Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዳማ የ5ጂ አገልግሎት የጀመረው ኢትዮ ቴሌኮም በሌሎች ከተሞችም ጥናት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአዲስ አበባ ውጭ የ5ጂ ኔትወርክ አገልግሎትን በአዳማ ከተማ ያስተዋወቀው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በተጨማሪ የክልል ከተሞች ኔትወርኩን ለመዘርጋት የዳሰሳ ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

ከአዳማ ውጪ በሌሎች ከተሞችም የ5ጂ አገልግሎት ለማስጀመር የዳሰሳ ጥናት እየሠራ መሆኑን ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም፣ የ5ጂ ኔትወርክ በከተሞቹ ምን ሊሠራ ይችላል? የሚለው አንዱ የዳሰሳ ጥናቱ የሚመለከተው ጉዳይ መሆኑን ገልጿል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. የ5ጂ የሞባይል ቴክኖሎጂ በቅድመ ሙከራ በአዲስ አበባ ከተማ መጀመሩን ይፋ ባደረገበት ጊዜ፣ በኔትወርኩ ካሉት አጠቃላይ ደንበኞች 110 ሺሕ ያህሉ አገልግሎቱን መጠቀም የሚችሉበት የሞባይል ቀፎ ባለቤት እንደሆኑ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ለኢትዮ ቴሌኮም የ5ጂ ሙከራ የስፔክትረም ምደባ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ምደባውም ለሙከራ መሆኑንና ይህም በጊዜ የተገደበና ክፍያ የማይጠየቅበት እንደሆነ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡ ነገር ግን የሙከራው ጊዜ አልቆ መደበኛው ምደባ ሲደረግ ክፍያም እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ከአዳማ ቀጥሎ በየትኛው የክልል ከተማ የ5ጂ አገልግሎት እንደሚያስጀምር አልተገለጸም፡፡ ባለፈው ዓመት የ5ጂ ስፔክትረም ምደባ የተደረገለት ለአንድ ዓመት የሙከራ ጊዜ እንደሆነና የሙከራ ምደባው የተሰጠውም በአዲስ አበባ፣ በአዳማና በሐዋሳ ከተሞች ሙከራ እንዲያደርግ መሆኑን ባልቻ (ኢንጂነር) ገልጸው ነበር፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም 99 በመቶ የኔትወርክ ሽፋን ያለው ቢሆንም ከጫፍ እስከ ጫፍ የ5ጂ አገልግሎቱን እንደማያስፋፋ የገለጹት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ በዓላማና በምክንያት የት አካባቢ ቢደረግ ችግር ይፈታል? ዕሴት ይጨምራል? የሚለው እየታየ የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የ5ጂ አገልግሎት ወሳኝ ተልዕኮ ላላቸውና በተመሳሳይ ወቅት መከናወን ላለባቸው ሥራዎች ማለትም ግብርና፣ ሕክምና፣ የማዕድን ፍለጋና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡

በአዳማ ከተማ የ5ጂ አገልግሎትን በሙከራ ደረጃ ከማስጀመሩ ውጪ ኩባንያው የአዳማ ከተማን ስማርት ሲቲ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት፣ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ፈጽሟል፡፡

በፕሮጀክቱ የአዳማ አስተዳደር የአይሲቲ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌ ብር ሥርዓት በመፈጸም የመንግሥት አገልግሎቶች የሚሰጥበት ሲሆን፣ ይህም የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያገኙትን አገልግሎት የሚያሻሽል እንዲሁም የአስተዳደሩን የአስፈጻሚነት አቅም የሚያሳድግ እንደሆነ በስምምነቱ ወቅት ተብራርቷል፡፡

በተያያዘም ኢትዮ ቴሌኮም በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የቴሌኮም አገልግሎት ያስጀመረባቸውን አካባቢዎችን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ቀደም ብሎ አገልግሎቱ ከጀመረባቸው ቆቦ፣ ሮቢት፣ ዞብል፣ ጎቢዬና ዋጃ አካባዎች በተጨማሪ አላማጣ፣ ኮረምና ዓዲ አርቃይ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ኩባንያው የጥገና ባለሙያዎችን አሠማርቶ የተቋረጠውን አገልግሎት ካስጀመረ ሁለት ሳምንታት እንዳስቆጠረ አስታውቆ፣ በቀሪ አካባቢዎች የሚደረገው ጥገና እግር በእግር የሚቀጥል መሆኑን ገልጿል።

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተደረገው የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት የሰላም ስምምነት፣ የተቋረጡ አገልግሎቶችን ማስጀመር ስምምነት ከተደረሰባቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች