የኢትዮጵያ መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር የታሸጉ ውኃ አምራቾች ይጠቀሙበት የነበረውን የውኃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ጠርሙስ ማቅለሚያ (ማስተርባች) በማቆማቸው፣ ኅብረተሰቡ ሙሉ በሙሉ በነጭ የውኃ ማሸጊያ ብቻ ያሉ ምርቶችን መጠቀም እንዳለበት የኢትዮጵያ ቤቨሬጅስ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር አስታወቀ፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌትነት በላይ (ኢንጂነር) ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት የታሸገ ውኃ አከፋፋዮች፣ ቸርቻሪዎችና ባለሱቆች በአሁኑ ጊዜ የታሸጉ ውኃ አምራቾች ያለ ማስተርባች የሚያቀርቡትን የነጭ ፕላስቲክ ጠርሙስ ብቻ ለኅብረተሰቡ ማሠራጨት አለባቸው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የታሸገ የውኃ ዋጋን ለመቀነስ ከሽያጭ ላይ ተሰብስቦ የሚከፈለውን አሥር በመቶ ኤክሳይስ ታክስ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲያነሳ ጠይቀዋል፡፡
የታሸጉ ውኃ አምራቾች ሲጠቀሙበት የነበረውን የውኃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ጠርሙስ ማቅለሚያ (ማስተርባች) በማስቀረቱ፣ አምራቾች ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሲጠቀሙበት የነበረውን በዓመት ውስጥ እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ወጪ እንደሚያስቀር ጌትነት (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡
ፕላስቲክን መልሶ በመጠቀም (Recycle) በማድረግ እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን ከፕሪፎርሙ (ጥሬ ዕቃው) ጋር በመቀላቀል መልሶ መጠቀም የሚቻል መሆኑን፣ ለአምራቾች ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አክለዋል፡፡
የፕላስቲክ ጠርሙሱ ተፈጭቶና ተቀነባብሮ ወደ ውጭ አገር በሚላክበት ወቅት ቀድሞ ከነበረው (ማስተርባች በነበረበት ወቅት)፣ በአንድ ዓመት ውስጥ በአማካይ በአንድ ቶን እስከ 15 ዶላር ተጨማሪ ገቢ እንዲገኝ ያግዛል ሲል ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
ማስተርባቹ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ሲያባብስ የነበረ ከመሆኑም ባሻገር አገር ውስጥ መልሶ ለመጠቀም (Recycle) ለማድረግ አመቺ አለመሆኑ፣ የማምረቻ ወጪን የሚጨምር መሆኑን አካባቢን በይበልጥ ይበክል እንደነበር እንዲሁም አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ላይ ያልተካተተበት መሆኑም ሲነገር ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቤቨሬጅስ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር በሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም. ከቀድሞው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሕጋዊ ሰውነት በማግኘት፣ የማኅበሩን አባላት ችግሩን ለመፍታትና ለአገሪቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ የተቋቋመ ነው፡፡
ማኅበሩ በአሁኑ ጊዜ በሥሩ ከሚገኙት የታሸገ ውኃ አምራቾች፣ የለስላሳ መጠጥ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ አቀነባባሪዎችና አምራቾች ውስጥ 134 ያህሉ አባላቱ እንደሆኑ ታውቋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የውኃ መያዣ የፕላስቲክ ጠርሙስን ሰማያዊ ቀለም እንዲይዝ የሚያደርገውን ይህን ጥሬ ዕቃ በአገልግሎት ላይ እንዳይውል ውሳኔ ያሳለፈው፣ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነው።
ከወራት በፊት በተላለፈው ውሳኔ መሠረት የታሸገ ውኃ አምራች ፋብሪካዎች ከጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ምርቱን መጠቀም አቁመዋል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ተፈጻሚነቱን የሚቆጣጠር ሲሆን፣ የቁጥጥር ሥራውን በከተማ አስተዳደሩና በየክልሎቹ የአካባቢ ጥበቃ ቢሮዎች እንዲያከናውን ለባለሥልጣኑ ኃላፊነት ደብዳቤ እንደተሰጠው ማኅበሩ ገልጿል፡፡