አልሳም ግሩፕ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት መንግሥት ባስቀመጠው የመንግሥትና የግል ትበብር መርህ መሠረት ለማሟላት በከተማዋ ‹‹አልሳም መንደር›› በሚል መጠሪያ የሪል ስቴት ልማት ለማከናወን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።
‹‹አልሳም መንደር›› በሚል መጠሪያ የሚከናወነው የሪል ስቴት ልማት ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በሚኘው ይዞታው ላይ እንደሆነ ያስታወቁት የአልሳም ግሩፕ ተወካይ አቶ ካሚል ሳቢር ናቸው።
አቶ ካሚል ይህንን ያስታወቁት በአልሳም ግሩፕ ሥር በሚገኙ ሁለት እህትማማች ኩባንያዎች በ2.6 ቢሊዮን ብር ወጪ ተገንብተው የተጠናቀቁ ሁለት የመኖሪያ ሕንፃዎችን (አፓርትመንቶች) ባለፈው ቅዳሜ በተመረቁበት ወቅት ነው።
‹‹አልሳም መንደር›› በሚል መጠሪያ የሚካሄደው ቀጣይ የሪል ስቴት ልማት ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ከሚገኘው አልሳም ጨለለቅ ሕንፃ ጀርባ በሚገኝ 1460 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ካሚል፣ ይዞታውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ በሊዝ መረከባቸውን አስታውቀዋል።
በዚህ ይዞታ ላይም 200 መኖሪያ ቤቶች የሚኖሩት ባለ 30 ወለል ከፍታ ሕንፃ እንደሚገነባ አስታውቀዋል። ግንባታውን ለመጀመርም አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ካሚል፣ የአዲሱ ሕንፃ ዲዛይን ተሠርቶ መጠናቀቁንም አመልክተዋል።
በዕለቱም በአልሳም ግሩፕ እህት ኩባንያዎች የተገነቡ ሁለት መኖሪያ ሕንፃዎች በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የተመረቁ ሲሆን፣ ከንቲባዋ የአልሳም መንደር የሪል ስቴት ግንባታ ለማስጀመርም የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል።
በከንቲባዋ ከተመረቁት ሁለት አፓርታማዎች ውስጥ አንዱ የሆነውና ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ አልሳም መንደር ውስጥ የተገነባው የመኖሪያ አፓርትመንት ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ይህ ሕንፃ በ3,572 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ 288 ባለ ሁለት መኝታ መኖሪያና 72 ባለ ሦስት መኝታ በአጠቃላይ 360 የመኖርያ አፓርትመንቶች ያሉት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በሳኩር ሪል ስቴት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ካሳንቺስ ራዲሰን ሆቴል ጎን የተገነባው ሕንፃ ደግሞ በ1,419 ካሬ ሜትር ቦታ ያረፈ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 800 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትና 56 ባለ 2 መኝታ እና 56 ባለ 3 መኝታ መኖሪያዎችን በአጠቃላይ 112 መኖሪያ ቤቶችን የያዘ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ እጅግ አንገብጋቢ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ይህንን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመመለስ በመንግሥት ጥረት ብቻ የሚቻል ጉዳይ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ ‹‹እኛ ስንመርጥ በርካታ የመኖሪያ ቤቶችን ሠርተን እናቀርባለን ያልነው በመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ የግሉ ዘርፍ ከልብ በሚሳተፍበትና ለሕዝባችን የገባነውን ቃል ዕውን እንድናደርግ እንደሚያስችለን በመተማመን ነው፤›› ብለዋል።
ለሪል ስቴት ልማት ውጤቶች ኩባንያቸው የመጀመርያው ያለመሆኑን የገለጹት አቶ ካሚል፣ ከዚህ ቀደም በሜክሲኮ አደባባይ የጨለለቅ ሕንፃዎችና ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ያለው የሊና አፓርትመንት ሕንፃ ቀደም ብለው የተገነቡና አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
አያይዘውም፣ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች ጉዳይ በመንግሥት ላይ ብቻ የሚጣል ባለመሆኑ በትብብርና በመደጋገፍ የሚፈጸም ነው ያሉት አቶ ከማል፣ ‹‹በእኛ በኩል በቀጣይ ከመንግሥት ጋርም ተባብሮ አብሮ የመሥራት ፕሮግራም አለን›› ብለዋል፡፡ በዚህ ዕሳቤ መሠረት የአዲስ አበባ አስተዳደር በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነትና ሽርክና የቤቶችን ልማት በሰፊው ለማካሄድ ለነደፈው ዕቅድ ተግባራዊነት ኩባንያቸው ለመሳተፍ ዝግጁ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
አልሳም ግሩፕ ከ30 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ማለትም በአስመጪነትና አከፋፋይነት፣ በላኪነት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሪል ስቴትና በመሳሰሉት የሥራ ዘርፎች ላይ የተሰማራ ኩባንያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ባለፈው ቅዳሜ በተመረቁት ሁለት አፓርትመንቶች ውስጥ የሚኘኙ መኖሪያ ቤቶች ከ90 በመቶ በላይ ተሸጠዋል፡፡