Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሙግት የነገሠበት የኅብረት ኢንሹራንስ ጠቅላላ ጉባዔና ውሳኔዎቹ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከፍተኛ ሙግት የነገሠበት የኅብረት ኢንሹራንስ ጠቅላላ ጉባዔ ክርክር የተነሰባቸው ጉዳዮችን በድምፅ እንዲለዩ በማድረግ የኩባንያውን ካፒታል ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰነ። ለዚህ ዓላማ የሚውሉ 150 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አዲስ አክሲዮኖች ለአዲስ ገዥዎች እንዲተላለፉም ውሳኗል፡፡ 

ኢንሹራንስ ኩባንያው ባለፈው ሐሙስ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የኩባንያውን ካፒታል አሁን ካለበት የ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት ከማግኘቱ በፊት አተገባበሩን የተመለከተ ሙግት በባለአክሲዮኖች መካከል ተፈጥሮ ነበር። 

የኢንሹራንስ ኩባንያውን ካፒታል ለማሳደግ ከሚወጡ አዲስ አክሲዮኖች ውስጥ 100 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለተመረጡ 30 ኩባንያዎች እንዲሸጡ የኩባንያው ቦርድ ሐሳብ ማቅረቡ ባለአክሲዮኖችን አከራክሯል።

 በዕለቱ የኢንሹራንስ ኩባንያውን ካፒታል ለማሳደግ የፈለገበትን ምክንያት የሥራ አመራር ቦርዱ ካብራራ በኋላ እንዲጨመር የታሰበውን የአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማሟላት አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያላቸው አንድ ሚሊዮን አዲስ አክሲዮኖችን ለሽያጭ ለማቅረብ መታቀዱን አስታውቋል። አዲስ ከሚወጡት የአንድ ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ውስጥ 900,000 ብር የሚያወጡትን ነባር ባለአክሲዮኖች ባላቸው የአክሲዮን ይዞታ ምጣኔ ተደልድሎ እንዲሸጥላቸው የስራ አመራር ቦርዱ ለጠቅላላ ጉባዔው ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ቀሪውን 100 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አዲስ አክሲዮኖች ደግሞ ከኢንሹራንስ ኩባንያው ጋር የሥራ ግንኙነት ላላቸው በጥቅሉ 30 ለሚሆኑ ኩባንያዎችና ግለሰቦች በ30 በመቶ የፕሪሚየም ክፍያ እንዲሸጥላቸው ቦርዱ ሐሳብ አቅርቦ ነበር። በቦርዱ የቀረበው ይህ ሐሳብ ግን ባለአክሲዮኖችን ለሁለት ከፍሎ አከራክሯል፡፡ 

አንዳንድ የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ለተጠቀሱት 30 ኩባንያዎችና ግለሰቦች አዲስ አክሲዮኖች እንዲሸጡላቸው በሚል የቀረበውን ሐሳብ በመቃወም አዲስ የሚወጡት አክሲዮኖች ለውጭ ሰው መሸጥ የለበትም፣ በሙሉ በሙሉ ለነባር ባለአክሲዮኖች እንዲተላለፉ መደረግ አለበት የሚል ክርክር አንሰተዋል።

ቦርዱ ግን እነዚህ አክሲዮን ሊሸጥላቸው ይገባል ብሎ በዝርዝር ያቀረባቸው 30 ኩባንያዎችና ግለሰቦች ለኩባንያው እየሰጡ ያሉትን ጠቀሜታ በአኃዝ ጭምር በማስደገፍ በማብራራት ለእነዚህ አካላት አክሲዮን መሸጥ አሁን ካለው ውድድር አንፃር ኩባንያውን ይጠቅማል የሚል አመክንዮ አቅርቧል። እንደውም አንዳንዶቹ የኩባንያው አጋሮች ለኩባንያው እያበረከቱ ያለውን ጥቅም በመጥቀስ አክሲዮን በመግዛት ባለድርሻ ለመሆን መጠየቃቸውን ቦርዱ አስረድቷል። በመሆኑም የኩባንያውን ጥቅም ለሌላ ከማሳለፍ ለጠቀሱት ኩባንያዎች የአክሲዮን ድርሻ መሸጡ የበለጠ እንደሚጠቅም አስረድተዋል፡፡ 

በተለይም የኢንሹራንስ ኩባንያው ዋነኛ አደራጅ በመሆን የሚጠቀሱት ታዋቂው የኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ በቦርዱ የቀረበውን ሐሳብ ቢደግፉም ለኩባንያው ዋነኛ ደንበኞች የሚሸጠው የአክሲዮን ድርሻ 150 ሚሊዮን ብር መሆን እንዳለበት ሞግተዋል፡፡ ይህንን ሐሳብ ለማቅረብ የተገደዱባቸውን ምክንያቶቻቸውንና ከሙያ አንፃር ጠቀሜታውን በዝርዝር ያቀረቡት አቶ ኢየሱስወርቅ ኩባንያውን ሊደግፉ ለሚችሉ ኩባንያዎችና ግለሰቦች ሊሸጥ የሚገባው የአክሲዮን መጠን መቶ ሚሊዮን ብር ብቻ እንዲሆን መወሰን የለበትም በማለት 150 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖች ቢሸጡ ለኩባንያው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉ ተከራክረዋል። የአቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉን ሐሳብ ከደገፉ ባለአክሲዮኖች መካከል የቀድሞ የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ይገኙበታል።

የአቶ ኢየሱስወርቅን ሐሳብ የተቃወሙ ባለአክሲዮኖች ደግሞ አክሲዮን ይሸጥላቸው የተባሉ ኩባንያዎች የተባለውን ውጤት ሊያስገኙ መቻላቸውን እንደሚጠራጠሩ በመግለጽ ተሟግተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለአዲስ ገዥዎች ይሸጡ የተባሉት አክኪዮኖች መጠን ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ሐሳቡን የተቃወሙና ሐሳቡን የደገፉ ባለአክሲዮኖች መቀራረብ ባለመቻላቸው ጠቅላላ ጉባዔው ክርክሩ በድምፅ ለመወሰን ተገዷል። በውጤቱም 150 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ኩባንያውን ለሚደግፉ አጋር ኩባንያዎችና ግለሰቦች እንዲሸጡ የሚለው ወገን አብላጫ ድምፅ አግኝቷል።

ከዚህ ስምምነት በኋላ ግን እንደገና ጠቅላላ ጉባዔውን ያሟገተ ሌላ አጀንዳ ተነስቶ ባለአክሲዮኑን ለሁለት የከፈለ ክርክር አስነስቷል፡፡ ይህም የ150 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች እንዲገዙ የሚፈቅድላቸው አዲስ ባለአክሲዮኖች የሚደለደልላቸው የአክሲዮን መጠን ከጠቅላላ የኩባንያው ካፒታል ከአንድ በመቶ መብለጥ የለበትም የሚለው የቦርዱ ሐሳብ ነው፡፡ በዚህ የቦርዱ ሐሳብ ላይ የማይስማሙ መሆኑን ቀድመው የገለጹት አቶ ኢየሱስወርቅ ናቸው፡፡ 150 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን የሚገዙት የተለያዩ ኩባንያዎች የሚይዙት የአክሲዮን መጠን ከኩባንያው ካፒታል ከሁለት በመቶ መብለጥ የለበትም በሚል እንዲስተካከል ተሟግተዋል። አቶ ኢየሱስወርቅ፣ የብሔራዊ ባንክ መመርያዎችን በመጥቀስ ለእነዚህ ሰዎች የሚሰጠው አክሲዮን ከሁለት በመቶ መብለጥ የለበትም ተብሎ ቢስተካከል ለኩባንያው የሚጠቅም መሆኑን ጠቅሰዋል። 

አቶ ኢየሱስ ወርቅ ባቀረቡት ሐሳብ ላይ ተቃውሞአቸውን ካሰሙት የኢንሹራንስ ኩባንያው ባለአክሲዮኖች መካከል አንዱ ኅብረት ባንክ ነው። ኅብረት ባንክ በመወከል በጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተገኙት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ ከበደ 150 ሚሊዮን ብር ጠቃሚ ናቸው ለተባሉ ኩባንያዎች አክሲዮን እንዲሸጥ መስማማታቸውን ገልጸው ፣ አንድ አዲስ ገቢ ባለአክሲዮን የሚገዛው የአክሲዮን መጠን ግን ከጠቅላላ የኢንሹራንሱ ኩባንያው ካፒታል ከአንድ በመቶ መብለጥ የለበትም በሚል ቦርዱ የቀረበውን ሐሳብ በመደገፍ የአቶ ኢየሱስ ወርቅ ክርክርን ተቃውመዋል። 

ለዚህም የሰጡት ምክንያትም ኅብረት ባንክ በኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ ያለውን የአምስት በመቶ የባለቤትነት ድርሻና የመወሰን አቅም ይቀንስበታል የሚል ነው፡፡ ሌሎች ባለአክሲዮኖችም 150 ሚሊዮን ብር ድረስ ለአዲስ ገቢ ባለአክሲዮኖች እንዲሸጥ መፈቀዱን ተቀብለው የባለቤትነት ድርሻቸው ግን ከአንድ በመቶ መብለጥ የለበትም በሚል ተሟግተዋል፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ በበኩላቸው በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ አዲስ የሚገቡት ኩባንያዎች የአክሲዮን ድርሻቸው ከሁለት በመቶ መብለጥ የለበትም ያሉት ኩባንያዎች እስከ ሁለት በመቶ ቢወሰዱ በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ሌላ ኩባንያዎች ውስጥ በተመሳሳይ አክሲዮን መግዛት ስለማይችሉ ከእነርሱ ጋር በይበልጥ ለመሥራት የሚያስችል ዕድል ስለሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ ኅብረት ባንክ ያለኝን ድምፅ ይቀንስብኛል ላለውም ተራፊ አክሲዮኖችን የመግዛት ዕድል ስለሚኖረው በዚያ ሊያካክስ ስለሚችል ምንም ጉዳት አያመጣም በማለት የአቶ መላኩ ሥጋት እንደሚቀርፍ አመልክተዋል፡፡ 

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መሠረት በዛብህ፣ አዲስ አክሲዮኖቹ ከሚሸጡላቸው ሰዎች መካከል በኩባንያው ላይ ከሁለት በመቶ በላይ ድርሻ ቢኖራቸው ኩባንያውን ይጠቅማሉ እንጂ ጉዳት የለውም ብለዋል፡፡ 

ባለአክሲዮኖቹ በዚህ ጉዳይ ላይም መቀራረብ ስላልቻሉ ጉዳዩ በድምጽ እንዲወሰን ተደርጓል። በውጤቱም ኩባንያውን የሚደግፉ 30 ኩባንያዎች የሚገዙት አክሲዮን ከጠቅላላ ካፒታሉ ከሁለት በመቶ አይብለጥ የሚለው አብላጫ ድምጽ አግኝቷል። ጠቅላላ ጉባዔ ክርክር የተሞላበት ቢሆንም ኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ በ2014 የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው ውጤት ግን ከባለ አክሲዮኖቹ ምሥጋና የተቸረው ነበር፡፡ 

ኩባንያው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው የዓረቦን መጠን ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሁለተኛ ደረጃ መቀመጡ አንዱ ሲሆን ያገኘው የትርፍ መጠንም እስከ ዛሬ ከተመዘገበው ሁሉ ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ 

የዓመቱን አፈጻጸም ለጠቅላላ ጉባዔው ያቀረቡት የኢንሹራንስ ኩባንያው ምክትል ቦርድ ሰብሳብ ወ/ሮ ፅጌረዳ ተስፋዬ ኩባንያቸው በ2014 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን 953.91 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ከ30 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ 

በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያው ካሰባሰበው ዓረቦን ውስጥ 860.8 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ሕይወት ነክ ካልሆነ የኢንሹራንስ ዘርፍ ሲሆን ቀሪው 93.08 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰበሰበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በተለይ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ በሁሉም የመድን ሽፋን ዓይነቶች ከፍተኛ ዕድገት የተመዘገበ ሲሆን በተለይ በአቭዬሽን መድን ሽፋን የ908 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡ የማሪን ኢንሹራንስ ደግሞ 58 በመቶ፣ የገንዘብ ነክ ኢንሹራንስ 47 በመቶ፣ የድንገተኛ የኢንሹራንስ ሽፋን ደግሞ 41 በመቶ ዕድገት የተመዘገበበት መሆኑ በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡ 

ኩባንያው በአጠቃላይ ለጉዳት ካሳ ክፍያ የዋለው የገንዘብ መጠን በ21 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ የከፈለው አጠቃላይ የካሳ ክፍያ 349.08 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ በቀዳሚው ዓመት ግን ኩባንያው ለካሳ ቅፍያ አውሎ የነበረው 288.9 ሚሊዮን ብር እንደነበር ምክትል የቦርድ ሊቀመንበሯ ገልጸዋል፡፡ የኩባንያው የካሳ ክፍያ በዚህን ያህል መጠን ለማደጉ ዋነኛ ምክንያት የሆኑት እያደገ ከመጣው የኩባንያው የዓረቦን ገቢ፣ ከተሽከርካሪ አደጋ መብዛትና የመለዋወጫ ዕቃዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 

የኩባንያው የ2014 ከታክስ በፊት 208.2 ሚሊዮን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን ይህ የትርፍ መጠን የ21.5 በመቶ ጭማሪ ያስመዘገበ ሲሆን፣ በዚህም አንድ አክሲዮን (የአንድ ሺህ ብር ዋጋ ያለው ነው) የሚያስገኘው የትርፍ ድርሻ 370.97 ብር ሆኗሎ። ይህም በ2013 የሒሳብ ዓመት ከነበረው 315.56 ብር ከፍ ያለ ነው።

ኩባንያው በተለያዩ ኩባንያዎች ካሉት ኢንቨስትመንቶች በ2014 የሒሳብ ዓመት 173.5 ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን ይህ ገቢው ከቀዳሚው ዓመት 26 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ 

ከዚህ ገቢ ውስጥ ከኢትዮጵያ የጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር ከኅብረት ባንክ 33.05 ሚሊዮን ብር የትርፍ ድርሻ አግኝቷል፡፡ በተወሰነ ጊዜ ለባንክ ካስቀመጠው ገንዘብ ደግሞ 85.26 ሚሊዮን ብር አግኝቷል፡፡ ከተለያዩ ሕንፃዎች ኪራይ ደግሞ 45.82 ሚሊዮን ብር መኘቱን የጠቀሱት ምክትል የቦርድ ሊቀመንበሯ ከሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ካለው አክሲዮኖች ግን ምንም ዓይነት የትርፍ ድርሻ አለማግኘታቸውን አሳውቀዋል፡፡ 

ኅብረት ኢንሹራንስ በኢንዱስትሪው ውስጥ 28 ዓመታትን የቆየ ሲሆን በ2014 የሒሳብ ዓመት ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሁለተኛውን ከፍተኛ የዓረቦን መጠን ማሰባሰብ የቻለ መሆኑ ተገልጿል፡፡ እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 463 ሠራተኞችንም ያሉት ኅብረት ኢንሹራንስ 519 ባለአክሲዮኖች ካሉት ኅብረት ኢንሹራንስ በአሁኑ ጊዜ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ ከ2.15 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች