ለተፈናቃዮች ተገቢውን የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ለማድረግ በቂ የሕግና ተቋማዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ፣ የተፈናቃዮችን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ የከፋ እንዳደረገው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ በኮንሶ ዞንና በሦስት ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ ተፈናቃዮች፣ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ከሐምሌ 24 እስከ ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ያደረገውን የክትትል ባቀረበበት ሪፖርት ነው፡፡
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ‹‹ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ ባለማግኘታቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ከመሆኑም ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት በዚህ አካባቢ የሚያገረሹ ግጭቶች የተፈናቀሉ ሰዎችን ለተደራራቢ ጉዳትና መፈናቀል እየዳረጉ ስለሆነ ለመፈናቀል መንስዔ የሆኑ ግጭቶችን ማስወገድ፣ በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው›› በማለት ገልጸው፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ያገኙ ዘንድ በትብብር እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢሰመኮ ክትትል ባደረገባቸው አካባቢዎች በአጠቃላይ 145,933 የተመዘገቡ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 53,400 ተፈናቃዮች በኮንሶ፣ 40,000 ተፈናቃዮች በደራሼ፣ 8,331 ተፈናቃዮች በአሌ እንዲሁም 44,202 ተፈናቃዮች በአማሮ የሚገኙ መሆኑን በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ተፈናቃዮቹ በግጭትና በመፈናቀል ሒደት ወቅት የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የደረሰባቸው መሆኑን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ የገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል የሞቱና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸው፣ በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት መፈጸሙ፣ የአካል አቅማቸው የተዳከመ አረጋውያንና ለመሸሽ ያልቻሉ አካል ጉዳተኞች ላይ ድብደባና እንግልት መድረሱ፣ እንዲሁም ቤቶቻቸው፣ ንብረቶቻቸው፣ ከብቶቻቸውና ሰብሎቻቸው መውደማቸውና መዘረፋቸውን አስታውቋል፡፡
ተፈናቃዮችን በተመለከተ በየጊዜው ወቅታዊ የሚደረግ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አለመኖሩን እንዲሁም የመታወቂያ ካርድን ጨምሮ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎት አለመኖሩ በተፈናቃዮች የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡