Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሰላም ስምምነቱ መሬት ወርዶ ኢኮኖሚውን ያትርፍ!

አገራችንን በብዙ ወደኋላ የመለሰው የሰሜኑ ጦርነት እንዲያበቃ በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነት እንደ ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ‹‹እንኳን ለዚህ በቃን›› የምንልበት ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ ይህንን ስምምነት ወደ መሬት ለማውረድ ቀላል ባይሆንም፣ ከጦርነት የማይሻል ነገር ስለሌለ ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ በምንም መስዋዕትነት ለበጎ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ የተከፈለውን ዋጋ በማሰብ ደግሞ ወደ ጦርነት ላለመግባት በሚያስችል ጥበብ የተሞላበት ዕርምጃ መጓዝ ይኖርብናል፡፡ 

ተደጋግሞ እንደተገለጸው ይህ ጦርነት ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ወንድምና እህቶቻችንን ገብረንበታል፡፡ በመከራ ያፈራነውን ንብረት አውድሞብናል፡፡ ደሃው ገበሬ እንደ ትልቅ ሀብት የሚቆጥረውን እንስሳቱን ጭምር ያጣበት ነው፡፡ ካዝናችንን አራቁቶብናል፡፡ ጠቅለል ብሎ ሲታይ የአገር ኢኮኖሚውን አንኮታኩቷል፡፡ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ተደማምረው የተጫነንን የኑሮ ውድነት የበለጠ እንዲብስ ያደረገውም ይህ ጦርነት ነውና ጦርነቱን ለማቆም ዛሬ የተደረሰበት ስምምነት ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው፡፡ 

ሰላም ለማውረድ የተደረሰው ስምምነት በትክክል መሬት ላይ ከዋለ የጥይት ድምፅ ከማቆም ባሻገር፣ ኢኮኖሚያዊ ስብራታችንንም ለመጠገንና ወደ ተሻለ ዕድገት ይወስደናል፡፡ በእርግጥ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመጠገንና የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ከፊታችን ብርቱ ሥራ ይጠብቀናል፡፡ የፈራረሱ መሠረተ ልማቶችን ለማበጀትና ወደ ቀድሞው ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ቀላል የማይባል መዋዕለ ንዋይ ይፈልጋሉ፡፡ የሚያስፈልገን መዋዕለ ንዋይም ቢሆን እንዲህ ቀላል አይሆንም፡፡ 

ነገር ግን ከሰላም የሚበልጥ የለምና ለዚህ የምናፈሰው ገንዘብና ጉልበት የምንቆጭበት አይሆንም፡፡ ነገር ግን ሁሉ ነገራችን በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም ብቻ የተወሰነ መሆን የለበትም፡፡ ዳግም ጦርነት እንዳይነሳና አላስፈላጊ ግጭቶች እንዳያንሰራሩ ለማድረግ ሊሠሩ የሚገባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡

በተሳሳተ ትርክት ውስጥ ያሉ ወገኖችን ወደ እውነታው መመለስ፣ ሰላም ለማስፈን በእጅጉ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ዘለዓለም በጦርነት የሚበላ ኢኮኖሚ እንዲኖረን መፍቀድ የለብንም፡፡ በተለይ ሄዶ ሄዶ ጠረጴዛ ላይ ለሚያልቅ ጉዳይ የምናጣው የሰው ነፍስ በእጅጉ ሊያሳዝነን ይገባል፡፡ ሰላም ለማምጣት በአንቀጽ ተከፋፍሎ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ በመፈረም ጦርነትን ማስቀረት እየቻልን በእብሪት የተፈጸመው ጥፋት ቢቆጨንም፣ ሰላም ለማምጣት የተገኘውን ዕድል በብልኃት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ለማንኛውም ሰላም ለማውረድ ዛሬ የደረስንበት ደረጃ የአገራችንን ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ ያደርጋል፡፡ አገር ለማዳን ሲባል ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ አዘንብሎ የነበረው ትኩረት፣ አሁን የተጎዳ ኢኮኖሚያችንን ለማከም ጊዜ ይሰጠናል፡፡ ለሸክም እየከበደ ያለውን የዋጋና የኑሮ ውድነት ለማቃለል በሚረዱ ተጨባጭ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንዲሰጥም ያግዛል፡፡ 

ስለዚህ እስካሁን መንግሥት ያለበት አጣብቂኝ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ከዚህ በኋላ የሚተገብራቸው ሥራዎች ግን ወሳኝ ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር ሥርዓት ያስፈልገዋል፣ ሕገወጥነትን መከላከል ያሻል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ስብራቱን ሊጠግኑ የሚችሉ አዳዲስ አሠራሮች መዘርጋትንም የሚጠይቅ መሆን ይገባል፡፡ 

በታሪክ አጋጣሚዎች የሚገኙ እንዲህ ያሉ መልካም ዕድሎችን ተጠቅሞ አገራዊ ኢኮኖሚን ለማሳደግ በሚችሉ በጥናት ላይ የተመሠረተ አዳዲስ የፖሊሲ ዕርምጃዎች ሁሉ ያስፈልጋሉ፡፡

በጦርነት ሰበብ ወይም ጦርነቱ በፈጠራቸው ተፅዕኖዎች የደረሰውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለማስተካከል ደግሞ ኃላፊነቱ የአንድ የመንግሥት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የየድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ 

የመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪያችን ሳይቀር የተመናመነው በጦርነቱ ሰበብ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ በብዙ መስዋዕትነት የተገኘውን አሁናዊ የሰላም ስምምነት መሬት ላይ ለማውረድ ከሚያስፈልጉን ነገሮች አንዱ የውጭ ምንዛሪ ነውና ይህንን የውጭ ምንዛሪ ግኝታችንን ከፍ ለማድረግ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ ወደ አገር እንዲልኩ ማድረግ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ይህንን ማድረግ በሰላም ስምምነቱ ሰነድ ላይ የተቀመጡ ቁልፍ ጉዳዮችን በቶሎ ለማስፈጸም ከመርዳቱም በላይ፣ በዋጋ ንረት እየተነገርን የምንቆይበትን ጊዜ ሊያሳጥርልን ይችላል፡፡ 

አሁን የተደረገው የሰላም ስምምነት በአግባቡ እንዲተገበር በማድረግ ከኢኮኖሚዊ ቀውሶች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት በተለይም የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ሕጋዊ አሠራሮችን ማጠንከር ፈፅሞ ሊዘነጋ አይገባም፡፡

ይህ አጋጣሚ ሕጋዊ አሠራሮችን እስከመጨረሻው ለማስከበር የሚተጋበት መሆን ካልቻለ ከችግር አንወጣም፡፡ በተለይም የገበያ ሥርዓቱን ጤናማነት ለማስጠበቅ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ያዝ ለቀቅ እየተባለ መሄድ የለበትም፡፡ በግንባር ከተደረገው ጦርነት ባልተናነሰ ከዚህ በኋላ መንግሥት ሊፋለመው የሚገባ ሌላው ጉዳይ ደግሞ ሌብነት ነው፡፡ እስካሁን ‹‹የመንግሥት ትኩረት አገር በማዳን ላይ ያተኮረ በመሆኑ፣ በውስጥ የሚገኙትን ሌቦች ለመቆጣጠር አልቻለ ይሆናል›› በሚል ነው የወስደነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሌቦች ላይ በተግባር የሚታይ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡

ዛሬ ከጦርነቱ በመለስ የዚህን አገር ኢኮኖሚ ካቃወሰ የዋጋ ንረትን አብሶ ሸማቾች በብዙ የተማረሩት እኮ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ሊሠሩ ባልቻሉ የመንግሥት አሠራሮች ጭምር መሆኑ መታሰብ አለበት፡፡ 

ገበያው እንዲረጋጋ የሚደረጉ ጥረቶችን ሁሉ ረዥም እጅ ያላቸው ከታች እስከ ላይ ያሉ ሹማምንት የሚፈጥሩት ችግር ጭምር በመሆኑ መንግሥት ሕጋዊ አሠራሮችን ለማስፈንና ሌቦችን ለማፅዳት ይህንን ጊዜ ሊጠቀም ይገባል፡፡ ዜጎች የጠነከረባቸውን የኑሮ ውድነት ችለው የቆዩት መንግሥት ያለበትን ችግር ጭምር በመገንዘብ ነውና በዚህ ረገድ መንግሥት የሕዝብንም ትብብር ጠይቆ ሕግ ያስከብር፣ ሌቦችን ይዞ ያሳየን፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት