Wednesday, November 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የገንዘብ እጥረት የኤሌክትሪክ ሽፋንን መቶ በመቶ ለማድረስ በተያዘው ዕቅድ ላይ እንቅፋት መሆኑ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ሕዝብ እ.ኤ.አ በ2030 ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኛል የሚለውን ዕቅድ የገንዘብ እጥረት እያስተጓጎለው መሆኑ ተገለጸ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አባል አገሮች ተሰባስበው ከቀረጹት ዘላቂ የልማት ግቦች እንዱ የሆነው ከስምንት ዓመታት በኋላ አገሮች ለሁለም ዜጎች ተመጣጣኝና አረንጓዴ ኃይል ያቀርባሉ የሚለው የሚገኝበት ሲሆን፣ ይህንን ተስማምተው ከፈረሙ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ይታወቃል፡፡

ከምሥረታው አንስቶ የተለያዩ መጠሪያዎች የነበሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2014 ዓ.ም. ብቻ 364,764 የሚደርሱ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉ ተገልጾ፣ ተቋሙ በንፅፅር በቀደመው ጊዜ ከነበረው አፈጻጸም የተሻለው ይህ አኃዝ አገሪቱ ከምትፈልገው አንፃር በቂ አይደለም ተብሏል፡፡

በብሔራዊ የኤሌክትሪክ ፕሮግራም መሠረት ኤሌክትሪክን ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ በየዓመቱ እስከ 3.6 ሚሊዮን ደንበኞችን በኤሌክትሪክ ማገናኘት የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ነገር ግን ባለፉት ስምንት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ የተገናኙት ደንበኞች ቁጥር ሩብ ሚሊዮን መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ዕቅዱን በታቀደው መጠን እንዳታሳካ ምክንያት ከሆኑት ችግሮች ውስጥ የበጀትና የግብዓት እጥረቶች ተጠቃሾች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ዕቅድ በሚፈለገው ፍጥነት ማስኬድ ስላልቻለች በዕቅዱ መሠረት ለመተግበር፣ አዲስ የሦስት ዓመት ስትራቴጂ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጿል፡፡

አገልግሎቱ የተያዘውን ዓመት ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚገለገልበትን አዲስ ስትራቴጂ ለሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ባለድርሻ አካላት ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ያቀረበ ሲሆን፣ በተቋሙ የአፈጻጸም ሒደት ላይ በነበሩ ጠንካራ ጎኖችና ባጋጠሙ ችግሮች ላይ ምክክር ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ተቋሙ አገልግሎቱን ለማሻሻል ከፍተኛ ተግዳሮት የሆነበት የፋይናንስ ችግር እንደሆነና ዘርፉ አንዴ መሠረተ ልማት ከተዘረጋለት ለረዥም ጊዜ አገልግሎት የሚቀርብበት ቢሆንም፣ ይህንን መሠረተ ልማት ለመገንባት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የኃይል ፍላጎት አለ ብለዋል፡፡ ያንን ፍላጎት ማሳካት የሚችል መሠረተ ልማት መገንባት አስፈላጊነቱን ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በአገሪቱ ከማመንጫ ጣቢያዎች የኃይል አቅርቦት ውስንነት ችግር ባይኖርም፣ የመነጨውን ኃይል ደንበኛው ጋር ማድረስና የኔትወርክ አቅም ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከዚህ ጋር ተያይዞ የፋይናንስ ውስንነት እንዳለበትና ይኼ ደግሞ በዋናነት ከውጭ ምንዛሪ ጋር የሚገናኝ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ምንም እንኳን ከአበዳሪ የፋይናንስ ተቋማትና ተቋሙ በራሱ ያገኘውን የውጭ ምንዛሪ ተጠቅሞ እየሠራ ቢገኝም፣ በሚፈልገው ፍጥነት መሥራት አለመቻሉ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

አቶ ሽፈራው እንዳስታወቁት፣ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በሚጠይቀው የአሌክትሪክ መሠረተ ልማት በተለይም የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታ ላይ አገሪቱ የሠራችው ሥራዎች እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከዚያ ጋር በተናበበ ሁኔታ የመነጨውን ኃይል ኅብረተሰቡ ጋር ለማድረስ የሚገነባው የመሠረተ ልማት ላይ ውስንነቶች አለ ብለዋል፡፡

ውስንነቱ የመነጨው ከበጀት እጥረት የተነሳ እንደሆነና አገሪቱ በአንድ ጊዜ እንደ ህዳሴ ግድብ ላሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችም ሆነ የኃይል ማሠራጫ ጣቢያዎች ግንባታ የሚውል ሀብት እንደማይኖራት የሚታወቅ ቢሆንም፣ በቀጣይ የኃይል ማስተላለፍ (ሰብስቴሽን)ና የሥርጭት (ዲስትሪቢዩሽን) መሠረተ ልማት ላይ ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶ ፋይናንስ ሊደረግ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

ይህ ብቻም ሳይሆን በሥርጭት መሠረተ ልማት ላይ የሚደርሰው ዝርፊያ፣ ገጠርን ከገጠር ለማገናኘት የሚበጀተው በጀት ውስን መሆን፣ የተበጀተውም በጊዜ አለመድረሱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን በአጭር ጊዜ ማዳረስ የሚለውን የተቋሙን ግብ ለማሳካት በሥጋትነት የሚነሱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የአሌክትሪክ መሠረተ ልማት ብቻ ሳይሆን የመነጨውን ኃይል የሚሰርቁ አካላት እንዳሉ፣ በሌላ በኩል ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥሩ እንቅስቃሴ የነበራቸውና የትራንስፎርመር ችግርን አቃለው የነበሩት የአገር ውስጥ የትራንስፎርመር ፋብሪካዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፈረሙትን ኮንትራት ለማሟላት የማይችሉበት ደረጃ እንደደረሱና በቀጣይ ለተቋሙ ሥጋት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

አቶ ሽፈራው የዲስትሪቢዩሽን ኔትወርክ ልማት፣ ተቋማዊ አደረጃጀትና የሰው ሀብት አቅም ግንባታ፣ ደንበኛ ተኮር አገልግሎት፣ እንዲሁም አስተማማኝ የፋይናንስ አቅም መገንባት ተቋሙ ይፋ ያደረገው ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ የተካተቱ የትኩረት መስኮች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ለማሻሻልና የደንበኞችን የእርካታ ደረጃ ለማሳደግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ የተጀመሩ ሥራዎች እንዲሳኩ ለተነደፈው ስትራቴጂ ትግበራ ስኬትም በየደረጃው የሚገኙ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን አካላት ሚና ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች