በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የቡግና ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ‹‹የጦር መሣሪያ ኃይል›› በታከለበት ሁኔታ ለሰዓታት ለእስር መዳረጋቸውን ተከትሎ የወረዳው ፍርድ ቤት ሥራውን አቋረጠ፡፡
ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደምም የዳኞች ክብር ያልጠበቁ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እንደቆዩ ገልጾ፣ በዳኛ ላይ እስር የፈጸሙ አካላት ተጠያቂነት እስከሚሰፍን ድረስ ከዓርብ ኅዳር 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራውን እንዳቋረጠ ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡
ለእስር የተዳረጉት ወ/ሪት መሠረት አርጋቸው የተባሉት የፍርድ ቤት ዳኛ ሲሆኑ በአራት የፀጥታ ኃይሎች ሐሙስ ኅዳር 1 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሆነ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አየነ ተስፌ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ዳኛዋ ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረን አንድ ባለጉዳይ በዋስ እንዲለቀቅ ውሳኔ ማሳለፋቸው ለእስሩ መነሻ ምክንያት መሆኑን የገለጹት አቶ አየነ፣ ‹‹አራት የፀጥታ ኃይሎች ዳኛዋ ሲያንገላቷት የተከላከለ ባልደረባዋንም አብረው ወደ ጣቢያ ወስደው አስረዋል፤›› ብለዋል፡፡
በወረዳ ፍርድ ቤቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ጌታሁን እንደሻው ተፈርሞ ዓርብ ኅዳር 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተላከው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው በወረዳው ፍርድ ቤት ዳኞች ከዚህ ቀደምም በፖሊስ አባላት ‹‹ማፌዝና ትዕዛዝ አለማክበር›› ይፈጸምባቸው ነበር፡፡ እንደ ደብዳቤው ገለጻ የፖሊስ ተቋም አባላት ድርጊቱን ሲፈጽሙ የነበሩት ዳኞች ‹‹በሠሩት መዝገብ ምክንያት ብቻ›› ነው፡፡
የወረዳ ፍርድ ቤቱ ሥራ ማቆሙን በገለጹበት በዳኛ መሠረት ላይ የተፈጸመው እስራት ሲያስረዳ ‹‹የጦር መሣሪያ ኃይል የተጨመረበት ሕገወጥ እስር›› እንደተፈጸመባቸው ገልጿል፡፡ አክሎም፣ ‹‹አሁንም ተጨማሪ የከፋ ድርጊት ላለመፈጸሙ ዋስትና ስለሌለ ይህንን ድርጊት በበላይነት የመሩም ሆኑ የፈጸሙ አካላት ሕጋዊ ተጠያቂነት እስኪሰፍን፤›› እና ‹‹ለዳኞች ጥበቃና ከለላ መኖሩ ወደፊት እስኪረጋገጥ ድረስ›› ሥራ ማቆሙን ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል፡፡
የፍርድ ቤቱ ዳኛ ወደ ጣቢያ በተወሰዱበት ምሽት ሳያድሩ መፈታታቸውን የገለጹት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አየነ፣ ‹‹ዓላማው ግን አስሮ ማሳደር ነበር›› ብለዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹አስረው ባያሳድሩም ፖሊሶቹ የፈለጉት አስረው ማሳየት ነበር አድርገውታል፤›› ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ስህተት ተፈጥሮ ከተገኘ ሊታረም የሚችለው ለበላይ ፍርድ ቤት በሚቀርብ ይግባኝ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ዳኞች እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ ወይም ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ እንደማይታሰሩ በመግለጽ ድርጊቱን ‹‹ሕገወጥ›› ብለውታል፡፡
‹‹ዛሬውኑ ፍርድ ቤት ተነስቶ ብቻውን በመሄድ የሚያመጣው መፍትሔ የለም›› ያሉት አቶ አየነ በሚቀጥለው ሳምንት መጀመርያ ሰኞ የዞኑ ፍርድ ቤት አመራሮች ከዞኑ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና ሌሎች አመራሮች ጋር በመሆን ወደ ወረዳው የመሄድ ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
‹‹ሁሉንም ባለድርሻ አካል በማናገር መሬት ላይ ያለውን ጉዳይ በማጣራት ተጠያቂነት እንዲሰፍን እንታገላለን፤›› ብለዋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ፣ የወረዳውን ፍርድ ቤት ዳኛ መታሰር በመጥቀስ ‹‹ዳኝነት ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶችን የሚመለከታቸው የክልል የሕግ አስፈጻሚ አካላት፣ የሕግ ተርጓሚ አካልና ሕግ አውጪ አካል አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ሕግ ይከበር። ሕገ መንግሥት ይከበር፤›› ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ አሳስበዋል፡፡
በክልሎች ውስጥ የፍርድ ቤት ዳኞች ‹‹በሕገወጥ›› መንገድ ሲታሰሩ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይህ ሁለተኛው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥቅምት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምሥራቅ ምድብ ችሎት የወንጀል ችሎት ዳኞች የሆኑት ዳኛ ደሳለኝ ለሚ፣ ዳኛ ሙሐመድ ጅማና ዳኛ አብዲሳ ዋቅጅራ ከሥራ ገበታቸው ላይ ተወስደው በአዳማ ከተማ መታሰራቸውን አስታውቆ ነበር፡፡