Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ወደን ሳይሆን ተገደን!

እነሆ ከመገናኛ ወደ ወሰን ልንጓዝ ነው። የጥርጣሬ ዘር የተዘራበት ጎዳና በከንቱ ያገለማምጠናል። ከፍቅራችን በፊት አለመተማመናችን እየቀደመብን ተቸግረናል። ይህ ይሆንብን ዘንድ የወጠነብን ማን መሆኑ ዘወትር እንዳብሰለሰለን ወጥተን እንገባለን። ከእህል የፍቅር ጥማት የሚያሰቃየን በጣም በዝተናል። ጎዳናውን ለሚያውቀው ለዚህ ሀቅ ማረጋገጫ ማኅተም አይጠይቅም። በደቦ እየሠሩ፣ በደቦ እየበሉ ብርድ ብርድ የሚለው አይጠፋም። አብዛኛው መንገደኛ ከስሜቱ ሕመም ይልቅ ለኪሱ ሕመም ቅድሚያ ሲያስብ፣ ወጥቶ ለመግቢያው ብቻ ሲጨነቅ፣ እየሳቀ የሚያፈዘውን እያወራ ሐሳቡን የሚሰርቀውን ስብራት ችላ ያለው ይመስላል። ሰው ከመሆን በፊት ሰው መሆን መኖሩን እንዳናስብ ኑሮ ግራና ቀኝ እየጠለዘ ቀልባችንን ነስቶናል። ይህን ለማስተዋል ደግሞ ታክሲ ተሳፍረን ጥቂት ዕፎይ እንዳልን ወያላው ብቅ ብሎ፣ “ሃያ አምስት ብር ነው የምትከፍሉት ያልፈለገ ይውረድ…” ብሎ ይነጅሰናል። ነጃሳ!

ወያላው ከአቅም በላይ የሞላችዋን ታክሲ እንቅብ በሚያህል መዳፉ እየነረተ፣ “የሞላ አንድ ሰው…” ሲል ይጮሃል። ደግሞ መለስ ይልና “ሃያ አምስት ብር ነው፣ እሱ ጋ ደግሞ ጠጋ ጠጋ በሉ፣ ቦታ አትያዙብኝ፣ መቻቻል፣ መጠጋጋት፣ መተካካት ልመዱ፣ ደግሞ እንኳን ለሰላም ስምምነቱ በሰላም አደረሳችሁ። አዎ! ዋናው ሰላም ነው! ሰላማችንን ግን በፊርማ ብቻ ሳይሆን በመጠጋጋት፣ በመቻቻልና በመተካካት መጠበቅ ይኖርብናል። እስኪ አስገቡት፣ እስኪ እሱ ጋ…” ይላል። ከተሳፋሪዎች አንዱ፣ “ይኼማ የሚናገረውን ቤቱ አጥንቶት ተዘጋጅቶበት የወጣ ይመስላል…” ሲል አጠገቡ የተቀመጠች ደግሞ፣ “የተዘጋጀበትን ሳይሆን እንደ ወረደ ነው የሚያወራው። ሲዘጋጁበትማ እቅጩን ከሚናገሩት ይልቅ የሚሸራርፉት ሀቅ ብዙ ነው…” ትለዋለች። ‘ወይ እንደ ወረደ?’ እንላለን እኛ ደግሞ፡፡ ምን እንበል ታዲያ!

“አይበቃህም? በፈጠረህ እንሂድ ማጅራታችንን እንዳታስመታን?” ጋቢና የተቀመጠ ጎልማሳ ወያላውን ይለማመጣል። ሾፌራችን ገብቶ ሞተሩን እያስነሳ ነው። “አይ አገሬ! አይ ኢትዮጵያ ደፋር ጠፋ! አሁን አንተን የመሰለ ደንዳና ማጅራት እንዳታስመታን ሲል አያፍርም? ያውም በአደባባይ?” ዓይን አውጣው ወያላ የትም የማያውቀውን ሰው እየዘረጠጠ በሩን ዘጋ። “ተው! ተው! ጀግንነት ቦታና ሰዓት አለው። የዘመኑ ጀግና ደግሞ ተጋፋጭ ሳይሆን ብልኃተኛ ነው። ከመጋፈጥ የተረፈን ነገር ስም ማጥፋትና አሉባልታ ብቻ ነው…” አለ ጎልማሳው አዋዝቶ። ቀልበ ቢሱ ወያላ በሙሉ ልቡ አያዳምጥም። ወደ አብዛኞቻችን ዘወር ብሎ ደግሞ፣ “ቆይ ግን ከጀግና በላይ ምን አለ?” እያለ የታክሲውን አምፖል ሲያበራው መጨረሻ ወንበር ተጨናንቀው ከተቀመጡ ወጣቶች አንዱ፣ “የሞተ ጀግና…”  ብሎ መለሰለት። “ኦ…ኦ… አሁን ፖለቲካ ልታስወሩኝ፣ ጀግና አይሞትም ብለናል ማለት ብለናል ነው። ሃያ አምስቷን ወዲህ በሏት?” ብሎ ወያላው ወደ ሥራው። እሱ የለኮሰው እሳት ተቀጣጠለ!

“በቀን በሚረባውም በማይረባውም ምክንያት ማጅራታችንን የምንመታው አንሶን፣ ደግሞ በጨለማ በማንም ሌባ እጅ እንሙት?” ጎልማሳው ነው። እየቆየ ከንክኖታል። “ኧረ ንገሩት ሌብነትም ሥራ ነው ከተባለ ሰንብቷል በሉት…” ሦስተኛው የጥንዶች መቀመጫ ላይ ተደርባ የተቀመጠች ወይዘሮ ትናገራለች። የእሷን መልዕክት ሳናደርስ ከፊታችን የተቀመጠ ተሳፋሪ ከወያላው ጋር ንትርክ ጀምሮ ታክሲዋን አደበላለቃት። “ጠዋት የመጣሁት በአሥር ብር ነው፣ ለምንድነው አሁን ሃያ አምስት ብር የምከፍለው? የመጣሁበት መንገድ ስመለስበት የሚረዝመው በማን ሥልጣን ነው? በአንተ?” ይጮሃል። ወያላው ምክንያቱን ሳያቀርብ አንድ ተሳፋሪ ጣልቃ ገብቶ፣ “ወንድሜ ምን አዳረቀህ ለአሥራ አምስት ብር? ስጠው ግድየለህም ስጠው….” ይለዋል። ሰውዬው ከሌሎች ከምለይ ብሎ ኩምሽሽ አለ። ‘እኮ በዚህ አያያዛችን የመብትና የግዴታ ነገር በዋኖቻችን ጥረት፣ ጨዋነትና ቅንነት ብቻ ፈር ይዘው እናያለን? ኧረ በየት አገር ነበር ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ ሲያንቆለጳጵሰው የታየው?’ ያስብላል። አያስብልም? እንጃ!

ደግሞ ትንሽ እንደሄድን ከሾፌሩ ጀርባ ከተሰየሙ ወጣቶች መሀል አንዱ፣ “‘የስ’ ገባ!” ብሎ በጩኸት አባነነን። ሞባይሉ ላይ አቀርቅሮ እናየው ስለነበር የኳስ ውጤት እየተከታተለ ነው ብለን ደምድመናል። ታዲያ አንዱ፣ “ማን አግብቶ ነው እንዲህ የሚጮህብን?” ከማለቱ፣ “ማንስ ቢያገባ ለራሱ እንጂ ለእኛ ኑሮ አይጠቅምም። ድከሙ ቢለን ነው በሰው ጉዳይ ‘ቢዚ’ ሆነን በባህር ማዶ ኳስ ተገትረን የምናድረው…” ብላ ወይዘሮዋ መለሰች። “እንዴት እንደዚያ ትላላችሁ? መኖሪያ ቤት ወይም የመኖሪያ መሬት ተነፍገን በሰው አገር መሬት ላይ የምትንከባለል ኳስ አፈቀራችሁ ተብሎ ጭራሽ ወቀሳ? ኧረ እየተሳሰብን ወገን፡፡ ጦርነት የሚያስቆም የሰላም ስምምነት ተፈራርመን እኛ እዚህ በነገር…” አለ ከወዲያ ማዶ አንዱ አፍቃሪ። ነገሩን ያዳውሩታል!

“ገባ!” ብሎ የጮኸው ወጣት በበኩሉ፣ “ኧረ አትጣሉ ገባ ያልኩት ካርዱን ነው…” ብሎን አረፈው። “ታዲያ አትናገርም እንዴ? ይኼማ ትልቅ ድል ነው፣ ማነህ ሾፌር  የእርግብ አሞራን ክፈትለት…” ስትል ወይዘሮዋ ተሳፋሪዎች በሳቅ አውካኩ። ሳቁ ጋብ ሲል ወይዘሮዋ ቀጠለች፣ “እውነት አለመታደል እንጂ እስኪ አሁን እንደ ወሬ ‘ኔትወርካችን’ ስኬታማነት የስልካችን ‘ኔትወርክ’ እንዲህ ልባችንን ማውለቅ ነበረበት?” ብላ ስትጠይቅ፣ ከመጨረሻ ወንበር እየደጋገመች ‘ወይኔ ጉዴ ዛሬ…’ የምትለዋ የመሸባት ልጅ፣ “የዓሳ ብልሽት ከአናቱ ነው አይደል የሚባል? ድሮም መሠረቱ ጥሩ ያልሆነ ሥራ አሻሻልንህ ቢሉት፣ አዳጎስነው ቢሉት ራስን ማታለል ነው…” አለች። ያለችውን እኛ ሰማን። ይብላኝላቸው አንሰማም አናይም ላሉት እንጂ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ጎማው ላይ በጥንቃቄ ተለክታ የተቀመጠች አግዳሚ ተጠባብቀው የተቀመጡ አራት ወጣት ተሳፈሪዎች ተሸክማለች። ሁለቱ ጨዋታ ጀምረዋል። “ኧረ አንተ ልጅ ተው ልብሴን አምጣ? በሕገ መንግሥቱ ይዤሃለሁ ተው?” ይላል አንደኛው። ወዲያ ማዶ የልጁን ልመና በደንብ ያላዳመጠ ችኩል ቀንድ ሲነክስ፣ “ሲሉ ሰምታ ምናምን አለች’ አሉ:: የሰላም ስምምነቱ በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ ይከናዋናል ሲባል የሰማ ሁሉ፣ ድንገት እየተነሳ ሲያብጠለጥለው የከረመውን ሰነድ ዋቢ እያደረገ በሕገ መንግሥት ሲል ግርም አይልም?” አለ። “ኧረ እያጣራህ ስማ፣ ከጉልበት ይልቅ ሕግ ይሻለናል እያለው እኮ ነው…” አለችው አጠገቡ በራሷ ዝምታ ተመስጣ የተቀመጠች የምትመስል ወጣት። ስንት ዓይነት ሰው አለ እኮ እናንተ፡፡ “እመልስልሃለሁ አልኩህ እኮ ትንሽ ቀን ታገሰኝ፣ የሆነ መሥሪያ ቤት ‘ኢንተርቪው’ ስላለብኝ ነው…” ይላል ልብስ ተዋሹ። ተሳፋሪዎች በመደነቅ ያዳምጣሉ። “ደመወዛችን መቶ ጉዳያችን ሚሊዮን” ያለው ሰው መደነቅ አለበት!

“የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም…” ሆኖ ማጣት አንገት ድረስ ሲያሰምጥ ገመና ብሎ ነገር ኃፍረት የሚረሳ ይመስላል። “እኔም እኮ ተቸገርኩ፣ ለራስህ ብቻ ነው እንዴ እንደ ዘመኑ ሀብታም የምታስበው? አላበዛውም ይኼ?!” ብሎ አዋሹ ትንሽ ቆይቶ፣ “የተማረው ሳይቀር በልብስ ያምናል። ትንሽ ልብስህ ቆሸሽ ካልህ ልብህም የቆሸሸ ይመስላቸውና ሌባ ያደርጉሃል። እንዴ እኔ ለምን ልሳቀቅ? በተቀጠርኩ በሳምንቴ በስንት ልፋት ያገኘሁትን ሥራ በልብስ ምክንያት ልጣ?” ሲል እየደጋገመ መጨረሻ ወንበር የተቀመጡት ወጣቶች እየተቀባበሉ፣ በዚህ ዘመን በለበሱት ብሷል ሌብነቱ። ምን ሌብነቱ ብቻ ጭቆናውም ነፃ አውጪ ነን ባሉት ፋፍቷል። ኧረ የዝንብ ያህል መታየታችንንም እንጃ… ይባባላሉ። ይኼን እየሰማች በወይዘሮዋና በእኔ መሀል የተቀመጠች ተሳፋሪ ጆሮዬን ልትነክስ ምንም ሳይቀራት አስግጋ፣ “ይኼን ያህል ሰው ሁሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው ተሞጋቹ ሞቶ ነው ተኝቶ?” አትለንም? ‘መሞቴን መኖሬን እኔ ምን አውቃለሁ፣ ስቅ ስቅ ሲለኝ አስታውስሻለሁ’ አለ አዝማሪው!

ወደ መዳረሻችን ተጠግተናል። ጨለማው በርትቷል። ታክሲያችን ፍጥነቷ ቀዝቅዞ ቦታ ለመያዝ የመንገዱን ዳር ትታከካለች። ለወትሮም ከምንወርድበት ሳትደርስ ስትቆም ወያላውም፣ “መጨረሻ! ውረዱ እባካችሁ!” ሲል ተሳፋሪዎች ተንጫጩ። “አልበዛም እንዴ?” ወይዘሮዋ ቱግ ስትል፣ “እንዴት አይበዛ? ወትሮም እንቁላል ሲሰርቅ ያልተቀጣ ልጅ በሬ መስረቁ አይቀርም። በትንሹ ያልታረቀ ጥፋት አድሮ የአገር ቡጉንጅ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ግድየለም እኔ እወርዳለሁ…” ብሎ ሃያ አምስት ብር አልከፍልም እያለ ሊጨቃጨቅ ጀምሮ ተሳፋሪው አብሮት እንደማበር ቅስሙን ሰብሮ ዝም ያስባለው ሰውዬ ወረደ። ወያላው፣ “ውረዱ ብያለሁ ውረዱ፣ ነገር እንዳታመጡ፣ እኔ ቤቴ በዚህ ጋ ነው፣ ላወርዳችሁ የምችለውም እዚህ ጋ ነው። ኮንትራት የያዛችሁ መሰላችሁ እንዴ አንወርድም የምትሉኝ? ወይስ የሰዎቹ አባዜ ተጋባባችሁ?” ይለናል ያ ሁሉ ሰው እየተንጫጫበት ምንም ሳይደነግጥ። ለሾፌሩ ስሞታችንን ብናቀርብም፣ “እኔ አያገባኝም ውረዱ ካለ ውረዱ ነው…” ብሎ ቆረጠልን። ምርጫ ያጡ ተሳፋሪዎች ለማን አቤት ይባላል እያሉ ወርደው በእግራቸው መትመም ጀመሩ። ታክሲዋ አውርዳን ወደ ሠፈር ውስጥ ታጥፋ ገባች። ከትምህርት ቤት የተለቀቅን ይመስል ግር ብለን ረጭ ያለውን ጎዳና ስናውከው በነገሩ በጣም የተበሳጨች አንዲት ተሳፋሪ፣ “ይበለን… ይበለን… መብታችንን በሥርዓት ማስከበር አናውቅማ፡፡ እነዚያ ጉረኞችም መሬት ላይ ሲደቆሱ አይደለም እንዴ ሮጠው ሄደው የፈረሙት፡፡ ወደው ሳይሆን ተገደው እንጂ በፈቃዳቸው አለመሆኑንማ እናውቃለን…” ብላ ቅኔውን ፈታችልን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት