Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሊቋቋም ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ኒውክሌርን ለኃይል ማመንጫነትና በተለያዩ ዘርፎች ለሚሠሩ ሥራዎች የማዋል ኃላፊነትን የሚወጣ፣ የኒውክለር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንዲሁም ኢንስቲትዩቱን የሚመራ የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምክር ቤት ሊቋቋም ነው፡፡

በኒውክሌር ዘርፍ የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚመራው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኢንስቲትዩቱና ምክር ቤቱን የሚያቋቁሙ ሁለት ደንቦችን አዘጋጅቶ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ አገራዊ የኒውክሌር ሳይንስ የሰው ሀብት ጥናት ልየታ በመሥራትም ለሥልጠና ከለያቸው 500 ሰዎች ውስጥ ለ250 ባለሙያዎች ሥልጠና መስጠቱን የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድና የመጀመርያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት መድረክ ላይ ገልጿል፡፡ በተጨማሪም በኒውክሌር ሳይንስ ዘርፍ ላይ አንድ የሦስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ)፣ አምስት ሁለተኛ ድግሪና አምስት የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲማሩ ወደ ሩስያና ቻይና መላኩን አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ በኒውክሌር ሳይንስ ዘርፍ ተቋም የማቋቋምና የአቅም ግንባታ እያደረገ ያለው ኢትዮጵያና ሩስያ ጥቅምት 2012 ዓ.ም. በሩስያ ሱሺ ከተማ በተፈራረሙት ስምምነት መነሻነት መሆኑን የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አለምነው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት በተካሄደው የሩስያ አፍሪካ ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ተገናኝተው መክረው ነበር፡፡ ሁለቱ መሪዎች ካደረጉት ከዋናው ጉባዔ ጎን ለጎን ካደረጉት ስብሰባ በኋላ የቀድሞ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) እና የሩስያ አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አሌክሲ ሊካኬቭ የኒውክሌር ኃይልና ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል መንግሥታቱ የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ሩስያ በኒውክሌር ዘርፉ ከምታደርጋቸው ድጋፎች ውስጥ የኢትዮጵያን የኒውክሌር መሠረተ ልማት ተቋማት ማቋቋምና ማልማት እንዲሁም የኒውክሌርና የጨረር ደኅንነት ደንቦችና ለኒውክሌር ቁሶች፣ ለጨረር (radiation) ምንጮችና ለኒውክሌር ማከማቻ ሥፍራዎች አካላዊ ጥበቃ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይኼንን በይነ መንግሥታዊ ስምምነት (Inter Governmental Cooperation) የተመለከተ አዋጅ ቀርቦለት ከሁለት ዓመታት በፊት ኅዳር 2013 ዓ.ም. አጽድቆታል፡፡

ኒውክሌርን በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ለማዋል በመጀመርያ ሊገነባ የታሰበው በጤና፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪና ሌሎች ዘርፎች የተለያዩ ጥቅሞች ላይ የሚውል የኔውክሌር ሪሰርች ሪአክተር እንደነበር የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር መብራቱ ገብረማርያም (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የኒውክሌር ሪሰርች ሪአክተር ኒውትሮን የሚያመነጭ ሲሆን ቁሶች በውስጣቸው ምን እንደያዙ ለመለየት እንዲሁም ለሕክምናና ሌሎች ሳይንሳዊ ምርምሮች የሚያገለግሉ ሬድዮ አክቲቭ ቁሶችን ለማምረት ያገለግላል፡፡ ለካንሰር ሕክምና የሚውለው ጨረር በዚህ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡

ይሁንና አሁን ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫም (Nuclear power plants) ለመገንባት ማቀዷን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

እነዚህን ሁለት ዕቅዶች የሚተገብረው በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ ሊቋቋም የታሰበው የኒውክለር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንደሚሆን የተናገሩት መብራቱ (ዶ/ር)፣የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመ በኋላ የቁጥጥር ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

ሌላ ደንብ የተዘጋጀለት የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምክር ቤት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ልምድ ያላቸውን ግለሰቦች በማካተት ኢንስቲትዩቱን የሚደግፍ እንደሚሆን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሚኒስቴሩ ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ ሚኒስቴሩ ለትግበራው ያዘጋጀው ሰነድ ለመንግሥት ውሳኔ ‹‹ወደ በላይ አካላት›› ተልኮ ውሳኔ እየጠበቀ ነው፡፡

የትግበራ ሥራ እንቅስቃሴው ቢጀመርም ‹‹በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል?›› የሚለውን በትክክል መናገር እንደማይቻል የተናገሩት ኃላፊው፣ በሌሎች አገሮች ልምድ ሪሰርች ሪአክተር ለመተግበር ቢያንስ ስድስት ዓመት እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫው ደግሞ በትንሹ የአሥር ዓመት ጊዜ እንደሚወስድ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች