ሁለት ዓመታት ያስቆጠረው ‹‹የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቼ ነው የሚያበቃው?›› ተብሎ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር የሰነበተው፡፡ የሰላም ፍንጭ ታየ እየተባለ በርካታ ግምቶች ቢኖሩም፣ ጠብ ያለ ነገር ሳይኖር ግጭቱ ቀጥሎ ነበር፡፡ በስተመጨረሻ ግን በአሥር ቀናት ንግግር የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት ተወካዮች ግጭቱን ለማቆም ተስማሙ፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት መፈረም ከተበሰረ ከአምስት ቀናት በኋላ ደግሞ የመንግሥትና የሕወሓት የጦር መሪዎች በኬንያ ናይሮቢ በስምምነቱ አፈጻጸም ሒደት ላይ እየመከሩ ናቸው፡፡ ለማቆም እጅግ ዘገየ ሲባል የነበረው ጦርነት፣ አሁን ደግሞ በተቃራኒው ወደ ሰላም የሚደረገው ጉዞ እየፈጠነ ያለ ይመስላል፡፡ ይህ ያልተጠበቀ ቢሆንም ብዙዎች የተደሰቱበት ይመስላል፡፡
በየትኛው ግንባር ምን ያህል ጦር ተደመሰሰ? በምን አቅጣጫ ማን ጥቃት ሰነዘረ? የዓውደ ውጊያ የበላይነቱን የማን ጦር ወሰደ? የሚሉ የጦር ሜዳ ወሬዎች በአጭር ጊዜ ተቀይረው የሰላም መድረኮችንና ስብሰባዎችን መቁጠር መጀመሩ በራሱ ትልቅ ለውጥ መሆኑን ብዙዎች እየተናገሩ ነው፡፡
ድሮን፣ ዲሽቃ፣ ክላሽ፣ መድፍና መትረየስ ተረስተው የሰላም ስምምነት አንቀጾች የዜና አውታሮች የዘገባ ግብዓቶች ሆነዋል፡፡ የሰላም ስምምነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ነክ ርዕሶችን ከውጊያና ከመተላለቅ ጉዳዮች በማላቀቅ ወደ ሰብዓዊ ዕርዳታ፣ መልሶ ግንባታና የመሠረተ ልማት ጥገና አጀንዳዎች የለወጠ ክስተት መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል፡፡
እሑድ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በሰጡት ማብራሪያ፣ የሰላም ስምምነቱን በተግባር የመተርጎሙ ጉዳይ በአጭር ጊዜ ዕውን እንደሚሆን ተናግረው ነበር፡፡ በማግሥቱ ሰኞ በኬንያ ናይሮቢ የመንግሥትና የሕወሓት የጦር መሪዎች ተገናኝተው፣ ስለትጥቅ አፈታትና ተያያዥ ሒደቶች እንደሚመካከሩም ገልጸው ነበር፡፡
በማግሥቱ ሰኞ የሕወሓት የጦር መሪ ታደሰ ወረደና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጨምሮ ዋና አደራዳሪዎቹ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆና የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የታደሙበት የምክክር ሒደት በኬንያ ናይሮቢ ተጀመረ፡፡
ይህ የምክክር መድረክ ደግሞ በዋናነት የሕወሓት አማፂያን ትጥቅ ስለሚፈቱበት ሁኔታ ያተኮረ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ ትጥቅ የማስፈታት፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት፣ እንዲሁም የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች መልሶ ሥራ መጀመር ጉዳይም ዋና አጀንዳዎች ነበሩ ተብለዋል፡፡
የሰኞው የናይሮቢ ስብሰባ ከሁሉ በላይ ስለሰላም ስምምነቱ ጥርጣሬና አይሳካም የሚል ሥጋት ለነበራቸው ወገኖች ግምታቸው የተሳሳተ እንደሆነ መልክዕት የተላለፈበት እንደነበር ብዙዎች ገልጸዋል፡፡ በፕሪቶሪያው መድረክ ስምምነቱን የተፈራረሙት አቶ ጌታቸው ረዳና ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ በናይሮቢው መድረክ ለስምምነቱ ገቢራዊነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ዋና አደራዳሪዎቹ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆና ኡሁሩ ኬንያታ ያሰሙት ንግግር ደግሞ የብዙዎችን ቀልብ የገዛ፣ በሰላም ስምምነቱ ላይ የሚኖረውን ተስፋ ያበዛ መሆኑን ብዙዎች በደስታ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡
‹‹ፕሬዚዳንት ኦባሳንጆ እንደተናገሩትም ይህ የሰላም ንግግር ሒደት የሚካሄደው አንዳቸው ከሌላቸው ጋር በደንብ በሚተዋወቁ ባልደረቦች መካከል ነው፡፡ በዚህ የሰላም ሒደት መጨረሻም ለአገራቸው ኢትዮጵያ በጋራ ሆነው መሥራት እንደሚችሉ እተማመናለሁ፡፡ ለቀጣናው ዕድገት እንዲሁም በአጠቃላዩ ለአኅጉራችን አፍሪካ ሰላምና ፀጥታ በጋራ እንሠራለን፡፡
‹‹እነዚህ ወንድሞቼ በደንብ የሚተዋወቁና የሚግባቡ በመሆኑ የኢትዮጵያን ግጭት ማስቆም ብቻ አይደለም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም አይቸገሩም ብዬ አምናለሁ፡፡ ፕሪቶሪያ ነበር ይህን የሰላም ሒደት የጀመርነው፡፡ ዛሬ በጣም ቀርበን በናይሮቢ ቀጥለናል፡፡ ቀጣዩን ስብሰባ መቀሌ ላይ እንደምናደርግ ተስፋ አለን፡፡ በመጨረሻ ደግሞ በአዲስ አበባ ተሰባስበን የሰላም ድሉን እንደምናከብር ተስፋ አለኝ፤›› ሲሉ የተናገሩት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የሰላም ሒደቱ ውጤታማ በሆነ መንገድ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
ሬድዋን (አምባሳደር) እሑድ ዕለት ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በሰጡት ማብራሪያ፣ የሰላም ስምምነቱን በተመለከተ እየተነሱ ላሉ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተው ነበር፡፡
ስምምነቱ ጊዜያዊ የግጭት ማቆም ስምምነት ወይስ የሰላም ስምምነት በሚል ለሚነሳው ጥያቄ ሬድዋን (አምባሳደር) ግልጽ የሆነ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የተትረፈረፈ ጊዜና አመቺ ዕድል እንደሌላት ገልጸው፣ ‹‹ተኩስ አቁም በማድረግ ሌላ ዙር የድርድር ጊዜና አጋጣሚ ከመጠበቅ ይልቅ በቀጥታ ወደ ሰላም ስምምነት ገብተናል፤›› ብለዋል፡፡
በስምምነት ሰነዱ ላይ የተቀመጡት አንቀጾች አንዳንዶቹ ምንም ዓይነት የአፈጻጸም ሒደት የማይጠይቁና ማብራሪያም ሆነ መግለጫ የማያስፈልጋቸው መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የመጠበቅ ጉዳይ›› ተብሎ የተቀመጠው ነጥብ፣ ከእነዚህ ተጨማሪ ሒደትም ሆነ መግለጫ ከማይጠይቁ አጀንዳዎች አንዱ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡
ተኩስ ማቆም፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማክበር፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል የፌደራል መንግሥትን ሥልጣን የመመለስ ጉዳዮች ደግሞ ዝርዝር ሒደቶችን የሚጠይቁ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ግጭት ማቆም የመጀመሪያው የሒደቱ ዕርምጃ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሁለተኛውና ቀጣዩ ግጭት ቀስቃሽና አባባሽ ፕሮፓጋንዳዎችን (የቃላት ጦርነቶችን) ማስወገድ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ሦስተኛው የዚህ ሒደት ዕርምጃ ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መላው ትግራይን እንዲቆጣጠር ማድረግ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በአራተኝነት ደረጃ በሁለቱ ወገኖች የጦር አዛዦች መካከል ግንኙነት መፍጠር ነው ብለዋል፡፡ ትጥቅ የፈቱ የሕወሓት ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ሕይወት የማስገባት ጉዳይ ቀጣዩ ዕርምጃ ነው ሲሉም ሬድዋን (አምባሳደር) ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በትግራይ ክልል ስለማስከበር ጉዳይ ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡት የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው፣ ሕወሓት የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን የሚፈታተንም ሆነ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ችግር ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ በአስቸኳይ ለመቆጠብ መስማማቱን አመልክተዋል፡፡ ሕወሓት ትጥቁን ፈቶና በሕገወጥ ምርጫ መሠረትኩት ያለውን መንግሥት በትኖ፣ በሰላማዊ መንገድ እንደ ማንኛውም ፓርቲ በፖለቲካ የሚሳተፍበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል፡፡
ሕወሓት ትጥቅ አልባ የፖለቲካ ድርጅት ይሆናል ብለዋል፡፡ ሕወሓት በኢፌዴሪ ፓርላማ ከተጣለበት የሽብርተኝነት ፍረጃ ነፃ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡ ሕወሓት ከትጥቅና ግጭት ርቆ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ይሆናል ብለዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሚደረገውን የፖለቲካ ሽግግር በተመለከተም ምርጫ እስኪደረግና በክልሉ አዲስ አስተዳደር እስኪመጣ አካታች የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ይመሠረታል ብለዋል፡፡ የሽግግር አስተዳደሩ የተለያዩ የትግራይ ፖለቲካ ኃይሎችን ያካተተ ይሆናል ብለዋል፡፡ የታጠቀ ኃይል በጊዜያዊውም ሆነ በምርጫ በሚመሠረተው አስተዳደር ውስጥ ቦታ አይኖረውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ክልሎች ደረጃውን በጠበቀና የአገሪቱን የትጥቅ መሥፈርት በተከተለ መንገድ ትጥቅ እንደሚታጠቁ ያመለከቱት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ የትግራይ ክልልም ሁኔታ ከዚህ የተለየ እንደማይሆን አመልክተዋል፡፡ የትግራይ ክልል በቂ የፖሊስ፣ የሚሊሻና የፀጥታ ኃይል እንደሚኖረው፣ ለፀጥታ ማስከበር ሥራ ደግሞ መደበኛ ትጥቅ የመታጠቅ ዕድል ይሰጠዋል ብለዋል፡፡
ይህን ሁሉ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ እሑድ ሲያብራሩ የዋሉት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ በማግሥቱ ሰኞ ኬንያ በነበረው መድረክ ላይም ተካፍለው ነበር፡፡ በዚሁ ጊዜም የሰላም ሒደቱ በተሻለ ሁኔታ እየተተገበረ መሆኑን መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ የሕወሓት ዋና ተደራዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳም ይህንኑ የደገሙ ሲሆን፣ በተለይ የመሠረተ ልማቶች ጥገናና መልሶ ግንባታ መፋጠን ሒደቱን ከዚህ በበለጠ እንደሚያፋጥነው ነበር የተናገሩት፡፡
በሰላም ሒደቱ አተገባበር ላይ ያተኮረው በኬንያ ናይሮቢ ሰኞ ዕለት የተጀመረው ሁለተኛ ዙር የሰላም ስብሰባ ትናንት ማክሰኞም ቀጥሏል፡፡ ለቀናት እንደሚቀጥል የተገመተው ስብሰባ ዓላማ ደግሞ ስለስምምነቱ አተገባበር ፍኖተ ካርታ የማዘጋጀት ሥራንም እንደሚያካትት በመዘገብ ላይ ነው፡፡
በናይሮቢ እየተደረገ የሚገኘው በዋናነት የሁለቱን ወገኖች ወታደራዊ አመራሮች ያቀፈው ስብሰባ፣ በመጪዎቹ አሥር ቀናት የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ ስለማስፈታትና መልሶ ወደ መደበኛ ሕይወት ስለማስገባት የተመከረበት መሆኑ ታውቋል፡፡ በእነዚህ ቀናት ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ኃይሎች ሙሉ ለሙሉ ትግራይ ክልልን የመቆጣጠር ሥራ ስለሚረከቡበት ሁኔታ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ይህን ስብሰባ በሚመለከት ባወጣው መግለጫ፣ ግንኙነቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመን ለመፍጠር ቁልፍ አጋጣሚ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የሁለቱ ወገኖች የጦር መሪዎች መገናኘት መደበኛ የግንኙነት ፍሰት ከመፍጠር በተጨማሪ ለሰብዓዊ ረድኤት፣ ለመልሶ ግንባታና ለመደበኛ መጓጓዣ የአየር በረራ አገልግሎትን ዳግም ለማስጀመር መሠረት እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡
እንደ ቀዳሚው የፕሪቶሪያ ስብሰባ ሁሉ በናይሮቢው ግንኙነት ወቅትም ኤርትራ አልተወከለችም የሚል ዘገባ የሠሩ መገናኛ ብዙኃን ነበሩ፡፡ በሌላ በኩልም በሁለቱም የሰላም መድረኮች የአማራና የአፋር ክልል ጥያቄዎች አልተነሱም የሚሉ ቅሬታዎችም ይሰማሉ፡፡ በሌላ በኩል ሕወሓት ወደ እዚህ ስምምነት መግባቱ ጨርሶ የተሳሳተ ዕርምጃ ነው በሚል በውጭ አገሮች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ተቃውሞ ሲያቀርቡ ታይተዋል፡፡
የትግራይ ምሁራን ዓለም አቀፍ ማኅበር (GSTS) የተባለው ወደ 5,000 የትግራይ ምሁራንን እንደሚያቅፍ የሚናገረው ተቋም፣ የሰላም ስምምነቱ አንዳንድ አንቀጾች የትግራይ ሕዝብን ጥቅም ይፃረራሉ ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡ ተቋሙ መግለጫ ካወጣባቸው ነጥቦች መካከል የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ ተቃውሟል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ትግራይን ከውጭ ጥቃት አይከላከልም ያለው ይህ መግለጫ፣ ስለፌዴራል መንግሥት ሥልጣን መመለስ፣ ስለሽግግር ጊዜ ፍትሕና ሌሎችም ጉዳዮች አሉኝ ያላቸውን ቅሬታዎች አቅርቧል፡፡
የሰላም ስምምነቱና አተገባበር ሒደት እየገጠመው ካለው ጥቂት የትግራይ ልሂቃን ተቃውሞ ውጪ፣ ከፍተኛ ድጋፍና ይሁንታን በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አግኝቷል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ የሰኞ ምሽት መደበኛ መግለጫቸውን የከፈቱት በሰላም ስምምነቱ አሜሪካ የተሰማትን ደስታ በመናገር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና የሕወሓት አማፂያን በሰላም ሒደቱ አተገባበር ላይ የሚያደርጉትን ንግግር እንደሚደግፉ የተናገሩት ኔድ ፕራይስ፣ ከዚህ ንግግርም በጎ ውጤት እንደሚጠብቁ ነው ያመለከቱት፡፡
በአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባሉ ብራድሊ ጀምስ ሻርማን ባወጡት መግለጫ የሰላም ስምምነቱን ትልቅ ዕርምጃ ሲሉ አድንቀዋል፡፡
የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንዲሁም የናይሮቢውን የሰላም ስምምነት ትግበራ ውይይት በተመለከተ፣ ሌላው ቀርቶ ከምዕራባውያን በተቃራኒ የቆሙ አገሮችና ፖለቲከኞች እያደነቁት ነው፡፡
ከእነ አሜሪካን ጋር በጂኦ ፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ ያለችው ኢራን በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የተጀመሩ ጥረቶችን እንደምታደንቅ ተናግራለች፡፡ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ከናኒ ኢራን የኢትዮጵያን የሰላም ጥረት ትደግፋለች ብለዋል፡፡