በበየነ ሞገስ
ላለፉት አራት በተለይም ሁለት ዓመታት አገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ነበረች፡፡ ጊዜያቱም ወያኔ በሕዝባዊ ማዕበል ሥልጣን የለቀቀበትና ወደ መቀሌ ጓዙን ጠቅልሎ የገባበትን በማስላት ነው፡፡ አገራችን በውጭም እንዲሁም በአገር ውስጥ በሚገኙ ባንዳዎች አማካይነት የሚደርስባት ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም፡፡ በጣሊያን ወረራ ወቅት ዋናውን ጠላት ለመለየት አስቸጋረ አልነበረም፡፡
ከሁሉ የሚከፋው የራስ ወገን ሆኖ፣ ወገኑን በቀለምም ሆነ በሌላው መስሎ ጠላትነቱ በተግባር እስካልታየ ድረስ ማንነቱን ለማወቅ አስቸጋሪ የሆነውን ባንዳ ነው፡፡ በዚህች ሁለት ዓመታት ባንዳዎች በአገራችን ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ምኅዳር ላይ ያሳደሩት ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም፡፡ ማንነታቸውንም ሆነ ተግባራቸውን ለመግለጽ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ባለመሆኑ ለታሪክ እተወዋለሁ፡፡
ባንዳዎች ከሚያደርሱት ተፅዕኖ በተጨማሪ ለማመን በሚከብድ፣ እንዲሁም ይሆናል ተብሎ በማይገመት መልኩ ‹በኃያላን› ተፅዕኖ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም 2015 ዓ.ም. ድረስ፣ የኢትዮጵያን ጉዳይ ለመመልከት አሥራ አራት ጊዜ ያህል ስብሰባ ተቀምጧል፡፡ የእነዚህ ስብሰባዎች ዓላማ ግልጽ ነበር፡፡ አፋፍ ላይ ሆኖ ከወራጅ ወንዝ ውኃ የሚጠጣው ጅብ ከሥር የምትገኘውንና ከእሱ የተረፈውን ውኃ የምትጠጣውን ‹ውኃውን አደፈረሽብኝ› አላት እንደተባለው፣ የምዕራባውያንና የአሜሪካን ፍላጎትም ምክንያት ፈልጎ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ በማስጣልና ይህንኑ የተዳከመ ኢኮኖሚ በማሽመድመድ፣ አገሪቱን መንግሥት አልባ ለማድረግ በዚህም ለወያኔ ወይም ለመሰሉ የሥልጣን መደላድሉን አመቻቸቶ ወይም እነሱ ሊጋልቡት ለሚችሉት አካል የመንግሥትን ሥልጣን ለማስያዝ መሆኑ አይካድም፡፡
መቼም ምዕራባውያንና አሜሪካ ወያኔን ዝለል ሲሉት ‹ለምን› የሚለውን ጥያቄ ለማቅረብ የሞራል ብቃት ስለሌለው፣ ‹ስንት ሜትር ልዝለል› በማለት መመርያ ለመቀበል በመዘጋጀት ትዕዛዛችውን ይፈጽማል፡፡ እነሱም የሚፈልጉት እንደዚህ ዓይነቱን ሞራለ ቢስ ታዛዥ ባሪያ ነው፡፡ ነገሩን በአንክሮ ለሚመለከተው የወያኔ አባላትና ደጋፊዎች ሌላው ቢቀር አንኳን በአፍሪካዊነታቸውና በጥቁርነታቸው ማንነታቸውን የማያስከብሩ ዝቃጭ መሆናቸውን ነው፡፡ ይህን እኩይ ፍላጎት በአምላክ ቸርነት ለእውነት በቆሙ መንግሥታት አማካይነት ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ለእነዚህ በፈተና ወቅት በጎናችን ለቆሙ መንግሥታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ውለታቸውን ምንጊዜም እንደማይረሳው አምናለሁ፡፡
ምዕራባውያንና አሜሪካ በአገራችን ላይ ያልሸረቡት ሴራና ተንኮል አልነበረም፡፡ የሆነውን አልሆነም፣ ያልሆነውን ሆኗል እያሉ ዜናቸው በእውነት ላይ የተመሠረተ ነው ብለን ጠዋትና ማታ በምናዳምጣቸው ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ አልጄዚራና በመሳሰሉ የዜና ማሠራጫዎች የተቀረውን ዓለም ሲያወናብዱ ከረሙ፡፡ በዓለም ላይ ለሚሠራጭ ዜና፣ በተንኮለኞቹ ምዕራባውያን/አሜሪካ ለሚወሰዱት የፖለቲካ አቋሞች ትንታኔ ለመስጠት በቂ ተሞክሮ እንዳገኘን በዚህ አጋጣሚ አምናለሁ፡፡
እነኝህ ውሸታምና የተንኮል ፈላስፎች አገራችንን ለማዳከም ከወሰዷቸው መጠነ ሰፊ ተግባራት ለምሳሌ ያህል ጥቂቱን እንጥቀስ ለሰሜኑ ወገናችን ዕርዳታ እናስገባ በሚል ሰላዮቻቸውን በማስረግ ለወያኔ ሠራዊት የመከላከያን የእንቅስቃሴ መረጃ በመንገር፣ በዕርዳታ ስም የጦር መሣሪያ በማስገባት፣ በመከረኛው የትግራይ ሕዝብ ስም የምግብ ዕርዳታ እንስጥ በማለት ለወያኔ ጦር ስንቅ በማቀበል፣ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው የመከላከያ ኃይል የወያኔን ምሽግ በሚሰብርባቸው ጊዜያት ተከምረው የሚገኙት የስንቅ ዓይነቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ይህን ሁሉ ሲያደርጉ የዜና ማሠራጫዎቹም ሆኑ መንግሥታቱ እርስ በርሳቸው እየተናበቡ መሆኑ ድርጊቱን የበለጣ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡
‹የዕብድ ገላጋይ ዱላ ያቀብላል› እንደሚባለው በወያኔና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በተፈጠረው ጦርነት ሰላም እንዲሰፍን ከማድረግ ይልቅ፣ እርስ በርሳችን በማስተላለቅ የረዥምና የአጭር ጊዜ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሞከሩ፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት በልምድ ሆነ በትምህርት የማይመጥኑትን አባላቸውን በኃላፊነት ደረጃ እንዲሰየሙ አደረጉ፡፡ ሰውየው በዚህ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ከተቀመጡ በኋላ ምን እያደረጉ እንደነበር በቅርብ የሚታወቅ በመሆኑ መዘርዘሩ አስፈላጊ አልመሰለኝም፡፡ እኝህን ሰው የዓለም ጤና ድርጅት እንዴት ለዚህ ቦታ እንደመረጣቸው በበኩሌ ለማወቅ ጉጉት አለኝ፡፡ ጊዜው ሲደርስ የተሸፈነው ሲገለጽ ያኔ የምናውቀው ይሆናል፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋልና ወያኔ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜኑ ዕዝ ሠራዊት ላይ ለመንገርም ሆነ ለመጻፍ የሚዘገንን ጥቃት ከፈጸመ በኋላ፣ ተመሳሳይ ወረራውን በሌሎች የተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች አስፋፍቷል፡፡ በዚህም ወረራ እንኳን የሰው ልጅ ሰይጣንም ይፈጽመዋል ተብሎ የማይገመት ድርጊት በአገራችንና ወገናችን ላይ ፈጽሟል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኝት ‹የተካደው ሰሜን ዕዝ› በሚል ርዕስ የቀረበውን የጋሻዬ ጤናውን መጽሐፍ ማንበቡ ይጠቅማል፡፡
ወያኔ አባሮ፣ አስሮና አሰቃይቶ በተለያየ መንገድ ሰቆቃ የፈጸመባቸው እነ ስዬና መሰሎቹ ባላቸው አቅምና መድረክ ሁሉ ኢትዮጵያን ለማጥፋት፣ ካልተቻለም ለማዳከም ጥረታቸውን በሚገርም ሁኔታ ከወያኔ ጎን በመሆን ቀጥለው ተመልክተናል፡፡ በውጭ የሚገኙ የዲያስፖራ አባላት መሬት ላይ በመንከባለል ጭምር ‹ብሶታቸውን› ለአሜሪካ መንግሥት፣ ባለሥልጣናትና ለሕዝብ ለማሰማት ሙከራ አደረጉ፡፡ ከሁሉ የሚገርመው በደቡብ አፍሪካ ከተደረሰው የሰላም ስምምነት በኋላ በቅርቡ እንደምንሰማው መንገድ በመዝጋት፣ ይህንን እንኳን የተስተካከለ አዕምሮ ያለው ቀርቶ ዕብድም ቢሆን በመልካም ሁኔታ የሚቀበለውን የዕርቅ ሒደት በመቃወም፣ ‹ለምን ሰላም ሰፈነ? ለምን ጦርነቱ አልቀጠለም? ለምን ወገኖቻችን ከመከራና ሥቃይ ተላቀቁ?› በሚመስል ሁኔታ የተደረገውን ሰላማዊ ሠልፍ ለተመለከተ ምን ዓይነት ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ያላቸው አካላት ላለፉት ዓመታት በላያችን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው እንደኖሩ ሊገነዘብ ይችላል፡፡ በተለያዩ ወገኖች እንደሚጠቀሰው እነዚህ አካላት በወገናችን በትግራይ ሕዝብ መከራና ሰቆቃ የሚነግዱ፣ በዚህም ከልዩ ልዩ አካላት የገንዘብ ምንጭ ያላቸው ናቸው የሚለውን ትርክት እውነተኝነት የሚመሰክር ነው፡፡
ለማጠቃለል ያህል መቼም የሰውን መልካም ተግባርና አስተዋጽኦ ማስታወስ መልካም ይመስለኛል፡፡ የተነጣጠረብንን ተንኮልና ሸር ሳስታውስና ከዚህ ሁሉ እንዴት እንደተረፍን? እንዴትስ እንደተወጣነው? የሚለውን ሳገናዝብ አንድ ታላቅ ሰው ትዝ ይለኛል፡፡ እንዲህ እያለ ኢትዮጵያን የመረቀና ምርቃቱም በከፊል የቀረበ፣
ሴራው ይክሸፍበት የመጣብሽ አድማ፣
እጁን ሳር ያድርገው – ጉልበቱን ቄጤማ፡፡
ካቀባበለብሽ ብረት ከደገነ፣
አምላክ ያግዝልሽ ላንቺ የወገነ፡፡
የወገኑን ደስታና ሐዘን በመጋራት፣ ሕይወቱን በሞላ ለአገሩና ለወገኑ በማዜም አቻ የማይገኝለት ጥላሁን ገሠሠን ለማመሥገንና ለማድነቅ ቃላት አላገኝለትም፡፡ በአካል ከተለይን ከዓመታት በኋላ በዚህ ቀውጢ ወቅት በመንፈስ ምርቃቱ ስላልተለየን ምሥጋናና አድናቆቴ ድርብርብ ሆኖ ይድረሰው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው beyenemoges@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡