Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኅብረተሰቡ አስፈሪ ብሎ የፈረጃቸውን ልጆች በመደገፍ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ እያሳየን ነው›› የቢቢአር ኤፍ የውባንቺ ፕሮጀክት ኃላፊ ፀደይ ተፈራ    

የብለ ብሎ ሩዥ ፋውንዴሽን  (ቢቢአር ኤፍ) በሕጋዊ መንገድ ከመመዝገቡ ከአራት ዓመታት በፊት አገልግሎት የሚሰጡት በበጎ ፈቃደኝነት ነበር፡፡ ለውባንቺ ፕሮጀክት መከፈት ምክንያት የሆነውም እነሱ በበጎ ፈቃደኝነት ያገለግሏቸው የነበሩና ከጎዳና በሚነሱ ልጆች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች በበጀት እጥረት ምክንያት መዘጋታቸው ነው፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል የሕፃናት ማሳደጊያዎች ሲዘጉ ወይም ልጆች በተለያየ ምክንያት ራሳቸውን ሳይችሉ ከማሳደጊያ ሲወጡ እነሱን ይዞ ድጋፍ የሚያደርግ አካል ባለመኖሩም የተረሱትን ታዳጊዎች የሕይወት መስመር ውስጥ አስገብቶ ለቁም ነገር ለማብቃት ሲሉ የቢቢአር ኤፍ ውባንቺ ፕሮጀክትን ዕውን አድርገዋል፡፡ ብለ ብሎ ሩዥ ፋውንዴሽን  (ቢቢአር ኤፍ) የውባንቺ ፕሮጀክት ኃላፊ ፀደይ ተፈራ ይህንን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ግንባር ቀደሙን ሚና መጫወታቸውን የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡ ፕሮጀክቱ ለታዳጊ ሕፃናት በሚያደርገው ድጋፎች ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡ ውባንቺ ፕሮጀክት እንዴት ተጀመረ?

ፀደይ፡ ሥራውን ቀድመን እናታለም ከሚባል ድርጅት ጋር እንሠራ ነበር፡፡ ታዳጊዎችን በመደገፍ በበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ እያደረግን እንደግፋት የነበረችው ውባንቺ የተባለች የ17 ዓመት ታዳጊ ወጣት ጓደኞቿን ለመጠየቅ ማታ ወጥታ ጠዋት ሞታ ተገኘች፡፡ የእሷ ሁኔታ እነሱን የሚረዳ ሥርዓት አለመኖሩን ያረጋገጠልን ነበር፡፡ በመሆኑም ይህንን ፕሮጀክት ለእሷ መታሰቢያ አድርገን ጀመርነው፡፡

ሪፖርተር፡ በከተማዋ ጎዳና የሚወጡት ዜጎች በሁሉም ዕድሜ ክልል ቢሆኑም የቢቢአር ኤፍ ውባንቺ ፕሮጀክት በታዳጊዎች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገው ለምንድነው?

ፀደይ፡ በአገራችን አንድ ልጅ ከግልም ሆነ ከመንግሥት ማሳደጊያ ቢወጣ/ብትወጣ እሱን/እሷን ተከትሎ ለመደገፍና ክትትል አድርገው ለቁም ነገር ለማብቃት የሚሠሩ ድርጅቶች በብዛት የሉም፡፡ ባብዛኛው ያሉት ሕፃናት ልጆችን የሚደግፉ ናቸው፡፡ ከ18 ዓመት በላይ ከሆኑ ደግሞ እነሱን በማቆያ አድርጎ ለመደገፍ ሕጉም አይደግፍም፡፡ ሆኖም በመሀል የተረሱና ድጋፍ የሚፈልጉ ታዳጊ ወጣቶች አሉ፡፡ በተለያየ ምክንያት ከመንግሥትና ከግል ማሳደጊያዎች ወይም ከኅብረተሰቡ ወጥተው ጎዳና የሚውሉና ጠባቂ የሌላቸውን 12 ዓመትና ከዚያ በላይ ሆነው 18 ዓመት ላልሞላቸው ታዳጊ ልጆች አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ይህ ዕድሜ በጣም ከባድና በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ነው፡፡ በዚህ ዕድሜ እነሱ ናቸው ትክክል፣ ሁሉን ነገር መሞከር ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም የቀለም፣ የክህሎትና ከማኅበረሰቡ ጋ ተቀላቅሎ የመኖር ችሎታ ላይ እያስተማርንና ከመስመር እንዳይወጡ እየደገፍን ራሳቸውን እንዲችሉ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡ በምን  ዓይነት መልኩ ነው ድጋፍ የምታደርጉት?

ፀደይ፡ መጀመሪያ ላይ ታዳጊ ስለሆኑና አብሮ ማኖር ከባድ ነው ብለን አስበን ሁለት ወይም ሦስት እያደረግን ቤት ተከራይተን ለየብቻ እናኖር ነበር፡፡ ነገር ግን ውባንቺ ስትሞት ድጋፍ ቢደረግም ራሳቸውን ችለው ለብቻቸው መኖር እንደማይችሉ የማንቂያ ደወል ሆነን፡፡ በመሆኑም የቤተሰብ ቤቶች መፍጠር ጀመርን፡፡

ሪፖርተር፡ የቤተሰብ ምንድነው?

ፀደይ፡ ከ12 እስከ 18 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ልጆችን ፈቃደኛ ከሆኑ እናቶች ጋር እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ እናቶቹ ብዙ ጊዜ ያላገቡ፣ አግብተው ይህንን ሥራ መሥራት የሚፈልጉ፣ አንዳንዶቹ ልጆቻቸው ደርሰው ራሳቸውን የቻሉ ወይም በተለያየ ሕይወት ሆነው ይህንን የሕይወት ጥሪ አድርገው የሚያስቡ ናቸው፡፡ ልጆችን ማሳደግ እግዚአብሔር ለእኔ የሰጠው መክሊት ነው ብለው የሚያስቡ ናቸው፡፡ የእኔ ወይም የአንቺ እናት ቤት ውስጥ ልጆቻቸውን ሰብስበው እንደሚያሳድጉት ከልጆቹ ጋር አብረው እየኖሩና እየተንከባከቡ የሚያሳድጉ ናቸው፡፡ በየቤተሰቡ ለኑሮ የሚያስፈልገውን በሙሉ የእኛ ድርጅት ይሸፍናል፡፡ ልጆቹን ይዘውና አሳድገው ኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲቀላቀሉ ያደርጋሉ፡፡ ዕድር፣ ዕቁብ፣ ቅርጫ በሁሉም ማኅበራዊ ሕይወት ይሳተፋሉ፡፡ በአንድ ቤት ሁለት እናት እናደርጋለን፡፡ ልጆቹ ትምህርት ቤት ይማራሉ፣ ኑሮዋቸውን ይኖራሉ፡፡ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ፣ ራሳቸውን የቻሉ ልጆች አሉን፡፡ እነዚህ ቅዳሜና እሑድ ሌሎችን ያግዛሉ፣ በዓልን አብረው ያከብራሉ፣ ሌሎቹን ይቆጣጠራሉ፡፡ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እናትና ልጆች፣ ወንድማማችና እህትማማች በመሆን ቤተሰባዊ ግንኙነት ፈጥረው ይኖራሉ፡፡ ከምናውቀው በስጋና በደም የተገኘ ቤተሰብ ካለመሆናቸው በስተቀር የምናደርገው ሙሉ በሙሉ እንደቤተሰብ እንዲኖሩ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ቤት፣ በጀት አለ፡፡ ሽሮ በርበሬ ያዘጋጃሉ፣ ምግባቸውን ይሠራሉ፣ ይማራሉ፣ አንድ ቤተሰብ የሚያስፈልገው ሁሉ ተሟልቶ ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡ ትኩረት ከምትሰጡት አንዱ ትምህርት ነው፡፡ የልጆቹ ውጤታማነት እንዴት ነው?

ፀደይ፡– ልጆቻችን እኛ ጋር ሲመጡ በዕድሜ አድገው በትምህርት ወደኋላ የቀሩ ናቸው፡፡ የ16 እና 17 ዓመት ልጅ ሦስተኛ ክፍል ሊሆን ይችላል፡፡ ከትምህርት ቤቶች ጋር ተባብረን ጥሩ ሥራ እንሠራለን፡፡ ትምህርት ላይ በደንብ ነው ኢንቨስት የምናደርገው፡፡ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ከእኛ ልጆች 95 በመቶ ያህሉ በደረጃቸው ስማቸው ከሚለጠፉት ተማሪዎች ውስጥ ናቸው፡፡ ስናመጣቸው ከመንግሥት ማሳደጊያ በተለያየ ምክንያት ሊወጡ ያሉትንና ከጎዳና ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ልጆቻችን ከሴክሽን 1ኛ የሚወጡ ናቸው፡፡ ፕሮጀክታችን የሚሰበስበው ኅብረተሰቡ የሚፈሩ ብሎ የፈረጃቸውን ነው፡፡ እኛ ለእነዚህ ሁለተኛ ዕድል ሰጥተን ደግፈን በማስተማራችንና ከኅብረተሰብ በመቀላቀላችን ሊለወጡ እንደሚችሉ ዓይተናል፡፡ ባንኮች ውስጥ የሚሠሩ፣ በኢንጂነሪንግ የተመረቁ፣ በነርሲንግ፣ በሕግ የጨረሱና ሥራ የያዙ አሉን፡፡ ኮሌጅ የሚማሩም አሉ፡፡ ይህ እነዚህ ልጆች ድጋፍ ካገኙ እንደሚለወጡ ያየንበት ነው፡፡

ሪፖርተርዕድሜያቸው ገፍቶ እናንተ ጋር መግባት ላልቻሉት ምን ታደርጋላችሁ?

ፀደይ፡ በተለያየ ምክንያት መንግሥት ማሳደጊያ ወይም ኅብረተሰብ ውስጥ ሆነው በዕድሜ ምክንያት እኛ ጋር መግባት ላልቻሉ ባሉበት ሆነው የቴክኒክና የሙያ ትምህርት ሥልጠና እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ሆነው በትምህርት ሳይገፉ ሕፃናት ጋ የሚኖሩ በማሳደጊያ ውስጥ አሉ፡፡ ዕድሜያቸው አልፎ ራሳቸውን ባለመቻላቸው በማሳደጊያ ውስጥ ለሚኖሩ የጀመርነው ፕሮጀክት  መንግሥት ለመጀመርያ ጊዜ በሰጠን 40 ሰዎች ነበር፡፡ ስራው በጣም ከባድ ነበር፡፡ ሌላ ሕይወት አያውቁም፡፡ የትምህርት ዝግጅታቸውን በማየትና በምርጫቸው በማስተማር እያበቃናቸው ነው፡፡ አሁን 30 ሰዎች ለመጨመር ዝግጅት ላይ ነን፡፡

ሪፖርተር፡ በቤት ውስጥ ከእናቶች ጋር እንዲኖሩ ከምታደርጉት በተጨማሪ የርቀት ድጋፍ አገልግሎትም አላችሁ፡፡ ይህንን ቢያብራሩልን?

ፀደይ፡ ከኅብረተሰቡ ወይም ከመንግሥት ማሳደጊያ ከባድ ሁኔታ አልፈው ኮሌጅ የሚገቡ ልጆች አሉ፡፡ ነገር ግን ሴቶቹ ሞዴስ ከመግዛት ጀምሮ ይቸገራሉ፡፡ ይህንን፣ የስቴሽነሪና ሌሎች ፍላጎታቸውን ለማሟላት ኮሌጅ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ እስኪመረቁ ድረስ ከ1,500 እስከ 1,800 ብር በወር እንሰጣለን፡፡ ክትትልም እናደርጋለን፡፡ የሕክምናና የምክር አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ክረምት ላይ እንዲሠሩ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ብዙ ልጆች አስመርቀናል፡፡ ሕፃናት የሕግ ታራሚዎች የምክርና የትምህርት ድጋፍ እንዲያገኙ እንረዳለን፡፡ ኮልፌና ቀጨኔ የሕፃናት ማሳደጊያ ላሉ ልጆችም የቤተ መጻሕፍት  ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከሥራ ሰዓት ውጪ ክፍት እንደሆን አድርገናል፡፡ የጥናት ፕሮግራም እንዲኖርና ልጆቹ ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ እየሠራን ያለነው ሥራ ውጤት እያመጣ ነው፡፡ መፀዳጃ ቤቶችን ማሳደስን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን እያደረግን ነው፡፡ ሽሮሜዳ አካባቢ ከጠዋት ጀምሮ እስከ 10 ሰዓት ቅጠል በመልቀምና በመሸጥ የሚያሳልፉ እናቶች ልጀቻቸው ከትምህርት እንዳይስተጓጎሉ ግማሽ ቀን ያስተምር የነበረ ፍቅር ለሥራ ትምህርት ቤት ውስጥ ተጨማሪ ክፍል አሠርተን ለ400 ተማሪ ሙሉ ቀን እንዲማሩ አድርገናል፡፡ ክበበ ፀሐይ የሕፃናት ማሳደጊያ ክሊኒክ የለውም ነበር፡፡ ክሊኒክ አሠርተናል፡፡ በቅርቡ ቁልፉን እናስረክባለን፡፡

ሪፖርተር፡ በቤተሰብ የምታሳድጓቸው ልጆች ዕድሜ ከባድና ከፍተኛ ክትትል የሚፈለግበት ነው፡፡ እንዴት እየተወጣችሁት ነው?

ፀደይ፡ልጆች በቤተሰብ ማደግ አለባቸው፡፡ ከ12 እስከ 16 ዓመት ያሉ ልጆች ከፍተኛ ክትትል የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እንኳን በሕፃናት ማሳደጊያ ያሉት ከወላጆቻቸው እናትና አባት ጋር የሚኖሩ ልጆች በጣም የሚያስቸግሩበት ዕድሜ ነው፡፡ ሁሉ ነገር እየተደረገለት ራሱን አስችየዋለሁ የተባለ ልጅ ከመስመር ሊወጣ ይችላል፡፡ እኛ ይህን ዕድሜ ተከታትለን፣ እያረምን እናሳድጋለን፡፡ ኑሮን እንዲያውቁ፣ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጪ ሥራ እንዲለምዱ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ያያችሁት ችግር ምንድነው?

ፀደይ፡የመጀመርያው ችግር ጎዳና የወጡ ወይም ሊወጡ ጫፍ የደረሱ ልጆችን ከወረዳ፣ ከክፍለ ከተማ ከከተማ አስተዳደር ጭምር ከታች ሁሉም ተከታትሎ መያዝ የሚያስችል ሥርዓት አለመኖሩ ነው፡፡ ማሳደጊያ ሲታይ በመንግሥት ያሉት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ጎዳና ያሉትና ቤተሰብ ጋር ሆነው በችግር ውስጥ የወደቁት  ይበዛሉ፡፡ ችግሩ ደጅና ኅብረተሰብ ውስጥ ነው ያለው፡፡ በቂ የማሳደጊያ ማዕከላትም የሉም፡፡ በተቋም ማሳደግ በራሱም የመጨረሻ አማራጭ ነው መሆን ያለበት፡፡ ቢቻል ማሳደጊያዎቹ ወደቤተሰብ ቤት ተቀይረው ልጆቹን ቢይዙ ጥሩ ነው፡፡ እናቶች ይቀያየራሉ፡፡ በርካታ ልጆች በአንድ ላይ ያድጋሉ፡፡ ይህ ሲሆን የእርስ በርስ ግንኙነታቸው ይላላል፡፡ ችግር ሲፈጠር ኃላፊነት የሚወስድ የለም፡፡ እኛ እየሄድንበት ያለው አሠራር ይህንን ችግር የሚቀርፍና ቤተሰባዊነትን የሚያጠናክር ነው፡፡ ማኅበራዊ ሕይወታቸው የጠነከረ ነው፡፡ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ይፈታል ብለን ተስፋ አድርገን ነው ውባንቺ ፕሮጀክትን የምንተገብረው፡፡

ሪፖርተር፡- ቤት ተከራይቶ ልጆቹን ከሚያሳድጉ እናቶች ጋር በማኖሩ በኩል ከአካባቢው ማኅበረሰብ የሚገጥም ችግር አለ?

ፀደይ፡ ችግር ይገጥመናል፡፡ ቤት መከራየት በጣም ትልቁ ችግር ነው፡፡ ሰዎች ለዚህ ሥራ ማከራየት አይፈልጉም፡፡ ውልና ማስረጃ ሄደው ሐሳብ የሚቀይሩ አሉ፡፡ ልጆቹ ሌባ እንደሆኑ፣ ከጎረቤት እንደማይግባቡ ነው ያለው ግንዛቤ፡፡ ተስማምተው ያከራዩ ደግሞ ከገባን በኋላ ውጡ ማለት፣ ኪራይ ዋጋ መጨመርና በአጠቃላይ ቀድሞ በተሳሳተ መንገድ ፈርጆ መቀመጥ አለ፡፡ በጎረቤት ያሉ ሰዎች ሲሰጉና ሲፈሩ ታያለሽ፡፡ ትምህርት ቤት ደግሞ የእኛ ልጆች ተለይተው ይታያሉ፡፡ የሥጋ እናት ከምታመጣው ልጅና በእኛ ልጆች መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ታያለሽ፡፡ ጥፋት አጥፍተው የእኛ ልጅ ሲቀጣ የሌላኛው ሳይቀጣ ታያለሽ፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ምን መፍትሔ አገኛችሁ?

ፀደይየሚዲያ ስትራቴጂ አውጥተን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ኅብረተሰቡ መማር አለበ፡፡አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር ችግሩ የእኔ አይደለም የምንልበት አይደለም፡፡ የጎዳና ልጆች ቁጥር እየበዛ ነው፡፡ በታዳጊ ወጣት ዕድሜ ውስጥ ያሉትም ይበዛሉ፡፡ መንግሥትም፣ እኛም ተባብረን ብዙ መሥራት አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ የቤት ችግርን ለመፍታት ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ አስገብተናል፡፡ ይሰጡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ለቤት ኪራይ የምንከፍለው ገንዘብ ብዙ ነው፡፡ የአምስት ዓመቱን ብናጠራቅም አንድ ትምህርት ቤት ወይም ክሊኒክ ይሠራልናል፡፡

ሪፖርተር፡- የታላቅ እህትና ወንድም ፕሮግራምም አላችሁ፡፡

ፀደይበሕይወታቸው ምሳሌ መሆን የሚችሉ ሰዎችን ለአንድ ልጅ አንድ ሰው እንመድባለን፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደታላቅ እህት፣ ወንድም፣ አክስትና አጎት ሆነው እንዲያወያዩዋቸው፣ እንዲያዋሯቸው፣ አርአያ እንዲሆኑ፣ አብረው እንዲዝናኑ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ወንድማዊና እህታዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ሥልጠና ሰጥተን ነው የምንሠራው፡፡

ሪፖርተርየጎዳና ሕፃናት ላይ ያለውን ችግር እንዴት መቀነስ ይቻላል?

ፀደይ፡ሕፃናት ላይ ያለው አሠራር መፈተሽ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ሕፃናት መለመኛ እየሆኑ ነው፡፡ እናቶች ይሁኑ አይሁኑ ባልታወቁ ሰዎች ታዝለው ሙሉ ቀን ሲለመንባቸው ማየት ከባድና ሕጋዊ መፍትሔ የሚፈልግ ነው፡፡ ለሙሉ ቀን ታዝሎ ለልመና መሣሪያ የሚሆን ሕፃን ማየት ተለምዷል፡፡ ልጆቹ ሲያድጉ የእናት ቀሚስ ይዘው አብረው ይዞራሉ፡፡ ልጆቹ ከመታዘል ብዛት ከጀርባ መውረድ እንኳን የማይፈልጉ አሉ፡፡ ይህ መቀየር አለበት፡፡ ልመና ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ነው፡፡ ለምንድነው ማዕከላት ኖረው፣ የእምነት ተቋማት ተባብረው ይህንን ድርጊት የማያስቆሙት፡፡ እናቶች ሠርተው ይምጡ፡፡ ሕፃናት ይዞ መለመን ግን በሕግ መከልከል አለበት፡፡ ሱስ ውስጥ የገቡ ልጆች በአግባቡና በቀጣይ መደገፍ አለባቸው፡፡ ከመንገድ የሚነሱ ልጆችም በፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ በሒደት መሆን አለበት፡፡ ሥራው ከባድ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ጎዳና ያሉ ልጆች ታሪካቸው አሳዛኝ ነው፡፡ መገለል፣ መገፋትና ሌሎችም ችግሮች አሉ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...