Wednesday, September 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የጦርነት ቀንበር ይሰበር!

በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ ሰንብቶ በፍፁም ሊታሰብ በማይችል ሁኔታ ለሰላም ስምምነት የበቃው ንግግር ተጠናቆ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲጀመር፣ የስምምነቱን ነጥቦች እያጣቀሱ ፀጉር ስንጠቃ ውስጥ የገቡ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ይስተዋላሉ፡፡ በንፁኃን ደም የጨየቀው አዳፋና አስከፊ ጦርነት ምዕራፉ የሚዘጋው፣ ጦርነትን በሩቅ ሆነው እንደ ፊልም የሚመለከቱ ራስ ወዳዶችና አስመሳዮች አደብ ሲገዙ ነው፡፡ የሰላም ንግግሩን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ትኩረት ሲከታተል የነበረው፣ አገሩ ከገባችበት ቀውስ ውስጥ በፍጥነት ወጥታ ሲናፍቀው የነበረው ዕፎይታ እንዲፈጠርለት ነው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው፣ አካላቸው የጎደለባቸው፣ ንብረታቸውን ያጡ፣ ከጎጆአቸው ተፈናቅለው የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በየሜዳው የተበተኑና ለከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የተዳረጉ ወገኖች ዕንባና ደም ምንም የማይመስላቸው ከድርጊታቸው ይታቀቡ፡፡ በሐሰተኛ ወሬ ሕዝባችንን ሰላም መንሳት ይብቃ፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም የምታገኘው የጦርነቱ ቀንበር ሲሰበር ነው፡፡

የሰላም ንግግሩ እንዲህ በአጭር ጊዜ ተቋጭቶ ስምምነት ላይ ይደረሳል ብሎ ለማሰብ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ከሰላም ንግግሩ በኢትዮጵያ እንደገና ሰላም የሚያሰፍን ተስፋ ይገኛል ብሎ መገመትም አዳጋች ነበር፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያን አውዳሚ ጦርነት በተፋጠነ ጊዜ ሊያስቆም የሚያስችል ትጥቅ የመፍታትና ግጭት የመግታት ስምምነት ላይ ይደረሳል ለማለት አይታሰብም ነበር፡፡ ስምምነቱ ዘላቂ ሰላምና ዕፎይታ እንዲያመጣ ብዙ ተግባራት መኖራቸው ዕሙን ቢሆንም፣ አሁንም ቀደም ሲል ከነበረው የጥፋት አስተሳሰብ መላቀቅ የግድ መሆን አለበት፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ሁለት ታጣቂ ኃይል እንደማይኖር ስምምነት ላይ ከተደረሰ፣ ለአገርና ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲባል ተግባራዊነቱን ማፋጠን ይገባል፡፡ ከእንግዲህ በኋላ በሕዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ‹‹የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ›› ዓይነት ምክንያት ድርድራ አያስፈልግም፡፡ የተጎዱ ወገኖች ምግብ፣ መድኃኒትና ዕፎይታ ያግኙ፡፡ የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ተስፋ ይሁን፡፡

የሰላም ስምምነቱ ፀንቶ ኢትዮጵያ ከአሰቃቂው ጦርነት ውስጥ መውጣት የምትችለው፣ በግራም ሆነ በቀኝ ያሉ ወገኖች ከጀብደኝነት አስተሳሰብ ሲላቀቁ ነው፡፡ ሕፃናት፣ አዛውንት፣ ነፍሰ ጡርና አጥቢ እናቶች፣ አቅመ ደካሞችና ሕመምተኞች ሳይቀሩ ለሞትና ለከፋ ጉዳት የተዳረጉበት ምዕራፍ መዘጋት አለበት፡፡ በስምምነቱ መሠረት ያላንዳች ማንገራገር ሰላም እንዲሰፍንና ዕፎይታ እንዲፈጠር፣ በመደበኛው ሚዲያም ሆነ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች የሚሳተፉ ወገኖች ከአፍራሽ እንቅስቃሴዎች መታቀብ አለባቸው፡፡ ከእሳቱ ርቆ ሌሎችን ወደ እሳቱ የመገፍተር አደገኛ አባዜ መገታት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሮች የሚፈቱት በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲሆን ጥርጊያውን ማመቻቸት እንጂ፣ ልዩነት በተፈጠረ ቁጥር ጠመንጃ መወልወልና ይዋጣልን ማለት ማብቃት ይኖርበታል፡፡ የሰላም ስምምነቱ የሴረኞችና የአሻጥረኞች ሰለባ እንዳይሆንና ሌላ ፍላጎት ባላቸው የውጭ ኃይሎች እንዳይጠለፍ ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ በሰላም ዕጦት ምክንያት የተሰቃዩና ተስፋ የቆረጡ፣ በሴረኞች ምክንያት ተስፋቸው አይደብዝዝ፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት አውዳሚ ጦርነት ሊጠቀስ የሚችል ትምህርት ቢኖር ከዕልቂትና ከውድመት ትርፍ አለመኖሩን ነው፡፡ ይልቁንም ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወትና የደሃ አገር አንጡራ ሀብት በእሳት ማቃጠል ነው፡፡ በዕብሪተኞችና በጥጋበኞች ምክንያት ንፁኃንን ያለ ኃጢያታቸው መፍጀት፣ ማሰቃየት፣ ንብረታቸውን ማቃጠል፣ ማፈናቀልና ሰብዓዊ ክብርን በማዋረድ ፆታዊ ጥቃት መፈጸም፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ማድረስና የተፈጠሩበትን ቀን ማስረገም ሊቆም ይገባል፡፡ ጦርነት በማስነሳት ይህንን ሁሉ ዕልቂትና ውድመት ለማድረስ የሚያስችል ምንም ዓይነት ምክንያት ሳይኖር፣ በስተመጨረሻ የሰላም ስምምነት ለመፈረም መብቃቱ ሲታሰብ ሕመሙ ከሚታገሱት በላይ ነው፡፡ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የነበረው ምልጃ፣ ተማፅኖና በዕንባ የታጀበ ልመና ተንቆ የግለሰቦችን ፍላጎት ለማስፈጸም የተሄደበት ርቀት ያስቆጫል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነውረኛ ድርጊት ከኢትዮጵያ ምድር በፍጥነት መወገድ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም ተጎናፅፋ ሕዝቧ በነፃነትና በእኩልነት ይንቀሳቀስ፡፡

ጦርነቱ ቆሞ ሰላምና ዕፎይታ የሚያስፈልገው በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ሕይወታቸው ተርፎ ምግብና መጠለያ ያጡ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም፣ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ለመጠገንና የተፈጠረውን ቁርሾ በማስወገድ የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር ነው፡፡ በሰላም ስምምነቱ መሠረት ቀሪዎቹ ተግባራት መከናወን ካልቻሉ የሚከተለው የተለመደው ዕልቂትና ውድመት ነው፡፡ በርቀት ሆኖ እሳት ማቀጣጠልና ስምምነቱን ለማጣጣል መሞከር የሚጠቅመው፣ የኢትዮጵያን መዳከምና መፈራረስ የሚመኙ ታሪካዊ ጠላቶችን ብቻ ነው፡፡ አሁንም ከአገርና ከሕዝብ በላይ የሚቀድም ምንም ዓይነት ፍላጎት መኖር የለበትም፡፡ ጥጋበኞች በሚያስነሱት ግጭት ንፁኃን መጎዳት የለባቸውም፡፡ በሕዝብ ስም እየቆመሩ አገርን ማተራመስ ያስከተለው መዘዝ፣ ወደፊት ከፍተኛ ዋጋ የሚከፈልበት ነው፡፡ በትክክል ቁጥራቸውን ለመግለጽ የሚያስቸግር ኢትዮጵያውያን ያለቁበትና ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት ጦርነት፣ ከኢትዮጵያ ምድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ በማድረግ አስከፊውን የጥፋት ምዕራፍ መዝጋት ይገባል፡፡ አውዳሚው ጦርነት እንደገና እንዳያገረሽ በሕግና በሥርዓት መኖር የሚያስችል ምኅዳር መፈጠር አለበት፡፡ 

ኢትዮጵያውያን በዚህ ወቅት ከምንም ነገር በላይ ልብ ማለት የሚገባቸው ጉዳይ፣ ከጀብደኝነት አስተሳሰብ በመላቀቅ በአገራቸው ሰላም በዘላቂነት እንዲሰፍን መተባበር ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ በተደጋጋሚ መልካም አጋጣሚዎች የመከኑባት አሳዛኝ አገር ናት፡፡ በተደጋጋሚ ከስህተቶች ለመታረም ፈቃደኛ ባልሆኑ ጀብደኞች ምክንያት በርካታ ዕድሎች አምልጠዋታል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን በፍፁም መባል አለበት፡፡ የአገር ጉዳይ ለማንም የማይተው በመሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን በዋና ዋና ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ተሳትፎአቸው ሲቀዘቅዝ ጥቂቶች መድረኩን ይረከቡና መጫወቻ ያደርጉታል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ላይ የተደረሰው በከፍተኛ መስዋዕትነት መሆኑን በመገንዘብ፣ ከአሁን በኋላ ጥጋበኞችና ዕብሪተኞች በአገር ዕጣ ፈንታ ላይ እንዳይወስኑ መደረግ አለበት፡፡ የአሁኑን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሰላም ተስፋ ያብብ፡፡ ከግልና ከቡድን ጥቅም በላይ የአገርና የሕዝብ ዘለቄታዊ ህልውና ይቅደም፡፡ ጀብደኝነት፣ ዕብሪትና ጥጋብ ከኢትዮጵያ ይወገዱ፡፡ የጦርነት ቀንበርም ተሰብሮ ይውደቅ! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...