የማንኛውም ጦርነት መደምደሚያ በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረግ ስምምነት እንደሆነ ዓለም የሚያውቀው ታሪክ ነው፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑ ችግሮቻቸውን መፍታት ባለመቻላቸው ምክንያት የሚፈጠር ጦርነት፣ ለዕልቂት የሚዳርገውም ሆነ ሕይወትን የሚያመሰቃቅለው ንፁኃንን እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ ከተካሄዱ ጦርነት እጅግ በጣም የከፋውና 50 ሚሊዮን ሕዝብ ያለቀበት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዕልባት ያገኘው፣ አሸናፊዎቹ የወቅቱ ኃያላን አገሮች ያልታ ላይ ባደረጉት ስምምነት እንደሆነ ታሪክ ይናገራል፡፡ ናዚ ጀርመን፣ ፋሽስት ጣሊያንና ሚሊታሪስት ጃፓን እጃቸውን ከሰጡ በኋላ ነው የሶቪዬት ኅብረት ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ስታሊን፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልትና የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል ታሪካዊውን የያልታ ስምምነት ያደረጉት፡፡ በወቅቱ በተለይ አውሮፓ በጦርነቱ ምክንያት ምስቅልቅሉ ወጥቶ ስለነበር፣ መልሶ የመገንባቱ ሥራ ነበር ትልቅ ትኩረት የተሰጠው፡፡ ጦርነት አልቆ በስምምነቱ መሠረት ሰላም ማስፈን ሲጀመር፣ በጦርነቱ የተጎዱ ሰዎችንና መሠረተ ልማቶችን መልሶ ማቋቋምና መገንባት የአገሬው ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡
በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የደረሰው ጥፋትና ቀውስ መታከም የሚኖርበት በኢኮኖሚ ማገገም እንደሆነ ብዙዎችን ያስማማል፡፡ ወገኖቻቸውን በጦርነቱ ምክንያት ያጡና ንብረታቸው የወደመባቸው ወገኖች፣ ከሥነ ልቦናዊ ድጋፍ በተጨማሪ መልሰው መቋቋም አለባቸው፡፡ ተጠፋፍተው የነበሩ ወገኖች ቤተሰብ ከቤተሰብ፣ ዘመድ ከዘመድ፣ ወዳጅ ከወዳጅ በፍጥነት እንዲገናኙ መደረግ ይኖርበታል፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል ዕጦት ምክንያት ጨለማ የዋጣቸው ወገኖች ብርሃን ማግኘት አለባቸው፡፡ ሥራቸውን ያጡ፣ ገንዘባቸውን ከባንክ ማውጣት ያልቻሉ፣ ገበያ ባለመኖሩ ምግብ ማግኘት ያዳገታቸው፣ መታከሚያ በማጣት ከከባድ ሕመም ጋር የሚታገሉ፣ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ከትምህርት ገበታ የተፈናቀሉና የተለያዩ ችግሮች ውስጥ የወደቁ ወገኖች በተቻለ ፍጥነት ወደ ቀድሞው ሕይወታቸው መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡ የእነዚህ ምስኪን ወገኖች ችግር ምንም የማይመስላቸው ኃይሎች አሁንም ጦርነቱ እንዲቀጥል እየወተወቱ ስለሆነ በቃ መባል አለበት፡፡ ከጦርነቱ ሥፍራ በርቀት ላይ ሆነው በሕዝብ ስም የሚቆምሩ በተባበረ ድምፅ ይገቱ፡፡
የሰላም ስምምነቱ በተሳካ መንገድ እንዲከናወን የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆን አለበት፡፡ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ከዚህ ቀደም የነበረው የጀብደኝነት መንፈስ ሲሰበር ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ከአጉል ባህሪ ተላቆ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ተግባር ማከናወን ነው፡፡ በአውዳሚው ጦርነት ምክንያት ወገኖቻቸውን በሞት የተነጠቁ፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ የወደቁ፣ ንብረታቸው የወደመባቸው፣ በረሃብ አለንጋ የሚገረፉ፣ በሕክምና ዕጦት ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ ላይ ያሉ፣ በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግሩ ሰቆቃዎች የደረሱባቸውና ተስፋ የጨለመባቸውን ወገኖች በፍጥነት መታደግ ነው፡፡ ምቾት ላይ ሆነው ሥቃይ ውስጥ ባሉ ወገኖች ስም የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊነት የሚቃወሙ ኃይሎች፣ ፀባቸው ከተቀናቃኞቻቸው ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንደሆኑ ይወቁት፡፡ ከዚህ በኋላ የጦር መሣሪያዎች ላንቃቸው ተዘግቶ ሰላም መስፈን አለበት እንጂ፣ የጥቂቶችን የጥጋብ አጀንዳ ለማስፈጸም ሲባል ንፁኃን መማገድ የለባቸውም፡፡ በንፁኃን ዕንባና ደም መነገድ ይብቃ፡፡
ይህ ወቅት በኢትዮጵያ ምድር ዘለቄታዊ ሰላም ለማስፈን የሚረዱ ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ መነጋገሪያ እንጂ፣ በአሸናፊነትና በተሸናፊነት ስሜት ትከሻ የሚያሳብጡበትና አንገት የሚደፉበት እንዳልሆነ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ አሁን አሸናፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲናፍቀው የነበረ ሰላም እንጂ፣ ለአገርና ለሕዝብ የማይጨነቁ ራስ ወዳዶች የሚያስተጋቡት ከንቱ ወሬ አይደለም፡፡ በጦርነቱ የደቀቁ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ምስኪን ኢትዮጵያውያን ዕፎይታ እንዲያገኙ ማድረግ ሲገባ፣ የተለመደውን ጀብደኛ መንገድ ለማስቀጠል የሰላም ስምምነቱን ማወክ አስነዋሪ ነው፡፡ ይህንንነ አውዳሚ ጦርነት የቀሰቀሰው የጥቂቶች ዕብደትና ጥጋብ እንደነበረ ማንም አይዘነጋውም፡፡ አሁንም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ጦርነት ጠማኞች የሰላሙን ተስፋ እንዳያጨናግፉ፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በኅብረት ድምፃቸውንና ትብብራቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይልቁንም በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍና መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ኢኮኖሚው አገግሞ የፖለቲካውን ስብራት እንዲጠግን፣ በግራም ሆነ በቀኝ ጎራዎች የተሠለፉ በሙሉ ይተባበሩ፡፡
የፖለቲካ ልሂቃን ከፀጉር ስንጠቃ ውስጥ ወጥተው ኢትዮጵያ በትክክል የምትመራበት ሥርዓት መሠረት እንዲይዝ ዕገዛ ያድርጉ፡፡ በፖለቲካው ምኅዳር ዙሪያ የሚያንዣብቡ ልሂቃንም ካለፉት ስህተቶች በመማር ለመልካም ተግባራት አርዓያ ሁኑ፡፡ በተለይ በፖለቲካው አካባቢ በጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ ተወዛግባችሁ የምታወዛግቡ ወገኖች፣ ከምንም ነገር በላይ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ያሳስባችሁ፡፡ ኢትዮጵያ የግለሰብ ወይም የቡድን ጥጋበኞች መፈንጫ እንዳትሆንና የፖለቲካ ምኅዳሩ ሥርዓት እንዲኖረው፣ በጨዋነትና በሥነ ምግባር ለመንቀሳቀስ ከፍተኛ ጥረት አድርጉ፡፡ በአድርባይነትና በአስመሳይነት ከመጣ ከሄደው ጋር እየተለጠፋችሁ የኢትዮጵያን ሕዝብ በኑሮ ውድነት መከራ የምታሳዩ አልጠግብ ባይ ነጋዴዎች፣ በዚህ አገር ከፍተኛ ዕገዛ በምትፈልግበት ወቅት ከቀልባችሁ ሆናችሁ መልካም ነገሮችን ለማከናወን ተዘጋጁ፡፡ በደሃ ሕዝብ ላይ ከመጠን በላይ ትርፍ እያጋበሱ በምቾት ለመኖር መሞከር ለጊዜው ቢያስደስትም፣ በታሪክና በመጪው ትውልድ የሚያስረግም ድርጊት መሆኑን ተገንዘቡ፡፡ ግብር ማጭበርበር፣ ጥራቱን ያልጠበቀ ምርት መሸጥና በስግብግነት መክበር የዝቅጠት ማሳያ ነው፡፡
ከአገርና ከሕዝብ የሚቀድም ምንም ነገር መኖር የለበትም፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ ሌሎች ክብራቸው፣ ዝናቸው፣ ጥቅማቸውም ሆነ ሌላ ፍላጎታቸው ከአገርም ሆነ ከሕዝብ በላይ ሊሆን አይገባም፡፡ ይልቁንም ክብርም ሆነ ዝና ለአገር ጥቅምና ለሕዝብ ደኅንነት አገልጋይ ይሁን፡፡ በዚህ መንፈስ ራስን መግራት ሲቻል ጥጋብና ዕብሪት ይበርዳሉ፡፡ ሥርዓተ አልበኝነትና ሕገወጥነት ይወገዳሉ፡፡ ራስን እንደ ተራራ እየቆለሉ ሌላውን መናቅ ነውር ይሆናል፡፡ ስግብግብነትና ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ያስነውራል፡፡ አገርና ሕዝብ ሲከበሩ የሕግ የበላይነት ይሰፍናል፡፡ ምርጫ ማጭበርበር፣ ተፎካካሪን ማሰቃየት፣ የሕዝብ ሀብት መዝረፍ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን መርገጥ፣ ፍትሕ መንፈግ፣ በደሃ ዕንባና ደም ማሾፍና የመሳሰሉት አሳፋሪ ድርጊቶች ይመክናሉ፡፡ ስለዚህ ከጦረኝነት አባዜ በመላቀቅ ሰላም ማስፈንና ለአገርና ለሕዝብ ዕፎይታ ለመስጠት ራስን መግራት የግድ ነው፡፡ በንፁኃን ዕልቂትና በአገር ውድመት ለማትረፍ መሞከር አያዋጣም፡፡ የተጀመረው የሰላም ማስፈን ሒደት ተጠናክሮ ይቀጥል፡፡ የግለሰቦችና የቡድኖች ትከሻ መለካካት ያብቃ፡፡ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ አገርና ሕዝብ ዕፎይ ይበሉ!