Wednesday, November 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዳማ ከተማ ግንባታ ጨርሰው ሥራ ባልጀመሩ 21 ባለሀብቶች ላይ ዕርምጃ ተወሰደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዳማ ከተማ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለመሰማራት መሬት ወስደውና መጋዘን ገንብተው ወደ ሥራ ሳይገቡ ከአራት ዓመታት በላይ በቆዩ 21 ባላሀብቶች ላይ ዕርምጃ መወሰዱ ተገለጸ፡፡

በከተማዋ ከኢንቨስትመንት ፍሰት ጋር ተያይዞ ነባር ባለሀብቶችን በመደገፍና ያሉባቸውን ችግሮች ፈቶ ወደ ምርት እንዲገቡ በማድረግ እንዲሁም አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሠራ እንደሚገኝ ለሪፖርተር ያስረዱት የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ፣ መሬት ወስደው ወደ ሥራ ያልገቡና ድጋፍ ተደርጎላቸው ባልተሻሻሉት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታውቀዋል፡፡

ኢንቨስትመንት የወጪና ገቢ ባህሪ ቢኖረውም ከአራት ዓመታት በላይ ወደ ሥራ ያልገቡና የቆዩ፣ መጋዘን ብቻ ሠርተው ሲያከራዩ የነበሩ ባለሀብቶች ዕርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በፍጥነት ወደ ሥራ ባለመግባታቸው ዕርምጃ የወሰደባቸው ባለሀብቶቹ በርካታ ቢሆኑም፣ 21 የሚሆኑት ልዩ የሆኑና መጋዘን ገንብተውና ጨርሰው በመቶ ሺዎችና በሚሊዮን ብር የሚያከራዩ መሆናቸውን አቶ ኃይሉ አስረድተዋል፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች ሙሉ በሙሉ ግንባታ ጨርሰው ማሽነሪዎችን ማስገባት እያለባቸው ያላስገቡ መሆኑ ተገልጾ፣ ከዓምና ጀምሮ ባለሀብቶቹ ላይ ዕርምጃ የመውሰድ ሒደቱ እንደተጀመረና በተያዘው ሩብ ዓመት ሙሉ በሙሉ በደብዳቤ ተገልጾላቸው መጠናቀቁ ታውቋል፡፡ ባለሀብቶቹ የተሰጣቸው መሬት ተነጥቆ ለሌላ ባለሀብት የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ እንደሆነም አቶ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡

በባለሀብቶቹ ላይ ዕርምጃ የተወሰደው ተደጋጋሚ ጥናትና ውይይቶች ተደርገው፣ ሌሎቹም እንዲማሩበት የተወሰደ የመጀመርያ ዙር ዕርምጃ እንደሆነ አቶ ኃይሉ አስታውቀዋል፡፡

ኢንቨስትመንትን በተመለከተ የከተማ አስተዳደሩ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች የመጀመርያው ነባር ባለሀብቶችን መደገፍና ያሉባቸውን ችግሮች ተፈቶ ወደ ምርት እንዲገቡ ማድረግ ሲሆን፣ በዚህም ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተገናኘ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር እንዲቀረፍ መደረጉ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ለኢንቨስትመንት ማበረታቻ የሆነውን መሬት በማቅረብ ረገድ በተለይም በሥራ ውስጥ የሚገኙና ለማስፋፊያ አገልግሎት የጠየቁ ባለሀብቶች መሬት ተፈልጎ በፍጥነት እንዲሰጣቸው መደረጉን ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

አቶ ኃይሉ እንደተናገሩት፣ በ2014 ዓ.ም. ብቻ 81 አዳዲስ ባለሀብቶች አዳማ ላይ እንዲያለሙ መሬት የቀረበ ሲሆን፣ በተጨማሪም 34 የሚደርሱ አርሶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡ ከዚህም በሻገር በአራት ማኅበራት የተደራጁ አርሶ አደሮች እንዲሁም ሥራ መጀመራቸው ተገልጿል፡፡

የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማስፋት እየተሠሩ ከሚገኙ ተግባራት ውስጥ መሬት እያላቸው፣ ሀብትና ገንዘብ እያላቸው ወደ ኢንቨስትመንት እንዳይገቡ ባይተዋር ተደርገው የቆዩ አርሶ አደሮችን በተናጠልም ሆነ በጋራ እንዲሠሩ እየተደረገ ያለው ተጠቃሽ መሆኑን አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ ዙሪያ ያለው አርሶ አደር ወደ ኢንቨስትመንት መግባቱ ለሌሎችም ባለሀብቶች ዋስትና ነው ያሉት የአዳማ ከተማ ከንቲባ፣ ይህም የኢንቨስትመንት አዳጋችነት እንዳይመጣ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ትልቁ የትኩረት አቅጣጫው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይም ኢንቨስትመንት ተጠቃሹ ጉዳይ እንደሆነ ተገልጾ፣ አዳማን በብዙ አማራጭ ማየት ቢቻልም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ማገዝ ቀዳሚው ጉዳይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ በሌላ በኩል የአምራች ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን መደገፍና ከተማዋን የሁሉም ማዕከል ማድረግ ሌላው ጉዳይ መሆኑን አቶ ኃይሉ አስታውቀዋል፡፡

የከተማዋ ሰላምና ደኅንነት ካልተረጋገጠ የትኛውንም ኮንፍረንስና ተዛማጅ አገልግሎቶችን ማቅረብ አዳጋችነቱን የሚናገሩት ከንቲባው፣ በዚህም ዙሪያ አስተዳደሩ እየሠራበት ይገኛል ብለዋል፡፡

ለኢንቨስትመንት በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ትልቁ ፈተና የነበረው የተሳለጠ አገልግሎት አለመቅረቡና ባለሀብቱ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ማለፉ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ አንፃር በከተማው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተዘርግቶ ማንኛውም ባለሀብት የመሬት አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎቹንም በአንድ ማዕከል እያገኘ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች