የአገራዊ ምክክር ኮሚሽንና የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች በተጀመረው አገራዊ ምክክር ላይ ተናቃዮችንና ‹‹የተገፉ ቡድኖችን›› ያላቸውን በምክክር ሒደቱ ማሳተፍን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ፈጸሙ፡፡
በአገራዊ ምክክር ሒደቱ አካታች ለማድረግና ተደራሽነት ላይ ይሠራል የተባለው ይህ ስምምነት ስብሰባና ሥልጠና ለማካሄድ፣ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግና በቀጣይ ሊስማሙባቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ያግዛል ተብሏል፡፡
የትብብር ስምምነቱን የተፈራረሙት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ መለሰ ሲሆኑ የሁለቱን አካላት ስምምነት ትግበራን የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ እንደሚቋቋም ተጠቁሟል፡፡
ከተቋቋመ ስምንት ወራትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የመጀመርያውን ሕዝባዊ ውይይቱን ከወራት በኋላ እንደሚጀምርና በቀጣይ ዓመት 2016 ዓ.ም. ውይይቱ እንደሚጠናቀቅ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
አገራዊ ብሔራዊ ውይይቱ በተያዘው ወር (ኅዳር) 2015 ዓ.ም. ላይ እንጀምራለን በሚል አስበው እንደነበር የገለጹት መስፍን (ፕሮፌሰር) ነገር ግን ወደ ውይይቱ ተንደርድሮ መግባት ተደናቅፎ ለመውጣት የሚዳርግ በመሆኑ በተለያዩ ዓለማት ተደረጉ የተባሉ ውይይቶችን እያዩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ብዙ አገሮች ያልተሳካላቸው አንድም በመንግሥት ወይም በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በመሆኑ እንደነዚህ ዓይነት ጣልቃ ገብነቶች ካሉ በሚገባ ለማየትና ውይይቱ ላይ መሠረት ጥሎ ለማለፍ የቅድመ ዝግጅቱንና ዝግጅቱን በደንብ ማጤን እንደነበረባቸው ተናግረዋል፡፡