Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ ዘርፉ ክፍት ከመደረጉ በፊት መጤን ያለባቸውን ጉዳዮች ያመላከተው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍን ለውጭ አገር ኩባንያዎች ክፍት ለማድረግ መንግሥት ገዥ ፖሊሲ ከማጽደቅ አልፎ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቱን አጠናቆ ከባለድርሻ አካላትና የዘርፉ ልሂቃን ጋር ምክክር እያደረገ ይገኛል። የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ የፋይናንስ ተቋማት ክፍት ማድረግ በረከቱና ሥጋቱ ምንድነው? በሚለው ዙሪያ ምክክሮች እየተካሄዱ ሲሆን፣ ዘርፉን ለውጭ ውድድር ክፍት ለማድረግ መታቀዱን የሚደግፉና አሁን ወቅቱ አይደለም የሚሉ ድምጾች እየተሰሙ ናቸው። ምክክሩም ሆነ የተጠቀሱት ሙግቶች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው።

የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው አይቀሬነቱን የተረዱት የዘርፉ ባለሙያዎች ስለ መግባት አለመግባታቸው ሳይሆን፣ እንዴት ባለ አግባብ ቢገቡ የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ ይሆናል?፣ አገር በቀል ባንኮችስ እንዴት በኢንዱስትሪው ላይ ተወዳዳሪ ሆነው ይቆያሉ? የሚለው ላይ የሚያንሸራሽሯቸው ሐሳቦች እያስተጋቡም ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከሰሞኑ ባደረገው የፖሊሲ ውይይት መድረክ ከቀረቡ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የፋይናንስ ዘርፉን ክፍት ማድረግ ምን ዓይነት ማነቆ፣ ውጤትና የፖሊሲ ጉዳዮች አሉት የሚለው ይገኝበታል፡፡ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍን ለውጭ ውድድር ክፍት ማድረግ የሚለው ሐሳብ ላይ ብዙ ‹‹ጩኸት›› እየተደመጠ ነው፣ በዋናነትም በሁለት ጎራ የተከፈለ ሐሳብ ተለይቶ መውጣቱን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ አንደኛው ጎራ አገሪቱ አሁን በምትገኝበት የቀውስ ሁኔታ ውስጥ ሆና የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች መክፈት ተገቢ አይደለም የሚል ሙግት ሲያነሳ፣ ሌላኛው ደግሞ ዘርፉን ለውድድር ክፍት ማድረግ ተገቢ መሆኑን ተቀብሎ ነገር ግን አከፋፈቱ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት የሚል ነው፡፡ በተለያየ የመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደረጉት እነዚህ ሙግቶች ጥሩ ሆነው፣ ነገር ግን በስሜት ሳይሆን በጥናት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል የሚል ሐሳብንም የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍን ክፍት ማድረግ ማነቆው፣ ውጤትና እንዲሁም የፖሊሲ ጉዳዮችን የተመለከተ ጥናት ያቀረቡት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ተመራማሪ የሆኑት ፈጠነ ቦጋለ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፣ ከውጭ ባንኮች መግባት ጋር ተያይዞ ዝም ብሎ መከራከር ሳይሆን፣ ጥናት ተደርጎ የሁለቱም ጎራ ክርክር ሳይንሳዊ በሆነ አመክንዮ መደገፍ እንዳለበት ያነሳሉ፡፡ ከዚያ ውጭ ከመሬት ተነስቶ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ክፍት መሆን አለበት፣ አይ የለበትም፣ ማለት ተገቢ አይደለም የሚል አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ ጥናትን መሠረት አድርጎ የሚቀርብ ሙግት ለሚመከለተው የመንግሥት አካል ውሳኔ ይጠቅማል ሲሉ ፈጠነ (ዶ/ር) ይመክራሉ፡፡

በፖሊሲ የውይይት መድረኩ ላይ የቀረበውና አንድ ዓመት የፈጀው ጥናት ሦስት ምልከታዎችን አስቀምጧል፡፡ ጥናቱ የባንክ ዘርፉ ላይ ትኩረት አድርጎ የተሰናዳ ሲሆን፣ በጥናቱ ከተዳሰሱ ጉዳዮች አንደኛው ከውጭ ከሚመጡ ባንኮች ከጉዳት ይልቅ ጥቅምን ለመውሰድ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ያነሳል፡፡ ይህ ሲታሰብ ደግሞ በዋናነት የቁጥጥር ሥርዓቱ በደንብ መጠንከር አለበት የሚለው ነጥብ ጉልህ ሥፍራን ይይዛል፡፡ አሁን ባለው የቁጥጥር ሥርዓት ዘርፉን ለውጭ ውድድር ክፍት ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ፣ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከውጭ የሚመጡ ባንኮች በቴክኖሎጂም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ውስብስብ ነገር ይዘው ስለሚመጡ ያንን መቆጣጠር የሚችል ሥርዓትን መዘርጋት ይገባል የሚለው ነው፡፡

ሁለተኛው ምልከታ የአቅም ግንባታ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ይህም በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂም ሆነ የፋይናንስ ዘርፉ መጠንከር አለበት የሚለውን የሚመለከት ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ባንኮችም ሆነ ኢንሹራንሶች አቅማቸውን ማጠናከር ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ ፈጠነ (ዶ/ር) እንደሚስረዱት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ ያንን ወደ ትግበራ ማስገባት የሚችል የሰው ኃይል ያስፈልጋል፣ በዚህ ደረጃ የሰው ኃይል ከሌለ ከሚመጡት ተቋማት ጋር መወዳደር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ሦስተኛው የጥናቱ ምልከታ የሚያስረዳው ከቅደም ተከተል ጋር የተገናኘ ሲሆን፣ ይህም የፖሊሲ ጉዳይን ይመለከታል፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የውጭ ባንኮችን መቀበል ተገቢ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ በማንሳትም መልስ የሚሹ ጉዳዮችን ያቀርባል። ለዓብነትም፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የተቀሰቀሰው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፖለቲካ አለመረጋጋቶችንና አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን በቅድሚያ ፈትቶ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት ማድረግ የተሻለ ጥቅም እንደማያስገኝ ጥናቱ ያመለክታል።

በብዙ መለኪያዎች ሲታይ የኢትዮጵያ ባንኮችም ሆነ የኢንሹራንስ ተቋሞቻችን ብዙ ነገር ይቀራቸዋል የሚሉት ተመራማሪው፣ ለገጠሩ ኅብረተሰብ ያላቸው የፋይናንስ ተደራሽነት፣ የኢንሹራንስም ሆነ የባንክ ተደራሽነቱ ገና ብዙ የሚቀረው ነው የሚል ሐሳብ ያነሳሉ፡፡ ምን ያህል ኤቴኤም አለ? ባንኮቻችን ምን ያህል ቴክኖሎጂ ነው የሚጠቀሙት? የኢንሹራንሶቹም ሆነ የባንኮቹ ደንበኛ አያያዝ እንዴት ነው? የሚሉት ጉዳዮች ከአፍሪካ አገሮች ጋር ሲታይ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የሚቀር ነገር እንዳለ እንረዳለን ይላሉ ፈጠነ (ዶ/ር)፡፡

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የፋይናንስ ዘርፍን ለውጭ ክፍት ማድረግ በአፍሪካ ውስጥ በተለይም የተረጋጋ የፋይናንስ ዘርፍ ከማስፈን አኳያ አዎንታዊም አሉታዊ የሆነ ግንኙነት አለው፡፡ ለአብነትም እ.ኤ.አ በ1998 የናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ 26 የባንክ ፍቃዶችን ሰርዟል (ከገበያ ውጭ አድርጓል)፡፡ በላቲን አሜሪካ አገሮችም በተለይም በ1990ዎቹ የባንኮች ተወዳዳሪነት እንዲወርድ ሰበብ ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል በእስያና በሌሎች የደቡብ አሜሪካ አገሮች የውጭ ባንኮች መግባት ፉክክርና ተወዳዳሪነትን ሲጋብዝም ተስተውሏል፡፡

የፋይናንስ ዘርፍን ለውጭ ተቋማት ክፍት ካደረጉ አገሮች ጋር ሲታይ ዘግየት ብለው የተቀላቀሉ አገሮች ብዙ ነገሮችን አስተውለው ለመወሰን ዕድል ስላገኙ በኢትዮጵያም ዘርፉ ለውውድር ከመከፈቱ አስቀድሞ ጉዳቱና ጥቅሙ ምንድነው? የሚለውን ከእነዚህ አገሮች መውሰድ እንደሚቻል ፈጠነ (ዶ/ር) ያስገነዝባሉ። አክለውም፣ ብዙ የዓለም ኢኮኖሚ ቀውስ መነሻው የፋይናንስ ዘርፉ እንደሆነና ይህም የጥንቃቄን አስፈላጊነት አመላካች እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

‹‹መጠንቀቅም ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን መጀመሪያ ማሟላት ይገባል፡፡ የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ የተረጋጋ መሆን አለበት፡፡ መረጋጋቱን ካስጠበቅን በኋላ የውጭ ባንኮች መግባታቸው ብዙ ጥቅም ይሰጣል፤›› የሚሉት ፈጠነ (ዶ/ር)፣ ለአብነትም የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ክፍት መሆን የአገር ውስጥ ባንኮች ተደራሽነትን በተለይም ለገጠሩ ኅብረተሰብ ዕድል እንደሚፈጥር ይገልጻሉ። ከዚህ ባሻገር የአገር ውስጥ ባንኮች ካለባቸው ችግሮች ተጠቃሽ የሆኑት ቴክኖሎጂ፣ የደንበኛ አያያዝ እንዲሁም የኢኖቬሽን ጉዳዮች የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን በመረዳት፣ ራሳቸውን በዚያ ልክ እንዲበቁ የሚያግዝና ለኅብረተሰቡም የሚጠቅም መሆኑን ያስረዳሉ።

የፋይናንስ ዘርፍን ክፍት ማድረግ የአገር ሀብት ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ፣ ውድድርን ለማበረታታት፣ የኢንቨስትሮች መተማመንና የካፒታል ፍሰትን ለመጨመር፣ ጉዳትን ለማሠራጨት (ዳይቨርሲፊኬሽን)፣ የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነትን ለመፍጠር እንዲሁም ምርታማነትንና ዕድገት ለማምጣት አስፈላጊ መሆኑን የቀረቡት ጥናቶች ያመላክታሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በቂ ዝግጅት ሳይኖር የውጭ ባንኮችን ማስገባት ቀውስ ሊፈጥር የሚችል ዕርምጃ መሆኑን፣ የሞኒተሪ ፖሊሲን ለመጠቀም የሚስችል ነፃነት እንዲቀንስ የሚያደርግ፣ ለዋጋ ተወዳዳሪነት ሲባል የገንዘብ የመግዛት አቅምን የሚያዳክም፣ ከካፒታል ግብይት ጋር በተያይዘ በሚደረጉ የገበያ ልውውጦች ገንዘብ ከአገሪቱ እንዲወጣ የማድረግ ተፅዕኖዎች  ሊስተዋሉ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸው ይገለጻል፡፡

የፖሊሲ ውይይት መድረኩ ላይ በቀረበው ጥናት እንደተመላከተው፣ ከብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥዎች ጋር በተደረገ ውይይት ለአጥኚዎቹ ከተገለጸላቸው ጉዳዮች ውስጥ የአገር ውስጥ ባንኮች እርስ በርሳቸው እንዲወሃዱ ማበረታት ይገባል የሚለው ይገኝበታል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ባንኮችን ለመቋቋም ባንኮች በቁጥር አነስ ብለው፣ ነገር ግን ተዋህደው ቢመጡ የተሻለ ሲሆን፣ በተለይም አዳዲስ የሆኑት ባንኮች በዚህ ላይ ትኩረት ቢያደርጉ የተሻለ ነው የሚል ሐሳብ ይገኝበታል፡፡ በእርግጥ ይኼ አካሄድ ጉዳትም እንዳለው የማይካድ ነው የሚሉት ተመራማሪዎች፣ ትናንሽ የሚባሉት ወይም አዳዲስ የሚባሉት ባንኮች የሚዋሃዱ ከሆነ ጥቂት ባንኮች ብቻ የፋይናንስ ዘርፉን የሚጠቅልሉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል በመጥቀስ ጥንቃቄ በታከለበት መንገድ ሊታይ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

እንደ ፈጠነ (ዶ/ር) ገለጻ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባንኮች በብዛት ተመሳሳይና የተለመደ አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሁም የአገልግሎትም ሆነ የቴክኖሎጂ ስብጥር የሌላቸው ናቸው፡፡ በተለይም ከትርፍ ግኝት አንፃር ካልሆነ በስተቀር በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባንኮች ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀሩ የሚገኙበት ደረጃ ጥሩ የሚባል አይደለም፡፡ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ክፍት ባደረጉ የሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች ትርፍና መረጋጋት ካልሆነ በስተቀር የተሻለ አገልግሎትና አፈጻጸም እንደተገኘበት በጥናት ተረጋግጧል፡፡

ጥናቱ በማጠቃለያው እንዳሳየው የውጭ ባንኮች መግባት ለዓብይ (ማክሮ) ኢኮኖሚው አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ያለው ሲሆን፣ በአጭርም ሆነ በረዥም ጊዜ ውስጥ ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የኢኮኖሚ ዕድገትን የማሻሻል ዕድል ይፈጥራል፡፡ በሌላ በኩል ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በተለይም የአገር ውስጥ ባንኮችን አቅም መዳከም የሚፈጥርበት ዕድል ስላለ የፖሊሲ ማዕቀፍ  ክለሳን እንደሚጠይቅ ያስረዳል፡፡

ፈጠነ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፣ ብሔራዊ ባንክ የጀመራቸው፣ ሠርቶ ያሳያቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ ቢታሰብም ብዙ ነገሮች እንደሚቀሩት መረዳት ይገባል፡፡ በጥናቱ እንደተመላከተውም፣ ብሔራዊ ባንክ ከፖለቲካ ጥገኝት ተላቆ በነፃነት ውሳኔ የመስጠት ሥልጣኑን ሊጠቀም ይገባል፡፡

ከፖሊሲ አንፃር ደግሞ የፋይናንስ ዘርፍን ከመክፈት አስቀድሞ ብሔራዊ ባንክ ብልሃት የታከለበት ነገር ግን አነስተኛ የቢሮክራሲ ፖሊሲዎችንና የቁጥጥር ዘዴዎችን ማበጀት እንደሚገባው ጥናቱ ያመለክታል፡፡ ዘርፉ ተከፍቶ የዘርፉ ተዋንያን ከገቡ በኋላም የወጡ ፖሊሲዎች፣ መመርያዎችና የቁጥጥር ሥርዓቶች በትክክል መተግበራቸውን የማዕከላዊ ባንኩ በአፅንኦት ሊከታተለው ይገባል፡፡

የፋይናንስ ዘርፉ ተዋንያንም ሆኑ ተቆጣጣሪው አካል የአቅም ግንባታ ሥራን አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚተገበረው ልክ እንዲያሰርፁ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ በተለይም የሰው ኃይል፣ የሳይበር ደኅንነት፣ ቴክኖሎጂና የፋይናንስ አቅም ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጥናቱ ያመለክታል፡፡

የቀረበውን ጥናት መሠረት አድርጎ በተካሄደ ውይይት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የኢኮኖሚ ምሁራን እንዳስታወቁት፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳና ሌሎችም አገሮች የፋይንናስ ዘርፍን ከፍተው፣ ሞክረው ከሰሩ፣ አተረፉ የሚለው ሳይሆን፣ እንዴት አድርገው ከፍተው ነው የተጠቀሙት፣ እንዴትስ ከፍተው ነው የከሰሩት የሚለውን መረዳት መንግሥትንም ሆነ ሕዝብን ከውዥንብር ይታደጋል፡፡

በመንግሥት በተወሰነው መሠረት የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ተብሎ የተቀመጡ አማራጮች የታወቀ እንደመሆኑ መጠን፣ የእነዚህ አማራጮች ጥቅማቸውና ጉዳታቸው ምንድነው የሚለውን ማየት ጠቃሚና ወሳኝ ነው፡፡

መንግሥት ባፀደቀው ፖሊሲና ይህንን ተከትሎ በተረቀቀው የባንክ ሥራ አዋጅ ማሻሻያ መሠረት፣ ለውጭ ባንኮች የሚሰጠው የባንክ ሥራ ፈቃድ በቁጥር የተገደበ እንደሚሆን ታውቋል።

ሪፖርተር ያገኘው የፖሊሲ ሰነድና ይህንን ሰነድ መነሻ አድርጎ የተረቀቀው የባንክ ሥራ አዋጅ ማሻሻያ እንደሚጠቁመው፣ መንግሥት ለረዥም ዓመታት ዝግ የነበረውን የአገር ውስጥ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ባንኮች ክፍት ሲያደርግ የሚመጡትን የውጭ ባንኮች በሙሉ ተቀብሎ ፈቃድ የሚሰጥ አይሆንም። 

በፀደቀው የፖሊሲ ሰነድ መሠረት ፈቃድ ማግኘት የሚችሉት የኢትዮጵያ ንዑስ ባንክ ለማቋቋም የሚጠይቁና የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ለማቋቋም የሚጠይቁ የውጭ ባንኮች ናቸው።

‹‹አዲስ ፈቃድ ከመስጠት አንፃር በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከሦስት እስከ አምስት ፈቃድ ለውጭ ባንኮች ሊሰጥ ይችላል። በተመሳሳይ ቅርንጫፍ መክፈት ለሚፈልጉ ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ የውጭ ባንኮች ብቻ ሆኖ፣ እያንዳንዳቸው መክፈት የሚችሉት የቅርንጫፍ ብዛትም ከሁለት እስከ አራት ቅርንጫፎችን ብቻ ይሆናል›› ሲል የፖሊሲ ሰነዱ አቅጣጫ አስቀምጧል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች