ዓለም በተለያዩ ችግሮችና ቀውሶች ተወጥራለች፡፡ በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት የፈጠረው የኑሮ ውድነት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጥሎት የሄደው አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲሁም የዓለም መንግሥታት ትኩረት እንዲሰጡትና ለችግሩ መፍትሔ እንዲያበጁ ሲወተውቱ ዓመታት ያሳለፉበት የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ተግዳሮት መሆናቸውን ቀጥለዋል፡፡
በተለይ የአየር ንብረት ለውጥ ጊዜያዊ አለመሆኑና በርካታ የዓለም ሕዝቦችን ለጎርፍ አደጋ፣ ለመሬት መንቀጥቀጥ፣ ለሰደድ እሳት ብሎም ለድርቅና ለረሃብ እያጋለጠ መሆኑ ደግሞ አገሮች ቅድሚያ አጀንዳ እንዲያደርጉ አስገድዷል፡፡
ሆኖም በተለይም የበለፀጉና ለአየር ንብረት ለውጡ መከሰት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት መንግሥታት፣ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ፣ የአየር ንብረት ለውጡን ለመቀልበስ ብሎም የችግሩ ሰለባ የሆኑትን ደሃና በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን ለመደገፍ እንቅፋት ሆኗል፡፡
ከዚህ ቀደም በተለያዩ አገሮች በተደረጉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔዎች ችግሩን ለመቀልበስ የካርበን መጠን ልቀት መጠንን ለመቀነስና የችግሩ ሰለባ የሆኑ አገሮችን ለመደገፍ የተገቡ ቃሎችም በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረጉ አይደሉም፡፡
እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ይረዳል የተባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ – ኮፕ 27 ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በግብፅ የተጀመረ ሲሆን፣ ለሁለት ሳምንታት የሚዘልቅ ይሆናል፡፡
በግብፅ ሻርም አል ሼክ በመካሄድ ላይ ባለው የኮፕ 27 ንግግር ያደረጉት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ፣ ‹‹ችግሩን ለመግታት በጊዜ ወደ ትግበራ የምንገባበት ነው፣ ወደኋላ ለማፈግፈግ መንገድ የለም፣ ያሉንን መልካም አጋጣሚዎች በማሳለፍ የትውልዱን፣ የልጆቻችንንና የልጅ ልጆቻችንን የወደፊት ኑሮ እያባከንን ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ ኒውስ እንደዘገበው፣ በአየር ለውጥ ምክንያት የዓለም ሕዝቦች እየጨመረ ለመጣው የተፈጥሮ አደጋ ሕይወታቸውን እያጡ፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላርም እየወደመ ነው፡፡
በናይጄሪያና በፓኪስታን እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው ጎርፍ አውሮፓ፣ አሜሪካና አፍሪካ የተከሰተው ድርቅና ሦስት አኅጉሮችን የመታው ሙቀት የዘንድሮን የከፋ የአየር ንብረት ለውጥ መከሰቱን የሚያሳዩ ናቸው፡፡
የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ይበልጥ እየተጎዱ ለሚገኙ ደሃ አገሮች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ከዚህ ቀደም የገቡትን ቃል በአግባቡ ለመፈጸም ያልቻሉ ሲሆን፣ በጉባዔው የተገኙት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ የኮፕ 27 ጉባዔ ተቋማዊ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ አሠራር እንዲኖር መስማማት አለበት ብለዋል፡፡
ሀብታም አገሮች የወደፊት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል አሠራር ለመገንባትና በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመደገፍ በዓመት 100 ቢሊዮን ዶላር መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ለመፈጸም የተገባው ቃል አልተተገበረም፡፡
የኮፕ 27 ፕሬዚዳንትና የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ፣ ‹‹ባለፉት ስምንት ዓመታት የተከሰተው ሙቀት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም የዓለም ሕዝቦችን የፈተነ በመሆኑ ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
ሳይንቲስቶች እንደሚገምቱት፣ የኢንዱስትሪ አብዮት ከመቀጣጠሉ በፊት ከነበረው የዓለም ሙቀት መጠን አሁን ላይ በ1.15 ሴልሺየስ ጨምሯል፡፡ ይህም የባህር ጠለል እንዲጨምር፣ የበረዶ ግግር እንዲቀልጥና ዓለም በከባድ ሙቀት እንድትመታ አድርጓል፡፡
ሆኖም ችግሩን ለመቅረፍ በየዓመቱ በሚካሄደው ጉባዔ የሚገቡ ቃሎች እምብዛም አይፈጸሙም፡፡ ዓናም በግላስኮው በነበረው የኮፕ 26 ጉባዔ የተለያዩ ቃሎች ተገብተው የነበረ ቢሆንም አልተፈጸሙም፡፡ ከተገቡ ቃሎች መካከል በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የችግሩ ግንባር ቀደም ተጠቂ በመሆናቸው፣ ቀድሞ የተገቡ የገንዘብ ድጋፎች እንዲፈጸሙ የሚል ነበር፡፡
አፍሪካ ወደ አየር የምትለቀው የካርበን ልቀት መጠን እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም፣ ልቀቱ እየጎዳቸው ከሚገኙ አኅጉሮች ከቀዳሚዎቹ ትመደባለች፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ለመሸከም የሚያስችል ኢኮኖሚ ያልገነቡት፣ በተለይም ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮች ደግሞ ለአየር ንብረት ለውጡ ተጋላጭ ሆነው እያፈራረቀ በሚከሰተው ጎርፍና ድርቅ እየተመቱ ነው፡፡
አፍሪካውያን ለችግሩ መፈጠር ያላቸው አስተዋጽኦ ኢምንት ሆኖ በችግሩ መጎዳታቸው፣ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በየዓመቱ ሲደረግ የሚነሳ አጀንዳ ቢሆንም ችግሩ አልተፈታም፡፡ የችግሩ ሰለባዎችም የአየር ንብረት ለውጥን የሚያስከትለው የጋዝ ልቀት ምን እንደሆነ የማያውቁ፣ ይህንን የሚያስከትሉ ቴክኖሎጂዎችን የማይጠቀሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ ዓመታት ያስቆጠረውና በየዓመቱ የሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ኮፕ 27 ጉባዔ ከመካሄዱ አስቀድሞም ከ42 የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ልዑካን ቡድኖችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ባለሥልጣናት በተገኙበት በጋቦን ሊበርቪል የአፍሪካ የአየር ንብረት ሳምንት ጉባዔ ከነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ማካሄዳቸው ይታወሳል፡፡
የአፍሪካ የአየር ንብረት ሳምንት ጉባዔ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ኮፕ 27 ጉባዔ ላይ ተመሳሳይ አጀንዳ ይዘው እንዲቀርቡ የሚያስችልና አፍሪካውያን የአየር ንብረት ለውጥን በውጤታማነት ለመዋጋት ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት አንድ የሚሆኑበት መድረክ ነው ተብሎም ነበር፡፡
በወቅቱ በግብፅ የሚካሄደው ኮፕ 27 የአፍሪካ ኮፕ ተብሎ እየተገለጸ ሲሆን፣ ጉባዔው አፍሪካ ወደፊት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርስባትን ጉዳት ለመቀነስ አሠራሮች ቅርፅ የሚይዙበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸው አስተዋጽኦ ጥቂት እያስተናገዱ ያሉት ጉዳት ደግሞ ከፍተኛ የሆኑባቸው 54ቱ የአፍሪካ አገሮች ድርቅ፣ ከባድ ጎርፍና ስደት እያስተናገዱም ነው፡፡
በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያና በኬንያ አንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ እያስከተለ ያለው ጉዳት እየተባባሰ ነው፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት እንደሚለውም፣ ኬንያ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያ ከባድ ለሆነ ሰብዓዊ ቀውስ እየተጋለጡ ነው፡፡
በሚያዝያ 2014 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ በካዋዙሉ ናታል አካባቢ የተከሰተው ከባድ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት 450 ሰዎች እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአገሪቷ ታሪክ ከፍተኛ የተባለው ጎርፍ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሲያፈናቅል፣ ከ12 ሺሕ በላይ ቤቶችን አጥለቅልቋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ ናይጄሪያና ሱዳን በጎርፍ ተመተዋል፡፡
በአፍሪካ በርካታ ዜጎች ከግጭትና ከእርስ በርስ ጦርነት ባለፈ የአየር ንብረት ለውጡ እያስከተለ በሚገኘው ድርቅና ጎርፍ ምክንያት ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ ነው፡፡
የዓለም ባንክ እንደሚለው፣ እ.ኤ.አ. በ2050 ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ሕዝቦች ውስጥ 86 ሚሊዮን እንዲሁም ከሰሜን አፍሪካ 19 ሚሊዮን ሕዝቦች የአየር ንብረት ለውጡ እያስከተለ ባለው አውሎ ንፋስና ማዕበል፣ ከፍተኛ ሙቀት፣ ድርቅና ከባድ ጎርፍ ምክንያት ከቀዬአቸው ይፈናቀላሉ፡፡
ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮች ሙቀት መጨመርና በረሃማ መሆን፣ የባህር ዳርቻዎች በአግባቡ አለመገንባትና ኅብረተሰቡ በግብርና ላይ የተመረኮዘ መሆን ለአየር ንብረት ለውጡ ይበልጥ ተጋላጭ ያደርገዋል፡፡
በዓለም ከሚመዘገበው የግሪን ሐውስ ልቀት ከመላ አፍሪካ የሚመነጨው አራት በመቶ ያህል ነው፡፡ አፍሪካ የካርበን ልቀቷ በጣም ጥቂት ቢሆንም፣ ምዕራባውያኑ በሚለቁት ከፍተኛ የካርበን ልቀት ምክንያት በሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ 118 ሚሊዮን ደሃ አፍሪካውያን ለከፋ ድርቅ፣ ጎርፍና ሙቀት ተጋልጠዋል፡፡ በ2030 ደግሞ ችግሩ ይብሳል፡፡
ከፍተኛ የካርበን ልቀት ያላቸው ሀብታም አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየተጎዱ ያሉ አገሮችን ኢኮኖሚ ለመደገፍ በየዓመቱ 850 ቢሊዮን ዶላር ያህል መስጠት አለባቸው፡፡
ከአሥር ዓመት በፊት ሀብታም አገሮች ደሃ አገሮችን ለመደገፍ በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት መስማማታቸውም ይታወሳል፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ ሀብታም አገሮች ደሃ አገሮች በአየር ንብረት ለውጡ ሳቢያ ከሚመጣባቸው መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ቀውስ ለማውጣት በዓመት ለመስጠት ቃል የገቡትን 100 ቢሊዮን ዶላር አልሰጡም፡፡
በአፍሪካ ያሉትን ጨምሮ በርካታ በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮችም ለታዳሽ ኃይልና ለኢንዱስትሪዎች የሚውለውን የድንጋይ ከሰል መተኪያ የሚሆን አቅም ለመገንባት ከሀብታም አገሮች ይለቀቃል ተብሎ የተገባው ገንዘብ ባለመለቀቁ ችላ ብለውታል፡፡
በአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ የተነሱት ሐሳቦች በኮፕ 27 ይነሳሉ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች የምዕራባውያን ተወካዮች፣ አገሮቻቸው የካርበን ሽያጭ፣ የአረንጓዴ ቴክኖሎጂንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ኢንሺየቲቭ እንዲያነሳሱ ይወተውታሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡