Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአገናኝ ኤጄንሲ የሚቀጠሩ ሠራተኞች ምንም ዓይነት መብት እንደማይጠበቅላቸው ኢሰመኮ አስታወቀ

በአገናኝ ኤጄንሲ የሚቀጠሩ ሠራተኞች ምንም ዓይነት መብት እንደማይጠበቅላቸው ኢሰመኮ አስታወቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች መብቶቻቸው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እንደማይጠበቅላቸው በጥናት ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በሁለት ዙሮች ማለትም ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. እንዲሁም ከግንቦት 24 እስከ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ ጅማና አዲስ አበባ ከተሞች፣ በሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሚቀጠሩ ሠራተኞች መብቶች አጠባበቅ ዙሪያ ክትትል ማድረጉን ኅዳር 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ክትትሉን ያካሄደው በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች፣ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች ቃልኪዳን፣ ዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳንና ሌሎች ዓለም አቀፋዊና አኅጉራዊ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች፣ ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ስምምነቶችና የውሳኔ ሐሳቦች እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ የሕግ ሰነዶች ጨምሮ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ላይ ዕውቅና የተሰጣቸው የሠራተኞች መብቶችን መሠረት በማድረግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከተጠቀሱት የተጣሱ መብቶች ውስጥ በቂ ክፍያ የማግኘት መብት፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና ጤናማ የሥራ ሁኔታዎችን የማግኘት መብት፣ በተገደበ የሥራ ሰዓት የመሥራት መብት፣ ዕረፍትና ፈቃድ የማግኘት መብት፣ የእኩልነትና ከአድልዎ ነፃ የመሆን መብት፣ የሥራ ዋስትና የማግኘት መብት፣ ማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት፣ የመደራጀት መብት፣ ቅሬታ የማሰማት መብትና ፍትሕ የማግኘት መብት ናቸው።

ችግሩን ለመቅረፍ ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን የሚወስን የደመወዝ ቦርድ በአስቸኳይ እንዲቋቋምና ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ መጠንን የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሥራ ገበያ ሁኔታና የመሳሰሉትን መሠረት በማድረግ በአፋጣኝ እንዲወሰን፣ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በቂ ሠራተኞችን በመቅጠርና የሠራተኞችን የሥራ ፈረቃ በማስተካከል የሠራተኞችን ወርኃዊ የሥራ ሰዓት በሳምንት ከ48 ሰዓት ወይም በወር ከ192 ሰዓት እንዳይበልጥና ከዚያ አልፎ ከተገኘ፣ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ላይ በተቀመጠው መሠረት የትርፍ ሰዓት ሥራ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው እንዲያደርጉ ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁ የሦስትዮሽ የሥራ ግንኙነቶችን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ባለመሆኑ፣ በዚህ ዓይነት የሥራ ግንኙነት ውስጥ የሚሳተፉትን የእያንዳንዱን አካላት ግዴታና የመንግሥትን ኃላፊነት በግልጽ የሚያስቀምጥ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲን የሚመለከት፣ ራሱን የቻለ ሕግ እንዲወጣ ኮሚሽኑ አክሎ ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮዎች፣ የሕግ ትምህርት ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር ኮንፌደሬሽንና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለሠራተኞች ስለመብቶቻቸውና ጥሰት ሲያጋጥም መብቶቻቸውን ስለሚያስከብሩባቸው መንገዶች ተከታታይነት ያለው ልዩ ልዩ የግንዛቤ ማስጨበጫና የመረጃ ማስፋፋት ሥራ እንዲሠሩ ጠይቋል፡፡

የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በሚቀጥሯቸው ሠራተኞች ስም ተቆራጭ የሚደረጉት የግብር፣ የጡረታ መዋጮና ሌሎችም ለሚመለከተው አካል ገቢ መደረጋቸውን፣ በየጊዜው ለሠራተኞችና ለተጠቃሚ ድርጅቱ ሪፖርት የማድረግ ግዴታ እንዳለበትም ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡

የሠራተኛና ክህሎት ሚኒስቴር ለኤጀንሲ ሠራተኞች መብት ትኩረት የሚሰጥ ናሙና የውል ቅጽ እንዲያዘጋጅና አግባብነት ያለው አካል ደግሞ አፈጻጸሙን እንዲከታተል አክሎ ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...