Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየሰላም ስምምነቱ ወሳኝ አንኳር ነጥቦች!

የሰላም ስምምነቱ ወሳኝ አንኳር ነጥቦች!

ቀን:

በሲሳይ መንግሥቴ አዲሱ (ዶ/ር)

መግቢያ

አሥር ገጽ ከሚሆነው የሰላም ስምምነት ሰነዱ ውስጥ በዋነኛነት አንቀጽ 2፣ አንቀጽ 6፣ አንቀጽ 7 እና አንቀጽ 10 በጣም ጠቃሚ ሐሳቦችን የያዙ ሲሆኑ በተወሰነም ቢሆን አወዛጋቢ የሆኑ ድንጋጌዎችንም ይዘዋል ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም አብዛኞቹ የሰላም ስምምነቱ ድንጋጌዎች ትህነግን ከጨዋታ ውጪ እንዳደረጉ የተመለከትን ቢሆንም፣ የተወሰኑት ድንጋጌዎች በሕይወት እንዲቀጥል ዕድል ስለሰጡትና በቀጣይም የመደራደር አቅም እንዲኖረው ስላደረጉት የተወሰኑ የስምምነት ሰነዱ አንቀጾችንና ሐሳቦችን በመጠቀም አንገቱን ቀና ለማድረግ መውተርተሩ አይቀርም፡፡ ለመሆኑ እነዚህ አራት ድንጋጌዎችን ብቻ ለይተህ ለምን ወሳኝ ናቸው አልህ ለሚለኝ ሰው፣ በመጀመሪያ የእነዚህ አንቀጾች ምን ይመስላል የሚለውን እንዳለ ላስቀምጥና ለምን ወሳኝ እንደሆኑ በትንሹ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡

Article 2 – Principles Underpinning the Permanent Cessation of Hostilities

The Parties shall be guided by the following principles: – 

  1. Accountability and justice in accordance with the FDRE Constitution and the AU Transitional Justice Policy Framework;

Article 6 – Disarmament, Demobilization, and Reintegration (DDR). The Parties: –

  1. Agree to finalize the overall disarmament of the TPLF combatants, including light weapons within 30 days from the signing of this Agreement;

Article 7 – Confidence-building measures. 1) The TPLF shall: –

  1. d) Refrain from conscription, training, deployment, mobilization, or preparation for conflict and hostilities;

Article 10 – Transitional Measures.

  1. The Government of Ethiopia shall implement a comprehensive national transitional justice policy aimed at accountability, ascertaining the truth, redress for victims, reconciliation, and healing, consistent with the Constitution of FDRE and the African Union Transitional Justice Policy Framework.
  2. The Parties commit to resolving issues of contested areas in accordance with the Constitution of the Federal Democratic Republic of Ethiopia.

ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች መልዕክትና የእኔ ግንዛቤ

እንግዲህ ከላይ የሰፈሩትን አንቀጾች ይዘትና ዋነኛ መልዕክት በደንብ አስተውሎ ለተመለከተ ሰው፣ ጠበቅ ያሉ ድንጋጌዎችና ለውዝግብ በር የሚከፍቱ ሐሳቦች ያሉት በእነዚህ አንቀጾች ሥር ባሉት ንዑስ አንቀጸች ውስጥ እንደሆነ ለመገንዘብ አይቸገርም፡፡ ለምሳሌ በአንቀጽ 2 (f) እና በአንቀጽ 10 (3) ላይ የሰፈሩትን ሐሳቦች ስንመለከት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትና በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ወቅት ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ ላይ ተመሥርቶ የተጠያቂነትና የሽግግር ወቅት ፍትሕ ሊሰፍን እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ ይህም ማለት ጦርነቱ ባደረሰው ጉዳት ልክና አስከፊ ገጽታ በሕገ መንግሥቱና በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ወቅት ፖሊሲ መርሆዎች መሠረት ተጠያቂ የሚሆን ወገን እንደሚኖር፣ እውነትን የማረጋገጥ፣ ለተጎጂዎች ዘላቂ መፍትሔ የመስጠት፣ የእርቅና ስብራትን የመጠገን ሥራዎችን የመሥራት ግዴታ እንዳለባቸው ያስቀምጣሉ፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ውዝግብ ሊነሳ የሚችለው፡፡ ለምን ቢባል ማን ነው ማንን ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችለው? ተጠያቂ የሚሆነውን ወገንስ እንዴትና በምን መሥፈርት ነው መለየት የሚቻለው? ወዘተ. ለሚሉት ጥያቄዎች የሚሰጡ መልሶች በራሳቸው አከራካሪ መሆናቸው አይቀርም፡፡

ሌላው አንቀጽ 6 (f) ላይ በማያሻማ መልኩ እንደተመለከተው ሁለቱም ወገኖች ስምምነቱ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ የትህነግን ታጣቂዎች ቀላል መሣሪያዎችን ጨምሮ፣ ሁሉንም ዓይነት ትጥቅ የማስፈታት ሥራውን ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል ይላል፡፡ ይህም በጣም ጠቃሚ ድንጋጌ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ትህነግ ምን ያህል የታጠቀ ኃይል እንዳለውና የትኛውስ ወገን ነው የትህነግ ታጣቂ ኃይል የሚለውን ለይቶ ለማወቅ የተለየ ስልት መከተልን የሚጠይቅ ነውና ይህም ሁኔታ በራሱ ሌላ ከባድ ኃላፊነትን ይዞ ይመጣል፡፡ በሌላ አነጋገር ቢያንስ ባለፉት 40 ዓመታት በአጠቃላይና ባለፉት 30 ዓመታት ደግሞ በተለይ አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ከሞላ ጎደል ትጥቅ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡

እናም ከዚህ ውስጥ አሁን ላይ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ታጣቂ ኃይል ወደየቤቱ ተመልሶ መሣሪያውን ቢደብቅና የሲቪል ልብሱን በመልበስ ሰላማዊ ሰው መስሎ ብቅ ቢል እንዴት ነው ለይቶ ማወቅ የሚቻለው? ይህንን ‹‹ወርቃማ ዕድል›› ትህነግም በደንብ እንደሚጠቀምበት ምንም አያጠራጥርም፡፡ በዚያ ላይ አንዳንድ ሞኝ ወይም የሰላም ስምምነት ሐሳቡ በደንብ ያልገባቸው፣ አልያም ሆን ብለው የትግራይን ሕዝብና ደጋፊዎቻቸውን ለማደናገር የሚሞክሩ የትግራይ ልሂቃንና ደጋፊዎቻቸው (ቅጥረኛ ፈረንጆች እንደሆኑ የሚታወቁት እነ ማርቲን ፕላውት (Martin Plaut)፣ ሸትል ትሮንቮል (Kjetil Tronvoll)፣ ዊሊያም ዳቪሰን (William Davison)፣ አሌክስ ዲ ዋል (Alex de Waal)፣ ሬኔ ሌፎርት (Rene Lefort)፣ ኬኔት ሮዝ (Kennet Roth)፣ ባሽር ሀሺይስፍ (Bashir Hashiysf) እና ሌሎችም ትህነግ ትጥቅ ይፍታ ተባለ እንጂ የትግራይ መከላከያ ኃይል (Tigray Defence Force (TDF)) ትጥቅ ይፈታል አልተባለምና ይኸ ኃይል የትግራይ ሕዝብ መድኅን ሆኖ ይቀጥላል በማለት ለመቀስቀስ እየሞከሩ ነው፡፡

እነዚህ ወገኖች የዘነጉት ነገር ቢኖር በስምምነቱ አንቀጽ 6 (a) ላይ “The Parties Agree and recognize that the Federal Democratic Republic of Ethiopia has only one defense force;” የሚል አስገዳጅ ድንጋጌ በስምምነት ሰነዱ ውስጥ ማስፈሩን ነው፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያ አንድ የመከላከያ ኃይል ብቻ እንደሚኖራት ሁለቱም ወገኖች ተስማምተው ፈርመዋልና የትግራይ መከላከያ ኃይል የሚባል ታጣቂ ቡድን ባለበት ሁኔታ የሚቀጥል አይሆንም፡፡ ለነገሩ አጉል ጉንጭ ማልፋት ስለሚሆን ነው እንጂ ይህ ኃይል ከትህነግ ውጭ ራሱን ችሎ እንዲቀጥል የሚያደርጉት የህልውና መሠረቶች አሉት ወይ የሚል ጥያቄ በማንሳት መሞገት ይቻል ይሆናል፡፡

በዚያ ላይ መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ፣ እንዲሁም የፌዴራል ደኅንነት ወደ ትግራይ ገብተው ሕግ የማስከበር ሥራቸውን እንደሚያከናውኑም በስምምነቱ ላይ ተቀምጧል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ በክልሉ ውስጥ ሁሉንም የትግራይ ኃይሎች የሚያሳትፍ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋምና ሕግና ሥርዓት ማስከበርን ጨምሮ፣ የዕለት ከዕለት የመንግሥት ተግባራትን እንደሚያከናውን ተሰምሮበታል፡፡ የፌዴራል መንግሥት የቅርብ ክትትልና ድጋፍም አይለየውም፡፡ ታዲያ እነዚህ ወገኖች የትግራይ መከላከያ ኃይል (TDF) የሚሉት ገዳይ ቡድን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥር ሆኖ እንዲቀጥል ፈልገው ይሆን ይህንን ትርጉም የለሽ ሐሳብ የሚያራምዱት? ኧረ እባካችሁ አታስቁን በሏቸው፡፡ አባቶቻችን እንዲህ ያለ ግራ የገባው ነገር ሲያጋጥማቸው፣ ‹‹የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር›› በማለት ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡

በአንቀጽ 7 (d) ላይ ደግሞ ትህነግ ወታደር እንዳይመለምል፣ እንዳያሠለጥን፣ እንዳያሰማራ፣ የማነሳሳት ሥራ እንዳይሠራ ወይም ግጭትና አለመግባባትን ለመፍጠር እንዳይዘጋጅ የሚያደርግ አስገዳጅ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህ ስምምነት መልካም ሐሳብ ይዞ እንደመጣ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ ትህነግ ይህንን መልካም የሆነ የስምምነት ሰነድ ያከብረዋል ወይ? ጊዜ አግኝቶ ራሱን ካደራጀ በኋላ እንደለመደው የትግራይን ሕዝብ በአጠቃላይና ባለፉት 40 ዓመታት በአምሳያው የቀረፀውን የትግራይ ወጣት ደግሞ በተለይ በቀላሉ አነሳስቶ የራሱ የሆነ የታጠቀ ኃይል እንዲኖረው ለማድረግ እንደማይሞክር፣ ወይም እንደማይሠራ ምን ዋስትና አለ ለሚለው ጥያቄ መልስ ያሻዋል፡፡

በመጨረሻም በአንቀጽ 10 (4) ላይ የተቀመጠው የተቀበረ ቦምብ እንዴት ነው ጉዳት ሳያደርስ የሚተነፍሰውና በሚፈለገው መንገድ ሊተረጎም ብሎም ሊተገበር የሚችለው የሚለው ጉዳይ ብዙዎቹን እያነጋገር እንደሆነ እየተመለከትን ነው፡፡ ይህ ንዑስ አንቀጽ ሁለቱም ወገኖች አጨቃጫቂ/አከራካሪ የሆኑ አካባቢዎችን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ይላል፡፡ ይህ ሲባል ምን ለማለት ተፈልጎ ነው የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት በዚህ ሐሳብ ዙሪያ ጉዳዩ በቀጥታ ያገባናል፣ ያሳስበናልም የሚሉ ሰዎች ወይም ወገኖች ምን ይላሉ? እንዴትስ ተረድተውታል? በሚለው ላይ ትንሽ ነገር ልበል፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ ቀላል ቁጥር የሌላቸው የአማራ ልሂቃን ደስተኞች አይደሉም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹማ በዚህም ምክንያት ትህነግ ከዚህ የሰላም ስምምነት ይበልጥ ተጠቃሚ ሆኗል እስከ ማለት ይደርሳሉ፡፡ ይህም የሆነው የአማራን ሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቁ ተደራዳሪዎች ስላልተወከሉ፣ ለጥያቄው በሕገ መንግሥቱ መሠረት መልስ ይሰጠው የሚለውን የመፍትሔ ሐሳብ እንዳለ ስለተቀበሉ ነው ይላሉ፡፡

በእነዚህ ወገኖች እምነት ጌታቸው ጀምበር (ዶ/ር)፣ አቶ ደመቀ መኮንንና አቶ ተመሥገን ጥሩነህ የአማራን ሕዝብ አይወክሉም፡፡ ለዚያም ነው በስምምት ሰነዱ ላይ የእነዚህ አከራካሪ አካባቢዎች ጉዳይ ተነስቶ ለአማራ ሕዝብ በሚጠቅም መንገድ እንዲወሰን ያልተደረገው በማለት ይሟገታሉ፡፡ ይህ ሙግት እስከምን ድረስ ሊወስድ ይችላል የሚለው ጥያቄ ግን በሚገባ ሊነሳና ሊመከርበት ይገባል፡፡ በተቃራኒው የትግራይ ልሂቃን ትጥቅ ማስፈታት በሚለው የስምምነት ሐሳብ ላይ በእጅጉ ቢበሳጩና ቢከፉም፣ አጨቃጫቂ/አከራካሪ አካባቢዎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት መፍትሔ ይሰጣቸዋል የሚለው ድንጋጌ ከሁሉም በላይ ለእነሱ እንደሚጠቅም አድርገው በመረዳታቸው ደስተኞች መሆናቸውን እየገለጹ ነው፡፡ አጨቃጫቂ/አከራካሪ የሚባሉት አካባቢዎች ወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የእነዚህ አካባቢዎች ልሂቃን ደግሞ ከበርካታ ዓመታት (ለውጥ ከመምጣቱ) በፊት ጀምሮ፣ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ አንስተው መታገላቸውና ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ጥያቄያቸውን ለቀድሞው የትግራይ ክልል ምክር ቤት አቅርበው፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምላሽ በማጣታቸው የይግባኝ አቤቱታቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበው በአሁኑ ወቅት ጉዳያቸው መታየት ጀምሯል፡፡ ይህም የሆነው ትህነግ ሕገ መንግሥቱን አክብሮ ለእነዚህ አካባቢ ሕዝቦች ጥያቄ መልስ ባለመስጠቱ ነው፡፡ እናም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ችግሩ በዘላቂነት ይፈታ ሲባል ቀደም ሲል ጀምሮ ሲሠራበት የነበረና በትህነግ እንቢተኝነት ተንጠልጥሎ የቆየ ጉዳይ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ አሁንም ቢሆን ትህነግ ሕገ መንግሥቱን አክብሮ ይሠራል ማለት ዘበት ነው፡፡

ስለሆነም ሕገ መንግሥቱ እስካልተለወጠ ወይም እስካልተከለሰ ድረስ ከእነ ችግሩም ቢሆን፣ ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ውጭ ሆኖ የአንድ አካባቢ ሕዝብ ችግሮች ይፈታሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው የሚሆነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በፖለቲካ ኃይሎችና በሚመለከታቸው አካላት መካከል በሚደረስ ስምምነት መሠረት፣ እንዲሁም የአብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ እስከሚለወጥ ወይም እስከሚከለስ ድረስ ጉዳዩ ተንጠልጥሎ ይቆይ ማለት ደግሞ ፍፁም ኃላፊነት የጎደለውና አላዋቂነትን የሚያስተናግድ፣ ብሎም ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የሚውል አቋም ከመሆን ውጭ ውኃ የሚያነሳ ሐሳብ ሊሆን አይችልም፡፡ እናም አሁን ባለው ሁኔታ በተጀመረው መንገድ ቀጥሎ ጥያቄው እንዲመለስ ይደረጋል፡፡

እናም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ችግሩ ይፈታ ሲባልስ ምን ማለት ነው? ጉዳዩ እንዴት ነው ሊታይ የሚችለው በሚለው ጥያቄ ላይም የተለያዩ ሐሳቦች ሲራመዱ ይስተዋላሉ፡፡ አንደኛው የሕዝቡን ስሜትና ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰን ይችላል የሚለው ነው፡፡ እውነት ነው ይህ ሐሳብ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 ጋር የሚስማማ/የሚጣጣም ነው፡፡ ምክንያቱም የዚህ ድንጋጌ መሠረተ ሐሳብ በክልሎች መካከል የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ሲነሳ ክልሎቹ ተነጋግረው እንዲፈቱት ዕድል ይሰጣል፡፡ ይኼ የማይቻል ከሆነ ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይወስናል ስለሚል ይህንን አማራጭ መከተል ለጊዜው አዋጭ ሊመስል ይችላል፡፡

ሆኖም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካዮች ከየብሔረሰቡ የሚመጡና አማራን በአጠቃላይ፣ የአማራን ፖለቲካ በተለይ በጥርጣሬ ዓይን እንዲመለከቱ ተደርገው የተቃኙ ሰዎች ስለሆኑ ይህን የመፍትሔ ሐሳብ በቀላሉ ሊቀበሉት እንደማይችሉ አስቀድሞ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በዚያ ላይ የአንዳንዶቹ ክልል ተወካዮች እዚህ ላይ በዝርዝር መግለጽ በማልፈልገው ምክንያት የራሳቸው የሆነ ሥጋት ያለባቸው መሆናቸውም ይታወቃል፡፡ ሁለተኛውና ከእስካሁኑ ልምድ ተነስተን ስንመለከተው አይቀሬ የሚሆነው የመፍትሔ ሐሳብ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ ወይም ማደራጀት የሚለው ነው፡፡ ይህ አማራጭ ለሁሉም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ለመወሰን የሚመችና ጊዜም የሚወስድ እንደሆነ ይታመናል፡፡

ይህም ሆኖ ይኼ የመፍትሔ አማራጭ ሐሳብ እንዴት ሊተገበር ይችላል? የሚለውን ጥያቄ በሁለት ከፍለን ብንመለከተው ይሻላል፡፡ አንደኛው ራያና ጠለምት ላይ ትህነግ የሠፈራ ፕሮግራም ስላላካሄደባቸው የነባሩ ሕዝብ ቁጥር ይበዛልና ሕዝበ ውሳኔ ቢካሄድ የሚያሠጋ ጉዳይ አይደለም የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው የወልቃይት-ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አካባቢ ሕዝብ በትህነግ ካድሬዎችና ታጣቂዎች አፈና፣ ግድያና በግፍ የማፈናቀል ተግባር ሳቢያ የነባሩ ሕዝብ ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጎ (ከአንድ ዓመት በፊት አቶ ብናልፍ አንዱዓለም የብልፅግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በነበሩበት ወቅት በሰጡት መግለጫ ላይ በወልቃይት-ጠገዴ አካባቢ ብቻ ከ500,0000 ሕዝብ በላይ እንደተፈናቀለ ገልጸዋል)፣ በተቃራኒው ከትግራይ አካባቢ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚቆጠር ሕዝብ መጥቶ በእነዚህ አካባቢዎች በመሥፈሩ ምክንያት ሕዝበ ውሳኔ ቢካሄድ የነባሩ ሕዝብ ጥያቄ ሊመለስ ይችላልን የሚለው ሥጋት ነው፡፡ እዚህ ላይ አከራካሪ ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ለምን ቢባል የትግራይ ልሂቃን የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ወደ ቦታቸው ከተመለሱ በኋላ እነሱ በሚሳተፉበት ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔው ይካሄድ ይላሉ፡፡ በተቃራኒው የወልቃይት-ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴና ሕዝብ፣ እንዲሁም ሌላኛው የአማራ ልሂቅ ደግሞ ይህማ ሊሆን አይችልም የሚል የመከራከሪያ ሐሳብ ማቅረባቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡

ሆኖም የተሻለ መፍትሔ የሚሆነው በሕዝበ ውሳኔው ወቅት ድምፅ መስጠት ያለበት ጥያቄ ያነሳው ነባር ሕዝብ እንጂ፣ ምንም ዓይነት የማንነት ጥያቄ የሌለው ሰፋሪ (እኔ ትግራዋይ ነኝ የሚል የኅብረተሰብ ክፍል) መሆን አይገባውም የሚለው ሐሳብ ቢተገበር ነው፡፡ እርግጥ ነው በአንድ አካባቢ ሕዝበ ውሳኔ ሲካሄድ የተወሰነውን የኅብረተሰብ ክፍል የማያሳትፍ ሊሆን አይገባውም የሚል ወገን መኖሩ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ከማንነት ጋር የሚያያዝ እስከሆነ ድረስ ይህንን የማንነት ሁኔታ መወሰን ያለባቸው፣ የጥያቄው ባለቤቶችና ጥያቄውን በማንሳት ምላሽ በሚጠብቁት የኅብረተሰብ ክፍሎች እንጂ የማንነት ጥያቄ የሌላቸው ነዋሪዎች ሊሆኑ አይገባም የሚለውን መርህ ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ በኦሮሚያ ክልል በዋነኛነትም በአርሲ፣ በወለጋ፣ በጅማና በኢሉአባቦር አስተዳደር ዞኖች ውስጥ የሚገኙ አማሮች በኦሮሞ ጉዳይ ላይ በሚደረግ ሕዝበ ውሳኔ ድምፅ እንዲሰጡ ይደረግ እንደ ማለት ነው፡፡  

ስለሆነም ቢያንስ በሠፈራ መልክ የመጡትን የትግራይ ተወላጆች በሕዝበ ውሳኔው ላይ ድምፅ እንዳይሰጡ ለማድረግ ሲባል ከ1984 ዓ.ም. በፊት የትግራይ ተወላጆችንም ጨምሮ በወልቃይት-ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ውስጥ የነበረው ሕዝብና ልጆቹ ለአካባቢዎቹ እንደ ነባር ሕዝብ ተቆጥረው በሕዝበ ውሳኔው ድምፅ እንዲሰጡ ቢደረግ፣ ይበልጥ ፍትሐዊ ይሆናል የሚል ግምት መያዝ ተገቢ ይመስላል፡፡ ከዚያም አልፎ እነዚህ አከራካሪ አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሔ እስኪያገኙ ድረስ በማን ሥር ሊቆዩ ይገባል የሚለው ሐሳብም ሌላኛው አከራካሪ ጉዳይ መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚህ ረገድ በ2013 ዓ.ም. አካባቢዎቹ ከትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ነፃ እንደወጡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በነበሩት አቶ አደም ፋራህ አስተባባሪነት የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ወደ አካባቢዎቹ በመሄድ ሕዝቡን አነጋግረው ነበር፡፡

በዚህም የአካባቢዎቹ (ወልቃይት-ጠገዴ ሰቲት ሁመራን ጨምሮ ጠለምትና ራያ) ነዋሪዎች ከአሁን በኋላ ወደ ትግራይ ክልል ለመመለስ ማሰብ የማይሆንና በፍፁም የማይታሰብ ነገር ነው ከማለት አልፈው፣ አንዳንዶቹ የዕድሜ ባለፀጋ አዛውንቶች ሳይቀሩ እንኳን ወደ ትግራይ ክልል ለመመለስ ፊታችንን ወደ እነሱ አዙረን መተኛት አንፈልግም እስከ ማለት ደርሰው እንደነበረም ይታወቃል (በነገራችን ላይ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እንደ አንድ የራያ ተወላጅ አላማጣ ከተማ ውስጥ በተዘጋጀው መድረክ ላይ በአካል ተገኝቶ የሕዝቡን ሐሳብና አስተያየት ማዳመጡን፣ እንዲሁም ትክክለኛ ስሜቱንም መመልከቱን ማስታወስ ይፈልጋል)፡፡ ይህንንም እውነታ ታሳቢ በማድረግ የብልፅግና ከፍተኛ አመራር የሕዝቡ ጥያቄ ዘላቂ መልስ እስኪሰጠው ድረስ አካባቢዎቹ አሁን ባሉበት ሁኔታ ይቆዩ የሚል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ አሁንም ቢሆን ይህ ውሳኔ ተግባራዊ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግ ፖለቲካዊ ሁኔታ መኖሩ አይቀርም፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰብዓዊ መብቶች፣ በሕግና በሥነ መንግሥት ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው sisaymengiste@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...