በትግራይ ክልል ሽሬ፣ አክሱም፣ ሽራሮና በሌሎች ቦታዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እያቀረበ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከጦርነት ቀጣና ነፃ በወጡ የአማራና የትግራይ ክልል አካባቢዎች ከጥቅምት 20 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እየቀረበ ይገኛል፡፡
ራያ፣ አላማጣ፣ ሽሬ፣ አክሱም፣ ሰግደም፣ ኮረምና ሽራሮ ድጋፍ ከተደረገላቸው አካባቢዎች ውስጥ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በሁለቱም ክልሎች ከ150 ሺሕ ኩንታል በላይ ስንዴ ከ370 ሺሕ በላይ ወገኖች መድረሱን፣ ከ952 ሺሕ በላይ የሚያጠቡ እናቶች፣ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮችና አቅመ ደካሞች ደግሞ 14,292 ኩንታል አልሚ ምግብ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
የተላከው ስንዴና አልሚ ምግብ በገንዘብ ሲተመን 340.5 ሚሊዮን ያህል ብር እንደሚገመትና በቀጣይም በሌሎች የሁለቱ ክልሎች አካባቢዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡
የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚላከውን አቅርቦት ለማሳለጥ ሲል በመጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. የወሰደውን ግጭት የማቆም ውሳኔ (Humanitarian Truce) ተከትሎ የረድኤት ድርጅቶች ወደ ክልሉ የሚልኩትን የሰብዓዊ ዕርዳታ በአየርና በየብስ ማጓጓዝ እንዲችሉ መፍቀዱ ይታወሳል፡፡
በዚሁ መሠረት ከመጋቢት 2014 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ድረስ አጋር አካላት በክልሉ ለሚያከናውኑት የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትና ድጋፍ ሥራ ማስኬጃና ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል የብር 1.99 ቢሊዮን የጥሬ ገንዘብ ዝውውር በUNHAS የመንገደኞች አውሮፕላን አማካይነት፣ የተመጣጠነ ምግብን ጨምሮ ከ205 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ በአየርና በየብስ ተጓጉዟል፡፡
ምግብ ነክ ያልሆኑ የጤና፣ የግብርና ዘርና ማዳበሪያን ጨምሮ የትምህርት፣ የመጠለያ፣ መመገቢያ፣ የአልባሳት፣ የፕሮቴክሽን፣ የውኃና የግል ንጽህና መጠበቂያና ሌሎች ከ28 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ የዕርዳታ ቁሳቁሶች በአየርና በየብስ የተላኩ ሲሆን፣ ከ2.5 ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ በየብስ ትራንስፖርት መጓጓዙን የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡