በቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሲኤስሲኢሲ) በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ለሁለተኛ ምዕራፍ ማጠናቀቂያ፣ ተቋራጩ ባቀረበው የተጋነነ ዋጋ ምክንያት በአፋጣኝ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ መንግሥት ውሉን ሊያቋርጥ እንደሚችል ተገለጸ፡፡
የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ከተጠናቀቀ ሦስት ዓመታት ያስቆጠረው ብሔራዊ ስታዲየም፣ የሁለተኛ ዙር ግንባታ ለማጠናቀቅ ተቋራጩ ያቀረበው የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ቢፈታም፣ ተጨማሪ የዋጋ ማስተካከያ ተጠይቆ የመጨረሻ ድርድር እየተደረገ መሆኑን፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ተናግረዋል፡፡
ተቋራጩ የጠየቀው የዋጋ ማስተካከያ መጀመሪያ በተደረገው ስምምነት መሠረት አስገዳጅ ባይሆንም፣ የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ግምት ውስጥ በማስገባት የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ ቢሞከርም፣ የተጠየቀው ተጨማሪ ማስተካከያ መጀመሪያ ከነበረው 5.5 ቢሊዮን ብር በሦስት እጥፍ ያደገ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ ይህንን ያስታወቁት የተቋማቸውን የ2015 ዓ.ም. የሥራ ዕቅድና የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡
ሚኒስትሩ ከሥራ ተቋራጩ የቀረበውንም የማስተካከያ ጥያቄ ከዋጋ መናር ጋር ግምት ውስጥ በማስገባት ለማስተካከል ቢሞከርም፣ ‹‹ሰዎቹ አገሪቱ ያለችበትን የፀጥታ ችግርና የዋጋ ንረት እየተጠቀሙና ጊዜ እየገዙ አላስፈላጊ ትርፍ ለማግኘት ጥያቄቸውን እያቀረቡ ቀጥለዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ለአብነት ነዳጅ በሊትር 28 ብር ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ዋጋ ሊጨምር መሆኑን እያሳወቁ እስኪጨምር በመጠበቅና ጉዳዩን በማጓተት፣ የነዳጅ ዋጋ 49 ብር ሲደርስ የዋጋ ጭማሪው ስሌት በአዲስ እንዲሠራ በማድረግ ያልተፈለገና ያልተገባ የጭማሪ ጥያቄ እያቀረቡ በመሆናቸው፣ ችግሩን ለማስተካከል በጣም አሰልቺና በርካታ ዙሮች ድርድር ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ከባህልና ስፖርት አልፎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ የቻይና ኤምባሲና የገንዘብ ሚኒስቴርን ጭምር ያሳተፈ ድርድር ቢደረግም እስካሁን ሊያስማማ የሚችል ውሳኔ መድረስ ባለመቻሉ፣ ኮንትራት እስከማጠፍ ሊደርስ የሚችል አማራጭ ውሳኔ ሊታይ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የስታዲየሙ ሁለተኛ ዙር ግንባታ የተጀመረው እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 2020 ቢሆንም፣ ለተቋራጩ ምንም ዓይነት የውጭ ምንዛሪ አለመከፈሉንና የሴራሚክ፣ የነዳጅ፣ የሲሚንቶና የብር ከዶላር ምንዛሪ አኳያ መውረድ ጋር ተዳምሮ የቀረበው የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ውሉ ሊሰረዝ እንደሚችልና ለዚህም ሌላ አማራጭ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ደኤታ መስፍን ቸርነት (አምባሳደር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ችግሩ የገጠመው የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቆ ሁለተኛው ምዕራፍ ከተጀመረ በኋላ ነው፡፡ መክፈል የነበረበት ቅድመ ክፍያ በውጭ ምንዛሪ ለኩባንያው በጊዜው ባለመከፈሉ ዘግይቶም ቢሆን መንግሥት ተስማምቶ ለመክፍል ባሰበበት ወቅት፣ ከዋጋ ንረቱ ጋር ተዳምሮ ኩባንያው መጀመሪያ ከተስማማበት 5.5 ቢሊዮን ብር ወደ 19 ቢሊዮን ብር ከፍ በማድረግ እንዲከፈለው መጠየቁን አስረድተዋል፡፡
በዚህም የተነሳ በቅርቡ በተካሄደው የአስፈጻሚ አካላት የ2015 ዓ.ም. አንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ላይ ድርድሩ አልቆ ግንባታው እንዲከናወን የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ፣ የቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስትሩ ባሉበት፣ እንዲሁም በቻይናው ሥራ ተቋራጭ በኩል የቻይና ኤምባሲ አገራቸውን ወክለው ቀርበው ለሁለት ጊዜ ውይይት ተደርጎ ከተጠየቀው አጠቃላይ 19 ቢሊዮን ብር ወደ 14 ቢሊዮን ብር ዝቅ ማለቱን፣ ነገር ግን መንግሥት አሁንም ከ13 ቢሊዮን ብር ዝቅ ባለ ዋጋ መስማማት እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡
‹‹ከዚህ በኋላ ፕሮጀክቱ መዘግየት ስሌለበት በመጨረሻ ዋጋ ላይ ድርድርና ውይይት ተደርጎ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ዝግጅት እያደረግን ነው፤›› ያሉት መስፍን (አምባሳደር)፣ ፕሮጀክቱ ግዙፍ በመሆኑ ኮሚቴ ተዋቅሮ ከቻይና አምባሳደር፣ ከፕሮጀክት አማካሪና ኮንትራክተሩ ጋር ቀጣይ ድርድር እንዲደረግ መመርያ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ለቋሚ ኮሚቴው ምናልባት ይህ ተቋራጭ አስቸጋሪ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነና መስማማት ካልተቻለ ወደ ሌላ አማራጭ የሚኬድ ከሆነ፣ ‹‹የሚመጣውን ተቋራጭ ለመቆጣጠርና ፕሮጀክቱን ለመከታተል ለማቋቋም ሐሳብ ስላለ የፓርላማው የቋሚ አባላት የተካተቱበት ኮሚቴ ለማቋቋም እየሠራን በመሆኑ ታግዙናላችሁ፤›› ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቀሰሙ ማሞ በበኩላቸው፣ ሚኒስቴሩ ፕሮጀክቱ እዲጠናቀቅ የሄደበት ርቀት የሚደነቅ እንደሆነ፣ ነገር ግን ከተቋራጩ ጋር ውል ማቋረጥ አደጋ እንዳለውና ሌሎች ተቋራጮችንም የልብ ልብ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ውሳኔ ይሆናል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ኮንስትራክሽን በባህሪው አዋጭ የሚሆነው ግንባታ ከጀመረው ተቋራጭ ጋር መጨረስ እንጂ፣ ውል አቋርጦ እንደ አዲስ መጀመር በራሱ ሌላ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል ያዋጣል በተባለው ዋጋ ተደራድሮ መጨረስ እንዲሚሻል አሳስበዋል፡፡
የስታዲየሙ ግንባታ በታኅሳስ 2008 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ 62 ሺሕ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው ነው፡፡ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በ2.4 ቢሊዮን ብር መጠናቀቁ ይታወሳል።