በበቀለ ሹሜ
ሀ) በእኔ ዕድሜ የማውቀውና የተሳተፍኩበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወጠጤነት የሚያጠቃው ነው፡፡ ‹‹ወጠጤ›› የተሰኘውን ቃል የተጠቀምኩት ፖለቲከኞችን በዕድሜ ያልበሰሉ ናቸው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ለመስጠት አይደለም፡፡ ከልምድ እንዳስተዋልኩት በዕድሜ ወጣት ሆነው አርቀው የሚያስተውሉ ለብርቅ እንዳጋጠሙኝ ሁሉ፣ ሁለት ፀጉር አውጥተውም የእነሱን ሐሳብ የሚቃረን/የሚነቅፍ ሐሳብ ሲገጥማቸው የበቀል ሸርና ዱላ የሚታያቸው፣ የተቻቸውን ሐሳብ ዕርባና ገምግሞ እንከኑን በማሳየት ላይ ወይም ከትችቱ በመማር ላይ ከመሥራት ይልቅ የእነሱን ሐሳብ በመቃረን የተዳፈረውን ሰውዬ በምን አጥምጄ ላስነክሰው፣ ወይም በምን ልበቀለው በሚል ሥራ ላይ የሚጠመዱ የሽማግሌ ወጠጤዎች ብዙ ዓይቻለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፌ ‹‹ወጠጤ›› ያልኩት ራሱን ፖለቲካችንን ነው፡፡ በወጣትም፣ በአዛውንትም ሲገላበጥ የቆየው ፖለቲካችን በአመዛኙ እንደ ወጠጤ ስሜት ፍል ነው፡፡ ችኩልና ቀለብላባ ነው፡፡ እንደ ጎረምሳ ስህተትና ጥፋቱን ማየት አይወድም፡፡ ጥፋተኛ ነህ መባልን ከጥቃት ይቆጥረዋል፡፡ ለምንድነው ፖለቲካችን እንዲህ ያለ ወጠጤያዊ ባህርይን አልፎ ለመጎልመስ ያልቻለው? ጥሎብን አይደለም፡፡ የእኔ አስተውሎት ለጥያቄው ያገኘለት መልስ ሁለት ነው፡፡ አንደኛው በወጠጤነት የምናየው ዓይነት ዞሮ ገባ ከሆነ አዙሪት የሚያወጣ የውስጣዊ ግፊት ማነስ ነው፡፡ በወጠጤነት ዕድሜ ውስጥ ራስንና አድራጎትን መርምሮ የተግባር ጥፋትን ከማየት ይልቅ ለጥፋት ማማካኛና ማላከኪያ እየፈለጉ ራስን ማታለል ይጣፍጣል፡፡ ጥፋትን ማየት እስካልፈለጉ ወይም ጥፋት ሲነገረን ከጥቃት ቆጥረን የምንጨስና ለበቀል የምንነሳ ከሆነ ጥፋታችንን ለማየት አንበቃም፡፡ ጥፋታችንን እስካላየን ድረስም ኃፍረትና ፀፀት አይነካንም፡፡ ኃፍረትና ፀፀት ካልነካንም ለመታረም አቅሙ አይኖረንም፡፡ ሳናፍር ሳንፀፀት ከአንገት በላይ ‹‹አዎ ስህተት ሠርተናል›› ልንል እንችላለን፣ ብለናልም፣ ግን በማግሥቱ ዞረን እዚያው ነን፡፡ የፖለቲካችን አንዱ ችግር በዚህ ዑደት ውስጥ የሚመላለስ መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ገበናችንን ብትንትን አድርጎ በመዘርገፍ አሳፍሮ የሚያቃና ብስለትና ጉልምስና ፖለቲካችን እንዳያኮርት ራሱን በራሱ የሚበላ ቀበኛ ያለበት፣ ሁሌ ከጥሬ የሚጀምር፣ ሁሌ በጮርቃነት የሚዳክር ሆኖ መቆየቱ ነው፡፡ ይህንን ሁለተኛውን ነጥብ ላፍታታው፡፡
እኔ ወጣት በነበርኩበት በ1960ዎች የወጣት ተራማጅ እንቅስቃሴ ውስጥ ሁለት ጥቅል መስመሮች ነበሩ፣ ኅብረ ብሔራዊና ብሔርተኛ፣ በ1960ዎች ዓመታት ውስጥ ገዝፎ ይታይ የነበረው ኅብረ ብሔራዊው እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በውጭም በአገር ውስጥም ከኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች የወጡ ተራማጅ ነን ባዮችን ሁሉ ያቀፈ ነበር፡፡ ነገር ግን ከውጭ የቀዱት ርዕዮተ ዓለማቸውንና የትግል ግባቸውን ብቻ አልነበረም፣ የልዩነቶች/የቅራኔዎች አረዳዳቸውንና አፈታታቸውንም ጭምር ነበር፡፡ ‹‹በአንድ ጊዜ ሁለት ትክክለኛ/ተራማጅ መስመሮች ሊኖሩ አይችሉም፡፡ አንዱ ትክክለኛ ከሆነ፣ ሌላው ስህተተኛ፣ አንዱ ተራማጅ ከሆነ ሌላው አድሃሪ፣ አንዱ አብዮተኛ ከሆነ ሌላው ፀረ አብዮተኛ ነው፣ ሦስተኛ መንገድ ሊኖር አይችልም፡፡ ሦስተኛ መንገድ ነኝ ባይ ቢከሰትም፣ ዞሮ ዞሮ የአንዱ መስመር ሠፈርተኛ ከመሆን አያመልጥም…›› በሚል አስተሳሰብ አማካይነት ነበር ልዩነቶችን ያስተናገዱት፡፡ በዚሁ የአስተሳሰብ ሥልት አማካይነት ጠላትና ወዳጅ/አናርኪስትና አብዮተኛ፣ ወዘተ. ተባብለው የተጣመደ ፖለቲካ ሲሳይ ሆነው ተበላሉ፡፡ በእነሱ መበላላት አሸናፊ ሆኖ መደላደል የቻለው የመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ወታደራዊ ሥርዓት የእነሱን ርዕዮተ ዓለምና የአስተሳሰብ ሥልት ቆዳውና መነገጃው አድርጎ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምን ከሚያወድሰውና ‹‹ልክ›› ከተባለው የፓርቲ አደራጃጀት ውጪ ለመደራጀት እንዳይችሉ አድኖ በመቀርጠፍ፣ በገፍ አስሮ በማሸትና ከፀረ አብዮት ‹‹በሚያፀዳ›› ፕሮፓጋንዳዊ ቅጥቀጣ አድቅቆ፣ በውድም በግድም ‹‹አብዮቱ››ን ካሺ/አገልጋይ ወይ አጎንብሶ ኗሪ ወይ ትግል እርሜ ብለው እስከ መሰደድ ድረስ የትግል ሐሞታቸውንና ህሊናቸውን መስለብ ቻለ፡፡
በእርስ በርስ መበላላትና በደርግ ቅጥቀጣ በኅብረ ብሔራዊው የፖለቲካ ሠልፍ ላይ የደረሰው ከባድ ጉዳት፣ በኢትዮጵያ ፀረ አፈና ትግል ውስጥ ትልቅ ክፍተት ፈጠረ፡፡ በኅብረ ብሔራዊው ትግል ውስጥ የ1960ዎቹን የትግል አወዳደቅ በደንብ መርምሮና ከጥፋታቸው ተምሮ የተሻለ ብስለትና ግንዛቤ የፈጠረ የፖለቲካ ዕድገትና የትግል ቅብብል እንዳይኖር አደረገ፡፡ ተሞካከረ የተባለው ‹‹ግምገማና እርማት›› ሁሉ ተልካሻና የሙጣጮች ወገኛ መትረክረኪያ ከመሆን የዘለለ አልነበረም፡፡ በዚህ በኩል የነበረው ጉድለት፣ ኅብረ ብሔራዊው ትግል ዳሽቆ መከነ/ከመድረክ ውጪ ሆነ ለማለት የሚያስደፍር ነበር፡፡ እናም ኅብረ ብሔራዊው ትግል ይዞት የነበረውን ዋና የተዋናይነት ሥፍራ ከሥር የነበረውና ተጋርዶ የቆየው ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ለመተካት ዕድል አገኘ፡፡ ዕድል ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ ራሱን ትክክለኛ የትግል መንገድ አድርጎ እንዲኮፈስና ራሱን እንዲያባዛ ተመቸው፡፡ በአጭሩ ብሔርተኛው ትግል የኅብረ ብሔራዊውን ትግል ውድቀት መማሪያ ሳይሆን መገበዣ አደረገው፡፡ ስደትና አጎንብሶ ማደር አልሆን ያላቸው ከኅብረ ብሔራዊ ትግል የተራረፉ ግለሰቦችም፣ ወደ ብሔርተኛ ትግል እየገቡ እዚያ ውስጥ በደረሰ የአመለካከት ግጭት ምክንያት በአንጃነት እየተወራረዱ ወይም የብሔርተኛ አስተሳሰብ ምርኮኛ እየሆኑ ቀለጡ፡፡
እዚያም እዚያም ተፈጥረው የነበሩት ብሔርተኛ ቡድኖች በሒደት እርስ በርስ እየተያያዙ ለመላ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ተስፋ ለመሆን የአመለካከት አቅም የነበራቸው አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹ ለይቶላቸው መነጠልን ዓላማቸው ያደረጉ ነበሩ፡፡ ከዚያ በመለስ ያሉት ደግሞ ‹‹የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መነጠል መብት››ን የፖለቲካ ውላቸው አድርገው የያዙ፣ አለዚያም የራሳቸውን ብሔርተኛ ጉዳይ ጉዳዬ ከማለት ያለፈ ዕይታና እንቅስቃሴ ያልነበራቸው ነበሩ፡፡ ወደ ደርግ ውድቀት መዳረሻ አካባቢ በኅቡዕ ሬዲዮ ደምቀው ይሰሙ የነበሩት የብሔርተኛ እንቅስቃሴዎችም ሆኑ ኅብረ ብሔራዊ ነን ያሉ እንቅስቃሴዎች፣ የኢትዮጵያን መላ ኅብረተሰብ ቀልብ መያዝና የጋራ የትግል መድረክ የመሆን ብቃት አልነበራቸውም፡፡ ብሔርተኞቹ በየብሔር ግቢያቸው ውስጥ የሚትረከረኩ ነበሩ፡፡ ኅብረ ብሔራዊ ነን ያሉት ቀደም ብሎ እንደተባለው ካለፈው ልምድ የረባ ትምህርት የቀሰሙና መጎልመስ የቻሉ አልነበሩም፡፡ አንደኛው (ኢሕዴአ/ኢፒዲኤ የተባለው) እንዲያውም፣ የሕዝብ ዕምቢታና አመፅ አነቃናቂ የመሆን ሚናን ሸሽቶ በአቋራጭ ወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣ እንዲመጣ የሚቀሰቅስና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ የወታደራዊ ግልበጣ ተስፈኛ ሆኖ እንዲያንጋጥጥ የሚወሰውስ ነበር፡፡ እናም የኢትዮጵያ ሕዝቦች እስከ ደርግ መውደቅ ድረስ የነበሩበት ሁኔታ፣ የጋራ ትግል መሰባሰቢያ የለሽ ሆነው እንደተንቆራጠጡና ግራ እንደተጋቡ የቆዩበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በ1981 ዓ.ም. ግንቦት ላይ የተሞከረውና ወደ ሕዝብ የለውጥ እንቅስቃሴ ሳይሸጋገር የከሸፈው የወታደራዊ ግልበጣ ሙከራም፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ የነበረበትን የግራ መጋባት ሁኔታ፣ የግልበጣ ጠንሳሾቹን ዝርክርክነትና ግልበጣን ፖለቲካው ያደረገውን ቡድንንና የእነ ሕወሓትን አጃጃይነት ያንፀባረቀ ነበር፡፡ ከወታደራዊው የግልበጣ ሙከራ መመታት በኋላ፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ብቻውን ከመቅረት ባልተሻለ ባዶነት ውስጥ ወድቆ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በስተኋላ ላይ ‹‹ኢሕአዴግ›› የሚሰኝ ኮት የለበሰው ቡድንም ቢሆን የትግራይ ብሔርተኛ/ጎጠኛ ስለመሆኑ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሥውር አልነበረም፡፡ አሸንፎ አዲስ አበባ ሲገባም፣ ከእነ ጥርጣሬውና ከእነ ሥጋቱ ሕዝብ ‹‹የተቀበለው›› ከሥርዓት አልባ ቀውስ ለማምለጥ በጊዜው በራፍ ላይ የነበረው (ሌላ አማራጭ ያልታየበት) ዕድል እሱ ስለነበር ነው፡፡
ከ1970 ዓ.ም. እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ የኢትዮጵያን መላ ኅብረተሰብ ያያያዘ ሕዝባዊ ፖለቲካ የከሰመበት የኦናነት ጊዜ (የኢትዮጵያ ትምህርት ቀመሶች የፖለቲካ ፆም ውስጥ የገቡበት ጊዜ) ሲሆን፣ በሕወሓት/ኢሕአዴግ አሸናፊነትና ንግሥ የተከናወነበት የታሪካችን ምዕራፍ ደግሞ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ አዕምሮ በክፍልፋይ አስተሳሰብ እየተቆራረሰና እየጠበበ የተሟሸበት ጊዜ ነው፡፡ እና ከ1970 ዓ.ም. አካባቢ አንስቶ እስከ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ከሥልጣን መንሸራተት ድረስ ለ40 ዓመታት ያህል ኅብረ ብሔራዊ የኢትዮጵያ ትግል ሽባ ሆኖ የቆየበት (ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ እትብቱ የተፋታበት) ጊዜ ነበር፡፡ በደርግ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባዶነት ውስጥ ቢወድቁም፣ ትስስራቸውና አስተሳሰባቸው በጫካ ብሔርተኞች እጅግም አልተሸነሸነም ነበር፡፡ የድኅረ ደርግ ጊዜው የሕወሓት/ኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን ግን፣ የጋራ ኅብረ ብሔራዊ የትግል መድረክ አልባ ከመሆንም ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በብጥስጣሽ አስተሳሳብ የመሟሸት ጥቃት የተካሄደባቸው ጊዜ ነው፡፡ በይፋና በሰፊው ሲካሄድ ከቆየው የአዕምሮና የኑሮ ሽንሻኖ ሥር የነበሩ ኅብረ ብሔራዊ ነን ያሉ ሕጋዊ ፓርቲዎች የሌሉ ያህል (የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ የጎለመሰ ኅብረ ብሔራዊ ትግል መገለጫ ከመሆን ይልቅ የቅራሪነት መገለጫ የሆኑ) ነበሩ፡፡ ሕዝብን በተለይ የአዲሱን ወጣት በቁርጥራጭ ብሔርተኝነት መታጠብ መከላከል ያልቻሉ፣ ራሳቸውም ሳያቁት በብሔርተኛ ሥሌቶች ይታኘኩ የነበሩ ናቸው፡፡ የእነዚህ ቡድኖች ድኩምነት የሩቅ ምክንያት የ1960ዎቹ ፖለቲከኞች ሰንካላነት እስከ ፈጠረው ክፍተት ድረስ ይሄዳል፡፡ የቅርብ ምክንያታቸው ደግሞ በራሳቸው ስንፍና ላይና በገዥው ቡድን አቆርቋዝነት ላይ ያርፋል፡፡
ሕወሕት/ኢሕአዴግ በትግራይም ሆነ በቀሪዎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከራሱ አባላትና አጋር ተብዬ ድርጅቶች ውጪ አቅም ያለው ተፎካካሪ እንዳይኖር አድርጎ ቡድኖችን ማዳቀቁ፣ በሌላ ፈርጅ የኢትዮጵያ ሕዝቦችም የሕወሓት/ኢሕአዴግ ጥገኛ ከመሆን በቀር ሌላ አገራዊ የፖለቲካ አለኝታ እንዳይኖራቸው፣ በሒደትም እንዳያዳብሩ የነፈገ ስነጋ ነበር፡፡ አቅም ያለው የፖለቲካ ድርጅት በሒደት ለመጎልበት አለመቻሉም መጋቢት 2010ን ይዞ ለውጥ ከፈነጠቀ በኋላ፣ ለውጡን በብልኃትና በአርቆ አስተዋይነት በመምራት ረገድ ለደረሰው ችግር አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ለ) በተደጋጋሚ እንደተባለው ሕወሓት/ኢሕአዴግ በ27 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የበዘበዘው ኢትዮጵያዊ ሰፊ ዕይታን ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱን የደኅንነትና የታጠቀ አውታርን ጭምር ነበርና ይህ ከባድ ዝርፊያ ካስከተለው ቅርቃር ለመውጣት ከጥገናዊ ለውጥ የተሻለ አማራጭ አልነበረም፡፡ እናም ከዚያው ከአገዛዙ ውስጥ የለውጥ ጮራ መፈንጠቁ ትልቅ መታደል ነበር፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ‹‹ሕጋዊና ሰላማዊ ተቃዋሚ ነን›› ሲሉ የነበሩትም ሆኑ፣ ከስደት ተመላሾቹ ብዙዎቹ የጥገናዊ ለውጡን ውድነት አጢነው ለውጡን ተንከባክቦ ለማሳደግ አልተንሰፈሰፉም፡፡ ከገዥው ክፍል ከመጣው የለውጥ ቡድን ጋር ተባብረውም ሆነ ለብቻቸው ተሰባስበው የለውጡ ንቁ አራማጅና ንቁ ድምፅ መሆን አልቻሉም፡፡ የለውጡ መንግሥትም ኑልኝ ብሎ ‹‹በለውጡ ዙሪያ በዚህ በዚህ ትልም ላይ እንሰባሰብ›› አላላቸውም፡፡ በሁለቱም በኩል በበሰለ አርቆ አስተዋይ ፖለቲካ የነገሮችን አመጣጥ ከእነ ንፋሳቸው እያስተዋሉ፣ ተቀናቃኞችን እያመናመኑ የለውጥ ደጋፊዎችን እያባዙ፣ ለውጡን ያለ መደነባበር የማራመድ ሚና በሁለቱም በኩል ጎደለ፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ የአፈና ሥርዓት ተቃዋሚ ነበርን/ነን ካሉት ነባርና አዲስ ገቦች፣ ኢትዮጵያዊ ዕይታ አለን ባዮቹ ቡድኖች በጥቅሉ የግብታዊነት ጭራ ከመሆንና ተመልካች ከመሆን በላይ ለለውጡ እጅግም አልተዋደቁም ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ድክመታቸው ሰበብ ሊያቀርቡ አይችሉም፡፡ ኢሕአዴግ በተለያያ ሥልት እየኮረኮመ ስላደቀቀን ነበር ለውጡን ለመምራት የተሳነን ሊሉም አይችሉም፡፡ የተራውን ሕዝብ ያህል እንኳ ንቁ ደጋፊና አጋዥ ለመሆን አለመቻላቸውም ሆነ በሽርደዳና በመቆነን የተካሄደው ጣት ቅሰራ በምንም ሊመካኝ አይችልም፡፡ ከመንግሥታዊው ቡድን ውጪ ትልቅ ስብስብ ፈጥረው የለውጡ ሕዝባዊ ሠፈር አንድ ድምፅ ለመሆን አለመላወሳቸው፣ እነሱ ተበታትነው አሉባልታ ሲሰልቁ፣ ኢሳትና የኦሮሞ ሚዲያ መረብ (ኦኤምኤን) የሚባሉ ‹‹ታጋይ›› ሚዲያዎች የሕዝብ ህሊና ዋና ቃኚ መሆን የሙትቻነታቸውን ልክ (እያሉ ያልነበሩ የመሆናቸውን ልክ) የሚያሳይ ነው፡፡
‹‹ለአንድነት የቆምኩ›› እና ‹‹ለብሔር መብት የቆምኩ›› በሚሉ ሠፈሮች ዘንድ ያሉትን የሁለት በኩል የጥበት ችግሮች እየዘከዘከ ሕዝቦችን በተግባባ ዕይታ የሚያስተባብር የሰከነ ፖለቲካ መጉደሉ (ወይም ሰላላ መሆኑ) ሳያንስ፣ ሕወሓትን እንደ ዋና ጠላት ጠምደው የቆጠሩ ‹‹ታጋይ›› ሚዲያዎችና ግለሰቦች ጥንቃቄና ስክነት በጎደለው (ቅራኔ በሚያጦዝ) ኩነናቸው የሕዝብ ህሊና ዋና ቃኚ መሆን መቻላቸው፣ የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶችን አንድ ላይ በኢትዮጵያ ህዳሴ አስተባብሮ ለኢትዮጵያ መቀጠል ተስፋ በሆነው ሠፈርና ከዚያ ባፈነገጠው ሕወሓታዊ ሠፈር መካከል ያለውን ስንጥቅና ቅራኔ በለስላሳ አያያዝ ወደ መርገብ የመጓዙን ዕድል ከባድና ሩቅ እንዲሆን አደረገው፡፡ ያም ያም በስሜት ቦትላኪና በደል አጧዥ በሆነበት ያልተገራ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ በቀለኛ የጥላቻ ፖለቲካ እየገረረ የጉዳዮች አያያዝ ብልህነትና ስክነትን እያጣ ለውጡ ‹‹የቅልበሳና የአሃዳዊነት መመለስ›› ሆኖ እየተሳለ፣ የእነ ወልቃይት ጉዳይ ቅራኔ ለማካረሪያ ሊነገድበት ቻለ፡፡ በበቀልና በጥላቻ የገነተሩ ሕወሓታውያን እየኮሰሱ በመሄድ ፈንታ ኃይል እያሰባሰቡ ከበፊት ጠበኞቻቸው ጋር ለበቀልና ለቅልበሳ ለመታረቅ ዕድል አገኙ፡፡ ተሸሽገውና በግላጭ በተለያየ ሥፍራ የታጠቁ የትርምስ ቡድኖችን ለማደራጀት ተመቻቸው፡፡ እነሱን ለጉድ ያሳጣና ያሳመመ እየመሰለው ‹‹ፀረ ሕወሓት/ፀረ ብሔርተኛ ነኝ›› ያለ የኩነና ቦትላኪ ሁሉ ሳያውቀው በውዥንብር እንዲያጭበረብሩና እንዲጠናከሩ ጠቀማቸው፡፡ እናም ብዙ ደም መፋሰስና ውድመት ውስጥ ላለመግባትም ሆነ ወደ ሥርዓት አልባነትና ወደ እርስ በርስ መፈሳፈስ ላለመንሸራተት ሲባል የተሸሸው ነውጠኛ የለውጥ መንገድ እንደተሸሸ አልቀረም፡፡ ከዚህ ለመሸሽ ሙጥኝ የተባለው የጥገና ለውጥ፣ መበታተን በሚያፋሽክበት ድባብ ውስጥ ብዙ ደም አፍሳሽ የውስጥ መፈናቀልና ስደት ውስጥ ከመግባት፣ እንዲሁም እዚያም እዚያም የታጠቁ ተቀጢላዎችን ካባዛው የሕወሓት ኃይል ጋር ግዙፍ ጦርነት ከማካሄድ ወጥመድ አላመለጠም፡፡
የጦርነታችንም ዋና ጉዳይ ለውጡን ከማዳንና ከማስቀጠል በላይ አገራዊ ህልውናን የማትረፍ ጉዳይ ሆኖ አረፈ፡፡ ተደጋግሞ እንደተነገረው ሕወሓት/ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ መንበር ላይ ሲወጣ ከቡድን በላይ የነበሩ አገረ መንግሥታዊ አውታሮችን ንዶ ሕወሓታዊ አድርጓቸው ስለነበር አገር የማዳኑ ጦርነት የጠየቀው ዋጋ እጅግ እጅግ ውድ ነበር፡፡ በመነሻው ምዕራፍ ላይ ሲታይ ሕወሓት ተሰባስቦ ትግራይ ውስጥ ተወሽቆ ትልቋን ኢትዮጵያን ከሚያስተዳድር ፌዴራል መንግሥት ላይ የሚያቅራራ አቅሙን አያውቅ ቡድን ይመስል ነበር፡፡ በዚህ የላይ ሥዕል ላይ በመመርኮዝ ‹‹ምንድነው ይህን ያህል ትዕግሥቱ? ለምን ሕግ የማስከበር ዕርምጃ አይወስድም?›› የሚሉ ጥቂት አልነበሩም፡፡ የፌዴራል መንግሥት በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ2011 እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ) የፀጥታና የመከላከያ አውታራቱን ከሕወሓታዊ ታማኝነት ምን ያህል እንዳፀዳ በይፋ የሚታወቅ ነገር አልነበረም፡፡ በጥቅሉ በመጋቢት (2010 እስከ 2012 ዓ.ም. የፈነጠቀው ለውጥ በመንግሥት የታጠቀ ኃይል ውስጥ ያለውን ኅብረ ብሔራዊ ጥንቅርንም እንደሚማርክ ዕውቅ ቢሆንም፣ የዕዝ ሰንሰለቱን ሕወሓታዊነት መመነጋገል ጊዜና ብልኃት የሚጠይቅ ከባድ ሥራ ነበር፡፡ በኋላ ከመንግሥት የተገለጸልንንና ሲሆን ያየነውን አገናዝበን የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት በ‹‹ሪፎርም›› አቃንቶና ‹‹አፅድቶ›› የያዘው የምድር ጦር ትግራይ ላይ ሕወሓት አግቶ ከያዘው ግዙፉ የሰሜን ዕዝና በገፍ ካሠለጠነው ልዩ ኃይል ጋር ሲነፃፀር በኃይል ሚዛን ይበለጥ ነበር፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ሕወሓቶች የሰሜን ዕዝን የእነሱ ሠልፈኛ የማድረግ ወይ ከዓይነተ-ብዙ መሣሪያዎች አለያይቶ ዕንቢተኛውን የማወራረድ ጥቃት መፈጸማቸው፣ በድብስብስነት ውስጥ ተሸሽጎ የቆየውን አሠላለፍ ከአዲስ አበባ እስከ ትግራይ ሰሜን ዕዝና መላ ኢትዮጵያ ድረስ አፈንጋጩንና አገሬን ባዩን ከሞላ ጎደል በየውግንናው እንዲሰማራ ያደረገ የመጀመሪያው ግዙፍ ክስተት ነበር፡፡ አገሬን ያለው ሠራዊትና ሕዝበ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ወኔ እሳት ጎረሱ፡፡ በሽሽግ የተሰናዳው የአየር ኃይል አቅም ከትግራይ ውጪ የነበረው የምድር ጦርና የሕወሓትን ጥቃትና የማስካድ ሴራ ተጋትሮ፣ ከሰሜን ዕዝ የቀረው ሠራዊት (የክፉ ቀን ዘመድ ዕገዛ ታክሎበት) የሕወሓት ኃይልን ሰባብሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቀሌን በመቆጣጠር በኃይል ሚዛን ቅየራ ረገድ የመጀመሪያውን ወሳኝ ዕርምጃ አደረገ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ጦርነት መግጠምና ለኢትዮጵያና ለሙያው የታመነ ሠራዊት የመገንባት ድርብ ሥራ አንድ ላይ በአንድ ጊዜ የማካሄድ ተግባር ኢትዮጵያ ነበረባትና፣ የኃይል ሚዛን ለውጡ የማይፍረከረክና የማይቀለበስ ሆኖ የመሟላቱ ነገር ገና ነበር፡፡ ከሕወሓቶች ጀርባ በተለያየ መልክ ዕገዛ የሚሰጡ የሩቅና የቅርብ አገሮች መኖራቸው ሳይረሳ፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት የትግራይ ሕዝብ ተቀባይነት በሕወሓቶች የተንኮል ሥራ ተበላሽቶና ፊት ለፊት ለማይታይ ያሸመቀ ጥቃት ተጋልጦ ከትግራይ ከወጣ በኋላ፣ ወደ አማራና አፋር የዘለቀ ወረራ የሕወሓት ጦረኞች በከፈቱበትም ጊዜ በኃይል ሚዛን ኢትዮጵያ ትበለጥ ነበር፡፡ በብዙ አቅጣጫ የተከፈተውን ጥቃት እየመከቱ፣ እያፈገፈጉ፣ እየመከቱ፣ በክተት አዋጅ ግብግቡን የመመገብና ሠራዊት ግንባታውን የማጣደፍ ሥራ ተሠራ፡፡ በድርብ ሥራ አቅም ማደስና መሙላት ከተቻለ ወዲያ፣ በብዙ ቦታ ተሠራጭቶና አዲስ አበባ መጣሁ እያለ ሲፎልል በነበረው የሕወሓት ኃይል ላይ በመልሶ ማጥቃት ፈጣንና ብርቱ ድቆሳ በተከናወነ ጊዜ ግን፣ የኃይል ሚዛኑ ዳግም እንዳይበገር ሆኖ ተቀየረ፡፡ ከዚያ ወዲያ የቀጠለው የመከላከያ ግንባታ የዘላቂ ዓላማ ጉዳይ እንጂ ከኃይል ሚዛን መናጋት ሥጋት ጋር የተያያዘ አልነበረም፡፡
ሐ) ሁለተኛውን የጥፋት ወረራ የኢትዮጵያ መንግሥት ደቁሶ ከመለሰ በኋላ፣ የነበረበት ወታደራዊ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታ ከበፊቱ በጣም የተለየ ነበር፡፡ ልበ ሙሉነቱና ብልህነቱ ሞልቶ ከወታደራዊ ዙሪያ ገብ ንቁነት ጋር የውስጥ ልማቱን እያከናወነ ‹‹የተናጠል ተኩስ ማቆም አድርጌያለሁ…፣ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና የግዛት አንድነት ማዕቀፍ ውስጥና በአፍሪካ ኅብረት በኩል ለመደራደር ዝግጁ ነኝ፤›› ብሎ፣ የሕወሓት ጦረኞች ወፈፌነታቸው ተነስቶባቸው ሦስተኛ ዙር ወረራ እስኪከፍቱ እየጠበቀ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህች አቋም ለኢትዮጵያ የምትጣፍጥ፣ ለሕወሓት ወፈፌዎች ሬት የነበረች፣ የሕወሓቶችን ‹‹የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት ይመለሱ፣ እነ ወልቃይት ይመለሱ፣ ካሳ ምንትስ…›› የሚል የድርድርን አስፈላጊነት ኦና የሚያደርግ ጅል ቅድመ ሁኔታ መሳቂያ የምታደርግ አቋም ነበረች፡፡ የኢትዮጵያን አቋም ጣፋጭና ሬት ጣዕም የሰጡትም የሚከተሉት ቅመሞች ነበሩ፡፡ ‹‹የአፍሪካውያንን ጉዳይ በአፍሪካውያን በመፍታት›› መርህ መሠረት በኦባሳንጆ የተጀመረውን ጥረት አክብሮ እንዲቀጥል መውደድ፣ ‹‹ያለ ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር መምጣት›› በቅድሚያ ተኩስ ማቆም የሚል ጥያቄን በቅድመ ሁኔታነት ውድቅ ለማድረግ የሚመች (ተኩስ የማቆምን ነገር የድርድር አንድ ይዘት የሚያደርግ) መሆኑ፣ ይህም ጉዳይ ከኢትዮጵያ አንድነትና ሕገ መንግሥት ጋር ተገናዝቦ ሲመጣ፣ የድርድሩ የማዕቀፍ ግቢ ከመነሻው የሕወሓትን አገር የመሆን ፍላጎትና ባለ መከላከያ ኃይልነት ኢሕገ መንግሥታዊ አድርጎ ያስቀመጠና በዚሁ ሐዲድ ላይ የሚጓዝ መሆኑ፡፡ እነዚህ ቅመሞች በአንድ ላይ ለዕንቢ ባይ መፈናፈኛ የማይሰጥ ወጥመድ ይሠራሉ፡፡ ከዚህ ወጥመድ ለማምለጥ ሕወሓቶች ሄደው ሄደው ሌላ የወረራ ዕብደት እንደሚፈጽሙም የኢትዮጵያ መንግሥት አስቀድሞ አውቆ እየተጠባበቀ የነበረ ይመስላል፡፡ እንዲያውም ቶሎ ወረራ እንዲፈጽሙ እያጣደፋቸው ነበር ቢባል ሳይሻል አይቀርም፡፡ እነሱ የአማራና የአፋር ወሰን አካባቢ የሚያደርጉትን መንፈራፈር አነሰም በዛ ባለበት እንዲረግጥ አድርጎ የኢኮኖሚ ስንቅ በልማት የማደርጀቱን ሥራ ማፋጠኑ፣ የመከላከያና የደኅንነቱን አውታራት ጥራት ማትባት መቀጠሉና እንደ ኦነግ ሸኔ ያሉ የሕወሓት ቅርንጫፎች ላይ ብርቱ ምንጣሮ ማካሄድ ውስጥ መግባቱ፣ ብቻህን ሳትቀር ቶሎ ወረራ ብትከፍት ይሻልሃል እያለ የሚያስፈራራ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ማለቂያ ያጣው ጦርነትና ወታደራዊ ምልመላ ብሶትና ጉምጉምታን እያሳደገ መሄዱ፣ ለሕወሓት እዚሁ እያለህ የሕዝብ ቁጣ እንዳይፈነዳብህ የሚል ሌላ ማስፈራሪያ ነበር፡፡ በዚያ ላይ የዕርዳታ መጉረፍ የትግራይን ሕዝብ ነፍስን ከማዳን ይልቅ ለሕወሓት ጦረኞች የመዋጊያ ስንቅና ለግዳጅ ምልመላ ማጥመጃ እንደሚውል እየታወቀውም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በልበ ሙሉነት በየብስም፣ በአየርም ዕርዳታ ለትግራይ ሕዝብ እንዲገባ መተባበሩ በትግራይ ሕዝብ ዘንድ አዎንታዊ የፖለቲካ ዋጋ የሚያስገኝ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ነጥብ የሚያስገኝ ነበር (ማለትም የኢትዮጵያ ዕርዳታ እንዲገባ መተባበርና ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ መሆን፣ ሕወሓት ኢትዮጵያን በማዕቀብና በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እነቁልኝ እያለ ኡኡታ ለማቅለጥ እንዳይችል፣ ምዕራባዊ ደጋፊዎቹም ኢትዮጵያን ለመሰቀዝ ሰበብ እንዲያጡ ያደረገ ውሳኔ ነበር)፡፡
የኢትዮጵያን መንግሥት ከልበ ሙሉነት ወደ መዝረጥረጥ ለማውረድና ደካማ ተደራዳሪ ለማድረግ የተደረጉ ሙከራዎችን ኢትዮጵያ ያወራረደችበት ንቃትና ቅልጥፍና ጊዜ መቀየሩን ለጠላትም ለወዳጅም ያወጀ ነበር፡፡ ጨለማን ተገን አድርጎ መሣሪያ በአየር ለማስገባት ቢሞከር የኢትዮጵያ አየር ኃይል መትቶ አቦነነው፡፡ በምዕራብ ከሱዳን ተንደርድሮ የኢትዮጵያን ሠራዊት ለማጥቃት የሞከረ የታጣቂ ቡድን እምሽክ ተደረገ፡፡ በሶማሊያ ድንበራችን በኩል በገፍ የመጣ የአልሸባብ ሠራዊት ወደ መታረጃው እንደሚነዳ ከብት ወደ ውስጥ በደንብ እንዲገባ ተደርጎ ላስ ተደረገ፡፡ ይህ ሁሉ ድል ለሕወሓቶችና ለአጋዦቻቸው ያንኑ ወረራ ከመክፈት በቀር ሌላ ማስገዳጃ እንፈጥራለን ብሎ ማሰብን ሱሚ ያደረገ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ‹‹ኤር ባስ›› እና ከ‹‹ቦይንግ›› ኩባንያዎች ጋር ያደረጋቸው ግብይይት ነክ ስምምቶችም ሆኑ፣ ከዓለም ባንክና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ጋር ያካሄዳቸው መግባባት የታየባቸው ንግግሮችም አነሰም በዛ የማዕቀብ ክንድን የማዛል ፖለቲካዊ ዋጋ ነበራቸው፡፡ ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የአፍሪካ ወጣቶች የአፍቃሪ – አፍሪካዊነት ስብሰባ ማካሄዳቸውም ኢትዮጵያ ብቻዋን አለመሆኗን የሚያስተጋባ ጠቀሜታ ነበረው፡፡
የሕወሓት ጦረኞች ሌላ መፈናፈኛ አጥተው ያለ የሌለ ኃይላቸውን በሦስተኛ ዙር ወረራ ሲያነቃንቁም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ራስን የመከላከልና አገር የማዳን ተፈጥሯዊ መብቱን ተጠቅሞ (በዲፕሎማሲያዊ ኩነናና በማዕቀብ ተጠቂ በማይሆንበት አኳኋን) ጦርነቱ ውስጥ እንዲገባ ነበር የፈቀዱለት፡፡ የተሰጠውን ፈቃድም የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያኮራ አኳኋን ሊጠቀምበት ችሏል፡፡ ‹‹መከላከል›› የምትባለዋን የቃል አጠቃቀም አጥብቆና ለሰላም ሲል ያለ ቅድመ ሁኔታ መደራደር ፅኑ አቋሙ መሆኑን እያስተጋባ፣ ሌላ ዙር ወረራ እንደማይመጣ አድርጎ አቅዶና በአራቱም ማዕዘን የኃይል እንቅስቃሴውን አሰማርቶ፣ ለሙሉ ድልና ለድል ልፋፋ ሳይጣደፍ፣ የአየር ጥቃትን ከምድር ምት ጋር አዋድዶ ጥናትና የውስጥ አርበኛ መረጃ በተሟላበት አኳኋን የሕወሓትን ወታደራዊ የመሣሪያና የማሠልጠኛ አቅሞችን እያደባየ፣ በግዳጅ የተሰባሰበ የሕወሓት ተዋጊ በፊት ለፊት ሲጠብቀው ከጀርባ ሰተት እያለ፣ ያፈገፈገና የሸሸ መስሎ ድግን በድግን የሆነ ወጥመድ ውስጥ እያስገባ፣ በዚህም ዘዴ ምርኮኞችንና እጅ ሰጪዎችን እያበራከተ፣ ሰምና ወርቅ ያለው የጦርነት፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ትንቅንቅ እንዴት ያለ ብዙ ጩኸት መከናወን እንደሚችል (የኃያላንን ጫናና የጣልቃ ገብነት ፍላጎት እንዴት ማንከርፈፍ እንደሚቻል) አሳየ፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን እንደ ትንሽ ልጅ የፖለቲካና የወታደራዊ ሀሁን ለማስተማር ይቃጣቸው የነበሩ ጮርቃ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ወፍራም ምላሳቸውን ሰብሰብ አድርገው፣ ሁሉም ነገር ሰምና ወርቅ እንዳለው እንዲማሩ አደረጋቸው፡፡ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ያሞገሱ መስሏቸው የውጊያ ታክቲኩን በይፋ እስከ ማውራት የዞረባቸው ወሬኞች ባይታጡም፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን ሰምና ወርቅ የተረዳና ያልዘባረቀ ትግልን በውጭም በውስጥም ያሉ አገር ወዳዶች ለማካሄድ ቻሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን ‹‹ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመደራዳር ዝግጁ ነኝ›› ባይነት በሸፍጥ ሳይጠረጥሩና ሳይቃወሙ፣ በጥቅምት መጀመሪያ አጋማሽ (2015 ዓ.ም.) የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከሕዝብ ጋር የተመሙባቸው፣ ምዕራባዊ ኃይሎች የጫና እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ የጠየቁ ሠልፎች በአገር ውስጥና በውጭ መቀጣጠላቸው፣ ሰምና ወርቅን የማወቅ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ከበሮ መቺው፣ የትንፋሽ መሣሪያ ነፊው፣ ክራር ከርካሪውም አንድ ላይ የተግባቡበት ኦርኬስትራዊ ኅብረ-ዜማ ማለት እንዲህ ነው! ‹‹የአሸባሪውን ቡድን ጥቃት እየተከላከልኩ ነው›› በሚል ዘይቤ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ፊት ሲገፋ፣ በአየርና በየብስ ጎዳና ዕርዳታ ፈጥኖ የሚገባበትን ሁኔታ አቅዶ የተዘጋጀበት መሆኑንም በዚህ ኦርኬስትራዊ ሙዚቃ ውስጥ ደምሩት፡፡ ያ ከመሟላቱ በፊትም የሕወሓትን ጦር እያራወጠ በገባባቸው ሥፍራዎች ሕዝብ እየሰበሰቡ ብሶት መስማትና ከሕዝብ ጋር መምከር፣ መሠረተ ልማት መልሶ መጠገን ቅድመ መሰናዶ የተደረገበት መሆኑን ማሳወቅና በመጋዘን የተገኘ ዕርዳታ ለሕዝብ ማዳረስ፣ መከላከያ ሠራዊት ለደረሰለት ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ በሕወሓት ዕገታ ውስጥ ለሚገኘው ሕዝብና ለዓለም ኅብረተሰብ የሚሰደው አዎንታዊ መልዕክትም የሙዚቃው አካል ነበር፡፡ የመከላከያ ሠራዊት እየፈጠነና እያካለለ ይበልጥ ወደ ውስጥ ሲዘልቅ የመግለጫው (የመንግሥት መግለጫ) አንድ አካል ሆና ብቅ ያለችው፣ ‹‹የፌዴራል ተቋማትን/የአየር ማረፊያዎችንና የትግራይ ሕዝብን የመጠበቅ ኃላፊነቱን የፌዴራል መንግሥት ይወጣል…›› ገደማ ያለች ንግግርም በቅኔ መንገድ የተነገረች፣ በአየር ጣልቃ መግባትን እንዳትሞክሩት የሚል ደወል ያላት የሙዚቃው አካል ነበረች፡፡ ‹‹ከተማ ከተገባ ሰው ተፈጀ… የዘር ጭፍጨፋ ሊፈጸም ነው!… ንፁኃን ላይ ጥቃት እየደረሰ ነው! ዓለም ምነው ዝም አለ!!›› የሚል ቀጣፊ የጩኸት ቱማታ በበረከተበት ሁኔታ ውስጥ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት በመረጃ በተደገፈ ጠንቃቃነት ከተሞችን እየተቆጣጠረ ለመሄድ መቻሉ ቱማታውን በልጦ መደነቅን ያስከተለ የሙዚቃ ኅብረ-ዝማሬው አካልም ነበር፡፡
እንዲህ ባለ ኦርኬስትራዊ ኅብር ውስጥ ከሚሰዋው የግዳጅ ተዋጊ ይልቅ፣ የሚማረከውና እጅ የሚሰጠው በርክቶ፣ የተሸሸገ መሣሪያ በጥቆማ እየተሰበሰበ ከመሄዱ ጋር፣ በሕወሓቶች ላይ የዞረ ቁጣና ዕልልታ ዝምታን ሰብሮ አደባባይ ለአደባባይ ቢገማሸር ኖሮ ጦርነቱ ሳያልቅ ባለቀ ነበር፡፡ የሰላም ውይይቱም እንደዚያው በሆነ ነበር፡፡ ሕዝብ ላይ የተተበተበው የአፈናና የፍርኃት መዋቅር ገና ስላልተበጣጠሰ የሕዝቡ የተንገሸገሸ ስሜት ይዘግይ እንጂ ኃይል አጠራቅሞ መናዱ አይቀርም፡፡ የሰላም ስምምነቱ አልዋጥ ያላቸው አንዳንድ ግትሮች ሌላ ዙር የሽምቅ ውጊያ ታሪክ በትግራይ ውስጥ ሊጀምሩ ቢሞክሩም፣ ሙከራቸው ወደ ሕዝባዊ ትግልነት የማደግ ዕድሉም የሞተ ያህል ነው፡፡ ምክንያቱም ከሁሉም ነገር በላይ፣ እነሱ የትግራይ ሕዝብ ብሶት መሪዎች ሳይሆኑ፣ በትግራይ ሕዝብና በቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደምና ዕንባ የታጠቡ ናቸውና፡፡ በ27 ዓመታት የፌዴራል ዋና ገዥነታቸው ጊዜ ከሠሯቸው በደሎች በላይ በሦስት ዙር ወረራዎቻቸው የፈጸሟቸው ግፎች አጋልጧቸዋል፡፡ ልጆቹ ጥላቻንና በቀልን እየተከተቡ የተማገዱበትና ብዙ አበሳ ያየው የትግራይ ሕዝብ ዕንባውን እያዘራ በነፃነት አየር ውስጥ ሆኖ ጉድ ሲያወጣ ደግሞ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጥፊነታቸው ፀሐይ የሞቀውና ማሳበቢያ የለሽ ይሆናል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ከሌላ የጦርነት ጉሰማ ጋር እሽክም ለማለት የተረፈ ሐሞት አይኖረውም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከሕወሓት በኋላ የሚመጣው የሕዝብ ሕይወትን የሚነካ የልማት እንቅስቃሴ፣ ሽምቅ ውጊያን መጋቢና ሸሻጊ የለሽ የሚያደርግ ነው፡፡
መ) እናም፣ ጦረኝነት ላይመለስ መሄዱ አይቀሬና ባለብዙ ትርጉም ነው፡፡ ከምዕራባዊው ዓለም እስከ ኢትዮጵያ ድረስ የተዘረጉት የጠባብ ጃጃቲያሞች በተለየየ የቡድን መልክ ያካሄዱት በጥላቻና በጭካኔ የተሞላ ግፍ፣ የብርሔተኝነትን/የጎጠኝነትን የመጨረሻ ዝቅጠት የሚወክል ነው፡፡ የአሁኑ የሕወሓት-ሸኔና ሌሎች ቅጥልጣዮች መደቋቆስም፣ ከእኛ ትውልድ የመጣውን ቂመኛ ብሔርተኝነት የመንቀል ሒደት ወሳኝ ምዕራፍ ነው፡፡ ሥር እንዳይቀጥል አድርጎ የመንቀሉ ሥራ ገና የማይናቅ ሥራ አለበት፡፡ የሆነች የኢትዮጵያ ዳርቻ አካባቢ ጠመንጃ ይዘው በሞትና ሕይወት መሀል እያቃሰቱ ትንሽ ጊዜ የሚያንቋርሩ ርዝራዦች ይኖሩ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ሁለገብ ግስጋሴና የዜጎች የሰብዕና ብልፅግና ጨረሩ እየበረታ ሲሄድ ግን እነሱም ክሽልል እያሉ ታሪክ ይሆናሉ፡፡
ሰንኮፍ ነቀላውን እያጠናቀቁ በቁሳዊና በመንፈሳዊ ባህል የለማችና የቀጣናዋ ፈርጥ የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባቱ ዋና ኃላፊነት፣ ‹‹የእነ ሮባ ጴጥሮስ›› ትውልድ ነው፡፡ ‹‹ሮባ›› እያልኩ ስናገር ሮባን የተጠቀምኩበት እንደ ተምሳሌት (ሲምቦል) ነው፡፡ ምክንያቱም ግዕዝን እስከ መር የተራመደው ሮባ የአዲስ ኅብራዊ ወጣቶችን ምሥል አሳምሮ ስለወከለልኝ ነው፡፡ ከ1960ዎች ትውልድ ርዝራዦች መሀል በሰንኮፍ ነቀላና በኅብረተሰብ ህዳሴ ኢትዮጵያን የጠቀሙም ሆኑ ኢትዮጵያን እስከ መበተንና እርስ በርስ እስከ ማጨራረስ ዓላማ ድረስ የዘቀጡ፣ ዘቅጠውም ዝቅጠታቸውን ለማውረስ የለፉና አሁን የመጨረሻ ቋራርታ ውስጥ የሚገኙት ሁሉ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የእኔ ትውልድ ፈርጆች ናቸው፡፡ የእነሱ አዎንታዊም ሆነ ሰንኮፋዊ ሚና የእኔም ገጽ ነው፡፡ ‹‹የሰሚ ያለህ›› በተሰኘ ያልታተመ ጽሑፌ ውስጥ የዚያን ትውልድ የፖለቲካ ድክመትና እሽቅድምድም ከእነ ለጣቂዎቹ ተችቻለሁ፡፡ ያኔ ስተች ግን ራሴን ከውጭና ከላይ ባደረገ ዓይነት ስሜት ነበር፡፡ አሁን ግን የራሴንም የወጠጤ ፖለቲከኛነት ገጽታ አስተውዬ ለማፈርና ለመፀፀት በቅቻለሁ፡፡ ያኔ የተፈጠረው የተጠማመደ መፈራረጅና መቀናደብ ሁሉ የእኔም የሁላችንም የቅሌትና የኃፍረት ገጽ ነው፡፡ የዚህ የኃፍረት ገጽታ እንደ እኔ የተሰማችሁና ፀፀት ያላችሁ የእኔ ትውልድ ርዝራዦች በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ውስጥ የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ ሰላምና መተሳሰብ ማገዝ ንሰሐ ይሆናችኋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለሌሎች ሆኜ መናገር ባልችልም በበኩሌ በሕወሓትነትና በሸኔነት የታየውን ዕብደት ከእነ ግፉ – ጉዴና ፀፀቴ ብዬ የኢትዮጵያን መላ ኅብረተሰብ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ከእስካሁኑ ቀጋ ልምዳችን ትምህርት ሰጪ የሆኑ ነገሮች ሲኖሩኝ ከማጋራት በቀር፣ ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ አለመፈትፈት የንሰሐዬ ማረጋገጫ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የእኔን የንሰሐ ይቅርታ ጥየቃ ለመሸርደድ ድፍረቱ አለኝ የሚል እንደማይኖርም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ሕወሓትና ሸኔዎች ይህን ሁሉ ግፍ ለማድረስ የሚያስችል አቅም ለመገንባት መቻልም ሆነ፣ ‹‹360›› ምንትስ የሚባሉና እንደ እነሱ ፖለቲካ የማይቆረጠም የኮክ ፍሬ የሆነባቸው ወጠጤዎች የተያያዙት የጥፋት አዛቋኝነት ሁሉ የፖለቲካችን ድህነት ውጤት ነው፡፡ በዚህ የፖለቲካ ድህነት ኩሬያችን ውስጥ ያልቆመ ፖለቲከኛ ደግሞ የለም፡፡
በዚህ ኩሬ ውስጥ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሁሉ እንዳለንበት አስተውለን፣ ጥፋታችንን ለመመርመር የምንደፍር ምን ያህል እንደምንሆን ለመገመት ግን በጣም እቸገራለሁ፡፡ ለዚህም የዕለት ተዕለት ኑሯችን ጥፋትን ማስተዋልና ይቅርታን ብዙም የማይወድ መሆኑን፣ የትናንትናም ሆነ የዛሬ ፖለቲካችን ገመናውን በአግባቡ የመመርመር ችግር ያለበት መሆኑን በእማኝነት መጥቀስ እችላለሁ፡፡ ‹‹ሕወሓት ኢትዮጵያን ክዶ የወራራት እኔ ካልገዛኋት ምን ታደርግልኛለች ብሎ ነው፤›› የሚል መሳይ ማጠቃለያ ሙሉ እውነቱን እንደማይናገርም ደፍሬ መናገር እችላለሁ፡፡ በኦነጋዊውና በሕወሓታዊ መስመር ውስጥ ምንም ነገር ቢያሳዩዋቸው የማይመለሱ በቁማቸው የተገነዙ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ በተለይ በሕወሓቶች ውስጥ የነበረ ትዕቢት፣ እንኳን በእናቶች የእንብርክ ተማፅኖና ዕንባ በሌላም የማይርስ እንደሆነም አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን እንደ ሸኔ ያለ ፖለቲካ የለሽ አራጅ ቡድን እንደምን ጆሮ ሊያገኝ ቻለ? እነ አረና ትግራይ የለውጡ ንቁ ተዋናይ በመሆን ፈንታ ስለምን ድንግርግሮሽ ሰለቀጣቸው? በጠንቃቃነቱና በብልህነቱ ዙሪያ-ገብ ኢትዮጵያን የማረከና የሚታፈር የፖለቲካ ማዕከል ፖለቲካችን ማኩረት ችሎ ቢሆን ኖሮ፣ የፖለቲካ ምኅዳራችን ያም ያም እየተነሳ ልናደፍ፣ ልንደቅደቅ የሚልበት ይሆን ነበር? እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በሚዛናዊ ህሊና ከመረመርን የፖለቲካችን ጉፋያነት የተጠያቂነትም ድርሻ እንዳለው ማየት አይከብድም፡፡
ይህንን ጉዳይ በማንሳቴ የሚበሳጩ (‹‹አሁን ወደኋላ ተመልሶ ይህንን መነካካት ለምን?›› የሚሉ) እንደሚኖሩ አልጠራጠርም፡፡ ጥፋትን/ስህተትን መለስ ብሎ መመርመር እየታረሙ ለመሄድ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ኃፍረትና ፀፀት የሚያውቅ መታረም ኖሮን ቢሆን ኖሮ፣ አንዳንድ የፖለቲካ ቡድኖች ብዙ ገመና ያለበትን የዱሮ የድርጅት ስማቸውን ዛሬ ይዘው ባልመጡ ነበር፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ኢሠፓ በሚል ስም ለፓርቲነት መዝግቡኝ የሚል ባልታየ ነበር፡፡ የመከላከያችንን ትልቅ ዕዝ በማረድ የተከፈተ ግፈኛ ጦረኝነት ፖለቲካ ነኝ ሲል እንዳየን ሁሉ፣ የሐሰት ሥራ እየፈበረከ በማወናበድና በጥላቻ እያወረ ልጆቹን ለግፈኛ ጦርነት በማገደበት የትግራይ ሕዝብ ፊት ቆሞ፣ የጭካኔ ትርዒቶች የፈጸመበትን አፋርና አማራ እያማተረ ከአሁን በኋላም ‹‹ፖለቲካ አለኝ›› የሚል ትኩስ ዓይን አውጣነት አፉን ሲከፍት አናይም ይሆናል፡፡ የዚህ ዓይነቱን ዓይን አውጣነት የሚወልደው ፀፀት አልባነት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ኃፍረት የለሽነቶችን ከጥፋት ባለ ድርሻነት ለመሸሽ መፅናኛ ልናደርግ አይገባንም፡፡ ማድረግ የሚገባን ከእነሱ አንፃር ቆሞ የእነሱ ጋራ የሚያህል ዓይን አውጣነት ማጉያ መነፅር መሆንና የእነሱ ኃፍረተ ቢስነት ደባል ለመሆን አለመፍቀዳችንን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ትናንትና የሠራነውን ስህተት/ጥፋት አሁንም ነገም ላለመድገም፣ መለስ ብሎ ያለፈ ልምዳችንን መመርመር አስፈላጊያችን ነው፡፡ ፖለቲካችንና አገራዊ ምክክራችን ይህንን ዘሎት እንደማይሄድ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሠ) ተካረው መታመስና መጠዛጠዝ ውስጥ በገቡ በየትኞችም ወገኖች አካባቢ እናቶች፣ አባቶችና ሕፃናት ለደረሰባቸው መስዋዕትነት መፈናቀልና የውስጥ ስደት፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከመደበኛ ሚዲያ እስከ ሶሻል ሚዲያ የተንቦጫረቅን ሁሉ/ዳር ቆመንም ስንሸረደድ የነበርን ሁሉ የህሊና ተጠያቂነት እንዳለብን ካላየንና ፀፀት ካልዘለቀን፣ ያለፈው የሕዝብ አበሳና የተትረፈረፈ መስዋዕትነት እንዳይደገም የሚያደርግ ፅኑ ቁርጠኝነት እንደ ምን ሊኖረን ይችላል? ጥንቃቄ፣ ስክነት፣ ብልህነትና አርቆ አስተዋይነት የፖለቲካና የመንግሥት አመራር ሁነኛ መሣሪያዎች መሆናቸውን አውቀን አጥብቀን ልንይዛቸው የምንተጋው በልቅ አፍና በዝርክርክ ፖለቲካ ምን ያህል ጉዳት እንደሚደርስ ስናጤንና ስናፍር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካና ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የፈለገው ዓይነት አለመግባባት ቢፈጠር በሚቻለው ሁሉ፣ በእርጋታና ባለመታከት በሰላማዊ ዘዴዎች ችግሮችን መፍታትንና በትንሽ በትልቁ የፀጥታ ኃይሎቻችንን መስዋዕትነት አለማድፋፋትን የምናጠብቀው፣ ከጎረቤት አገር የጉልበት ሥራ ቢገጥመን እንኳ ለተመሳሳይ አፀፋ ከመቸኮል ፈንታ ለንግግር ትልቅ ቦታ ልንሰጥ የምንችለው፣ ከልምዳችን ስንማርና ለሰዎች መስዋዕትነት መሳሳትን ስናውቅ ነው፡፡ ፖለቲካችን ምን ያህል ድኩም እንደነበር ስንመረምርና በድኩምነቱም ምን ያህል የሕዝብ መከራ መንስዔና አባባሽ እንደነበር ስንረዳ፣ በፖለቲካችን መዘዝ ሕዝባችን የከፈለው መከራና መስዋዕትነት ሲያንገበግበን ነው ፖለቲካችንን አርሞ የማብሰል ተግባርን የምናውቅበት፡፡
ከልምድ ተምሮ የመታረም ጉዳይ ለነገ የማሰብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የአሁናችንም ጥያቄ ነው፡፡ ረቡዕ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና በሕወሓቶች መካከል የተደረሰው ስምምነት ተፈጻሚነት ከትናንት ልምድ መማር አለመማራችን የሚፈተንበት ነው፡፡ ‹‹ቀንደኞቹ ሳይያዙ/አይቀጡ ቅጣት ሳይቀጡ ሰላምማ እንዴት ብሎ!…›› እያሉ ከወዲህ የሚቃጠሉ ሰዎችና ባህር ማዶ ተቀምጠው ስምምነቱን በክህደትነት እየኮነኑ ‹‹ረዥም የትጥቅ ትግል ውስጥ ካልተገባ!›› የሚሉ ሰዎች ከልምድ መማር ይቅርና ሰብዓዊ ርኅራኄ የጠፋባቸው፣ ከእነሱ ውጪ ያለውንና ወደ ጦርነት ዓውድማ የሚሰማራውን የሰው ነፍስ ከጭራሮ የበለጠ ዋጋ የማይሰጡ ናቸው፡፡ ‹‹ስምምነቱ መሬት ላይ የተገኘውን ድል የሚያንፀባርቅ ስለሆነ፣ ሕወሓቶች ቢያፈገፍጉ እንኳ በግድ ተፈጻሚ መሆኑ አይቀርም…›› የሚል ሐተታ የሚረጭ ቡትለካም ከልምድ መማር አልነካካውም፡፡ ‹‹በግዳቸው›› የሚል ትዕቢት፣ ማንገራገርና ተጨማሪ መስዋዕትነት እንዲከተል ይጋብዛል፡፡ ስምምነቱን የጀግናው መከላከያችንና የፌዴራል መንግሥት ድል ባደረገ ጠባብ ግንዛቤ ተወጥሮ ጉራ ችርቸራ ውስጥ መግባትም ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ ጦርነት ሰዎች ደም እየተራጩ የሚረግፉበት እንጂ፣ የውኃ መራጨት ግጥሚያ አይደለም፡፡ ከወዲህም ሆነ ከወዲያ ሲረግፉ የነበሩት ደግሞ የገዛ ወገኖቻቸው እንደመሆናቸው በሁለት ወገን የሚደርሰው ጉዳት ልብን የሚያስለቅስ እንጂ፣ ጉራ የሚያስቸረችር አይደለም፡፡ ጦርነት ለዘለቄታው መቆሙ ዕፎይታነቱም ድልነቱም የመላ ኅብረተሰባችን ነው፡፡ ከልምድ በአግባቡ የተማረ የፖለቲካ ሰው ሕወሓቶች የጥቅምት 23ቱን ስምምነት በመፈረማቸው፣ ለዘላቂ ሰላም ያዋጡትን አስተዋጽኦ ማስተዋልም ይገባዋል፡፡ ጉዳያቸው የጥቂት ግለሰቦችን ነፍስ ማትረፍ ቢሆን፣ በሰላም ውይይት ሽፋን ሾልከውና ውይይቱን በትርፍ የለሽነት አቅልለው ዘወር ማለት ይችሉ ነበር፡፡ ከዚያም አልፈው የትጥቅ ትግል እጅግም ዕድሜ እንደማይኖረው እያወቁም፣ ለምንተፍረታቸው ሲሉ ‹‹ወዳጅ አገር›› ውስጥ ተቀምጠው የትጥቅ ትግል ጀምረናል ሊሉ ይችሉ ነበር፡፡ ከዚህ ዓይነት ነገር ተቆጥበው ያንን የመሰለ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ቢያንስ በይፋ ከእንግዲህስ የትግራይ ሕዝብ መድማቱ ይብቃ የሚል ውሳኔ ላይ መድረስን የሚጠቁም ነው፡፡ ይህም ተመሥገን የሚያሰኝ ነው፡፡ ስለሆነም ከሁለት በኩል ድንፋታና የበቀል ፊር ፊር የምንወድ ሰዎች አደብ የመግዛት ጥረት ይታይብን! ቢያንስ ከኢትዮጵያ ቤተ እምነቶች በኩል የመጣ ተማፅኖናና ሰላሙ ዕውን እንዲሆን የሚካሄድ ፀሎት ይክበደን!! ለኢትዮጵያ ሰላም የለፉ ሁሉ ምሥጋና ይድረሳቸው!!!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡