Thursday, September 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል አፍሪካ ጁስ ኩባንያ ላይ ባደረሱት ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ

ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል አፍሪካ ጁስ ኩባንያ ላይ ባደረሱት ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ

ቀን:

ከአዲስ አበባ በ175 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአርሲ ዞን ጀጁ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ‹‹አፍሪካ ጁስ ቲቢላ አክስዮን ኩባንያ›› ላይ የ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት የስምንት ወር ሕጻን ልጅን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ፡፡

ታጣቂዎቹ ቅዳሜ ጥቅምት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት ላይ በከፈቱት ጥቃት፣ የኩባንያው ጁስ መጭመቂያ ፋብሪካ በሚገኝበት መንበር ሕይወት እርሻ ግቢ ውስጥ የሚኖሩ አራት ሠራተኞችና ታጣቂዎቹ ከአካባቢው ይዘው ያመጧቸውን አምስት ሰዎች መግደላቸውን የኩባንያው ሠራተኞችና አንድ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኃላፊ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

ለኩባንያው ሠራተኞች የሕክምና አገልግሎት የሚሰጠውና በአዳማ ከተማ የሚገኘው መድኅን ቤዛ ሆስፒታል ደግሞ ጥቃት የደረሰበት አንድ ግለሰብ ወደ ሆስፒታሉ እየመጣ ሕይወቱ ማለፉንና በጥይት የተመታ ሌላ የኩባንያው ሠራተኛ ደግሞ አሁንም በሕክምና ላይ እንደሚገኝ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

የኩባንያው ሠራተኞች እንደሚገልጹት ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የከፈቱት ከምሽቱ  1፡45 ሰዓት አካባቢ ሲሆን፣ በኩባንያው ግቢ ውስጥ የሚገኙ ቤቶችን ‹‹ገንጥለው›› በመገባት ዘረፋና ጥቃት ፈጽመዋል፡፡

የኩባንያው ሠራተኛ የሆነች ሴትና የስምንት ወር ልጇ እንዲሁም ሌሎች ወንድና ሴት ሠራተኞች በታጣቂዎቹ ጥቃት ሕይወታቸው እንዳለፈ በኩባንያው ግቢ ውስጥ ነዋሪ የሆኑና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የፋብሪካው ሠራተኞች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በግቢው ውስጥ የተገደሉት ሌሎች አምስት ወንዶች ታጣቂዎቹ ከአካባቢው ይዘው በመምጣት ግቢ ውስጥ እንደገደሏቸው ሠራተኞቹ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በኩባንያው ውስጥ ያለውን ድርሻ በሚያስተዳድረው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ውስጥ ኃላፊ የሆኑ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ኃላፊ አራቱን የኩባንያው ሠራተኞች ጨምሮ አምስት ሰዎች ስለመገደላቸው ሪፖርት መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡

ጥቃት ከደረሰባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው የኩባንያው የሕክምና ባለሙያ፣ ጥቃቱ በደረሰበት ቅዳሜ ዕለት አዳማ ከተማ ወደሚገኘው መድኅን ቤዛ ሆስፒታል መግባቱን አንድ የሆስፒታሉ ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ኃላፊዋ በሕክምና ላይ የሚገኘው የኩባንያው ሠራተኛ በጥይት ጥቃት እንደደረሰበት ገልጸው፣ የጉዳቱን መጠን በትክክል ለመናገር እንደሚቸገሩ አስረድተዋል፡፡

‹‹ወደ እኛ እያመጡት ሕይወቱ ያለፈ አንድ ሰው አብሮ መጥቶ ነበር›› ያሉት ኃላፊዋ፣ ሕይወቱ ያለፈው ወንድ ግለሰብ አስከሬን መመለሱንና ሆስፒታሉ ሌሎች ሕይወታቸው ያለፈ ሠራተኞችን አለመቀበሉን ተናግረዋል፡፡

በጥቃቱ የተገደሉት እናትና ልጅ ቀብራቸው በአዳማ ከተማ ሲፈጸም፣ የሌሎቹ ሠራተኞች ቀብር ፋብሪካው በሚገኝበት ጀጆ ወረዳና በአርቦዬ ከተማ መፈጸሙን ሠራተኞቹ ገልጸዋል፡፡

ታጣቂዎቹ ካደረሱት በሰዎች ላይ ካደረሱት ጥቃት በተጨማሪ የሠራተኞቹ መኖሪያ ‹‹ሙሉ በሙሉ›› መዘረፉንና ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ሠራተኞቹ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው የሚገኙ ፀጥታ ኃይሎች ፋብሪካው ግቢ ውስጥ የደረሱት ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ሰለሞን ሪፖርተር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጡ ከተናገሩ በኋላ፣ ዘገባው እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ለተደረገላቸው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ምላሽ አልሰጡም፡፡

 የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሙሳ ፊሮ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳና ኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ለተደረገላቸው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪና አጭር የጽሑፍ መልዕክት ምላሽ አልሰጡም፡፡

አፍሪካ ጁስ ቲቢላ አክስዮን ኩባንያ ዋና ፋብሪካው የሚገኝበት መንበር ሕይወት እርሻን ጨምሮ ትፍሰ ገነትና ደጋጋ የተባሉ እርሻዎች አሉት፡፡ በኩባንያው ድረ ገጽ ላይ ያለው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ኩባንያው አንድ ሺሕ ሔክታር የሚጠጋ የእርሻ መሬት አለው፡፡

በእርሻው ላይ ፓሽን ፍሩት፣ ማንጎ፣ ፓፓዬ፣ ብርቱካንና ሌሎች ፍራ ፍሬዎች የሚመረቱ ሲሆን፣ ኩባንያው በፋብሪካው ማንጎና ፓሽን ፍሩን እየጨመቀ ጁስ ለሚያመርቱ ሌሎች ኩባንያዎች በግብዓትነት ያቀርባል፡፡ በተጨማሪም ጤፍ፣ ስንዴና ጥርጣሬዎች በእርሻው ላይ እንደሚመረቱ ከኩባንያው ሠራተኞች የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

እ.አ.አ እስከ 2009 ድረስ እርሻዎቹ በመንግሥት ሥር የነበሩ ሲሆን፣ ከ2009 ጀምሮ አፍሪካ ጁስ (africaJUICE BV) የተባለ የኔዘርላንድ ኩባንያ 88 በመቶውን ድርሻ ይዞ እየሠራ ይገኛል፡፡ ቀሪው የመንግሥት ድርሻ የሚተዳደረው በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...