የሰላም ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሃይማኖት ተቋማትን የፋይናንስ ፍሰትና ብክነት፣ የቦታ አሰጣጥ እንዲሁም በእምነት ተቋማት አካባቢ የሚታየውን የድምፅ ብከለት የመሳሰሉ ጉዳዮችን ሊመራ የሚችል የአዋጅና ፖሊስ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የሃይማኖት ተቋማትንና የመንግሥትን ግንኙነት በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 ላይ ‹‹መንግሥትና ሃይማት የተለያዩ›› መሆናቸው ተደንግጎ በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም የሃይማኖት ተቋማት የሚመሩበት አጠቃላይ የፖሊሲ፣ አዋጅ፣ መመርያና ግልጽ የሆነ ማስፈጸሚያ ሕግ አለመኖሩን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታየ ደንደአ ተናግረዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር እሰካሁን ድረስ እየተጠቀመበት ያለ በመመርያ ደረጃ የወጣ አሠራር ቢኖርም ሁሉን አቀፍና ረዥም ርቀት ሊያስኬድ የሚችል ሕግ አለመኖሩ ችግር መፍጠሩን እክለው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ይህን ፖሊሲና አዋጅ ለማዘጋጀት በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ማሻሻያ ተቋም ጋር በመሆን የተለያዩ አገሮችን ልምድ በመውሰድ፣ ነገር ግን አገራዊ ሁኔታውን ግምት ውስጥ ያስገባ ሕግ ለማርቀቅ ጥናት ስለመጀመሩ ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡
አክለውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃይማኖት ተቋማት አካባቢ እያደገ የመጣና በሦስት መንገድ ሊገለጹ የሚችሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል የእምነት ተቋማት በውስጣቸው ከግልጽነት፣ ከመልካም አስተዳደርና ከፅንፈኝነት ጋር በተገናኘ በእያንዳንዱ ሃይማኖት የሚፈጠር ግጭት፣ በተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት መካካል ተገቢ ያልሆነ ውድድርና ፍረጃ አልፎ አልፎም ራስን እስከማጥፋት የሚደርሱ ግጭቶች እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ የመንግሥትና የሃይማኖት ሚዛናዊ ግንኙነት ተብሎ የተቀመጠውን በሚገባ በማወቅ የመንግሥት ኃላፊዎች ገለልተኛ በመሆን እያንዳንዱን ሃይማኖት ያለማገልገልና የሃይማኖት ተቋማትም ሕጉን ተከትለው መብቻቸውን ያለማክበርና ግዴታቸውን ያለመወጣት ሁኔታዎች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል፡፡
የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ እንዲሁም መተማመንና ግልፀኝነት ለመፍጠር ከተቋማቱ ጋር በመሆን ዕቅድ ተነድፎ ተከታታይ ኮንፈረንስ እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሰላም ሚኒስቴር አንድ አዲስ የሃይማኖት ተቋማት ሲቋቋም መሥፈርቱን ዓይቶ ዕውቅና እንደሚሰጠው ሁሉ የፍትሕ ሚኒስቴር ለአዳዲስ ሃይማኖቶች ዕውቅና የሚሰጥበት አሠራር መኖሩን የገለጹት አቶ ታየ በተጨማሪም በአዋጅ የተቋቋመው የወንጌል አማኞች ኅብረት የተቋቋመበት አዋጅ ግልጽ ባለመሆኑ በሁለቱም ረገድ ቋሚ ኮሚቴው ዕገዛ ያድርግልን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጠቅላላ ጉበዔ ዋና ጸሐፊ በበኩላቸው በእምነት ተቋማት መካከል ትንኮሳና ያፈነገጠ ተግባር አለመኖሩን ገልጸው ይልቁንም በእምነት ተቋማቱ ውስጥ ባሉ ግለሰቦች፣ አስተማሪዎችና በግለሰብ ደራጃ ፍቃድ ያላቸው ሰዎች ዘንድ የሚታዩ ያፈነገጡ ተግባራት ስለመኖራቸው አብራርተዋል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ ጉባዔውም እንደሚፈልግና በግለሰብ ደረጃ ፈቃድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ አካላትም ፈቃድ የሰጠው አካል ፍቃዳቸውን ሊነጥቃቸው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ከሕገ መንግሥቱ ወጣ ባለ መልኩ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ተጠያቂ እንዲሆኑ ፓርላማው ዕገዛ ያድርግ ብለዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት በኅብረት እንደሚንቀሳቀሱ አሁን ላይ ተፈጠረ የተባለው ስምምነት ከመምጣቱ በፊትና ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በአንድ ድምፅ ጦርነት ይቁም ብለው ጥሪ አቅርበው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በ2014 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በአገሪቱ ውስጥ ስለሚታይ ሌብነት ማብራሪያ ሲሰጡ ከዘረዘራቸው የሌብነት ማሳያ ተቋማት ውስጥ የእምነት ተቋማትን ጠቅሰው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የእምነት ተቋማት ታክስ አንኳ ባይከፈሉ ወደ ተቋማቱ የሚገባው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ መዋል እንዳለበትና ግለሰቦች ሀብት አያከማቹ እንደፈለጉ አገር የሚያተራምሱበት አካሄድ እንደማይኖር በመጥቀስ የሚሰበሰበው ገንዝብ ለእምነት ተቋማቱ ልማት መዋል አለበት ማለታቸው ይታወሳል፡፡