የዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ ውድድሮችን መሠረት ያደረገ የአገር ውስጥ ሻምፒዮናዎችን መርሐ ግብር ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ሊያከናውናቸው ላቀዳቸው ውድድሮች በቂ የመሮጫ ትራክ ባለመኖሩ ዝግጅቱ ላይ ጫና እንዳደረገበት ገለጸ፡፡ ለዓለም ሻምፒዮናና ለኦሊምፒክ ጨዋታ ቅድመ ዝግጅት ከወራት በፊት የአገር ውስጥ ውድድሮችን መርሐ ግብር ይፋ ያደረገው ፌዴሬሽኑ፣ አትሌቶች በአጭርና በመካከለኛና ርቀት ላይ ለሚያደርጉት ዝግጅት የትራክ ዕጦት እንቅፋት እንደሆነባቸው አመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ካላት ውጤት አንፃር ተመጣጣኝ የሆኑ ትራኮች እንደሌሏት የተጠቀሰ ሲሆን፣ በተለይ የአዲስ አበባ ስታዲየም ጥገና ረዥም ጊዜ መውሰድ ችግሩን እንዳባባሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ ተናግረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ስታዲየም በዘለለ የትራክ አማራጭ ያለው በኢትዮጵያ ስፖርት አካዴሚ ቢሆንም፣ ትራኩ በአካዴሚው ውስጥ ለሚገኙ ሠልጣኞች ከሚሰጠው ግልጋሎት ባሻገር፣ በብሔራዊ ቡድንና በግል አትሌቶች መዘውተሩን ተከትሎ እያረጀ መምጣቱ ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው ተነስቷል፡፡
በዚህም ምክንያት የዓመታዊ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውድድሮችን ሊያጓትት እንደሚችል የተጠቀሰ ሲሆን የሻምፒዮናዎቹን መርሐ ግብር ተከትሎ፣ የአዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሳት ማጠናቀቅ ካልተቻለ የውድድሩን ዝግጅት ሊያስተጓጉል እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
የልምምድና የማዘውተሪያ ሥፍራ ግንባታን የማከናወን ሥልጣኑ የፌዴሬሽኑ እንዳልሆነ የሚያስረዱት አቶ ዮሐንስ፣ በተለይ የአዲስ አበባ ስታዲየም ግንባታ በቅርብ ካልተጠናቀቀ ጫናው እንደሚበረታ ገልጸዋል።
‹‹ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የማዘውተሪያ ሥፍራን ለመገንባት በአዋጅ የተሰጠው ሥልጣን የለም፡፡ የማዘውተሪያ ሥፍራን የመገንባት ኃላፊነት ያለው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ችግሩ እንዲፈታ ከሚኒስቴሩ ጋር እየተወያየን ነው፤›› በማለት አቶ ዮሐንስ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ችግሩን ያቀልልኛል ብሎ በማለም በለገጣፎ ለገዳዲ የአሸዋ ትራክ መገንባቱንና ለአትሌቶች የልምምድ አማራጭ መፍጠሩንም ይገልጻሉ፡፡
‹‹የመሮጫ ትራክ አለመኖር በአኅጉር አቀፍ እንዲሁም አገር አቀፍ ውድድሮች ላይ ጫና ይፈጥራል፤›› በማለት አቶ ዮሐንስ አክለዋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ችግሩን ለመፍታት ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ተቀራርቦ እየሠራ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ በቅርቡም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ከመሥሪያ ቤቱ ጋር በጉዳዩ ላይ መወያየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ረቡዕ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የጤና፣ የማኅበራዊ፣ የባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ዓመት የአንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት፣ የአዲስ አባባ ስታዲየም ዕድሳት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በቅርቡም ለውድድር ዝግጁ እንደሚሆኑ ተወስቷል፡፡ ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዳቀረቡት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ማብራሪያ ከሆነ፣ ለመጨረሻው ምዕራፍ ግንባታ የበጀት ዕጥረት ችግርን ለመቅረፍ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየሠሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ መሥሪያ ቤቱ በገጠመው የበጀት እጥረት ምክንያት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር መሠረታዊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡
ዓመታዊ የውድድር መርሐ ግብሩን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ አሥር ውድድሮችን በተለያዩ ክልሎች ላይ ለማከናወን ማቀዱን ይፋ አድርጓል፡፡ ከእነዚህም ውድድሮች መካከል አንዱ 11ኛውን የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከጥር 23 እስከ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በአሰላ ከተማ የሚያደርገው ነው። ይሁን እንጂ የአሰላ ስታዲየም ትራክ ማርጀቱን ተከትሎ ውድድር ማስተናገድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡
ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ ውድድሮችን ሲያስተናግድ የቆየው የአሰላ ከተማ የመሮጫ ትራክ፣ በኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አማካይነት ጥገና ይደረግለታል ተብሎ ቃል ቢገባም፣ ጥገናው አለመከናወኑ ቅሬታን ማስነሳቱ ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም የኦሮሚያ ክልል ስፖርትና ወጣቶች ቢሮ የበጀት እጥረት እንደገጠመው ጠቅሶ፣ ጥገናውን አከናውኖ ለውድድር ዝግጁ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በዓለምና አኅጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚካፈሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፣ በትራክ ዕጦት ምክንያት ፊታቸውን ወደ ጎዳና ውድድሮች እያዞሩ መሆናቸው እየታየ ነው። በዚህም ምክንያት ብሔራዊ ቡድኑ በትራክ ላይ ያለውን ለዘመናት የዘለቀ ውጤት በሒደት እንዳያጣው የሚለው የብዙኃን ሥጋት ሆኗል። እንደ አሠልጣኞች አስተያየት ከሆነ በትራክ ዕጦት ምክንያት መደበኛ ልምምዳቸውን በጎዳና ላይ እያሳለፉ የሚገኙ አትሌቶች ተበራክተዋል።