ባለፈው ሳምንት መገባደጃ በአፍሪካ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ የተለያዩ አገሮች በተካሄዱ የማራቶን፣ የግማሽ ማራቶን እና የአገር አቋራጭ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአብዛኛው በድል ተወጥተዋል፡፡
በዓለም አትሌቲክስ የላቀ ደረጃ ያለው የኒውዮርክ ማራቶን ባለፈው እሑድ የተካሄደ ሲሆን በሁለቱም ጾታዎች ቀዳሚ የሆኑት ኬንያውያን ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያውያኑ 2ኛ እና 3ኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡ በወንዶች ምድብ ሹራ ቂጣታ በ2:08:54 ሰዓት 2ኛ ሲወጣ በሴቶች ጎተይቶም ገብረሥላሴ በ2:23:39 ሰዓት 3ኛ ሆና አጠናቃለች፡፡
በሌላ በኩል በቱርክ-ኢስታንቡል ማራቶን፣በሴቶች ምድብ ከአንድ እስከ ሦስት ተከታለው የገቡት ሲጫሌ ደለሳ (2:25:54)፣ መሠለች ጸጋዬ (2:29:01) እና እታለማሁ ስንታየሁ (2:31:38) ናቸው፡፡ በወንዶች ምድብ፣ ታደሰ ተመቻቹ (2:11:58) እና ዓለሙ ደቻሳ (2:12:15) አምስተኛና ስምንተኛ ሆነው ፈጽመዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ስዌቶ ማራቶን በወንዶች ምድብ ዳባ ኢፋ (2:18:58) እና ጋዲሳ በቀለ (2:19:27) አንደኛና ሁለተኛ ሲወጡ፤ በሴቶች ምድብ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ የወጡት ኢትዮጵያውያቱ ጫልቱ በዶ (2:40:56)፣ ዓመለወርቅ ፍቃዱ (2:43:14) ትነበብ ነብዩ (2:44:32) መሆናቸውን ዲደብሊው ዘግቧል።
በስዊዘርላንድ የጄኔቭ 20 ኪሎ ሜትር ውድድር ያሸነፈችው ሄለን በቀለ ስትሆን የወሰደባት ጊዜ 1:06:3 ሰዓት ነው፡፡ በተያያዘ ዜና በስፔን ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ፉክክር ያሸነፉት በወንዶች ምድብ አዲሱ ይሁኔ፣ በሴቶች ምድብ መሰሉ በርሔና ዘርፌ ወንድማገኝ ሁለተኛና ሦስተኛ ወጥተዋል፡፡