ሦስት ግዙፍ ብሔራዊ ሙዚየሞች ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓም. ከቱሪዝም ሚኒስቴር የቀረበለትን የ2015 ዓ.ም. የዘርፉን ዕቅድና የመጀመርያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ካዳመጠ በኋላ፣ ሁለቱንም ውደቅ አደረገ፡፡ ሚኒስቴሩ የዓመቱን ዕቅድና የሩብ ዓመቱን አፈጻጸም ሪፖርት እንደገና አዘጋጅቶ በማኔጅመንት አፀድቆ እንዲያመጣ ታዟል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሚኒስቴሩ ሦስት ዓይነት የተለያዩ ግቦችን ማቅረቡና በሰነድ የቀረበው ሪፖርትና ገለጻ የተደረገው ልዩነት ስላለው ለመገምገም አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም ሚኒስቴሩ ያቀረበው ዕቅድ ሌላ ነው፡፡ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር በኩል ያቀረበው የዘርፉ ዕቅድ ሌላ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስቴሩ ያቀረበው ዕቅድ የተለየ ነው፡፡ የትኛው ላይ ሆነን እንገምግም? ይህ የወደቀ ወይም ደካማ ብዙ የሚቀረው ሪፖርት ነው፤›› ሲሉ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር) ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው አባልና ከደብረ ማርቆስ የተወከሉት የብልፅግና ፓርቲ አባል ሚኒስቴሩን ተችተዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግርማ ግን ሪፖርቶቹን ሲያቀርቡ፣ ሰነዶቹ ማለፍ ያለባቸውን ሁሉ ሒደቶች ያለፉ መሆናቸውን ጠቅሰው ነበር፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር ከቀድሞ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተገንጥሎ የቱሪዝም ሚኒስቴር ተብሎ እንደገና ከተቋቋመ ገና አንድ ዓመቱ ሲሆን፣ የራሱ የቱሪዝም ዘርፉ ለብቻው የ10 ዓመት ዕቅድ እንደሌለው፣ ነገር ግን ከሦስት ዓመት በፊት የወጣ የባህልና የቱሪዝም የ10 ዓመት ዕቅድ እንዳለ ተጠቅሷል፡፡ ይሁንና ሚኒስቴሩ የ2015 ዓ.ም. ዕቅድ ከ10 ዓመታትና ከአምስት ዓመታት የቱሪዝም ዕቅዶች የተቀዳ ነው ማለታቸውም በቋሚ ኮሚቴው ተተችቷል፡፡
‹‹ቱሪዝም ሚኒስቴር በክልሎችም አደረጃጀት አልፈጠረም፤›› የተባለ ሲሆን፣ ዕቅዱ ከታች ሳይመጣ እንዴት በፌዴራል ደረጃ ብቻ ሊያወጣ ይችላል ተብሎ ተጠይቋል፡፡
‹‹ተቋማዊ አደረጃጀቱ ጉራማይሌ ነው፡፡ በክልሎች የተለያየ ነው፡፡›› ክልሎች እየጠየቁ ያሉት፣ ‹‹የቱሪዝም ሚኒስቴር አለ ወይ እያሉ ነው፤›› ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው አንድ አባል ጠይቀዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው አንዳንድ በሚኒስቴሩ የተጀመሩ ሥራዎችን ቢያበረታታም፣ ለምሳሌ የሆቴልና አስጎብኚ ድርጅቶች ለሚያቀርቡት የድጋፍ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አለመቻሉን እንደ ክፍተት ጠቅሰዋል፡፡ ለቅርስ ጥበቃ የሚመደቡ ገንዘቦች አጠቃቀም ላይም ጥያቄ ተነስቷል፡፡ በፀጥታ ችግር ምክንያት ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ከሰቆጣ፣ ላሊበላና ትግራይ ሰነዶች ስለጠፉ ሊገኝ እንዳልቻለ ሊታወቅ ባለመቻሉ መሠረዝ እንዳለበት የቅርስ ባለሥልጣን ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል ግን ለቋሚ ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት ውስጥ ያልተካተቱ ትልልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች በዕቅድ ተይዘው እየተሠሩ እንደሆነ ሪፖርተር ለመረዳት ችሏል፡፡
አዲስ ‹‹ብሔራዊ ሙዚየም›› ራሱን የቻለ የሰው ዘር አመጣጥ ሙዚየምና ‹‹ሉሲ ሙዚየም› የተሰኙ ግዙፍ አገራዊ ቅርስ ፕሮጀክቶች ግንባታ በዝግጅት ሒደት ውስጥ እንዳሉ፣ የቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፊሰር አበባው አያሌው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ለሚኒስቴሩ ተጠሪ ነው፡፡
አዲሱ ብሔራዊ ሙዚየም በአዲስ አበባ ሐምሌ 19 መናፈሻ ቦታ ላይ የታሰበ ሲሆን፣ ከዓባይ ግድብም የማይተናነስ ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡ ብሔራዊ ሙዚየሙ በአዋጅ የሚቋቋም ሲሆን የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር የበላይ ጠባቂ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ብሔራዊ ሙዚየም ተበታትነውና በቦታ እጥረት አንድ ላይ የታጎሩ፣ እንዲሁም ያልተሰበሰቡ የአገሪቱ ቅርሶች መገኛ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዝኃነት በሙዚየሙ ከሚንፀባረቁ ጽንሰ ሐሳቦች አንዱ ነው፡፡
ሌላው ግዙፍ ፕሮጀክት ‹የሰው ዘር አመጣጥ ሙዚየም› ሲሆን፣ በዕቅድ ከተያዘ 15 ዓመታት እንዳለፉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ሙዚየም አምስት ኪሎ ከነባሩ ሙዚየም ፊት ለፊት 4 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት የተከፈለበት ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር ለባለሥልጣኑ ሊያስረክብ አልቻለም፡፡ ለዚህ ሙዚየም ግንባታ ቀድሞ የተደረገው ጥናትና ዋጋ የቆየ በመሆኑ እየተከለሰ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሦስተኛው ትልቅ ፕሮጀክትና ባለሥልጣኑ በዕቅድ የያዘው የሉሲ ሙዚየም ሲሆን፣ ይህም ሉሲ በተገኘችበት ሀዳር በተባለው ሥፍራ አፋር ውስጥ ይገነባል፡፡ ለዚህኛውም የተሠራው ጥናት እየተከለሰ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ምንም እንኳን መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ከለውጡ ወዲህ መሻሻሉ ቢገለጽም፣ በጀት ለእነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መልቀቅ ላይ መዘግየቱ ተነግሯል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ የብዙ ቅርሶችና የግዙፍ ታሪክ ባለቤት ናት፡፡ ይህንን የሚመጥን ሙዚየም ያስፈልጋታል፡፡ ምንም የሌላቸው አገሮች ሙዚየም ገንብተው ገንዘብ ይሰበስባሉ፡፡ መንግሥት እነዚህን ግዙፍ ሙዚየም ግንባታዎች ቢያስጀምር ከአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ገንዘብ ሰብስቦ ለማጠናቀቅ ቀላል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እነዚህ ሙዚየሞች ራሳቸው የገቢ ምንጭ ይሆናሉ፡፡ ለኢትዮጵያ የዕውቀት ምንጭም ትልቅ አስተዋትኦ ይኖራቸዋል፡፡ በዚህ አገር ለስታዲዮሞች የሚሰጠው ትኩረት ለእነዚህ ሙዚየሞች ቢሰጥ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነበር፤›› ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ቋሚ ኮሚቴው አዳዲስ ዕቅዶችን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፣ የታቀዱ ፕሮጀክቶችንም ማስፈጸም ላይ መንግሥትን ጫን ብሎ እንዲጠይቅ አሳስበዋል፡፡