱን ያከናወነው ኢዮብ ቆልቻ (ዶ/ር) እንደሚለው የችግሩ ስፋት በመላው የአገራችን ክፍል ውስጥ የሚገኝ መሆኑ በጥናት የተረጋገጠ ቢሆንም፣ የወጣትና አፍላ ወጣቶች እንዲሁም የሕፃናት ወደ ከተሞች ፍልሰት ላይ ግን እንደ ወላይታ ማኅበረሰብ በከፍተኛ ፈተና ውስጥ የሚገኝ ማኅበረሰብ ማግኘት አይቻልም።
ዶ/ር ኢዮብ በጥናቱ እንደሚጠቁመው ከወላይታ ወደ መላው የኢትዮጵያ ከተሞች የሚደረገው ፍልሰት በርካታ መንስዔ የሚሆኑ ምክንቶችን ያስቀምጣል። እንደ አንኳር ምክንያት የሚመዘዘው ምክንያት ደግሞ በአካባቢው የሚገኘው ሥር የሰደደ ድህነት ሲሆን ለተከታታይ ዓመት በክልሉ ተግባራዊ የተደረጉ የማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፖሊሲዎች ውድቀት መሆኑን ይደመድማል።
በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው የፍልሰትን ችግር በአንድ ጀምበር ተነስተው በአዋጅ ማቆም ባይቻልም ቅሉ የችግሩን መንስዔውን በአግባቡ በመተንተን፣ ምክንያቶቹን በጥናት ተደግፎ በመለየት ትክክለኛና የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታዎች ከግንዛቤ ያስገባ ስትራቴጂ፣ ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች በመቅረጽና ተግባራዊ በማድረግ አንድም ችግሩን መቀነስ በሌላ መልኩ ደግሞ ተግዳሮቱን ወደ ምቹ ሁኔታ በመቀየር በአግባቡ ማኔጅ ማድረግ የሚቻል ነው የሚል እምነት አለኝ። ችግሩኮ ችግሩ ችግር እንደሆነ የሚያምን መሪዎች ማጣታችን ይሆን? እና እነዚህ ልጆች እንደ በቀለ ሞላ እንዲሆኑ በዚህ መንገድ መሄድ አለባቸው? የአገሪቱ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ከመጫወቻ ሜዳው ውጭ የተፋቸው፣ በትምህርት ቤት ገበታ መገኛ፣ ባልጠነከረ ሰውነትና ጉልበታቸው፣ ባልተፈታ አፋቸው መግባቢያ ማድረግ በማይችሉት ቋንቋቸው፣ መብትና ግዴታቸውን በውል በማይገነዘብ የዕውቀት ደረጃቸው እንደ ሕፃናት መቦረቅያ ጊዜያቸው ነገ ትልቅ ሰው የሚሆነው እንደ በቀለ ሞላ ለመሆን የላቦራቶሪ ሙከራ ቢደረግባቸው ችግሩ ምንድነው የሚሉ አያሌ ናቸው!
የእኔ ጥያቄ እነዚህ ሕፃናት ምን ኃጢዓት ቢሠሩ ነው ጦርነት፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ የመንግሥት መዋቅር መክሰም ወይም ሌላ ተፈጥሯዊ ከባድ አደጋ ካልተከሰተበት የወላይታ ክልል በኢትዮጵያ ጎዳናዎች እንዲህ መብረቅ እንደበተነው ፍየል የተበታተኑት? አባቶቻቸውስ ምን ኃጢአት ቢሠሩ ነው ልጆቾቻቸው ለዚህ ሰቆቃ ሲዳረጉ ቁጭ ብለው እያዩ መቆዘማቸው? ችግሩ የማንነው? የቱ ጋ ያለ መስተጋብር ተሰብሮ ለዚህ ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ ያስገባን? ችግሩን በአንድ አካል በአጭር ጊዜ ሊፈታ የሚችል ነውን? ችግሩ እንዲፈጠርስ ድርሻቸውን ያበረከቱት አካላት እነማን ናቸው? ጥያቄው ማለቂያ የለውም? ችግሩን የኢትዮጵያ አንዱ የማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግር ነው ብሎ የሚረዳ መሪዎችስ አሉን ወይ?
ብዙ ነቢይና ፓስተር፣
ብዙ ሰባኪና ዘማሪ፣
ብዙ ዶክተርና የተማረ ሰው፣
ብዙ ሙዚቀኛና የጥበብ ሰው፣
ብዙ አማኝና ሠራተኛ ለፍቶ አዳሪ በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ እንዴት እንደዚህ ዓይነት አሰቃቂና የሚጋጭ ሁነት በዚህ ልክ ጎልቶ ሊፈጠር ይችላል?
ችግሩስ በለጋስነት አንድ የኪዊ ቀለም ገዝቶ በመጣል የሚፈታ ነው? በአንድ ቀን እዝነት በምትሰጠው አሥር፣ መቶ ወይም ሁለት መቶ ብር የሚፈታ ነው? ያረጀ ልብስህንና ጫማህን አውጥተው ስለ እግዜር በመጣል ወይም አንድ ቀን ሰብስቦ ምሳ በመጋበዝ የሚፈታ ነውን፣ እርዛታቸውና ረሃባቸውን በዚህ መንገድስ መፍታት ይቻላልን? እንዲህ ሁኑ እንዲህ አታድርጉ ብሎ ሌክቸር በማድረግ የሚፈታ ነው? ይኼ ከንፈር መምጠጥ ካልሆነ በስተቀር 20 እና 30 ሆነው በአንድ በአውቶቡስ ተራ፣ ሃናማርያም፣ ጉርድ ሾላ፣ በጠባብ ክፍል ውስጥ በድርድር እየተኙ ጎህ ሳይቀድ በአሠሪዎቻቸው የጉልበት ብዝበዛ ወደ ተፈረደባቸው ሥራ እየተሰማሩ ከመኖር አያግዳቸውም፡፡ ከአሠሪዎቻቸው ከጉልበት ብዝበዛ የሚጣል ፍርፋሪ ካለ በልተው ያም ካልኖረ ደግሞ ከሆቴል ቡሌ ለምነው፣ ያን ካጡ ደግሞ በፈጣሪ ስም ለምነው ያንንም ካጡ በረሃብ ከመሞት በሕይወት የመኖር ደመ ነፍሳዊ ዕርምጃ እየወሰዱ ዕለቱን ከመግፋትና ከመኖር ያለመኖር ጋር ጦርነት ገጥመው እየወደቁ እየተነሱ ከመኖር አያተርፋቸውም።
ጥያቄው እነዚህ ሕፃናትና ወጣቶች የኢትዮጵያ ዜጎች አይደሉም ወይ? በአገሪቱ ውስጥ ይህን ጉዳይ በግንባር ቀደምትነት እንዲከተታል በአዋጅ ሥልጣን የተሰጠው ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለምን እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አያያቸውም? የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ለምን እንደ ኢትዮጵያውያን ቆጥሮ በዓመታዊ ዕቅዱ ውስጥ ሊያካትታቸው አልቻለም? የጤና ሚኒስቴር በጎዳና ላይ በሚኖረው የኑሮ ስቃይ ለተለያዩ የጤና እክሎች ለአስገድዶ መድፈር፣ ለእርግዝና፣ ለኤችአይቪና ለሌሎች አባለዘር በሽታዎች የሚዳረጉ ወጣቶች፣ አፍላ ወጣቶችና ሕፃናት ጉዳይ ለምን አይገደውም ለምን እንደ ዜጋ አያያቸውም? ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ፍኖተ ካርታው ትልም ውስጥ አቅፏቸው ‹‹አንድም ሕፃን ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆን የለበትም›› የሚለው ዓለም አቀፍ ፖሊሲ ወደ እነዚህ ልጆች ሲደርስ አቅሙን ለምን ያጣል?
ጥያቄው ባንክና ታንኩን ከቁጥጥሩ ሥር ያደረገው እስከ አፍንጫ ባደራጀው የሳይበር ሠራዊት ውዳሴ ማህሌት የሚወርድለት፣ የያሬድ ዜማ የሚደረደርለት መንግሥት ብልፅግና ለምን የእነዚህን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው ከደቡቡ የአገራችን ክፍል 90 በመቶ ደግሞ ከወላይታ የፈለሱ የጎዳና ላይ ሰቆቃ የሚመሩ ወጣቶች አፍላ ወጣቶችና ሕፃናት የኢትዮጵያ ዜጎችን ጉዳይ ከአገሪቱ አንገብጋቢ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳ ቆጥሮ ሥራ ለመሥራት የለገመ መርፌ ቅቤ አይወጋም ዓይነት ልግመኝነት ያዘው ነው!!
በሺዎች የሚቆጠሩ የላይኛው መደብ ዜጎች ልጆች እንዲሞላቀቁበት ቢሊዮን ዶላሮች ለቅንጡ ፓርኮች ሲያፈስ ጀግንነት የሚሰማው መንግሥት፣ በመቶ ሚሊዮኖች የመሠረተ ልማት መጣል በእጁ መዳፍ ውስጥ ያለ አቅም ሆኖ የሚገኘው መንግሥት፣ ለምን በአፍንጫው ሥር እንደ ዳሸን ተራራ የገዘፈውን ችግር ላለማየት ‹‹የእናቴ ቀሚስ…›› ለመጫወት ዳዳ ነው፡፡
በመስኮታቸው ከውጭ ወደ ውስጥ እንጂ ከውስጥ ወደ ውጭ ማየትን በማይከለክሉት እስከ ሃያ ሚሊዮን ብር ተመዥርጦ በሚገዙት ቪ8 አሊያም ቪ9 መኪኖች በእነዚህ ጎዳና ሕፃናት ድንጋይ በከነዱበት የሚርመሰመሱት የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሕዝባቸው ተወካዮች ናቸው ብሎ መውሰድስ እንዴት ይቻላል? የእነዚህን ዜጎች ሰቆቃ እንዳላዩ ለማለፍ የሚያስችል ክህደት፣ እንዳልሰሙ ለማለፍ የሚያስችል የኢሞራል ድፍረትስ በምን ቃላት ሊገለጽ ይችላል? የዚህን ችግር ጥልቀት ስለማያውቅ ነው ወይስ የዚህ ሕዝብ ችግር የሚያሳስብ ሆኖ ስላልተሰማነው ዝምታን የመረጠው ነው፡፡
በዚህ በምንኖርበት ከተማ አዲስ አበባ፣ በኮንዶሚንየም ግንባታ መሬታቸውን ተነጥቀው የነበሩ አዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን አርሶ አደሮች፣ ወንዶች በሀብታም ቤት ጥበቃ፣ ሴቶች የቤት ሠራተኞች ሆነው ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ የገቡ የኦሮሞ ወንድሞቻችንን ለማቋቋም፣ ቤት አልባዎችን ከእነልጆቻቸው፣ ሲለጠጥ የአክስትና የአጎት ልጆቻቸው ድረስ አዱገነት ላይ ፀሐይ በሞቀው ሁናቴ የኮንደሚኒየም ቤት ለማደል፣ የከተማ ግብርና ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዲሳተፉ፣ የሥራ ዕድል እንዲጠቀሙ ለማድረግ በምን ያህል ቁርጠኝነትና ትኩረት እንደተንቀሳቀሰኮ ዓይተን፣ ታሪክ መዝግበንና ከትበን ያደርን እኛ የእነዚህ ብላቴናዎች ሰቆቃ ከቁብ የሚቆጥር አመራር በጠፋበት አገር ውስጥ የዜግነት ደረጃቸውንስ መጠየቅ ነውር የሚሆነው በየትኛው የሞራል ሕግና በየትኛው ሸንጎ ፍርድ ነው?
ከዚህ የዕለት ጉርስ አግኝቶ ለማደር ከሚደረገው የከተማ የኑሮ የጦር ሜዳ ውሎ የሚያስጥላቸው ጠፋ? የእኔ ሕዝብ ነው ብሎ የሚንቀሳቀስ ባለቤት እንዴት ጠፋ ነው ጥያቄው፣ ዜጋዬ ናቸው የሚል አመራር፣ ባለሀብት፣ አርቲስት፣ መያድ፣ የሃይማኖት ተቋም፣ ዓለም አቀፍ አሊያም አገር አቀፍ ድርጅት እንዴት ካገሩ ታጣ ነው ጥያቄው? ችግራቸው የልጄ ችግር፣ ረሃባቸው የልጄ ረሃብ፣ ሰቆቃቸው የልጄ ሰቆቃ ነው ብሎ መቀበል የሚችል ልብ ያለውስ መሪ እንዴት ባገሩ ተሰለበ ነው ጥያቄው!
ወላይታ ላይ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ብልፅግናም ይሁን ቱሳ ወይም ሶህዴፓ ይሁን ወህዴግ፣ ወብንስ ይሁን ኢዜማ ለምን ይኼን እንደ አንኳር የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቁጠር ዳተኝነት ውስጥ ገቡ ነው ጥያቄው? ባልደራስና አብን አዲስ አበባ ሲወዳደሩ ችግሩን እንደ አገር አቀፍ ችግር በመቁጠር እንዴት በማኒፌስቶ ውስጥ ለማመልከት ሸከካቸው ነው ጥያቄው፣ ኢዜማ የሚያልማት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚነሱ ችግሮች ውስጥ እንዴት የዚህን ችግር ከዝርዝሩ ውስጥ አጣው ነው ጥያቄው፣ ለነገሩ ወንድሜ አሁን አሁን የመንግሥት ሹማምንት የሚያዳምጧቸው ምሁራን በብዕራቸው ጫፍ የመበልፀግ መንገድ በእሳት የተፈተነ እንደ በቀለ ሞላ እንቁላል ከመሸጥ ሲነሳ፣ እንደ ዓለም ትላልቅ ራፐሮች ከጎዳና ላይ የጭቅቅት ኑሮ ሲመዘዝ ነውና ተውዋቸው ለፍተው ይሳካላቸው ብሎ ዕውቀቱን በብዕራቸው ጫፍ እያመረቱ ከመምከር ሳይቆጠቡ ይኼንን ሐሳብና አቋማቸውን ያለምንም ኃፍረት በአደባባይስ ያራመዱ ፖሊሲ አውጪዎች ዓይናቸው ለምን ተከደነ ብለን ብንደነቅ ስህተቱ እኛው ጋ ነው፡፡ ጉድጓድ ሥር ለተገኘው ሰው መሪው ማነው ነው ብሎ ጥያቄ እንደው ለቀባሪው ማርዳት ካልሆነ ሌላ ምን ኖሯል ይሆናል?
ለመሆኑ በአዲስ አበባ ላይ ከሚሠራው ወንጀል ከዚህ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ጋር የተቆራኘው ከ90 በመቶ በላይ እንደሆነ መረጃው ያለው ሰው ምን ያህል ነው? በየጉራንጉሩ የሚደረገው የማጅራት መቺነት ወንጀልስ ምንጩ ይህ አስደንጋጭ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሰቆቃ መሆኑስ ጥናት የሚያሻው ጉዳይ ነውን? ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ጎዳናዎች በፍልሰት ምክንያት በሰቆቃ ሕይወታቸውን የሚመሩ ወላይታውያን ቁጥር አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ የእነዚህ ወጣትና ሕፃናት ሴትና ወንድ ወላይታውያን በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ ሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ መቂ፣ ቢሾፍቱ፣ አፋር ሎጊያ፣ ቤኒሻንጉል አሶሳ፣ ባህር ዳር ውስጥ በሊስትሮ ሥራ፣ በግንባታ የቀን ሥራ፣ በሎተሪ ማዞር፣ በሸክም፣ በሚዛን ሥራ፣ ሴቶቹ ገላ በመሸጥ፣ በቤት ሠራተኝነት፣ በዕጣ ማጫወት፣ በመንገድ ላይ ንግድ፣ በብረታ ብረትና የሃይላንድና የመጠጥ ውኃ ፕላስቲክ በመሰብሰብ፣ በቆራሊዮ፣ በመኪና እጥበት፣ በረዳትነት የተሰማሩት ቁጥራቸውንስ ምን ያህል እንደሆነ ይታወቃልን? በኢትዮጵያ ውስጥ ለእነዚህ ሥራዎች ተመልምለን ብቁ ሆነን የተገኘንበት ታሪካዊ ግጥምጥሞሽንስ የሚቆረቁረው ምን ያህሉ ሰው ነው?
ይህን መጠየቅ አይገባም? መንግሥትስ እንደ ዜጋ ስለማይቆጥራቸው ሕገወጥ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል ብሎ ለሊስትሮው የቀለሳትን የበረንዳ ጥላ ያፈርስበታል፣ መንገድ ላይ አዟሪውን ብረቱን ይዘርፍበታል፣ ከዕጣው አዟሪ ዕጣውን ይመነትፈዋል፣ ከመንገድ ላይ ነጋዴው ሽንኩርትና ቃሪያ ሳይቀር ወስዶ ይበትንበታል፡፡
አንተ እዚህ መጥተህ ስለሥራ ክብርነት ሌክቸር ልታደርገኝ ትሞክራለህ፡፡ መጽደቁ ቀርቶብኝ አለች ዳልጊቴ! በሥራ ክቡርነት ሰነፍ ከሆነና ቁጭ ብሎ ከሚበላ ሰው ውጭ ማን ላይስማማ ይችላል? የተሻለ ሥራ መመኘት፣ ሥራ ከማያከብሩት ጋር እየተዋጋ ከመሥራት ይውጣ ብሎ ማለትስ ሥራን መናቅ ሆኖ ሊቆጠር ይችላል? አልገባኝም፡፡
ነገር ግን ዋናው ነገር ወዲህ ነው፡፡ አማራጮች ተዘግተውበት የፋብሪካ ሠራተኛ መሆን የሚችል ሰው ሊስትሮ፣ ሐኪም መሆን የሚችል ሰው ሎተሪ አዟሪ፣ ጥሩ ኢንጂነር መሆን የምትችልን ልጅ የወሲብ ንግድ ላይ እንድትገኝ፣ ጥሩ ኮንትራክተር መሆን የሚችል ወጣት የባሬላ ተሸካሚ፣ ጥሩ አርቲስት መሆን የሚችል ልጅ ማጅራት መቺ፣ ጥሩ ነጋዴ መሆን የሚችል ልጅ መንጩ ሰሪ፣ ጥሩ ማኔጀር መሆን የሚችል ልጅ የብረት ቁርጥራጭ ሰብሳቢ እንዲሆን ያደረገው ብዙዎች እንደሚያስቡት ‹‹ልጅ በዕድሉ ያድጋል›› ከሚባለው ስንኩል አስተሳሰብ የመነጨ ብቻ አይደለም ይህ ውጤት እንዲመጣ ያደረገ፡፡ የማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት ዝንፈት ውጤት እንጂ፡፡ ይህ ሥርዓት ይህን ፍዳ ፈርዶ አስገድዶ ሲያበቃ በመስኮት በኩል አጮልቆ ማንኛውም ሥራ ክቡር ነው ብሎ የሽንገላ ዓይነት አይነ ደረቅነት ሽሙጥ ጣል ያደርግብሃል፡፡ ይኼ አፓርታይዳዊ ስላቅ አይገባኝም፡፡ በዚህም ስላቁ እነዚህን ዝቅ ተብለው የሚሠሩ የዕለት ጉርስ ለማግኘት የሚሠሩ አነስተኛ ሥራዎች ሕገወጥ ናቸው ብሎ ፈርጆ ሲያበቃ ሠሪዎችን ከመኪና ጋር እያጋጨ ሲያባርርና ሲያስር ዕቃቸውን ሲዘርፍ ይውልና ማታ በቴሌቪዥን ብቅ ብሎ የሥራ ወዳዱ ምናምን እያለ ቢደሰኩርብኝ ታይታ ነው እልሃለሁ፡፡ ጫፍ የወጣ ግብዝነት…. ምን ያድርጉ አይብሉ ይሙቱ ምንስ አማራጭ አዘጋጅቷል?
ለመሆኑ አሁን ስሙን መጥራት በማልፈልገው ክፍለ ከተማ ብቻ በአንድ ወረዳ በቅርቡ መጥተው በተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩ ከ90 ሺሕ በላይ ወላይታዎች ለምርጫ ቅስቀሳ በነበረው መረጃ በብሎክ መመዝገባቸውን፣ ይህ ተሰምቶ ሰዎች መደንገጣቸውንስ ይነግሩህ ይሆን፣ አዲስ አበባ ላይ ቅድመ ምርጫ የተሰበሰበው መረጃ የወላይታዎች ቁጥር ወደ ሦስተኛ ቁጥር ከፍ ያደረገ መሆንስ ያሳውቁህ ይሆን ወይስ እንደው ውዳሴ ብቻ ነው የሥራ ዘርፉ?
አሁንኮ የቸገረን ነገር ችግሩን ችግር እንደሆነ ለማመን ዝግጁ የሆነ መሪ ማጣታችን ነው፡፡ በወላይታ ምርጫ የሚወዳደሩት ዕጩዎች ይህ ጉዳይ አይመለከታቸውም? ጥቁር መስተዋት ያለው ቪ9ቸውን እያሽከረከሩ በጎናቸው ስለሚያልፉ ጉዳዩ አይመለከታቸውም ማለት እንችላለን? አባቱ ከሚኖርበት ቀዬ አይደለም የዚህ ልጅ ውልደት? አባቱ ከሚያመልክበት ቤተክርስቲያን አይደለም የዚች ልጅ አመጣጥ፣ ከእናቱ ቀበሌ አይደለም የዚህ እንቦቃቅላ ልጅ መሰደድ፣ ከእህቶቹ ትምህርት ቤት አይደለም የዚች ሴት ልጅ ትምህርት አቋርጦ መምጣት? በሷስ ስም ጭምር አይደለም ወይ በጥቁር ጎማ ባለው ቪ8 የሚሄደው? እሱ ወርዶ አለሁላችሁ ያላለ? ያላጽናና እና ችግራችሁን አውቃለሁ ያላለ? ማን እንዲመጣ ነው ሪኮመንዴሽንህ? ይኼን እንኳን እንዴት ከአቢቹ መኮረጅ ያቅታቸዋል?
እነዚህ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ሥራ አጥ ወገኖች ማኅበራዊ መሠረቴ ናቸው ብሎ መጥቶ ማናገር እንኳ ጽድቅ ቢሆን፣ በአንድ ምርጫ ቅስቀሳው ውስጥ አካቶ ያወራ ግለሰብና ዕጩ እንዴት እናጣለን? ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይህን አድርገዋል? በየዕለቱ ይኼን ትዕይንት እንደ በቅርበት የሚመለከቱት ይህንን አድርገዋል? የእኛው ተወካዮች ስለምርጫ ቅስቀሳ ባነር፣ ቢልቦርድ፣ ቲሸርት ሕትመት ላይ ሚሊዮኖችን በመከስከስ ውስጥ ለሰከንድ የህሊና ማስታወስ እንኳን ማድረግ ማንን ገደለ? በየአዳራሹ ግብዣ ላይ በየአደባባዩ ሩጫ ላይ ከመኳተን ውጭ የእነዚህን ልጆች ችግር መንግሥት የሚያውቀው ችግር ነው፣ ፕሮጀክት ተቀርጾ ይፈታል ብለው ለማሰብ ጭንቅላታቸውን ለሰከንድ አሠርተዋል? ኢዜማ ይኼ ችግሬ ነው ብሏል? ሌሎችስ ዝርዝራቸውን መዘርዘር የሚደክመኝ ፓርቲዎችስ ይኼን ለማሰብ አስበዋል? አልቻሉም፡፡ አይችሉምም ምክንያቱም በሞቀ ቤታቸው የተቀመጡ የእነዚህን ችግር ወደ አደባባይ ማውጣት የሚገባቸው፣ እንደ ማኅበራዊ ችግር አጥንተው የችግሩን ጥልቀት ለመንግሥትና ለፖሊሲ አውጭዎች ማሳየት ያለባቸው ሰዎች ‹‹አንዱን እግሬን ጅብ እየበላ ነውና እስኪጨርስ ዝም በል ድምፅ ካሰማህ ሰምቶ ወደ አንተ እንዳይመጣ›› ዓይነት የለሆሳስ ንግግር ራሳቸውን አስገዝተው ዝም! ጭጭ! ብለዋልና፡፡
የራሱ ተወካይ ልሂቃን የሕዝብ ተወካዮች ምሁራንና ማኅበራዊ አንቂዎች ችግር ነው ብለው ያልተስማሙበትን ነገር እንዴት አንድ መንግሥት አይደለም አንድ ተራ ግለሰብ ችግር ነው ብሎ ሊያምንና ሊያሳምን ይችላል፡፡ ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም ነዋ ከነተረቱ… ለመሆኑ ከትምህርት የተገለሉ መሆናቸው ሊያሳስበን አይገባም? የጤና አገልግሎትስ የት ያገኛሉ የሚለው ሊያሳስበን አይገባም? እንደ ዜጋ የሚቆጠሩ ናቸው ወይ የሚለው ሊያሳስበን አይገባም? የሚደርስባቸው የጉልበት ብዝበዛ፣ ስድብ፣ ማንጓጠጥ፣ መብት ረገጣ ሊያሳስበን አይገባም? ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ወንዶች የሚደርስባቸው የመደፈር ችግር፣ ለሃሺሽ ሱሰኝነት፣ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት የተዳረጉ ወጣቶች ጉዳይ ሊያሳስበን አይገባም? ይህ ሁሉ ችግር ባለበት ይኼን ችግር የሚያስተናግድ ተቋም የማጣት ጉዳይ አያሳስበንም?… ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የተጠኑ የተወሰኑ ጥናቶች አሉ፤ ማጋራት እችላለሁ፡፡ ሕይወታቸው እጅግ አሳዛኝና ሰላማዊ ከተማ ላይ በየዕለቱ የሚደረግ ቀውስና ሲዖል ውስጥ የሚደረግ ነውና በዚህ ውስጥ ደግሞ ተረግዘው ተወልደው የሚያድጉ የነገው ኢትዮጵያውያንም አሉበት፡፡
ስደተኞች ዓረብ አገር ስለሄዱ ብቻ ነው የስደተኞች ቆንስላ ተቋቁሞ ችግራቸውን ማየት ያለበት? ከዓረብ አገር የበለጠ የኑሮ ስቃይ ውስጥ ያሉ እዚህ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የዚህ አገር ዜጎች ጉዳይ ለምን አያሳስበንም? ቋንቋ አያውቁ፣ ቀበሌ አያውቃቸው ትምህርት ቤት አያውቃቸው፣ ሆስፒታል አያውቃቸው፣ የሚሠሩት ሥራ ተመን አያውቁት፡፡ የመብት፣ ረገጣ ስድብ ሲያልፍም ዱላ፣ ያለምክንያት መታሰር፣ ከሁለቱም ወገን ይደርስባቸዋል፣ ታጉረው ነው የሚኖሩትና ጅዳና ኦማን መገኘት አለባቸው ስደተኛ ለመባል? አዲስ አበባ ፊንፊኔ፣ ቱንጋ እና በረራ ትባል የለም እንዴ? ጆሮ ያለው ይስማ ችግሩ ከሁላችንም በላይ ነው፡፡ ሁላችንም ካልተሠለፍን የማንፈታው ነው… በአንድ ወቅት የአማራ ክልል መንግሥት ተመሳሳይ ችግር እንደገመጠው በውል ተገንዝቦ ብዙ ሚሊዮን ብሮች መድቦ በ120 አውቶቡሶች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሕይወታቸውን በተለያየ መንገድ የሚመሩ አማራዎች ወደቀያቸው ለመመለስ ሲንቀሳቀስ አላየንም?? ዓይኔን ግንባር ያድርገው ካልተባለ በስተቀር!
እንደው… ይኼን ነገር በውል ተገንዝቦ መሥራት የሚችል ሰውና መዋቅር ማግኘት ባንችል ችግሩ እንዳለ ሐሳብ የሚያነሱትን ሰዎች ከመዝለፍ፣ ብዙ ከመማር ይልቅ በብዙ አታካራና ስም ልጠፋ ጊዜ ማሳለፍ ምን የሚሉት ማወቅ እንደሆነ ግራ ይገባኛል፡፡ ከአምስት ሚሊዮን የሚልቀው የአዲስ አበባ ሕዝብ የሚያውቀውን፣ ፀሐይ የሞቀውን፣ አገር ያወቀውን ሃቅ ችግር በማኅበራዊ ሚዲያ ሁለትና ሦስት ሺሕ ሰው ላይክና ሼር እንዲያደርግ አድርጋችኋልና በፎቶ ለጥፋችኋል ብሎ የሥነ ምግባር መምህር ሊቅ ሆኖ ራስን መጀቦን አይታየኝም፡፡
ይህ ችግር እንደ ሌለ ማስመሰል ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ዓይነት ግብዝነት ይመስለኛል። የእነዚህም ልጆች ምስል ወይም ፎቶግራፍ ለጥፎ ችግር አለ ብሎ የሚቻለውን ከመጮህ ውጪ ገንዘብ በስማቸው ሰብስቦ ለግል ጥቅም ያዋለ ሰው የሞት ፍርድ ባይደገፍም የብዙዎች ሞት ምክንያት ነውና የማያንስ ቅጣት እንዲጣልበት ይሞገት እንጂ፣ አይ ሁሉ ሸጋ ነው አገር በብልፅግና ጎዳና ላይ ነው፣ ብሎ ተስፋቸው ጨልሞ ሰቆቃ ውስጥ ኑሯቸውን የሚገፉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይን እያዩ ዝም፣ እየተመለከቱ ልጉም ማለት ከህሊና ጋር የሚደረግ የአድር ባይ ሙግት ይሆናል፡፡ በፎቶ ብቻ አይደለም የሚላስ የሚቀመስ አጥተው የወደቁ፣ ቀባሪ ማዘጋጃ ቤት አጥተው በአዲስ አበባ ጉራንጉርና ጥጋ ጥግ ሁሉ ወድቀው የጅብ መንጋ ሲሳይ የሆኑት አደባባዩ ይቁጠራቸው፡፡ ይህን ሰቆቃ በምርመራ ጋዜጠኝነት ፈልፍሎ ለእንደራሴዎች ሸንጎና ለፖሊሲና ስልት ተላሚዎች ለማድረስ የምንወጣው የሊማሊሞ ዳገት ምንኛ እንጦረጦስ ነው? ከዜግነት ግዴታው ባሻገር?!
ይህን ያለመታከት በመሥራት ከእናንተ የጉዳዩ ባለቤቶች ጭምር የሚደርስብኝን ዘለፋ ብችል በዚህ ሥራዬ አንድ ቀን መንግሥት ራሱ፣ በዶ/ር ዓቢይ አህመድ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ የእነዚህን ተጎጂ የኅብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት ያደረገ ፕሮጀክት ነድፎ ሥራ ላይ እስከሚያውል ድረስ ጥረቴን እቀጥላለሁ፡፡
ነገር ግን ከመንግሥት የሚጠበቅ ሲሳይ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በያገባኛል መንፈስ ከሚሰበሰቡ ማናቸውን ስብስቦች ጋር በመሆን ችግሩን ማቃለል የሚቻልበት ሁኔታን ለመፍጠር እማስናለሁና ጽናቱን ይስጠኝ፡፡ ይኼ ጩኸትም ጫጫታም አይደለም፡፡ የራሱ ልጅ ሳይሆን የአጎትና የአክስት ልጅ እዚህ ውስጥ ቢኖር ሊኖር የሚችለውን መሯሯጥና ጩኸት የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ችግር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ነው፡፡ ችግሩ ከግለሰብም ከአንድ ተቋምም በላይ ነው፡፡ ለመፍታትም በዋናነት የመንግሥትና የሁሉንም የጋራ ግንባር መፍጠርን የሚሻ፣ ከሠራን ሊለወጥ የሚችል ክደን ቁጭ ካልን ሊቀጥል የሚችል ነው፡፡
ስለዚህም የመጀመሪያው ሥራ በችግሩ ችግርነት ዙሪያ ግልጽ አቋም መያዝ፣ እንደ ሕዝብ ቀጣይ ሊያጠፋ በሚችል አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መገኘታችንን ማመንና ሁሉ አቀፍ ወደሆነ የማኅበረሰብ ትራንስፎርሜሽን የሚወስዱ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ወደፊት ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ወደ መፍትሔው መምጣት አይቻልም፡፡
- ምሁራን የችግሩን ጥልቀት አጥንቶ የማቅረብ የተሠሩ ጥናቶችን መፈተሽ አዳዲስ ጥናቶች ማድረግና የችግሩን ጥልቀት በአግባቡ መረዳት የሚያስችልና ችግሩን መፍታት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ለመቅረጽ የሚያስችሉ መረጃዎችን ማቅረብ፣
- የፕሮጀክት ሰዎች ይህን ችግር ለዘለቄታው የሚፈታ ፕሮጀክት መንደፍና መቅረጽ፣
- የመንግሥት ሰዎች ፖለቲካዊ ውግንና በማሳየት ችግሩ የሚፈታበት አግባብ ለመፈለግ በእውነተኛ ቁርጠኝነት መቆምና ሀብት ማፈላለግ፣ የመሠረተ ልማቱን ችግር መፍታት፣ ይኼን ችግር የሚከታተለው መዋቅር ከተኛበት የረዥም ጊዜ እንቅልፍ እንዲነቃ ማድረግ፣
- ባለሃብቶች የወላይታ ወጣቶች ትረስት ፈንድን በአንድ ቋት ሞቢላይዝ በማድረግ የሀብት ማሰባሰብ ሥራ ውስጥ መግባት፣
- የልማት ማኅበሩ ይኼን ሥራ እንደ አንድ አቅጣጫ ይዞ የመሪነት ሚናውን መወጣት፣
- የፀጥታ አካላት በሕፃናት ንግድ ላይ የተሰማሩትን አካላትን መረብ መበጣጠስና የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ ወደ ሕግ እንዲቀርቡ ማድረግ ላይ መሳተፍ ቢችሉ መልካም ነው እላለሁ፡፡
በግሌ ለዚህ ሐሳብ ተግባራዊነት የሚጠበቅብኝንና የምችለውን በሙሉ ለማድረግ ዝግጁም ቁርጠኛም ነኝ፡፡
ምን እንደማስብ ታውቃላችሁ በሊቃ ትምህርት ቤት ብቻ በሁሉም ወረዳዎች ብንገነባ ከእነዚህ ልጆች ከግማሽ በላዩን ዶክተርና ኢንጂነር ማድረግ እንችላለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ከቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ብቻ በቂ ትምህርት ማግኘት ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው mengemeku@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡