Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉአገር ማለት ምን ማለት ነው? አገርን መውደድ እንዴት ይገለጻል?

አገር ማለት ምን ማለት ነው? አገርን መውደድ እንዴት ይገለጻል?

ቀን:

በሀብታሙ ግርማ ደምሴ

መግቢያ

በዚህ መጣጥፍ ጸሐፊ እምነት ለፖለቲካችን አለመረጋጋት አንዱ ምክንያት በተለያዩ አገራዊ (ፖለቲካዊ) ጉዳዮች ያለ የተዛባ አመለካከት ነው፡፡ የተዛባ ትርክት ወይም ያልጠራ ዕሳቤ (አመለካከት) ከሚስተዋልባቸው ቁልፍ የፖለቲካ አጀንዳዎቻችን መካከል የሚከተሉት ናቸው፡፡

  • ስለአገር ምንነት፣ አገርን ስለመውደድ መገለጫዎች ያለ አተያይና ግንዛቤ

ስለአገረ መንግሥትና ብሔረ መንግሥት ያለ አተያይና ግንዛቤ

በመሆኑም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ሕዝባዊ ክፍፍልና ተቃርኖዎችን እያስከተሉ ያሉ በሚል ከላይ የተጠቀሱ ፖለቲካዊ/አገራዊ አጀንዳዎች ሊኖረን የሚገባን አመለካከት፣ ወይም ግንዛቤ በተስተካከለ ሁኔታ በመግራት በኩል ጠቃሚ የሆኑ ዕሳቤያዊ ማዕቀፎችን (Conceptual Framework) ወይም መርሆችን (governing Principles) ማበጀት ነው

አገር ማለት ምን ማለት ነው? አገርን መውደድ እንዴት ይገለ?

ኢትዮጵያዊያን አገራችንን እንደምንወድ በተገኘው አጋጣሚ እንገልጻለን፡፡ ነገር ግን በተግባር አገርን መውደድ ምን እንደሆነ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ የሚስተዋል ችግር ነው፡፡

  • ለመሆኑ አገር ማለት ምን ማለት ነው?
  • አገርን መውደድ እንዴት ይገለጻል?

ኢትዮጵያን መውደድ እንዴት ይገለ?

በእኔ ግንዛቤ አንድ ሰው አንድን ነገር ይወደዋል ብሎ ለመገንዘብ እንደ መሥፈርት መሆን ያለባቸው ሦስት ተያያዥ ነገሮች አሉ፡፡

አንደኛው ስለሚወደው ነገር ግንዛቤ ለማግኘት (ለማወቅ) በሚያጠፋው ጊዜ፣ ጉልበት ወይም ኢነርጂ ነው፡፡ ሁለተኛው የሚወደውን ነገር የግሉ ለማድረግ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት (ጊዜ፣ ጉልበት ወይም ኢነርጂ) ለመክፈል ቁርጠኝነት ነው፡፡ ሦስተኛ የሚወደውን ነገር ካገኘ በኋላ የእርሱ አድርጎ ለማቆየት በሚያጠፋው ጊዜ፣ ጉልበት ወይም ኢነርጂ (emotion) ነው፣ መሆን አለበት፡፡

እንግዲህ መውደድ የምንለው ሥነ ልቦናዊ እንደመሆኑ በቁጥር ለመለካት ከባድ ነው፣ የመውደዱ ነገር በሁኔታዎች ውስጥ ሊለዋወጥ ይችላል፡፡ እዚህ ጋር የቦታ፣ የጊዜና ሌሎች ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡

እውነተኛ ወዳጅ ከሚወደው ጋር ባለው ቁርኝት መርሁ ፍቅር እስከ መቃብር እንጂ ከራስ በላይ ንፋስ አይደለም፡፡ ደስታው ሁሉ በሚወደው ነገር ውስጥ ስለሆነ (የሚወደውን ነገር) ማጣት አይፈልግም፡፡ ከዚያ ይልቅ አቅሙ የሚችለውን ሁሉ አድርጎ የራሱ አድርጎ ለማቆየት ይጥራል፡፡ ወዳጅ ስለሚወደው ነገር አብዝቶ ጊዜውንና መንፈሱን ስለሚሰጥ በሚወደው ነገር ላይ አጠቃላይ አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ውቅር ላይ አጠቃላይ ግንዛቤ አለው፡፡ በመሆኑም የሚወደውን ነገር ህልውና (በአዎንታም ሆነ በአሉታ) የሚጎዱ ነገሮችን ለመረዳት ይጥራል፣ ያውቃልም፡፡ ስለሆነም ወዳጅ የሚወደውን ነገር ማጣት ስለማይፈልግ የኋለኛውን ህልውና የሚጎዱ ማንኛውንም ተግባራት ሊፈጽም ይቅርና ሌሎች እንኳን (በማወቅም ሆነ ባለማወቅ) ሊጎዱት ቢሞክሩ ዘብ (ጋሻ) ሆኖ በመቆም ከጥቃት ይጠብቀዋል፡፡

በአጠቃላይ አገሬን እወዳለሁ የሚል አገሩን ስለመውደዱ የሚገልጽ ከቃላት (ከዘፈን) ባለፈ ተጨባጭ ነገር ሲተገብር መታየት አለበት፡፡ አገርን ማወቅ ሲባል ቢያንስ የሚከተሉትን ሦስት ጉዳዮችን ለማወቅና ለመመርመር መጣር ማለት ነው፡፡ አንደኛው አገር የምንለው ጽንሰ ሐሳብ ምን ማለት እንደሆነ፣ በዚህም ኢትዮጵያን እንደ አገር መረዳት፣ ሁለተኛው አገር ሀብት መሆኑን መገንዘብ፣ ሦስተኛው የአገርን (የኢትዮጵያን) ሥነ ሕዝባዊና ሥነ መንግሥታዊ ታሪክን በአግባቡ በመረዳት አገሪቱን ለማስቀጠል የሚያስፈልገውን መረዳት እና/ወይም ዋጋ መክፈል መቻል ነው፡፡

አገር የሚለውን ጽንሰ ሐሳብመርመር

አገር የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ሕዝቦች የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅና የሚጋጩ ፍላጎቶቻቸውን ለማስጠበቅ በአንድ መንግሥት ሥር ለመተዳደር የሚገቡት ቃል ኪዳን ነው፡፡ በመሆኑም አገር በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ውስጥ ሕዝቦች (ዜጎች)፣ መንግሥት፣ የተለያዩ ተፎካካሪ ወይም የሚጋሩት ፍላጎቶች ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ እነዚሁ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደ አንድ አገር ሕዝብ ሆነው በጋራ ለመተዳደር መነሻ ወይም መሠረት የሚሆናቸው የጋራ ጉዳይ፣ ይህን የጋራ ጉዳይ የሆነውን በአንድነት የመኖር አጀንዳ ሊያሳኩበት የሚችሉበት መንገድ (ሒደት)፤ እንዲሁም እነዚህ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በአንድነት ለመኖር እንዲችሉ በጋራ የሚስማሙበት የጥቅምና ግዴታ የውል ስምምነት ሰነድ ናቸው፡፡

ስለሆነም አገር በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ውስጥ አገረ መንግሥት፣ ሕገ መንግሥት፣ የፖለቲካ ልሂቃንና ብሔረ መንግሥት የሚባሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ በመሆኑም አገር ስለሚባለው ነገር የሚኖረን ዕውቀት እነዚህን ጉዳዮች ማወቅ ነው፡፡

በአንድ አገር የሚኖሩ የተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ፖለቲካዊ ልዩነቶቻቸውን በጎን አድርገው፣ ነገር ግን የጋራ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ተግባራትን የሚከውን አካል አገረ መንግሥት ይባላል፡፡ አገረ መንግሥቱ ይህን የሕዝቦች የጋራ ጥቅም የማስጠበቅ ኃላፊነቱ በዝቅተኛ ደረጃ ሊከውን የሚገባው ተግባር ሲሆን፣ ዋነኛ ተግባሩ ብሔረ መንግሥት ለመመሥረት ለሚደረጉ ሒደቶች መሠረት የሆኑ ተግባራትን ማካሄድ ነው፡፡ ይህም የተራራቁ የፖለቲካ ፍላጎቶችን ለማቀራረብ የሚስችሉ ሕገ መንግሥታዊ፣ ተቋማዊና አስተዳደራዊ መሠረተ ልማቶችን (Soft infrastructures) መገንባት ነው፡፡ በመሆኑም የአገረ መንግሥት አስፈላጊነት የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ወደፊት በጋራ አብረው መኖራቸው ጥቅም እንዳለው ማሳየት፣ የአብሮነታቸው ዋስትና እንዲኖር መሠረት የሚሆነውን የጋራ ኑሮ መመሥረቻ የውል ሒደትን ማስተባበር፣ በጋራ የተስማሙበትን የቃልኪዳን ሰነድ ውሎች ሳይሸራረፉ እዲከበሩ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ ነው፡፡

የተለያዩ ኅብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅሞች ወክለው በመደራደር በጋራ ሊያድሩበት የሚችሉበት መንግሥታዊ ሥርዓት የሚዋቀርበትን አግባብ የሚበይኑበት፣ በአንድነት ለሚመሠርቱት መንግሥት ርዕይ የሚቀመጥበት ሒደት ሕገ መንግሥት የማፅደቅ ሒደት ይባላል፡፡ ይህን የጋራ ተጠቃሚነት ይረጋገጥ ዘንድ የተለያዩ የኅብረተሰብ አካላትን ጥቅሞች ወክለው የሚከራክሩ/የሚደራደሩ ግለሰቦች/ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህም የፖለቲካ ልሂቃኖች የምንላቸው ናቸው፡፡ ሕዝቦች በጋራ ለመተዳደር የሚገቡበት የቃልኪዳን ሰነድ ሕገ መንግሥት ይባላል፡፡ ሕገ መንግሥት የተለያዩ የማኅበረሰብ/ሕዝብ ክፍሎች በጋራ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸው ላይ የተስማሙበት የቃል ኪዳን ሰነድ በመሆኑ፣ ለብሔረ መንግሥት ምሥረታው ስኬት ትልቅ ዕርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ 

ነገር ግን ሕገ መንግሥት ስለፀደቀ ብቻ ብሔረ መንግሥቱ ዕውን ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ የብሔረ መንግሥቱ ዕውን መሆን የሚወሰነው ሕገ መንግሥቱን ለማክበርና ለማስከበር በሚኖረው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ያጸደቁት የፖለቲካ ኃይሎች የመሠረቱት መንግሥት የሕገ መንግሥቱን እሴቶች በማክበርና በማስከበር፣ በዜጎች አዕምሮ ውስጥ የአገርን ምስል ማኖር አለበት፣ አገር ማለት ሕዝቡና መሬቱ ብቻ ሳይሆን ሕዝባዊ (የጋራ) ሥነ ልቦና መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ በመሆኑም አገር ማለት እያንዳንዱ ዜጋ በኑሮው (በሕይወቱ) ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ ዋስትና የሚሆነው ሥርዓት ማለት ነው፡፡ የአንድ አገር ዜጎች (በባህል፣ በቋንቋ፣ በእምነትና በአስተሳሰብ ከሚጋሩትም ሆነ ከማይጋሩት ከሌሎች የአገሩ ዜጎች ጋር)  በሥነ ልቦና የተዛመዱ ናቸው፡፡ ለአንድ አገር ዜጎች የአንዳቸው ችግር ለሌላኛቸውም ሕመም ነው፣ የአንዳቸው ደስታ ቢያንስ ለሌሎቹ ሐዘን (ባያስደስት እንኳን) አይሆንም፡፡

በኅብረተሰባችን ውስጥ ስለአገር ጽንሰ ሐሳብ ያለው ግንዛቤ የተንሸዋረረ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ አስረጂዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለተወሰነው የኅብረተሰብ ክፍል ኢትዮጵያ ርስቱና ከአምላክ ተሰጠች ዘለዓለማዊ ስጦታ ስትሆን፣ ለአንዳንዱ ኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዥ ናት፡፡ አገርን ከመንግሥታትና ከመሪዎች ያለ መለየት ችግርም እንዲሁ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት(ታት) እና/ወይም በመሪ(ዎች) እንጂ፣ በአገር ላይ ቂም አይያዝም የሚለውን የሥነ መንግሥት መርህ የሚጥስ አመለካከት ወይም ተግባራት በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ተመልክተናል (እየተመለከትንም ነው)፡፡ በመንግሥታት/መሪዎች ላይ ተስፋ መቁረጥ ያለ ቢሆንም፣ በአገር ግን ተስፋ መቁረጥ አይገባም፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያዊነትን በመገንባት ሒደት አንዱ ተግባር መሆን ያለበት ትውልዱን  ስለ አገር ጽንሰ ሐሳብ ማስተማር ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ውስጥ የአገር ጽንሰ ሐሳብን ባለመረዳት ምክንያት የተወለዱ በርካታ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ እንዲሁም የደኅንነት ጋሬጣዎች ሲከሰቱ ኖረዋል፡፡ ዛሬም ይህ ችግር አለ፡፡ መላ ካልተበጀለት በቀር ለነገው ትውልድ ችግሩ ተባዝቶ መተላለፉ አይቀሬ ነው፡፡

ኢትዮጵያን እንደ አገር ካለመገንዘብ ከሚመነጩ አንዱ ሕዝቦች ለበርካታ ዘመናት በአንድ አገረ መንግሥት ሥር መቆየታቸውን፣ ዛሬም ሆነ ነገ እንደ አንድ ሕዝብ በጋራ ለመኖር ዋስትና አድርጎ መገንዘብ ነው፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የአገረ መንግሥቱ ዋና ተግባር የሚሆነው ብሔረ መንግሥት ለመመሥረት የሚስፈልጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው እንጂ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ በመሆኑም በጋራ መንግሥት ሥር ለበርካታ ዓመታት መተዳደር መቻል ብቻውን እውነተኛ አገር ስለምንለው ጽንሰ ሐሳብ ሙሉ ምስል አይሰጠንም፡፡ ሕዝቦች የቱንም ያህል በአንድ መንግሥት ሥር ቢቆዩ የሚያስተዳድራቸው ሥርዓት ቀደም ሲል የተገለጹትን የአገረ መንግሥት ተግባራትን ካልፈጸመ ገዥያቸው እንጂ መንግሥታቸው ሊሆን አይችልም፡፡ በገዥዎች ሥርዓት ውስጥ ሕዝባዊ አንድነትን ለማስፈን አይቻልም፡፡ በመሆኑም ሕዝቦች የሚተዳደሩበት ሥርዓት መልክ/ባህሪ ስለአገራቸው የሚኖራቸውን ፍቅር/ክብር ይወስናል፡፡ ሥርዓቱ እንደ መንግሥት ሳይሆን እንደ ገዥ ከሆነ ዜጎች የአገር ፍቅርና ክብር አይኖራቸውም፡፡ በተቃራኒው ፍትሐዊ ሥርዓት ካለ ዜጎች አገራቸውን የሚወዱና ለአገራቸው ህልውና መስዋዕትነት ለመክፈል የማይሳሱ ይሆናል፡፡ በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የረዥም ዘመናት የጋራ አገረ መንግሥትነት ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች በጋራ እሴቶቻቸው ላይ ተመሥርተው ብሔረ መንግሥት ለመመሥረት ካልጣሩ ከመነጣጠል አደጋ ሊርቁ፣ አገራቸውንም ከመፍረስ ሥጋት ሊታደጉ አይችሉም፡፡

አገር የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ባለመገንዘብ ከሚፈጠሩ መደናገሮች መካከል ሌላው በባህል፣ ቋንቋ  ወይም እምነት መለያየት አገር ለመመሥረት እንቅፋት አድርጎ መውሰድ ነው፡፡ በመሆኑም ተፈጥራዊ የሕዝብ ልዩነቶችን ጨፍልቆ አዲስ ማንነት በመፍጠር አንድ አገር መገንባት የሚለው አስተሳሰብ ነው፡፡ ትናንት ኢትዮጵያን የመሠረቱት አባቶቻችን አንድ ባህል፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት በሚል መርህ ብዝኃነትን የሚጎዱ ተግባራት በመከወናቸው፣ የብሔር ጭቆና ትርክት የፖለቲካ ዋናው መታገያ መንገድ ተወስዶ ዛሬ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን አለ፡፡

ሌላው አገር የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በወጉ ካለመገንዘብ የሚመነጭ የአመለካከት ችግር የአንድ አገር ጥንካሬ መሠረቱ ሕዝባዊ አንድነቱ መሆኑን በሚገባ ለመረዳት አለመቻል (አለመሞከር) ነው፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሥነ ልቦና መቀራረብ ወይም መራራቅ በአገራዊ አንድነት ላይ ስለሚኖረው ትልቅ ፋይዳ በተራው ዜጋም ይሁን በአገር መሪዎች ዘንድ እምብዛም ትኩረት ተነፍጎት ኖራል፡፡ ነገር ግን የሕዝባዊ አንድነቱ መሠረቱ ደግሞ ዜጎች እርስ በርሳቸው ያላቸው የሥነ ልቦና ቁርኝት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር የሚኖራት ጥንካሬ አንዳችን ሌላኛችንን ለመረዳት በሚኖረን ዝግጁነት ነው፣ የሌሎችን ጉዳት የራሳችንም ጉዳት ባደረግንበት ልክ ነው፣ የአንዱ ቁስል ለሌላውም ሕመም መሆን ሲችል ነው፣ የኢትዮጵዊነት ልቡ የአንዳችን ችግር ሌላችንም ችግር ሆኖ መሰማቱ ነው፣ ኢትዮጵያን መውደድ ማለት እርስ በርሳችን መዋደዳችን ነው፡፡

አገር የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በአግባቡ ካለመረዳት ከሚስተዋሉ አመለካከቶች መካከል ሕዝባችን የቀድሞና የአሁኑ ሥርዓተ መንግሥታትንና መሪዎቹን የሚመዝንበት አግባብ ወይም መሥፈርት ነው፣ መንግሥታትን (መሪዎችን) የምንመዝንበት አግባብ በአብዛኛው በዘፈቀደ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ትውልድ እንደምናስተውለው የመመዘኛ መሥፈርት በአመዛኙ የመንግሥታቱ/መሪዎቹ ውክልና ለብሔራችን ወይም እምነታችን ካላቸው ቅርበት ወይም ርቀት ነው፡፡ ይህ ባለፉት ሥርዓታትና መሪዎቻችን ላይ ያለን ዘፈቀዳዊ አረዳድ በማኅበረሰባችን ውስጥ ሕዝብን ከሕዝብ በመከፋፈል አገራዊ አንድነታችንን እንዲላላ ምክንያት ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥታት/መሪዎች መመዘን ያለባቸው ሥርዓቶቹ አገረ ብሔር ለመመሥረት ከሄዱበት ርቀት ነው፡፡ የመንግሥታቱ ባህሪ ዴሞክራሲዊ፣ አምባገነን ወዘተ… ዓይነት ባህሪ ቢኖረውም እነዚህ መመዘኛ መሥፈርቶች ሥርዓቶቹ ብሔረ መንግሥት ለመመሥረት ከሄዱበት ርቀት አንፃር ሚዛን ውስጥ አይገቡም፡፡ ምክንያቱም መንግሥታዊ ሥርዓቱ ኢኮኖሚን ቢያሳድግ፣ ትምህርትን ቢያስፋፋ፣ መሠረተ ልማት ቢያስፋፋ፣ ወዘተ… የሕዝቡን በዘለቄታ በአንድነት የሚኖርበት የፖለቲካ መደላድል የሆኑትን ሕገ መንግሥታዊ፣ ተቋማዊና አስተዳደራዊ ሥርዓት ካልዘረጋ ሌሎች መልካም ሥራዎቹ ሁሉ ዋጋቸው እምብዛም ነው፡፡

በመሆኑም ሥርዓተ መንግሥታት (መሪዎች) መመዘን ያለባቸው ዋነኛ መሥፈርት፣ ሕዝቡ በአንድነት ይኖር ዘንድ መሠረት የሆኑትን የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ ለማዘጋጀት የሄዱበት ርቀት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዓቱን ስብራቶች ለመጠገንና የፖለቲካ መረጋጋት ይሰፍን ዘንድ ሕዝቡ በፍትሐዊነት በአብሮነት እንዲኖር የሠሩት ሥራ ነው፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ እንዲሁም ነገ የፖለቲካ ሥልጣን የያዘ ሥርዓተ መንግሥት መገምገም ካለበት ይህን ተግባር ለመከወን በነበረው፣ ባለው ወይም በሚኖረው ቁርጠኝነትና ተጨባጭ እንቅስቃሴዎች ነው፡፡

አገር ብት መሆኑን መገንዘብ

አገሩን የሚወድ አገሩን የራሱ ለማደርግ መጣር አለበት፡፡ የጥረቱ መገለጫም አገሩ የእርሱ እንድትሆን መክፈል የሚገባውን ነገር ለማድረግ ባለው ቁርጠኝነትና  አበርክቶ ነው፡፡ አገሩን የእርሱ እንድትሆን ዋጋ የከፈለ በመሆኑ አገሩን እንደ ሀብቱ ይቆጥራል፣ ሀብቱ መንፈሳዊና ቁሳዊ መልክ አለው፡፡ ነግዶ ማትረፍ በአገር ነው፣ ሠርቶ ማደር በአገር ነው፣ አንገትን ቀና አድርጎ መሄድ በአገር ነው፣ ፀቡም ፍቅሩም የሚያምረው በአገር መሬት ነው፡፡

አገር ሀብት መሆኑን ለማወቅ በፈረሰ አገር ውስጥ ኖሮ ልዩነቱን ማየት አይጠይቅም፣ ወይም ባዕድ አገር ሄዶ የመገለልና የመድሎ ገፈት መቅመስን አይጠይቅም፣ ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለውና ማመዛዘን የሚችል አገሩ የህልውናው ጉዳይ እንደሆነች መገንዘብ አይሳነውም፡፡

ኢትዮጵያ እንደ አገር ለዘመናት ያላቋረጠ የባዕዳንን ሴራ ተቋቁማ ዛሬ እኛ እጅ የደረሰችው እልፍ ትውልዶች በከፈሉት ደምና አጥንት መሆኑን ለሁላችንም የተደበቀ እውነት ወይም እውቀት አይደለም፡፡ አገሩን እንዲሁ በዋዛ ሳይሆን በመስዋዕትነት የተገኘች በመሆና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማወቅ አለበትና ይህ ከሆነ ሁሉም ዜጋ አገሩ ሀብቱ እንደሆነች ስለሚገነዘብ እንዲሁ በዋዛ በፈዛዛ ማጣት አይፈልግም፡፡ እርሱም ለልጆቹ አገሩን ያገኘው ሠርቶና ለፍቶ እንጂ እንዲሁ በነፃ እንዳልሆነ ስለሚያስገነዝባቸው፣ ልጆቹም አገራቸውንና ሀብታቸውን እንዲሁ ለልጆቻቸው የሚያወርሱበት ስንቅ ይኖራቸዋል፡፡

አገር የምትቀጥለው በዚህ መንገድ ነው እንጂ፣ እንዲሁ እጃችን አጣጥፈን የእግዚአብሔር ቃልኪዳን ያላት መለኮታዊ ባህሪ በመስጠት አይደለም፡፡

አገር ሀብት እንደመሆኑ በአግባቡ ካልተጠበቀ ሊወድም እንደሚችል፣ በአግባቡ ከያዝነው ግን ሀብቱ እያደገ እንደሚሄድ መረዳት አለብን፡፡ በመሆኑም ከአባቶቻችን የተረከብነው አገር (ሀብት) የማያልቅ ጥሪት አድርገን መውሰድ  የለብንም፡፡ በዚህም የማያልቅ ጥሪት አድርገን በዝብዘን ወደ ጥፋት (ውድመት) እንዳንመራው ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ጥንቃቄ ካላደረግን አገር ከእጃችን ልትወጣ እንደምትችል በአጽንኦት ልንገነዘብ ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አባቶቹ ነፃነቷን አስጠብቀው ያወረሱትን እርሱም እሴት ጨምሮበት ለልጆቹ የማውረስ የሞራል ግዴታ አለበት፡፡

አገርን መውደድ አገርን ለማስቀጠል በሚከፈል መስዋትነት ይገለጻል

አገርን መውደድ አገርን ለማስቀጠል በሚከፈል መስዋዕትነት ይለካል፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አገሩን መውደዱ የሚለካው አገሪቱ ውስጥ ያሉ ብዝኃ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ እምነትና የፖለቲካ ዕሳቤዎችን አክብሮ ማስከበር የሚያስችል ተክለ ሰብዕና በመገንባት ነው፡፡ አገር የሚገነባው በአንድ ወጥ ባህል፣ ቋንቋ  ወይም የፖለቲካ ዕሳቤ ሳይሆን በስብጥር ሕብሮች መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገናል፡፡ በዚህም ከዕሳቤያችን፣ ባህላችን፣ ቋንቋችን፣ ሃይማኖታችን የተለየ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን፣ እናቶቻችና አባቶቻችን ክብር ሊኖረን ይገባል፡፡ ይህ ለእነርሱ ክብር ብለን ብቻ የምናደርገው ሳይሆን የራሳችንን የስብዕና መሠረቶች ለማስከበር ነው፡፡ እምነታችንን፣ ባህላችንን፣ ቋንቋችንንና ፖለቲካ ዕሳቤዎቻችን ሌሎች እንዲከብሩልን እኛ ቀድመን እነርሱን ማክበር አለብን፡፡ እንዲህ ሲሆን አብሮነታችን ይጎለብታል፣ እኔ ብቻ ልድመቅ፣ የእኔ ብቻ ፊት ይቅደም፣ የሌሎቹ አያገባኝም የሚሉ ዕሳቤዎች በመሠረቱ አብሮ የሚያናኑር ሳይሆን የሚያቃቅር ነው፡፡

ዛሬ የአገራችን ሉዓላዊነት በውጭ ኃይሎች የመደፈር ሙከራ እየተደረገበት ያለው፣ በልሂቃኖቻችን መካከል ይህ መሠረታዊ ሰብዕና በእጅጉን በመሸርሸሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ታሪክ ሆና የምትቀረው የፖለቲካ ሽኩቻው ከልሂቃን አልፎ ሕዝባዊ መሠረት ሲይዝ ነው፡፡ እስካሁን የአገርን አንድነት አስጠብቆ ያቆየው በሕዝቡ (በማኅበረሰቡ) ውስጥ ያልጠፋው በጎ ስብዕናዊ መሠረት ነው፡፡ በዚህ ረገድ እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ አማኝ መሆኑና የሃይማኖት አስተምህሮዎች የሕዝቡን የሞራልና ሥነ ምግባር መሠረቶችን በማነፅ ረገድ ፋይዳቸው ጉልህ በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሕዝባዊ (ማኅበረሰባዊ) የሰብዕና ጥሪት ከጊዜ ወደ ጌዜ እየተሸረሸረ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ሕዝቡ በልሂቃኑ መካከል እንዳለው የመናናቅና የጠላትነት መንፈስ ከያዘ ያን ጊዜ አገር ፈረሰ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የፖለቲካችን መገለጫ የሆነው የልሂቃን የስብዕና ስሪቶች (መጠላለፍ፣ ቂም፣ በቀልና የተበዳይነት ሥነ ልቦና)  ከፖለቲካ ልሂቃን ጎራ ወጥቶ ሕዝባዊ (ማኅበረሰባዊ) የሰብዕና መሠረት ሊይዝ ባለመቻሉ አገር እንደ አገር ሊቆይ ይችላል፡፡ ይህ ሕዝባዊ (ማኅበረሰባዊ) መልካም ሰብዕና የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን መገለጫ በሆነው በጎ ያልሆነ ሰብዕና እንዳይዋጥ፣ በዚህም የአገርና ሕዝብ ህልውና እንዳያበቃለት መከፈል የሚገባው ማንኛውም መስዋዕትነት ሊከፈል ይገባል፡፡ በእውነተኛነት አገሩን የሚወድ እንዲህ ያለውን መስዋዕትነት ለመክፈል አይሳሳም፡፡ አገርን በተግባር መውደድ የሚገለጸው በእንደዚህ ዓይነቱ በጎ ተግባር ነው፡፡

አገር በምንለው ጽንሰ ሐሳብ ውስጥ ሕዝብና ልሂቃን አሉ፡፡ ሕዝብ የግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ ድምር ነው፡፡ ሕዝብ የአገር መሠረት ነው፡፡ ጠንካራ ሕዝባዊ እሴት ጠንካራ አገርና መንግሥት ለመፍጠር መሠረት ነው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ያለን ሕዝቦች ለአገር ያለን ስሜት አንድ ዓይነት ሊሆን አይችልም፡፡ አንዳንዱ አገሩን አጥብቆ የሚወድ ሊሆን ይችላል፣ መርሁም ኢትዮጵያ ትቅደም (Ethiopia First) ሊሆን ይችላል፡፡ ለአንዳንዶች ደግሞ ብሔረሰባቸው ሊበልጥባቸው ይችላል፣ ይህ ዓይነት የተከፋፈለ የሕዝብ የፖለቲካ አመለካከት የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፡፡ በዓለም በርካታ አገሮች በአገራቸው የውስጥ ጉዳይ በከፍተኛ ርቀት የተከፋፈሉ ሕዝቦች አላቸው፡፡ የዓለም አገሮች (የአውሮፓና የአሜሪካ አገሮችን ጨምሮ) የውስጥ ፖለቲካን ከመረመርን በበርካቶቹ አገሮች ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚሳየን የመገንጠል ዓላማን ያነገቡ (በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ ትግል የሚደገፉ) ኃይሎች እንዳሉ ነው፡፡

ነገር ግን የአገሮቹ የፖለቲካ ሥርዓት መሠረት፣ እንዲሁም የየአገሮቹ የፖለቲካ ልሂቃን በአብዛኛው ማለት በሚቻል ሁኔታ የክፍፍሎቹን መነሻ ምክንያች ለማጥበብና ዜጎችን ለማቀራረብ ሲሠሩ እንጂ ቅራኔዎችን ለማስፋት ሲጥሩ አይስተዋልም፡፡ ይህን የሚያደርጉም በከፍተኛ የአገር ክህደት ወንጀል የሚጠየቁ፣ ለዚህም የፖለቲካ ሥርዓቱ ቁርጠኛ ነው፡፡ ለዚያም ነው ተጠናቆ ያለቀ አገር የለም የሚባለው፡፡ በእርግጥም የፌዴራሊዝምና ሥነ መንግሥት ምሁራን እንደሚገልጹት የብሔረ መንግሥት ግንባታን የጀመሩ እንጂ የጨረሱ አገሮች የሉም፡፡ በመሆኑም በአገሩ ጉዳይ ላይ የተለየ የፖለቲካ አቋም ያለውን ዜጋ አገሩን እንደማይወድ፣ አልፎም እንደ ከሃዲ ወይም ባንዳ መቁጠር አይገባም፡፡ ይልቁንም የተሳሳተ ፍረጃ ከመስጠታችን በፊት ለምን እንዲህ ዓይነት አቋም ሊይዝ እንደቻለ ለመገንዘብ መጣር ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ይህን በአገሩ ላይ ያለውን አመለካከት በበጎ እንዲቀይር ማድረግ የምንችለው እኛው ራሳችን ነን፡፡

በእውነቱ ከሆነ ማንም ተጠቃሚ የሆነባትን አገር ሊጠላ አይችልም፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ታሪካቸው በተሟላ ሁኔታና በአግባቡ ያልተጻፈ ሕዝቦች ስለአገራቸው አንድ ዓይነት ስሜት ይኖራቸዋል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ አንዳንዱ የኢትዮጵ ታሪክ አይወክለኝም የሚል ይኖራል፣ አንዳንዱ ደግሞ ያለፈው ሥርዓት የሃይማኖት ጭቆና አድርሶብኛል ብሎ በአገሩ ሙሉ እምነትና ፍቅር ላይኖረው ይችላል፡፡ ይህ አዲስ ነገር ሊሆንብን አይገባም፡፡ በእርግጥ የቅራኔ ታሪክን ብቻ እያነሱ ሕዝብን ለመከፋፈል ማዋል ተገቢ አይደለም፡፡ ነገር ግን የቅራኔ ታሪክ መካድ ወይም ማሳነስ ይበልጥ አገራዊ አንድነታችንን ይጎዳዋል፡፡ ስለሆነም ባለፈው የአብሮነት ታሪካችን ያጎደለባቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ ታዲያ እነዚህን ኢትዮጵያዊያን ባንዳ ወይም ከሃዲ ከማለት ተቆጥበን፣ ይልቁንስ ቁስላቸውን በፍቅር ለመሻር መትጋት አለብን፡፡ ቁስላቸውን የምንሽረው በዋናነት ስሜታቸውን ለመረዳት በመሞከር ነው፡፡ ለወዳጃችን ምሬቱን፣ ሥቃዩንና ብሶቱን የመረዳትን ያህል ስጦታ የለም፡፡ ኢትዮጵያውያን አገራችንን የመውደዳችን መገለጫ፣ ለአገራችን ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት ውዱ ስጦታችን አንዳችን ሌላችንን ቁስልና ሕመም ለመረዳት በምናሳየው ዝግጁነት ነው፣ አገርን መውደድ ከዚህ በላይ ሊገለጽ አይችልም፡፡

እንግዲህ እንዲህ ያለው በሳል ሰብዕና እንደ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ የአገር ሕዝብ በጋራ ስንኖር ለሚኖሩን ግንኙነቶች የተግባቦት ጤናማነት መሠረት በመሆኑ፣ ግንኙነቶቻችንን ሁሉ ሰላማዊ በማድረግ ጠንካራ አገርና ሕዝብ ለመመሥረት ዋስትና ይሆናል፡፡ በመሆኑም አገርን መውደድ ማለት እርስ በርስ ተዋደን መኖር ማለት እንደሆነ መገንዘብ አለብን፣ ኢትዮጵያን እንወዳለን የምንል ሁሉ እንደ ግለሰብ የሚኖረን መልካም ስብዕና ለምንወዳት አገራችን ሰላም፣ ዕድገትና ሕዝባዊ አንድነት መሠረት በመሆኑን መልካም እሴቶችን ማዳበር አለብን፡፡

ለአንባቢያን እንደ ማስታወሻ፡- ይህ አጭር ጽሑፍ በታኅሳስ ወር 2014 ዓ.ም. ለኅትመት ከበቃው ‹‹ኢትዮጵያን እንዴት እናሻግራት?›› ከሚለው መጽሐፌ ምዕራፍ አሥራ አራት፣ ገጽ 178 እስከ 193 ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው ruhe215@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...