Saturday, December 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የጦር መሣሪያ ላንቃ ተዘግቶ አዲስ ምዕራፍ ይጀመር!

አሁንም መልሰን መላልሰን መገንዘብ ያለብን፣ ለአገር ህልውና ከሰላም ውጪ አማራጭም አቋራጭም አለመኖሩን ነው፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ደግሞ ለእኩልነት፣ ለነፃነትና ለማኅበራዊ ፍትሕ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ፋይዳ ቢስ የሆኑ ሰበቦችን በመደርደር ግጭት ለመቀስቀስ ከመነሳት በፊት፣ በእርጋታ ተቀምጦ የመነጋገር ባህልን ማዳበር ይገባል፡፡ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ማናቸውም ችግሮች መፈታት ያለባቸው በእኩልነትና በሰጥቶ መቀበል መርህ በመነጋገር እንጂ፣ የአንድን ወገን ፍላጎት በሌላው ላይ በጉልበት ለመጫን በመሞከር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ለዓመታት ከመከራ አዘቅት ውስጥ መውጣት አቅቷት የድህነት መጫወቻ የሆነችው፣ በሠለጠነ መንገድ ተነጋግሮ ልዩነትን ለመፍታት በጎ ፈቃድ በመታጠቱ ነው፡፡ ያለፉት ሁለት ዓመታት አውዳሚ ጦርነት እንኳን ሊካሄድ ቀርቶ ሊታሰብም አይገባውም ነበር፡፡ ሰሞኑን የሰላም ስምምነቱ ሲፈረም ብዙዎች ስሜታቸውን በፀፀት ሲገልጹ የነበሩት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ከማለቃቸውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ከመበተናቸው በፊት ለምን ስለሰላም ማሰብ አልተቻለም እያሉ ነበር፡፡ በጦር መሣሪያ ዕልቂትና ውድመት እንጂ ልማትም ሆነ ዕድገት አይታሰብም፡፡ የጦር መሣሪያ ላንቃ መዘጋት አለበት፡፡

በኢትዮጵያ ከሁለት ተፋላሚ ጎራዎች ውጪ ሌሎች አማራጭ ያላቸው መኖራቸው እየተዘነጋ ወይም ሆን ተብሎ እየታለፈ፣ ኢትዮጵያውያን ሳይወዱ በግድ የመከራ ገፈት ቀማሽ እየሆኑ በርካታ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ አገራቸውም ነዳጅ አልቆበት ዳገት ላይ እንደ ቆመ ተሽከርካሪ ቁልቁል እየተንሸራተተች፣ የሲኦል ምድር ሆና ትውልዶች በችግር እየተጠበሱ ተፈራርቀዋል፡፡ ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን ከማንም በፊት የሥልጣኔ አሻራ ያሳረፉባቸውን በርካታ ቅርሶች ትተው ቢያልፉም፣ ተከታታይ ትውልዶች ግን ከሥልጣኔ ተራርቀው የኋላቀርነትና የድህነት መጫወቻ ሆነው መዘባበቻ ሆነዋል፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚደረገው ትንቅንቅ ሕግ የማይዳኘው፣ ምራቃቸውን የዋጡ የአገር ሽማግሌዎች ምክር የማይገታው፣ እንደ ዘመኑ የዕድገት ደረጃ በሙያና በልምድ የዳበሩ ልሂቃን ሐሳብ የማያካፍሉበት፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ገለል እየተደረገ የአሸናፊና የተሸናፊ ድርሳናት እየተከተቡበት ድንቁርና የሰፈነበት የቅርብ ጊዜ ሁነት እንደነበርም መቼም አይዘነጋም፡፡ ሁለት ኃይለኞች ተፋልመው አንደኛው ሲያሸንፍ ተሸናፊውን ከመድረኩ ገለል አድርጎ፣ አገርን እንደ ምርኮ በመከፋፈል አዘቅት ውስጥ መክተት በዚህ ዘመን ጭምር በሚገባ የተስተዋለ እውነት ነው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ የሰቆቃ አዙሪት ውስጥ በመውጣት አገርን ማስቀጠል ይገባል፡፡

ከዕልቂትና ከውደመት አባዜ ለመላቀቅና በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ መኖርን ለመለማመድ እንዲቻል፣ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት መክሰም ይኖርባቸዋል፡፡ አገር አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥማት የተለያየ አተያይና የልምድ ተሞክሮ ያላቸው ልሂቃን፣ ምን ቢደረግ ጥሩ ነው ብለው ለመፍትሔ የሚረባረቡበት ምኅዳር ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የበደልና የግፍ መፈጸሚያ ሆና ልጆቿ አሳራቸውን ሲበሉ ዘመናት ነጉደዋል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጭምር ነውረኛ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ጉልበተኝነት የሁሉም ነገር የበላይነት ማሳያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ እንዲህ ዓይነት አስነዋሪ ድርጊቶች አሁንም ተባብሰው እንዲቀጥሉ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ አሉ፡፡ የሰላም ተስፋ ለምን ታየ ብለው የከፋቸው እየተስተዋሉ ነው፡፡ ኢትዮጵያን አዘቅት ውስጥ የከተታት እንዲህ ዓይነቱ ነውጠኝነት ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት መኖርን መልመድ ከጥፋት ስለሚያድን፣ ጠመንጃ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ይውጣ፡፡ ለሐሳብ ጥራት እንጂ ለጉልበት ቦታ አይሰጥ፡፡ በእኩልነት የሚኖርበት ሥርዓት እንዲገነባ እንጂ ጥቂቶች የሚፈነጩበት ሥርዓተ አልበኝነት እንዳይንሰራፋ መተባበር ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ የበላይነት መስፈን ያለበት ሕጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚያሻቸው ጉዳዮች ሲያጋጥሙ፣ ይዋጣልን እየተባለ እጅጌ የሚሰበስቡበት የጉልበተኞች ፍልሚያ ቀርቶ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ ነው፡፡ ሁሉም ነገር በሥርዓት ሲመራ ሕግ የበላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሰዎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው በቃል ሳይሆን በተግባር ይረጋገጣል፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እየታፈኑ መሰቃየት ወይም ማሰቃየት አይቻልም፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የሚያዘው በጉልበት ሳይሆን፣ ወቅቱን ጠብቆ በሚካሄድ ምርጫ ብቻ ይሆናል፡፡ ልዩነት ተፈጥሮ ችግር ሲያጋጥም የሕግና ተያያዥነት ያላቸው ባለሙያዎች ምክረ ሐሳቦች ያቀርባሉ፡፡ ንግግሩም በስሜት ሳይሆን በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ ሆኖ፣ አሻሚና አወዛጋቢ ምልከታዎች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ ሐሳቦቹ ለውሳኔ የሚረዱ ግብዓቶች በመሆናቸው ከተለያዩ ማዕዘናት በመቅረባቸው፣ ለውሳኔ ጥራት ይረዳሉ እንጂ ጉዳት አይኖራቸውም፡፡ በዚህ መንገድ የመነጋገር፣ የመከራከርና የመደራደር ባህል እንዲዳብር ጥርጊያውን ማመቻቸት ይገባል፡፡ የሰሞኑን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ከአንዳንድ ወገኖች የሚሰሙ ‹‹ካልደፈረሰ አይጠራም›› ዓይነት ፉከራዎች ፈር ቢይዙ ይመረጣል፡፡ ኢትዮጵያውያን ዘመናትን የተሸጋገሩባቸው አባጣ ጎርባጣዎች ከፍተኛ መስዋዕትነት አስከፍለዋቸዋልና፡፡

ለሰላም መስፈን ብዙኃን አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ መደመጣቸው በአንድ በኩል ሥልጡን የሆነ የዳበረ ውይይት እንደሚያስፈልግ፣ በሌላ በኩል ለአገር ከማይጠቅሙ ድርጊቶች በመላቀቅ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት መልካም ጅምር እንዲኖር ይረዳል፡፡ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በተለያዩ መስኮች የዳበረ ልምድ ያላቸው ልሂቃን ለዘለቄታ ሰላም መስፈን ትኩረት ሰጥተው አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ፣ በሌሎች መስኮች አገራቸውን ማገዝ ለሚፈልጉ ልሂቃን ትልቅ ብርታት ይሰጣል፡፡ እዚህ ላይ እየተነጋገርን ያለነው የሰላም ተስፋው ክፋታቸውን ስላመከነባቸው ከንቱ ፕሮፓጋንዲስቶች ሳይሆን፣ ከእነሱ በተሻለ ጥልቅና ሰፊ ሐሳብ ስላላቸው አርቆ አሳቢ ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ጦርነት አውዳሚና ትውልድ ገዳይ መሆኑን የተረዱ ወገኖች፣ አገራቸው ኢትዮጵያ የነፃነትና የእኩልነት እንድትሆን ሲሉ ነው ለሰላም መስፈን የሚታገሉት፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የበርካታ ፍላጎቶች፣ ሐሳቦችና የጋራ እሴቶች ኅብር ስለሆነች የጥቂቶች መጫወቻ እንዳትሆን ነው የሚለፉት፡፡ የሰላም መንገድን የሚቃወሙ ግን የለመዱት ከፋፋይነትና ረግጦ ገዥነት እንዲቀጥል ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም፡፡ ይህ ግን ተቀባይነት የለውም፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለውይይትና ለድርድር ባዕድ የሆነው የፖለቲካ ምኅዳሩ ምሁር ጠል፣ ለመካሪና ለዘካሪ ያስቸገረ፣ ለማኅበረሰቦች ተሳትፎ ቦታ ያልነበረው፣ የአስመሳዮችና የአድርባዮች መፈልፈያና መራቢያ ስለነበር ነው፡፡ ክፋት፣ ሴራ፣ አሻጥርና ኋላቀርነት የተፀናወቱት ከመሆኑም በላይ አርቆ አስተዋይነት ያልፈጠረባቸው ደካሞችና ሰነፎች ስለሚተውኑበት፣ ለአገር ሰቆቃ እንጂ ብሥራት አልነበረውም፡፡ እርስ በርስ መጋደል፣ መሳደድ፣ ስም መጠፋፋት፣ ወጣቱን ትውልድ መበከልና የአገርን ሚስጥር ለባዕዳን ማቀበል አሳፋሪ ልማዶች የሰፈነበት በመሆኑ፣ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ያለ ኃጢያታቸው ፍዳቸውን ዓይተዋል፡፡ ያንን የወደቀ አስተሳሰብ አንለቅም ብለው የሚንገታገቱ ኃይሎች እስቲ እንነጋገር፣ እንደራደር፣ የጎደለ ካለ አብረን እንሙላ ሲባሉ እዚያው አረንቋ ውስጥ ካልተገኘን ማለታቸው ያሳፍራል፡፡ ከዚያ አሳፋሪ የታሪክ ስብራት ተላቆ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የታሰበውን አገራዊ ምክክር በፍጥነት መጀመር የግድ ይላል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የጉልበት መንፈስ ተሰብሮ የሐሳብ ልዕልና ይናኝ፡፡ ኢትዮጵያን የሚታደጋት ጥራት ያለው ሐሳብ እንጂ የተቀባበለ ጠመንጃ እንዳልሆነ በተግባር ይረጋገጥ፡፡ የጦር መሣሪያ ላንቃ ተዘግቶ አዲስ ምዕራፍ ይጀመር!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...