Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹ታላቁ ሩጫ ለከተማ ገጽታ ግንባታ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ መደገፍ ያስፈልጋል›› ወ/ሪት ዳግማዊት...

‹‹ታላቁ ሩጫ ለከተማ ገጽታ ግንባታ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ መደገፍ ያስፈልጋል›› ወ/ሪት ዳግማዊት አማረ፣ የታላቁ ሩጫ ዋና ሥራ አስኪያጅ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚዘወተሩ ሕዝባዊ የአደባባይ በዓላት በዘለለ፣ በርካቶችን የሚያሳትፈው ታላቁ ሩጫ ቀዳሚው ነው፡፡ ለአትሌቶች ውድድር ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ‹‹ፌስቲቫል›› ተደርጎ ተቆጥሯል፡፡ ጤናን ለመጠበቅና ለመዝናናት የሚካፈሉት በርካቶች ናቸው፡፡ ታላቁ ሩጫ ብዙኃኑን ማሳተፍ ከጀመረ ዘንድሮ 22ኛ ዓመቱ ላይ ሲደርስ፣ የሴቶች አምስት ኪሎ ሜትር ውድድር ደግሞ 20 ዓመት ሞልቶታል፡፡ ከወራት በፊት በዓለም ላይ ከሚከናወኑ የጎዳና ውድድሮች ምርጡ በመባል የተመረጠው ታላቁ ሩጫ፣ በኢትዮጵያ ለሰባት አትሌቶች የስኬታቸው ምክንያት መሆን ችሏል፡፡ በተለያዩ አገሮች እየተዘወተሩ የመጡት የጎዳና ላይ ውድድሮች ለከተሞች ገጽታ ግንባታ ብሎም ለቱሪዝም ምንጭ መሆናቸውን ተከትሎ ከመንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ፣ ድጋፍና ትብብር ሲደረግላቸው ይስተዋላል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ይህ ልምድ እምብዛም ነው፡፡ ስለአጠቃላይ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሁለት አሠርታት በላይ ካስቆጠረው ጉዞውና የዘንድሮ ውድድር ጋር በተያያዘ ዳዊት ቶሎሳ ከታላቁ ሩጫ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሪት ዳግማዊት አማረ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ታላቁ ሩጫ ከጀመረ 22ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ዓመታዊ ሕዝባዊ ውድድር ከመሆኑ ባሻገር፣ ለከተማው እንዲሁም ለአትሌቱ ምን ፋይዳ አምጥቷል ማለት ይቻላል?

ወ/ሪ ዳግማዊት፡- በዓለም ላይ ከስኬት ማማ ላይ የደረሱ ግለሰቦች፣ እነሱ የደረሱበትን የስኬት መንገድ ሌሎችም እንዲከተሉ ለማድረግ ሲጥሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በቅርጫት ኳስ፣ በሙዚቃ፣ እንዲሁም በሌሎች የሥራ ዘርፎች ላይ ስኬትን መጎናፀፍ የቻሉ አካላት ሌሎችም መንገዳቸውን እንዲከተሉ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ስሟ በይበልጥ የሚነሳው በአትሌቲክስ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለም መድረኮች ላይ የአገራቸውን ባንዲራ ይዘው ከመጓዝ ባሻገር፣ ባመጡት ውጤት ያፈሩትን ገንዘብ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ የታላቁ ሩጫ ውድድር ማሰናዳት ከጀመረ በኋላ በርካታ አትሌቶች በዚህ ውድድር ላይ አልፈው ስኬታማ መሆን ችለዋል፡፡ ለምሳሌ አሰለፈች መርጋን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አትሌቷ መጀመርያ በታላቁ ሩጫ ነበር ውድድሯን የጀመረችው፡፡ ከዚያ በኋላ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የአገሯን ሰንደቅ ዓላማ አንግባ ከመካፈል ባሻገር፣ ባመጣችው ስኬት ሆቴል ገንብታ ለሌሎችም መትረፍ ችላለች፡፡ ኃይሌ ገብረሥላሴንም መመልከት ይቻላል፡፡ ሌሎችም በርካታ አትሌቶች በዚህ ውድድር አልፈው ስኬታማ መሆን ችለዋል፡፡ ስኬታቸውንም ለሌሎች የሚያስተላልፉበት አጋጣሚ ይፈጥራሉ፡፡ ታላቁ ሩጫም እንደዚያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተለያዩ አገሮች የጎዳና ላይ ሕዝባዊ ሩጫን፣ የአገራቸውን እንዲሁም ከተማቸውን ገጽታ ለመገንባት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡ የእኛ አገር ልምድ ምን ይመስላል?

ወ/ሪ ዳግማዊት፡- ታላቁ ሩጫ ለ22 ዓመታት ውድድር ሲያዘጋጅ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖለት አይደለም፡፡ ለእኛ በጣም አድካሚ ነው፡፡ በጣም ደስ የሚለው ግን ሌሎች ደጋፊ አሉት፡፡ በሌላው ዓለም ይህን የመሰለ ሕዝባዊ ውድድርን በከተማ ማዘጋጃ ቤቶች ከፍተኛ ድጋፍ ሲደረግላቸው ይታያል፡፡ እኛ አገር ግን ይህ ሩጫ በተለይ ለከተማዋ ያለውን አስተዋጽኦ የተመለከተው የለም፡፡ በዓለም ላይ የሚታወቁት የለንደን፣ የኒውዮርክ ማራቶን፣ የመሳሰሉት የጎዳና ውድድሮች በሌላ ጉዳይ ለአንድ ሰዓት የማይዘጉት መንገድ ለውድድሮች ግን 12 ሰዓታት ሊዘጉ ይችላሉ፡፡ ውድድር አዘጋጆችን በገንዘብ ይደግፋሉ፡፡ ታላቁ ሩጫ የደረሰበት ደረጃ ቀላል አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነት የጎዳና ውድድሮች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡ በርካታ ጎብኚዎች ውድድሩ ላይ ሊካፈሉ ይመጣሉ፡፡ በቅርቡ ባስጠናነው ጥናት መሠረት 700 የውጭ አገር ተካፋዮች መጥተው፣ 1.8 ሚሊዮን ዶላር የቱሪዝም ገቢ ያስገኘንበት ጊዜ ነበር፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ይመጣሉ፡፡ ታላቁ ሩጫ ለአትሌቶች ከከፈተው ዕድል ባሻገር፣ ለከተማው የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይህ ዓመታዊ መርሐ ግብር ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ…›› ዓይነት ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በዓለም ላይ የሚከናወኑ ዓመታዊ ሕዝባዊ የጎዳና ውድድሮች አብዛኛውን የገንዘብ ድጋፍ ከከተማ አስተዳደሮች ያገኛሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ታላቁ ሩጫ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በገንዘብ ደረጃ ተደጋግፎ የሠራበት አጋጣሚ አለ?

ወ/ሪ ዳግማዊት፡- ሌላው ዓለም ላይ ያለው ልምድ ከእኛ ጋር የተራራቀ ነው፡፡ እኛ ይህንን ውድድር ለማሳካት ስፖንሰር ፍለጋ የበርካታ ድርጅቶችን ደጅ እንጠናለን፡፡ በጣም ልፋት አለው፡፡ የሌሎች አገሮች ማዘጋጃ ቤቶች ለመሰል ውድድር አዘጋጆች ከመተባበር ባሻገር የገንዘብ ድጋፍ ያደርጉላቸዋል፡፡ ዓለም ላይ ጎዳና ውድድሮች ተበራክተዋል፣ ቴክኖሎጂያቸውም እየተሻሻለ ነው፡፡ ታላቁ ሩጫ ዓለም ላይ ከሚሰናዱ ምርጥ የጎዳና ውድድሮች አንዱ ሆኗል፡፡ እነሱ ለሚያሰናዱት ውድድሮች የተለያዩ መሣሪያዎች በፈለጉት መጠን ማግኘት ይችላሉ፡፡ እኛ ግን ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተን ነው የምንገዛቸው፡፡ እኛ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ አትሌቲክስን እያስተዋወቅን እንገኛለን፡፡ 40 ሺሕ ሰዎች አወዳድሮ ወደ ቤት በሰላም እንዲመለስ ማድረግ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ ውድድሩ ለከተማዋ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ መርዳትና መደገፍ ያስፈልጋል፡፡፡ ታላቁ ሩጫ ለከተማዋ እያደረገ የሚገኘው አስተዋጽኦ በገንዘብ የሚተመን አይደለም፡፡  

ሪፖርተር፡- የዘንድሮ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዝግጅት ምን ይመስላል?

ወ/ሪ ዳግማዊት፡- በዘንድሮ ውድድር እንደተለመደው 500 አዋቂ አትሌቶች ይካፈሉበታል፡፡ በግል የሚሳተፉ አትሌቶችን በማጣሪያ ለይተናል፡፡ በእንጦጦ በተደረገ ማጣሪያ ውድድር 100 አትሌቶች ተሳትፈው 50 አትሌቶች ተለይተዋል፡፡ ሌሎች በክለባቸው አማካይነት ይመዘገባሉ፡፡ ሌላው 40 ሺሕ የተመዘገበ ተሳታፊ አለ፡፡ ከዚህም ባሻገር ከተለያዩ ክልሎች አትሌቶች ተጋብዘዋል፡፡ ዘንድሮ በበቆጂ ለመጀመርያ ጊዜ በተካሄደ ውድድር ላይ አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች በውድድሩ ተጋብዘዋል፡፡ ከኬንያ፣ ከዑጋንዳና ከኤርትራ የሚሳተፉ አትሌቶች ይኖራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሥር ኤጀንሲዎች የሥራ ኃላፊዎች ለበጎ አድራጎት ለሚውለው ውድድር ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ከ50 በላይ የፓርላማ አባላት፣ ከ20 በላይ አምባሳደሮች እንዲሁም ከ250 በላይ የውጭ አገር ተሳታፊዎች ይኖራሉ፡፡ ዘንድሮ የአዋቂ አትሌቶች የሽልማት ዋጋ ከ100 ሺሕ ወደ 150 ሺሕ ብር አድጓል፡፡ በሦስት ቀለማት የተከፈለው ውድድር፣ ፈጥኖ ለሚያጠናቅቅ አረንጓዴ ቲሸርት፣ እየተዝናና ለሚያሳልፍ ቢጫ፣ እንዲሁም ልጅ የያዘ ቀይ ቲሸርት የለበሱ ቀላቅሎ ይካሄዳል፡፡ ስለዚህ አሥር ሺሕ ሰው አረንጓዴ ቲሸርት፣ 20 ሺሕው ቢጫ፣ እንዲሁም 10 ሺሕ ሰው ቀይ ቲሸርት ይለብሳል፡፡  

ሪፖርተር፡- ታላቁ ሩጫ ከመስቀል አደባባይ ከሚጀምረው ዓመታዊ ውድድር ባሻገር፣ በእንጦጦ እንዲሁም በበቆጂ የጀመራቸው አዳዲስ ውድድሮች አሉ፡፡ ውድድሩ እንዴት ተጀመረ?

ወ/ሪ ዳግማዊት፡- የእንጦጦ ውድድር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜ በ200 ሰው ነበር የተጀመረው፡፡ ውድድሩን ከጀመርን 14 ወራት ሆኖናል፡፡ አሁን የተሳታፊ ቁጥሩ 700 ደርሷል፡፡ የእንጦጦ መንገድ ጠባብ ስለሆነ ቁጥሩን ልንገድበው ሐሳብ አለን፡፡ ውድድሩ በነፃ ነው፡፡ ተሳታፊዎች በኦንላይን ይመዘገባሉ፡፡ የተመዝጋቢው ቁጥር መጠን ሲደርስ ወዲያው እንዘጋዋለን፡፡ በአምስት ደቂቃ 200 ሰው ይመዘገባል፡፡ ሁሉም ተሳታፊ የገባበትን ሰዓት የሚመዘግብ ሰዓት መቆጣጠሪያ መሣሪያ (ታይሚንግ ቺፕስ) እግራቸው ላይ ይቀመጥና የገቡበትን ሰዓት መገምገም ያስችላቸዋል፡፡ ሌላው የሴቶች ዓመታዊ ውድድር 20ኛ ዓመት ላይ ደርሷል፡፡ ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት የሴቶች ሩጫ ሲጀመር መንገድ ላይ ቆመው የሴቶችን መሮጥ እንደ ነውር የሚመለከቱ ነበሩ፡፡ አሁን ግን የሚያጨበጭብ ኅብረተሰብ ነው ያለው፡፡ የሴቶች ውድድር ሴቶችን በጣም የሚነቃቃና የሚያበረታታ ሆኖ ነው የቀጠለው፡፡ ሲጀመር 4,500 ተሳታፊ የነበረው ውደድር አሁን 15,000 ተሳታፊ ማለፍ ችሏል፡፡ ሌላው የሐዋሳ ግማሽ ማራቶን በአዳዲስ ርቀቶች ውድድሩን እያከናወንን እንገኛለን፡፡ በበቆጂም የጀመርነው ዓመታዊ ውድድር በየዓመቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታላቁ ሩጫ በዓመታዊ ውድድሩ ላይ ምን አሻሽለዋል ማለት ይቻላል?

ወ/ሪ ዳግማዊት፡- የመጀመርያ ከወረቀት ነፃ የሆነ የምዝገባ ሒደትን ማሳደግ የቻልንበት አንደኛው ነው፡፡ በአንድ ቀን 40 ሺሕ ሰው መሰብሰብ ቀላል አይደለም፡፡ የስፖርት ቴክኖሎጂ ማሳደግ ፍላጎት ነበረን፡፡ ምዝገባዎች በኦንላይን መሆኑ፣ የተሳታፊ ደኅንነት፣ መንገድ ላይ ምንም ዓይነት ቆሻሻ እንዳይጣል ማድረግ፣ እንዲሁም ተሳታፊን ቁጥር መጨመር መቻላችን በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡ ሌላው ዝግጅታችንን መቆጣጠርን ከመቻል አንፃር ማሳደግ ችለናል፡፡ ከዚህም ምክንያት የተለያዩ ታዋቂ ሰዎችን መጋበዝ ችለናል፡፡ ከዚያም ባሻገር ኢትዮጵያና ኬንያ ያላቸውን ግንኙነት በውድድሩ ማጠንከር ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- በየዓመቱ የታላቁ ሩጫ ውድድርን ከማከናወን ባሻገር በሌላ ዘርፍ የመሰማራት ዕቅድስ አላችሁ?

ወ/ሪ ዳግማዊት፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የስፖርት ትጥቅ በጣም ውድ ነው፡፡ ጥራት ያላቸውና በአገር ውስጥ የሚመረቱ ትጥቆችን የመሸጥ ፍላጎት አለ፡፡ የተወሰኑ የስፖርት ትጥቆች ለማቅረብ ከተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...