በአገር አቀፍ ደረጃ ማኅበረሰቡን ሱስ ያስይዛሉ ተብለው የተቀመጡ በርካታ ማነቃቂያዎች ቢኖሩም፣ ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶችን ለማነቃቂያነት የሚጠቀሙ መኖራቸው ይነገራል፡፡
ሱስ የማስያዝ ባህሪ ያላቸውን መድኃኒቶች አምራች የሚባለው የማኅበረሰብ ክፍል እንደ መዝናኛነት እንደሚጠቀመውም ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ‹‹ትራማዶል›› የተሰኘው ለሕመም ማስታገሻ የሚጠሰው መድኃኒት ከሐኪም ትዕዛዝ ውጪ የሚጠቀሙ ዜጎች መበራከታቸው ሲገለጽ ይስተዋላል፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ጠቅላላ ሐኪምና መምህር የሆኑት ናሆም ግሩም (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ትራማዶል ቀለል ላሉ ሕመሞች የሚወሰድ መድኃኒት አይደለም፡፡ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ሕመም ያላቸው ሰዎች የሚታዘዝ ነው፡፡ ‹‹ትራማዶል›› ኦፖይድ የተሰኘ የመድኃኒት ካታጎሪ የሚመደብ ሲሆን፣ ያላግባብ ወይም ለረዥም ጊዜ ከሕክምና ትዕዛዝ ውጪ ሲወሰድ ‹‹ሱስ›› ያስይዛል፡፡
በመድኃኒት የሚመጣ ሱስ
ናሆም (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ መድኃኒት በአግባቡ አለመውሰድ ሙሉ በሙሉ የተከለከሉ በመውሰድ የሚመጣ የሱስ ዓይነት መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከታዘዘላቸው መጠን በላይ መውሰድና ቀኑን ረዘም አድርጎ መጠቀም ለሱስ ያጋልጣል፡፡ መድኃኒትን ከሕክምና ውጪ የሚጠቀሙ ዜጎች በይበልጥ ለሱስ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በ‹‹ትራማዶል›› ሱስ ውስጥ የሚገቡት በአግባቡ ባለመጠቀም ምክንያት ቢሆንም፣ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትራማዶልን ለሕክምና ከሚጠቀሙት ይልቅ ሱሳቸውን ለማበርከት የሚጠቀሙ ዜጎች ቁጥር አይሏል፡፡
ወጣቶች ትራማዶልን ለምን ይጠቀማሉ?
መድኃኒቱን የሚያዘወትሩ ያነቃቃናል፣ ያስደስተናል፣ ጥሩ ስሜት እንዲሰማንና ኃይል ያለን እንዲመስለን ያደርገናል እንደሚሉ ዶክተሩ ይገልጻሉ፡፡
ትራማዶል፣ ፒቲዲንና ሌሎችም መድኃኒቶች ከሕክምና አገልግሎት ውጪ የሚጠቀሙ ዜጎች መበራከታቸውን በተለይም ለሕክምና አገልግሎት ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ፒቲዲንን በይበልጥ እንደሚጠቀሙ ናሆም (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ፒቲዲን የተሰኘውን መድኃኒት የሚወስዱ ባለሙያዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን፣ በመርፌ መልክ የሚሰጡ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሞርፊንና ፒቲዲን በሆስፒታል ውስጥ በልዩ ማዘዣ የሚገዙ መድኃኒቶች መሆናቸውን፣ አንዳንድ ባለሙያዎች በቀላሉ እንደሚያገኙት ገልጸዋል፡፡
በሕክምና ቦታዎች የሚሰማው ሁለቱን መድኃኒቶች አዘውትረው የተጠቀሙ ባለሙያዎች እስከ ሞት መድረሳቸው ነው፡፡ በባለሙያዎች መድኃኒቶቹን የሚወስዱት የሚያጋጥማቸውን የሥራ ጫና ለመቋቋም በሚል እንደሆነ ያክላሉ፡፡
ባለሙያዎች ምስጢሩን ስለሚያውቁና በራሳቸው ማዘዣ መግዛት ስለሚችሉ በቀላሉ እንደሚያገኙት አስረድተዋል፡፡ ትራማዶል በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ወጣቶች በአብዛኛው ይወስዱታል፡፡ በባህሪያቸው መሞከር ስለሚመርጡም ነገሮችን ይሞክራሉ ያሉት ናሆም (ዶ/ር) ከጓደኞቻቸው ጋር በቀላሉ በጋራ ሆነው የመሞከር አዝማሚያ ስላላቸው በቀላሉ ይለምዱታል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ጥናት እንዳልተደረገ ገልጸው፣ በአሜሪካ ከ12 ዓመት በላይ የሚገኙ ሦስት ሚሊዮን ያህል ታዳጊዎች፣ በስዊድን ደግሞ ከ32 በመቶ በላይ የማኅበረሰብ ክፍል ከሕክምና ትዕዛዝ ውጪ እንሚወስዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ጠቁመዋል፡፡
በአፍሪካ በናይጄሪያ፣ በጋና፣ በቶጎ፣ በቤኒን፣ በግብፅና በሊቢያ ትራማዶልን ከሕክምና አገልግሎት ውጪ የሚጠቀሙ ዜጎች ቁጥር ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት ትራማዶል ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ቢያዝም፣ የእርስ በርስ ጦርነት ባለባቸው አገሮች ለወጣቶች በመስጠት ለጦርነትም አገልግሎት እንደሚውል፣ የቦኮሐራምና የአልሸባብ ቡድኖች ሲያዙም የሚገልጹት እነኚህ መድኃኒቶች እንደሚሰጣቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ወንጀል ሠርተው ማረሚያ የገቡ ዜጎች ለሕክምና ሲመጡ ትራማዶል እንዲታዘዝላቸው የሚፈልጉ መኖራቸውን፣ መድኃኒቱን የሚጠቀሙ ለሌሎች በሽታዎች የመጋለጥና በወንጀል የመሳተፍ አዝማሚያ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡
መድኃኒቱን ሲያቋርጡ ድብርትና መደንዘዝ፣ ራስን መሳት፣ መንቀጥቀጥ፣ ማስመለስና ለሌሎች የማይሰሙ ድምፆች እንደሚሰማቸው አክለዋል፡፡
ከማኅበረሰቡ ምን ይጠበቃል?
በተለይም ትራማዶልን የሚጠቀሙ የሰባተኛ፣ የስምንተኛና የሁለኛ ደረጃ ተማሪዎች መሆናቸውን፣ ከአሥር ዓመታት በፊት ጫት የማይቅም ሰው እንደ ፋራ የታየበት ጊዜ እንደነበር ያስታወሱት ናሆም (ዶ/ር) አሁን ላይ በታዳጊዎች ትራማዶልን የማይወስድ እንደ ፋራ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ትውልድን የማዳንና የመጠበቅ ኃላፊነተ አለበት፡፡ ወላጆች የልጆቻቸውን ውሎና የሚጠቀሙትን ነገሮች ማየትና መፈተሽ እንዳለባቸው በተለይም ታዳጊዎችን ማሰብና መታደግ የሁሉም ኃላፊነት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ችግር ውስጥ ያሉትንም በትክክል የማከምና እንዲያገግሙ የሕክምና ባለሙያዎች ማማከር እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች፣ ፋርማሲዎች፣ ቤተሰቦች (ወላጆች) መንግሥት በዚህ ጉዳይ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውና በአገር አቀፍ ደረጃ በአዕምሮ ጤና ላይ የሚሠሩ በተቋማት ስለሌሉ ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የአዕምሮ ሐኪም የሆኑት ዮናስ ላቀው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በተለያዩ ምክንያት ሱስ ውስጥ የገቡ ዜጎች ሕክምና ማግኘት እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡
ከትራማዶል በተጨማሪ ሌሎች ሱስ የማምጣት ዕድላቸው ከፍተኛ የሆኑ መድኃኒቶችን የሚወስዱ ዜጎች መኖራቸውን፣ ሱስ ያለባቸው ዜጎች በተገቢው መንገድ ሕክምና ማግኘት እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡
ፒቲዲን የሚወስዱ ዜጎች ሲያቋርጡ ከፍተኛ ሕመም፣ ንፍጥ በንፍጥ መሆን፣ ማላብ፣ ማስመለስና ሌሎችም ሕመሞች እንደሚሰማቸው በአቻ ግፊት እንደቀልድ በመጀመር፣ በድብርትና በሌሎች ምክንያቶች እንደሚጀምሩት ዮናስ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡
ከወጣቶች ጋር በግልጽ ማውራት፣ ማገዝና መረዳት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ፣ በትምህርት ቤቶች፣ ለማኅበረሰቡ በክልከላና በጥብቅ በቁጥጥር ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ በግልጽ በማውራትና ኃላፊነትን በመወጣት መፍታት እንደሚቻል አክለዋል፡፡
ሱስ አምጪ ነገሮች ተፈጥሮዓዊ መሆናቸውን የገለጹት ዮናስ (ዶ/ር) በክልከላና በዘመቻ ብቻ ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል፣ ትምህርት ቤቶች፣ ወላጆች፣ ማኅበረሰቡ ሱስ የያዛቸውን ሰዎች ከማግለል ይልቅ ለማወያየትና ለማገዝ መጣር እንደሚገባም ይገልጻሉ፡፡
ከፍተኛ ቁጥር የሚይዘው ወጣቱ በመሆኑ፣ የሥራ አጥ ቁጥር፣ ጦርነትና የኑሮ ውድነት ሌሎችም ችግሮች ከአካላዊ ሕመም በተጨማሪ፣ አዕምሮዓዊ ሕመም የሚያስከትሉ መንግሥት ለአዕምሮ ሕመም ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ቁጥጥር የሚደረግባቸው መድኃኒቶች ዳይሬክተር ወ/ሮ አስናቀች ዓለሙ በበኩላቸው፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በይበልጥ የትራማዶል ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ማወቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከዳሰሳ ጥናት በፊት ያለማዘዣ የሚሰጡ መድኃኒቶች እንደነበር፣ ነገር ግን ቁጥጥር የሚደረግበት ለማድረግ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግና ሲገቡም በልዩ ማዘዣ እንዲደረግ ተሠርቷል፡፡
የናርኮቲክና ሌሎችም እንዳይሸጡ የተከለከሉ መድኃኒቶች መሆናቸውን፣ ሆኖም ራስን በራስ ማከም በአገር አቀፍ ደረጃ መጨመሩንና ችግሩን ለመፍታት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ ባለሥልጣኑ አሁንም በማኅበረሰቡ ጥቆማ መሠረት ሌሎችም መድኃኒቶች ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርጉ አክለው ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሯ እንደተናገሩት፣ ወጣቱ ትውልድ በአሁኑ ጊዜ ያላግባብ እየተጠቀመባቸው ከሚገኙ መድኃኒቶች ውስጥ ትራማዶል አንዱ ሲሆን፣ በተለይም የመድኃኒት ችርቻሮ ተቋማት በስፋት በሚገኙባቸው በከተሞች አካባቢ ችግሩ ጎልቶ ይታያል፡፡ ችግሩ በወቅቱ ካልተቀጨ አሳሳቢ ወደ ሚባል ደረጃ ሊጨምር ይችላል፡፡
ከሕክምና ዓላማ ውጪ ትራማዶልን የሚጠቀመው የወጣት ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ ወጣቶች በቀጥታ ወደ መድኃኒት ችርቻሮ ተቋማት በመሄድ ትራማዶልን በቀላሉ እንዲገዙ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት አዋጅ ቁጥር 1112/2011 ‹‹ናርኮቲክ መድኃኒት›› ማለት በተባበሩት መንግሥታት በወጣውና ኢትዮጵያ ባፀደቀችው የናርኮቲክ መድኃኒቶች ስምምነት መሠረት ቁጥጥር የሚደረግበት መድኃኒት ሆኖ በአስፈጻሚ አካሉ እንደ ናርኮቲክ መድኃኒትነት የተመደበ መድኃኒትን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ትራማዶልም በናርኮቲክ መድኃኒትነት የተመደበ ነው፡፡
በመሆኑም ትራማዶል የሚባለው መድኃኒት በመድኃኒት ችርቻሮ መሸጫ ተቋማት ላይ በዘፈቀደ እንዳይሸጥ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በተለያየ ጊዜ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን በመውሰድ በልዩ መድኃኒት ማዘዣ ብቻ እንዲሽጥ ለሁሉም የክልል ጤና ተቆጣጣሪዎች እንዲያውቁት በማድረግ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል፡፡
ይህንን የሚተላለፉ ሲገኙ ኅብረተሰቡ ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በነፃ የስልክ መስመር 8482 እንዲያሳውቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡