ሲንቄ ሴቶች ነፃነታቸውንና መብታቸውን የሚያስከብሩበት፣ ማኅበራዊ ኃላፊነት የሚሸከሙበት ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ባህላዊ ሥርዓት ነው፡፡
ይህ እናቶች በእጃቸው ከሚይዟት ዘንግ (በትር) ተያይዛ ተምሳሌትነቷ ከሰላምና ግጭት አፈታት አኳያ ሴትን የማብቃት ምልክት ሆና የሚያገለግል ልዩ ሥርዓት መሆኑን ስለ ትውፊቱ የሚያብራራው ‹‹THE ESSENCE OF SINQE/SIQQO CULTURAL SYSTEM AND ITS ROLE IN THE OROMO COMMUNITY›› የሚባለው መጽሐፍ ነው፡፡
እንደ መጽሐፉ ማብራሪያ፣ ሲንቄ/ሲቆ ‹‹ሀሮሬሳ›› ከሚባልና ከሌሎች ከማይነቅዙ ከተመረጡ የዛፍ ዓይነቶች ተቆርጣ የምትዘጋጅ ቀጥ ያለችና ያልተጣመመች ዘንግ/ በትር ስትሆን፣ የጋብቻ ዕለት እናት ለምትድራት ልጇ የምትሰጣት እስከ ዕለተ ሞቷ የማትለያት የክብር መገለጫ ስጦታዋ ናት፡፡

ይህች የሰላም ምልክት ሴቶች ክብራቸውን የሚያስጠብቁባት፣ ሰላምን የሚያወርዱባት፣ ፈጥነው የሚለምኑባት፣ የሚመርቁባት፣ ጋብቻንና ጉዲፈቻን ሕጋዊ የሚያደርጉባት፣ ሥልጣን የሚጋሩባትና ሀብት የሚያገኙባት፣ ከገዳ ሥርዓት ጋር ተያይዛ የምትሄድ ለሴቷ ተብላ የተደነገገች በሴቶች ብቻ የምትከናወን ባህላዊ ሥርዓት ናት፡፡
ይህ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ የሴቶች ሚና በከፍተኛ ደረጃ የሚገለጽበት ‹‹ሲንቄ/ሲቆ›› የሚባለው ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት በተመዘገበው የገዳ ባህላዊ ሥርዓት ውስጥ መካተቱ ይታወቃል፡፡
የግጭት መፍቻ፣ የጾታዊ ጥቃት መከላከያ፣ የሴቶች የሰላም በትር በመባል የምትታወቀውን ተምሳሌታዊ የሲንቄ/ሲቆ ባህላዊ ሥርዓት ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ በሴቶች የሚከናወነው የግጭት አፈታት ሥርዓት መሆኑም ስለ ትውፊቱ የሚገልጸው ጥናታዊው መጽሐፍ ይገልጻል፡፡
የገዳ ሥርዓት ሲመሠረት ለአባ ገዳው ‹‹ሎጋ ቦኩ እና ከለቻ›› ለሴቷ ደግሞ ‹‹ሲንቄ፣ ጫንጮ እና ጭጮ›› በተለያዩ ክብረ በዓላትና ውሳኔ በሚሰጡበት ቦታዎች ላይ እንዲጠቀሙበት የገዳ ሥርዓቱ ደንግጓል፡፡
እንደ ሲንቄ ያሉ ባህሎችን በዘመናዊ ትምህርት ውስጥ በማካተት ለትውልዱ ማሳወቅ እንደሚገባ በየጊዜው የባህል ባለሙያዎችም ሆኑ ኃላፊዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ሲያሳስቡ መስማማታቸው አልቀረም፡፡
ይህን ትውፊታዊው የሴቶች ልዕልና የሚታይበትን ሥርዓት ትውልዱ እንዲያውቀው ተደራሽ ከሚያደርጉ መሣሪያዎች አንዱ ኪነት ነው፡፡ በተለይ የሙዚቃ ከያኒያን ድምፅን ከምስል ጋር አገናኝተው የሚሠሯቸው ሥራዎች በቀላሉ ጆሮና ዓይን ገብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ይህን ከተረዱት አንዱ የሙዚቃ ባለሙያው አኒስ ጋቢ ነው፡፡ አኒስ በሙዚቃ ትምህርት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ የተማረና በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ አስተማሪ በመሆን የሙዚቃ ክህሎቱን ማዳበሩ ይነገርለታል፡፡
በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች በነጎድጓድ ድምፁ ሌሎች ደግሞ በኦዳ
አዋርድስና በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚሠራቸው ሥራዎች
የሚያውቁት አኒስ፣ አባቱ አቶ ጋቢ ኤዳኦ በኢትዮጵያ ታዋቂ ከሆኑ የኦሮሚኛ ሙዚቀኞች አንዱ መሆናቸውን የሙዚቃዊ መረጃ ያሳያል።
አኒስ በሙዚቃ ቤተሰብ ውስጥ ማደጉ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሙዚቀኛ የመሆን ፍላጎትና ህልም በውስጡ እንዲሠርፅ አድርጓልም ብሏል፡፡
አኒስ በቅርቡ ‹‹ሀደ ሚልኪ›› የተሰኘውን ኦሪጂናል ነጠላ ዜማ ይዞ ብቅ ማለቱን ያስታወቀው ‹‹ሙዚቃዊ›› የተሰኘው ተቋም ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንደገለጸው፣ ‹‹ሀደ ሚልኪ›› በኦሮሞ ባህል ውስጥ ሴቶች ያላቸውን ትልቅ ሥፍራ የሚያሳይ ሙዚቃ ነው፡፡ የሴቶች መብትና የፍትሕ ሥርዓቱን ‹‹የሲንቄን ሐሳብ›› በሰፊው አሳይቷል። የሙዚቃ ቪዲዮው በትዳር አጋሯ በደል ሲደርስባት የነበረችን ሴት የሲንቄ እናቶች መጥተው ሲታደጓት ያሳያል።
ሲንቄ ሥርዓት በኦሮሞ ባህል ውስጥ ለሴቶችና ሕፃናት ደኅንነት የሚቆሙ የእናቶች ስብስብ ሲሆን፣ በኅብረተሰቡ ውስጥም ትልቅ ተቀባይነት አላቸው የሚለው መግለጫው፣ የሲንቄ እናቶች ለሴቶችና ሕፃናት ደኅንነት ከመቆም ባለፈ የተጣላን በማስታረቅ በችግር ጊዜ ወደ ፈጣሪ በመጸለይ የድርሻቸውን ያደርጋሉ ይላል፡፡ ይህንኑ ሒደት አኒስ አሳይቷል፡፡
‹‹ይኼ ሙዚቃ በታዋቂው የጃዝ ሙዚቀኛ በጆርጋ መስፍን የተቀናበረ ሲሆን፣ የኢትዮ ጃዝና የምዕራብ አፍሪካ ድምፆችን አዋህዶ ለየት ያለ ዜማን ፈጥሯል። ይህ ነጠላ ዜማ የአኒስን በቅላፄ የተሞላ ድምፅ ለየት ባለ መልኩ ከማጉላቱ በተጨማሪ በተለያዩ የባህላዊና የዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች አሸብርቋል፤›› የሚለው ሙዚቃዊ፣ በዚህ የሙዚቃ ሥራ ላይ ሌንጮ ገመቹ በግጥም፣ ጆርጋ መስፍን በሪአሬንጅመንት እንዲሁም እንደ ሔኖክ ተመስገንና ቴዎድሮስ አክሊሉ ያሉ አንጋፋ ሙዚቀኞችም ተሳትፈውበታል ብሏል፡፡
አኒስ ከ‹‹ሙዚቃዊ›› ጋር ያለው ግንኙነት የጀመረው በአጋጣሚ ቢሆንም፣ ህልሙ ዕውን እንዲሆን አንድ ዕርምጃ የተራመደበት ሥፍራ ነው ያለው ሙዚቃዊ፣ ‹‹ሀደ ሚልኪ›› የተሰኘው ነጠላ ዜማው በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በዓለም አቀፍ መተግበሪያዎች መለቀቁንም አስታውቋል፡፡