በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ ከተካተቱት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መካከል እንዱ የሆኑት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በሚመሩት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠሩት ሥራ “የተሳካ” እንዲሆን እንደሚፈልጉ ነገር ግን “የተቧደኑ ሰዎች” ሥጋት እንደፈጠሩባቸው ተናገሩ፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፕሬዚዳንት የሆኑት ሚኒስትሩ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲ የተሾሙ አመራር መሆናቸው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥራዎች ጋር “ተቀላቅሎ” እየታዩ መሆኑን ገልጸው፣ ሚኒስቴሩን የሚገመግመው የሕዝብ ተወካዎች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዕገዛ እንዲያደርግላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በለጠ (ዶ/ር) ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት ረዕቡ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ሚኒስቴሩ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድና የመጀመርያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም በቀረበበት የግምገማ መድረክ ላይ ነው፡፡ ሚኒስትሩ፣ የመሥሪያ ቤቱን ዕቅድና አፈጻጸም አስመልክቶ ሪፖርት አቅርበው፣ ቋሚ ኮሚቴውም ጥያቄዎችን አቀርቦ መልስ ተሰጥቷል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተሮችና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች ለቋሚ ኮሚቴው ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡ በኋላ የሚኒስቴሩን ምላሽ ያጠቃለሉት ሚኒስትሩ በለጠ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ለጥያቄዎቹ የማጠቃለያ ምላሹን ከሰጡ በኋላ መድረኩ “ነፃ መድረክ” እንደሆነ እንደሚያምኑ ገልጸው፣ “የራሴን ሐሳብ መስጠት እጀምራለሁ” በማለት ሥጋታቸውን መግለጽ ጀምረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የፌዴራል መንግሥት ተቋም መሆኑንና የተቋሙ “ስኬትና ጉድለቶቹ” መመዘን ያለባቸው ከመንግሥት ተቋምነቱ አንፃር ብቻ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
‹‹በጣም በእጅጉ ሥራዎች የተሳኩ እንዲሆኑ መንግሥት ተቋሙ በሰጠው ሥምሪት ልክ የጎላ ሚና ተጫውቶ ውጤታማ የሆነ ተቋም እንዲሆን በጣም እፈልጋለሁ፤›› በማለት ፍላጎታቸውን የገለጹት በለጠ (ዶ/ር)፣ ‹‹የዚህ ወይም የዚያ ፓርቲ በመሆን የሚሳካልኝ፣ የዚህ ወይም የዚያ ፓርቲ አባል ባለመሆን የማይሳካልኝ አይደለም፤›› በማለት የተቃዋሚ ፓርቲ አባልነታቸው ከመንግሥት ኃላፊነታቸው ጋር ግንኙነት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡
ገዥው ፓርቲና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ ኃላፊነት የሰጧቸው “እምነት ስለተጣለባቸው” መሆኑን ያስታወሱት በለጠ (ዶ/ር)፣ ይህንን የተረዱ ግለሰቦች በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ቢኖሩም በሥራቸው ላይ “እንቅፋት” እየፈጠሩ ያሉ ሰዎች መኖራቸውን በነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ሰብሳቢነት ለሚመራው ቋሚ ኮሚቴ ገልጸዋል፡፡
ይህንን ሲያብራሩም፣ ‹‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃላፊነትና እምነት በእኔ ላይ ሲሰጡ ይህንኑ ሙሉ በሙሉ በመገንዘብ ሥራዬን የሚያግዙ ሰዎች በቀኝም በግራዬም እንዳሉ ሁሉ፣ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ሚሽንን ከሌላ ነገር ጋር በማደባለቅ ሥራ የሚያበላሹና የሚያጓትቱ ሰዎች በተቋሜ ውስጥ አይጠፉምና ይህ እያደረ ሥጋት እየፈጠረብኝ የመጣ ጉዳይ [ነው]›› ብለዋል፡፡
አክለውም ይህንን ጉዳይ ለቋሚ ኮሚቴው ማስረዳትና ዕገዛ ማግኘት እንደሚፈልጉ የተናገሩ ሲሆን፣ ‹‹ሥራ ለማበላሸት የሚንቀሳቀሱ የተቧደነ ሥራ የሚሠሩ ሰዎችም ላይ ዕይታዎች እንዲኖራችሁ ለማድረግ ዕድሎችን እፈጥራለሁ፤›› በማለት ያጋጠማቸውን ሥጋት ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል፡፡
ይሁንና ሚኒስትሩ ሥጋት የፈጠሩባቸውን ሰዎች ማንነትና በምን የኃላፊነት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አልገለጹም፡፡
ከበለጠ (ዶ/ር) ንግግር ቀጥሎ በተሰጡ ምላሾች ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ዕድል የተሰጣቸው የቋሚ ኮሚቴው አባል ብዙአየሁ ደገፉ (ረዳት ፕሮፌሰር) ጉዳዩን አንስተው፣ ሚኒስትሩ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የሠሩት ሥራ የሚበረታታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ቀጥለውም በቋሚ ኮሚቴው ውስጥ የአብንና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲዎች አባላት እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ‹‹እኛ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ ሌላ ፓርቲ አባል ቢኖርም በጋራ ለአንድ አገር ነው የምንሠራው፤›› ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ በለጠ (ዶ/ር) ላይ ሥጋት እንዲፈጠር ያደረገውን ሁኔታ ቋሚ ኮሚቴውም ሆነ መንግሥት የማይቀበሉት እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹ይህንን ሥጋት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢያችን ተቀብለው እስከ ማጣራት የምንሄድበት ነው፤›› ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በፓርቲ፣ በብሔር፣ በሃይማኖትና ሌሎች መነሻዎች የተነሳ በግለሰቦች ላይ የሚደርስ መገለል ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ገልጸው፣ “ሰው በሆነ ምክንያት ከተገለለ ትልቅ በሽታ እንዳጠቃው” እንደሚቆጠር ገልጸዋል፡፡
እንደዚህ ዓይነቱን ድርጊት ቋሚ ኮሚቴው የሚቀበለው እንዳልሆነ ተናግረው፣ ‹‹በዚህ ደረጃ ችግር መኖር የለበትም ብለን ነው የምንገምተው፡፡ ካለ ግን ይህ የምንታገሰው ጉዳይ አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡
በ2013 ዓ.ም. የተካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ ያሸነፈው ብልፅግና ፓርቲ፣ መስከረም 2014 ዓ.ም. መንግሥት መሥርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን ሲያቋቁሙ ከተካተቱት ሦስት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መካከል አንዱ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት በለጠ (ዶ/ር) ባለፈው አንድ ዓመት መሥሪያ ቤቱን ሲመሩ የቆዩ ሲሆን፣ ከየካቲት 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር ሆነው ፓርቲውን እየመሩ ነው፡፡