Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ለውጭ ባንኮች የሚሰጠው የባንክ ሥራ ፈቃድ በቁጥር የተገደበ እንደሚሆን ታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የውጭ ዜግነት ያለው የባንክ ሠራተኛ ፖለቲካ ላይ ተሳትፎ ከተገኘ ይሰናበታል 

መንግሥት ባፀደቀው ፖሊሲና ይህንን ተከትሎ በተረቀቀው የባንክ ሥራ አዋጅ ማሻሻያ መሠረት፣ ለውጭ ባንኮች የሚሰጠው የባንክ ሥራ ፈቃድ በቁጥር የተገደበ እንደሚሆን ታወቀ።

ሪፖርተር ያገኘው የፖሊሲ ሰነድና ይህንን ሰነድ መነሻ አድርጎ የተረቀቀው የባንክ ሥራ አዋጅ ማሻሻያ እንደሚጠቁመው፣ መንግሥት ለረዥም ዓመታት ዝግ የነበረውን የአገር ውስጥ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ባንኮች ክፍት ሲያደርግ የሚመጡትን የውጭ ባንኮች በሙሉ ተቀብሎ ፈቃድ የሚሰጥ አይሆንም። 

ይልቁንም ልክ የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ውድድር ክፍት ሲያደርግ፣ ለሁለት የውጭ ቴሌኮም ኩባንያዎች ብቻ ፈቃድ ለመስጠት እንደወሰነው ሁሉ፣ የባንክ ዘርፉንም ለውጭ ውድድር ክፍት ሲያደርግ ለመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ፈቃድ የሚሰጠው ለተወሰኑ የተመረጡ የውጭ ባንኮች እንደሚሆን ሰነዶቹ ያመለክታሉ። 

በፀደቀው የፖሊሲ ሰነድ መሠረት ፈቃድ ማግኘት የሚችሉት የኢትዮጵያ ንዑስ ባንክ ለማቋቋም የሚጠይቁና የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ለማቋቋም የሚጠይቁ የውጭ ባንኮች ናቸው።

በመሆኑም በተጠቀሱት ሁለት የባንክ ሥራ ዓይነቶች በእያንዳንዳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠው የባንክ ሥራ ፈቃድ ከአምስት እንደማይበልጥ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው የባንክ ፖሊሲ በግልጽ አመላክቷል።

‹‹አዲስ ፈቃድ ከመስጠት አንፃር በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከሦስት እስከ አምስት ፈቃድ ለውጭ ባንኮች ሊሰጥ ይችላል። በተመሳሳይ ቅርንጫፍ መክፈት ለሚፈልጉ ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ የውጭ ባንኮች ብቻ ሆኖ፣ እያንዳንዳቸው መክፈት የሚችሉት የቅርንጫፍ ብዛትም ከሁለት እስከ አራት ቅርንጫፎችን ብቻ ይሆናል›› ሲል የፖሊሲ ሰነዱ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ ከአምስት ዓመታት በፊት ወይም በኋላ በልዩ ሁኔታ አጢኖ ተጨማሪ የንዑስ ባንክ ወይም ቅርንጫፍ ፈቃድ እንዲሰጥ ሊወስን እንደሚችል የፖሊሲ ሰነዱ ይገልጻል። 

ይህንን መሠረት አድርጎ የተሰናዳው የባንክ ሥራ አዋጅ ረቂቅ ማሻሻያ፣ ለውጭ ባንኮች የሚሰጠው የፈቃድ ብዛት ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመርያ እንደሚወሰን ይገልጻል።

የውጭ ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ የሚሰበሰብ ወይም ተቀማጭ ገንዘብ ወይም ሌላ ዕዳ የማይሰበስብ ቅርንጫፍ እንዲከፍቱ ሊፈቀድላቸው እንደሚችል፣ ነገር ግን ሁለቱንም ዓይነት ሥራ ለመሥራት ፈቃድ እንደማያገኙ የባንክ ሥራ አዋጁ ማሻሻያ ረቂቅ ያመለክታል። 

በአዋጁ ረቂቅ ማሻሻያ መሠረት የተቀማጭ ገንዘብ የሚሰበሰብ ቅርንጫፍ ለመክፈት ያሰበ የውጭ ባንክ፣ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመርያ የሚወሰነውን አነስተኛ የካፒታል ማስያዣ ማቅረብ ይጠበቅበታል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ባንኮች መፈቀዱን ተከትሎ የውጭ ዜግነት ያላቸው የፋይናንስ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የሚቀጠሩበትን ሁኔታና የጊዜ ገደብም የፖሊሲ ማዕቀፉ ወስኗል። 

በዚህም መሠረት የውጭ ዜግነት ያላቸው የፋይናንስ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ በሚቋቋሙ የውጭ ባንኮችም ሆነ የአገር ውስጥ ባንኮች ላይ ሊቀጠሩ የሚችሉት በከፍተኛ የሥራ አመራር መደብና ለተወሰኑ ዓመታት ለማገልገል ብቻ እንደሚሆን ያመለክታል።

‹‹አንድ ባንክ ከሦስት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለሙያዎችን በሥራ አስፈጻሚነት ወይም በከፍተኛ የሥራ አመራር መደብ ወይም በልዩ ባለሙያ (ስፔሻሊስት) መደብ በኮንትራት ወይም በሌላ አገር ከሚገኝ የራሱ ተቋም በማዘዋወር በኢትዮጵያ እንዲቀጥር ሊፈቀድለት ይችላል›› ሲል የፖሊሲ ማዕቀፉ በግልጽ አመልክቷል።

ይህም የሚሆነው በሚፈለገው የሥራ መደብና ተመሳሳይ የትምህርትና የሥራ ልምድ የያዙ ኢትዮጵያውያን አለመኖራቸው ሲረጋገጥና በብሔራዊ ባንክ ሲፈቀድ ብቻ እንደሆነም የፖሊሲ ሰነዱ ይገልጻል።

ከዚህ በተጨማሪ ወደ ኢትዮጵያ በገቡ የውጭ ባንኮች ላይም ሆነ ለውጭ ባንኮችና ዜጎች የአክሲዮን ድርሻ በሸጡ የኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ ከላይ በተገለጸው መሠረት፣ የሚቀጠሩ የውጭ ዜጎች በአገር ውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተሳትፎ ማድረጋቸው ከተረጋገጠ፣ እንዲሁም የወንጀል ድርጊት ከተመዘገበባቸው ወዲያውኑ ከሥራ መሰናበት እንዳለባቸው የፖሊሲ ሰነዱ ያመለክታል።

ይህንን የፖሊሲ ሰነድ መሠረት በማድረግ የተሰናዳው የባንክ ሥራ አዋጅ ረቂቅ ማሻሻያም በአንቀጽ 10 ንዑስ 6 ድንጋጌው ላይ አካትቷል።

‹‹በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ሲሳተፍ የተገኘ ወይም እምነትን በመጣስ ወይም በማጭበርበር ወንጀሎች የተፈረደበት የውጭ ዜጋ የሥራ ውሉን ባንኮች በቀጥታ ያቋርጣሉ፣ ወይም ዳይሬክተር ከሆነ ከሥልጣን ያስወግዳሉ›› ተብሎ በረቂቅ ማሻሻያው ላይ ተካቷል።

በዚህ ረቂቅ የሕግ ማሻሻያ ላይም በአሁኑ ወቅት የባለድርሻ አካላት ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች