Wednesday, November 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤሌክትሪክ  መሠረተ ልማት ሀብት ቆጠራና የዋጋ ትመና ጥናት እየተደረገ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመላ አገሪቱ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያና ማሠራጫ መሠረተ ልማት ብዛትና ወቅታዊ ዋጋ በተመለከተ ጥናት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙት የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች በወቅቱ ባለመጠገናቸው ከአቅም በላይ እየሠሩና ለኃይል መቆራረጥ መንስዔ መሆናቸውን፣ ካሉት መሠረተ ልማቶች ከፍተኛውን መጠን የሚይዙት ያረጁ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይጠቀሳል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የለውጥና የመልካም አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ጤናው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አገሮች የሕዝብና የቤት ቆጠራ እንደሚያደርጉት ሁሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎትም ምን ያህል ምሰሶዎች እንዳሉት፣ የት እንደሚገኙ፣ ከምሰሶዎች አቅራቢያ ምን ያህል ቤቶች እንደሚኖሩ፣ በአንድ ምሰሶ ምን ያህል ሰዎች እንደሚጠቀሙ፣ የተበላሹ ቆጣሪዎች ምን ያህል እንደሆኑ፣ ትራንስፎርመሮች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ፣ ማርጀት አለማርጀታቸውንና የመቼ ዘመን ሥሪት እንደሆኑ የሚለዩበትን መረጃዎች በመሠረተ ልማት ሀብት ጥናቱ ይካተታሉ፡፡

‹‹ካሉት ትራንስፎርመሮች አብዛኞቹ ያረጁ መሆናቸውን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቀየር እንደሚገባ፣ ሌሎችም ጉዳዮች ከዚህ ቀደም በሥርዓቱ የተካተቱ ስላልነበሩ፣ ስለሆነም በቋሚ ንብረት ምዝገባ ዋጋቸውን እንደገና የመተመን ሥራ ተከናውኗል፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ እሱባለው፣ ይህ በመሆኑም እግረ መንገዱን የተቋሙን የኤሌክትሪክ ኔትወርክ ጥራት መረጃ መሥራት እንዳስቻለ አክለዋል፡፡

‹‹ጥናቱ ለምሳሌ ጥገና ለማድረግ ቢታሰብ ለየትኛው ቦታ ቅድሚያ መስጠት ይሻላል? የት አካባቢ የሚገኝ ደንበኛ ነው እየተሰቃየ ያለው? የሚለውን ዝርዝር መረጃ ይሰጣል፤›› ብለው፣ ንብረቱን ብቻ መቁጠር ሳይሆን ተቋሙ ወደ አይኤፍኤስአር IFRS የሒሳብ አሠራር እየገባ ስለሆነ፣ ለዚያም አንዱ መሥፈርት የንብረት ዋጋ ትመና በመሆኑ ያንን ለማቀላጠፍ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጥናቱ በዓይነቱ ለመጀመርያ ጊዜ የተደረገ መሆኑን የተናገሩት አቶ እሱባለው፣ ተቋሙ ከዚህ ቀደም በግምታዊ የሀብት ቆጠራ ምን ያህል ሀብት እንዳለው እንደሚያውቅ፣ በዚህ ወቅት የሚደረገው ሀብቱን በአካል ተገኝቶ መቁጠር ብቻ ሳይሆን የኔትወርኩን የጥራት ደረጃ የሚፈተሽበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እያንዳንዱ የኤሌክትሪክ ምሰሶ ምልክት (ታግ) ቁጥር እየተሰጠው ስለሆነ በቀላሉ ለመለየት የሚቻል መሆኑን፣ ከትንሽ ጊዜ በኋላ የደንበኞች የትራንስፎርመር ኢንዴክስ (አንድ ደንበኛ ኃይል እያገኘ ያለው ከየትኛው ትራንስፎርመር ነው)፣ እንዲሁም ትራንስፎርመሩ ችግር ሲገጥመው ምን ያህል ደንበኞች ችግር ውስጥ እንደገቡ በቀላሉ ለማወቅ የሚያስችል ጥናት እንደሚደረግም ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመካከለኛ መስመሮችና የትራንስፎርመሮች የሀብት ጥናት መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን፣ የእያንዳንዱ ደንበኛ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ የት ይገኛል?  ጥሩ ቦታ ነው ወይ? ተጨማሪ የኃይል መቆጣጠሪያ የገጠመ ደንበኛ አለ ወይ?  የሚለው እንዲሁ እየተጠና እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

በአባወራ ደረጃ 4.3 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ካሉት የመሠረተ ልማት ሀብቶች መካከል የመካከለኛ ቮልቴጅ መስመሮች ርዝመት 54,300 ኪሎ ሜትር የሚደርሱ ሲሆን፣ የዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመሮች እንዲሁ 67,706 ኪሎ ሜትር እንደሚዘረጉ ተገልጿል፡፡

አገልግሎቱ ከኤሌክትሪክ ጄኔሬተሮች መጥነው የሚቀበሉ 44,977 ትራንስፎርመሮችና 39 ያህል ሰብስቴሽኖች እንዳሉት ተገልጿል፡፡ በመላ አገሪቱ ከሚገኙት ከ16,000 ሺሕ በላይ መንደሮች ውስጥ 7,900 መንደሮች እስካሁን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳገኙ ታውቋል፡፡ አሥራ አንድ የክልል አካባቢዎች ደግሞ ከግሪድ (ከኃይል ቋት) ውጪ ያለግሪድ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደደረሳቸው አቶ እሱባለው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች