በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ሥርዓተ ትምህርትን ለማጠናከርና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማዳበር መንግሥት እየሠራ ቢሆንም፣ በተለያዩ መስኮች የዳበረ ዕውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ማግኘት ፈተና ነው፡፡
በተለይ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን በበቂ ሁኔታ በተግባር የተደገፈና ልምድ ያካበተ ትምህርት ባለማግኘታቸው አንድም ሥራቸው ላይ በሌላ በኩል ደግሞ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ሆነዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሠልጣኞችና ምሩቃን አብዛኛው ሥራቸው ከፍተኛ ወጪ ከተደረገባቸው ማሽኖችና ቴክኖሎጂዎች ጋር የተያያዘ በመሆኑም በትልቅ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ምሩቃኑን ለመቅጠር ይሠጋሉ፡፡ ተማሪዎች አፓረንትሽፕ ሲወጡ እንኳን ማሸን የማያስነኩ ተቋማት ብዙ ናቸው፡፡ የተፈጠረውን የዕውቀት ክፍተት በመሙላት ለተመራቂዎችም የሥራ ዕድል፣ ለራሳቸውም ባለሙያ ለማግኘት ምሩቃንን ደግሞ በማሠልጠን ወደ ሥራ ማስገባትም እየተለመደ መጥቷል፡፡
ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ከዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ 42 ምሩቃንን ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ሥልጠናውን ወስደው ወደ ሥራ ከገቡት መካከል ወጣት ዮናስ ሻዶም ይገኝበታል፡፡
ወጣት ዮናስ ከተግባረዕድ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተመርቆ ከወጣ አንድ ዓመት ከአምስት ወር ገደማን አስቆጥሯል፡፡ ተመርቆ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ሥራ ለማግኘት ወደ ተለያዩ ተቋማት ቢሯሯጥም አንድም ቦታ የሥራ ዕድል ሳያገኝ መቅረቱን ያስረዳል፡፡ ከተግባረዕድና ቴክኒክና ሙያ በጥሩ ውጤት ተመርቆ ቢወጣ በተማረበት ሙያ ሥራ ማግኘት ባለመቻሉ ከባድ ችግር ውስጥ ገብቶ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ከተመረቀበት ቴክኒክና ሙያም በአውቶሞቲቭ ተመርቆ ቢወጣም አብዛኛውን ጊዜ የሚማሩት ትምህርት ተግባርን ያማከለ ባለመሆኑ ወደ ሥልጠና በገባበት ጊዜ አንዳንድ ነገሮችን ለመሥራት ሲቸገር እንደነበረ ይናገራል፡፡ ትምህርት ላይ እያለ የነበረው ቆይታና አሁን ያለበት ቦታ የትዬለሌና የማይገናኝ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ዮናስ፣ ከብዙ እንግልት በኋላ የሥራ ዓለምን መቀላቀሉን ያስረዳል፡፡ ከዚህ በፊት የትምህርት ማስረጃ ለተለያዩ ተቋማት ቢያስገባም፣ ተቀባይነት አለማግኘቱንና እንደሱ ዓይነት በርካታ ምሩቃን ጥሩ ውጤት ኖሯቸው ሥራ ሳያገኙ መቅረታቸውን ይናገራል፡፡
በተለያዩ ዘርፎች ላይ በጥሩ ውጤት ተመርቀው የሥራ ዕድል የማያገኙ ምሩቃን በርካታ መሆናቸውን የሚናገረው ወጣቱ፣ በተማሩበት መስክ ሥራ እንዲያገኙ እንደ ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ ዓይነት ድርጅቶች ሊበዙ ይገባል ይላል፡፡
ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ ሥልጠና ሰጥቶ የሥራ ዕድልን ለማመቻቸት ጊዜና ቀጠሮ በያዘ ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸው ምሩቃን መወዳደራቸውን፣ ከተወዳደሩት ምሩቃን ውስጥ 42 ተመራቂዎች የሥራ ዕድሉን ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡
ከእነዚህም ምሩቃን ውስጥ አንዱ እሱ መሆኑን የሚናገረው ወጣቱ፣ ድርጅቱ ባስቀመጠው ቦታ ላይ በመሥራት አንድም ቤተሰቦቹን በሌላ በኩል ደግሞ አገሩን ለመርዳት ሙሉ ለሙሉ ዝግጅት ማድረጉን ይናገራል፡፡
በማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ ውስጥ ሥልጠና በወሰደ ወቅት የተለያዩ ሙያዎችን መማሩንና የተግባር ሥልጠና ማግኘቱን ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡ በተለይ በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር ሆኖ እየታየ ያለው በተማሩበት የሥራ መስክ ሥራ አለማግኘት መሆኑን በማስታወስም፣ እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች መንግሥትም ሆነ ባለሀብቶች እንዲቀርፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መልካሙ አሰፋ እንደገለጹት፣ ተቋሙ ለስድስተኛ ጊዜ ባዘጋጀው ሥልጠና ላይ 3,570 የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን የተመረቁበትን ማስረጃ አስገብተዋል፡፡
በተለያየ የሙያ ዘርፍ ላይ ካስገቡት ምሩቃን ውስጥ በተለያዩ መሥፈርቶች በመለየት 42 ምሩቃን በቂ ሥልጠና በመስጠት ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አቶ መልካሙ አስረድተዋል፡፡
ወደ ተቋሙ የትምህርት ማስረጃቸውን ያስገቡት አብዛኛዎቹ ምሩቃን ውጤታቸው ከፍተኛ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ ሥልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረጉት ተቋሙ ባዘጋጀው የሥራ ማስታወቂያ መሠረት መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናውን ወስደው ለሥራ የበቁት ምሩቃን በዲግሪና በዲፕሎማ የተመረቁ ተማሪዎች መሆናቸውን፣ እነዚህም ተማሪዎች በቂ የሆነ ክህሎት እንዲያዳብሩ ተደርገው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
ምሩቃኑ በሥልጠና ወቅት ግርታ እንደገጠማቸውና በልምድ የካበተ ችሎታ ላይ ያን ያህል እንደነበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውሰዋል፡፡
ለውድድሩ የቀረቡት 3,570 ተማሪዎችን በተለያዩ ዙሮች በቀጣይ ሥልጠናውን ወስደው ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚደረግ መሆኑንና ይህም የብዙ ሥራ አጥ ወጣቶችን ችግር ሊያቃልል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ሥልጠናውንም ከወሰዱት መካከል የማርኬቲንግ፣ የአካውንቲንግ፣ መካኒካል ኢንጂነሪንግ፣ የአይሲቲ፣ የሒዩማን ሪሶርስና የቢዝነስ ማኔጅመንት ምሩቃን ይገኙበታል፡፡ በመገጣጠሚያ ፋብሪካ ውስጥ ደግሞ የኤሌክትሪክ ሙያተኞች፣ የኢንጅነሪንግና ዘርፎች ምሩቃን ሥልጠናውን መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡
ሥልጠና ለወሰዱ ምሩቃን ለትራንስፖት የሚሆን የኪስ ገንዘብና ለሥልጠናው የሚሆኑ ግብዓቶች እንደተሟላላቸው አቶ መልካሙ አስታውሰዋል፡፡