Saturday, December 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

[ክቡር ሚኒስትሩ ከፕሮፓጋንዳ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢው ጋር ስለ ሰሜኑ የሰላም ስምምነት ትግበራ መረጃ እየተለዋወጡ ነው]

 • እኔ ምልህ፡፡
 • አቤት ክቡር ሚኒስትር?
 • የሰሜኑ ተዋጊዎች ከሠራዊታችን ጋር መቀራረብ ጀመሩ የሚባለው እውነት ነው? 
 • አዎ። እውነት ነው ክቡር ሚኒስትር። 
 • ከማንም ትዕዛዝ ሳይጠብቁ ነው ከእኛ ሠራዊት ጋር መቀላቀል ጀመሩ የተባለው?
 • አዎ። 
 • እንዴት ሊሆን ይችላል? 
 • እንዴት መሰልዎት ክቡር ሚኒስትር…
 • እ…
 • ከሰሜኑ ተዋጊዎች መካከል አንዱ ታጣቂ ብቻውን ሆኖ አቅራቢያው ወደሚገኙ የእኛ ወታደሮች እየጮኸ እንደቀረባቸው ነው የገለጹልኝ።
 • ምን እያለ ነው የሚጮኸው?
 • እንዳትገለው …እንዳትገለው እያለ ነው የቀረባቸው።
 • እና የእኛ ወታደሮች ዝም ብለው ጠበቁት?
 • ታጣቂው ብቻውን ስለነበረ ሥጋት አልፈጠረባቸውም። ነገር ግን በጥንቃቄ ነበር ይከታተሉት የነበረው።
 • እሺ…
 • ታጣቂው አሁንም አትግደለው እያለ ወደ አንዱ የእኛ ወታደር መጠጋቱን ቀጠለ።
 • አትግደለው የሚለው፣ አትግደሉኝ ለማለት ነው?
 • የእኛ ወታደሮች እንደዚያ ነበር የመሰላቸው።
 • እና ምን እያለ ነበር። 
 • ታጣቂው ግን አትግደለው ነበር የሚለው። 
 • ምኑን ነው አትግደለው የሚለው? 
 • ትምባሆውን ነው ክቡር ሚኒስትር። 
 • ምን?
 • አዎ፣ አንዱ የእኛ ወታደር እያጨሰ ነበር። አትግደለው የሚለው አትጨርሰው ለማለት ፈልጎ ነው ክቡር ሚኒስትር።
 • ምን ድራማ ነው የምታወራልኝ። 
 • ይመስላል ክቡር ሚኒስትር፣ ነገር ግን የተፈጠረውን ነው ያጫወትኩዎት።
 • እና ከዚያ በኋላ ምን ተፈጠረ? 
 • የእኛ ወታደሮች በነገሩ እየተገረሙም፣ እየሳቁም አዲስ ትምባሆ ለታጣቂው አቀበሉት።
 • ከዚያስ?
 • ከዚያ በኋላማ አካባቢው ሳቅ በሳቅ ሆነ። ይህንን የሰሙ ሌሎች ታጣቂዎችም ቀስ እያሉ መሣሪያቸውን እያሰቀመጡ ትምባሆውንና ሳቁን መቀላቀል ጀመሩ። የሚበላውንም በጋራ ተካፈሉ።
 • ይደንቃል። 
 • በጣም እንጂ ክቡር ሚኒስትር። ለማያውቅ ሰው እኮ የተጋጨነው በዚህ ነው የሚመስለው፡፡
 • በምን?
 • በሲጃራ! 
 • አንተ መቼም ቀልደኛ ነህ። እኔ ምልህ?
 • እየሰማሁ ነው ክቡር ሚኒስትር ይቀጥሉ።
 • እና ታጣቂዎቹ አሁንም ከእኛ ወታደሮች ጋር አንድ ላይ ናቸው እያልከኝ ነው። 
 • አዎ ክቡር ሚኒስትር። እንዲያውም በጋራ መሥራት ጀምረዋል።
 • ምንድነው በጋራ የሚሠሩት ደግሞ?
 • በውጊያው የሞቱ ሰዎችን በጋራ እየቀበሩ እንደሆነ ነው የሰማሁት።
 • አትለኝም?!
 • እውነቴን ነው! ምን ችግር አለው እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • አይ የለም… ያንን ጉዳይም በጋራ እንዳይሉ ሠግቼ ነው።
 • የቱን ጉዳይ?
 • የትጥቁን ጉዳይ!
 • ትጥቅ መፍታቱን?
 • እ…
 • ምን ሊሉ ይችላሉ?
 • በጋራ እንፍታ!

[ክቡር ሚኒስትሩ አመሻሹን ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው ስለ ሰላም ስምምነቱ ያልገባቸውን ይጠይቋቸው ጀመር]

 • እኔ ምልህ?
 • እ… አንቺ ምትይው?
 • እንዲያው አንድ ነገር ልጠይቅህ ነበር? 
 • ስለምን? 
 • ተፈረመ ስለተባለው የሰላም ስምምነት?
 • ስለስምምነቱ ምን? 
 • የሰሜኑ ኃይል ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱን ሰምቼ ስገረም ሌላ የተስማማው ጉዳይ እንዳለም ሰማሁ?
 • ምን?
 • የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት ተስማምቷል የሚል። እውነት ነው?
 • አዎ። ትጥቅ ከፈታ በኋላ የፌዴራሉ መንግሥት የሽግግር መንግሥት ያቋቁማል። 
 • እና ይህንን ተስማምቶ ተቀብሏል?
 • አዎ። ምንድነው ያስገረመሽ?
 • ያልተፈቀደ ምርጫ አካሂዶ መንግሥት መመሥረቱ አይደል እንዴ አንዱ የግጭቱ ምክንያት? 
 • አዎ፣ ትክክል ነሽ።
 • የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚፈቅድ ከሆነ እዚህ ሁሉ እልቂት ውስጥ ለምን ገባን? ያሳዝናል! 
 • ልክ ነሽ። ያሳዝናል ከማለት ውጭ ምን ማለት ይቻላል።
 • እንዲያው እነዛኞቹንም ትጥቅ ብታስፈቷቸው ሰላም እናገኝ ነበር። 
 • የትኞቹን?
 • በምዕራብ በኩል ያሉትን።
 • እነሱን ትጥቅ ለማስፈታት እንኳ መድከም የሚያስፈልግ አይመስለኝም። 
 • ለምን?
 • ከክላሽና ዲሽቃ የዘለለ ከባድ መሣሪያ የላቸውም።
 • ቢሆንስ? መፍታት አለባቸው!
 • ቀላል መሣሪያ ማስፈታት ከጀመርንማ አንዘልቀውም። 
 • እንዴት?
 • ስንቱን አስፈትተን እንችለዋለን? 
 • እኔ ግን ትጥቅ ባይኖራቸው እንኳን ማስፈታት አለባችሁ ባይ ነኝ!
 • ትጥቅ ባይኖራቸውም?
 • አዎ!
 • እና ሌላ ምን እናስፈታቸው?
 • ፀጉራቸውንም ቢሆን ይፍቱ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለተከበረው ምክር ቤት ካቀረቡ በኋላ ከምክር ቤቱ አባላት የሚነሱ ጥያቄዎችን እየተቀበሉ ማብራሪያ በመስጠት ላይ ናቸው]

ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ለሕዝብ ይፋ ያደረገው ነገር ከምን እንደደረሰ ቢያብራሩልን? ምንድነው ይፋ ያደረገው? ጥያቄውን ትንሽ ቢያብራሩት? ከአራት ዓመት በፊት በኦጋዴን አካባቢ ነዳጅ መገኘቱን ለሕዝብ በቴሌቪዥን አብስሮ...

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የካቢኔና የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባል የሆኑ ከፍተኛ አመራር የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያደመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል አግኝቼ ላነጋግርዎት የፈለግኩት። ጥሩ አደረግህ፣ ምን አሳሳቢ ነገር ገጥሞህ ነው? ክቡር ሚኒስትር ተወያይተንና ተግባብተን ያስቀመጥናቸው አቅጣጫዎች፣ በተለይም...

[ጉባዔው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ክቡር ሚኒስትሩን ለመጠየቅና ምላሽና ማብራሪያቸውን ለማድመጥ ተሰብስቧል። የጉባዔው አባላትም ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎቻቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር፣ ይህ ጉባዔ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ለመስጠት በመካከላችን ስለተገኙ አመሰግናለሁ። ክቡር ሚኒስትር፣ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የብሪክስ አባል እንድትሆን የሰጡት በሳል አመራር የሚደነቅ ነው። አገራችን...