ስዊድናዊው አልፍሪድ ኖቤል ዳይናማይት የሚለውን ፈንጂ በመፈልሰፍና እያመረተ በመሸጥ በጣም ከፍተኛ ገንዘብ አግኝቶ ሀብታም ሆነ። አንድ ቀን ጠዋት ተነስቶ ጋዜጣ ሲያነብ እሱ መሞቱን በመግለጽ ስለ እራሱ የሕይወት ታሪክ የተጻፈውን ጽሑፍ አነበበ። በወቅቱ የሞተው ወንድሙ ሲሆን ጋዜጠኛው ግን አልፍሬድ ኖቤል የሞተ መስሎት ነበር።
አልፍሬድ ኖቤል የእራሱን የሕይወት ታሪክ ከጋዜጣው ላይ ሲያነብ በጣም ደንገጠ፣ አዘነም። እስከዚያን ቀን ድረስ አልፍሬድ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚጠቅም ነገር እንደሠራና ከሞተም በኋላ ሰዎች በሠራሁት በጎ ሥራ ያስታውሱኛል ብሎ ያስብ ነበር፡፡ ጋዜጣው ላይ የእሱ የሕይወት ታሪክ ግን ‹‹በሞት ነግዶ ያተረፈው ሀብታም ሞተ›› በማለት የእሱ ሥራ ለሰው ልጆች ስቃይና መከራ መዋሉን በሰፊው ያትታል፡፡
አልፍሬድ ኖቤል ይህን ታሪኩን ካነበበ በኋላ ሰዎች የእሱን ውስጣዊ እውነተኛ ማንነትና ለሰዎች ያለውን ቅን አስተሳሰብ አንዲረዱለት ለማድረግ ቆርጦ ተነሳ፡፡ ብዙ ከአሰበ በኋላም ከመሞቱ በፊት ኑዛዜውን ጻፈ። በዚህም ኑዛዜ ፈጠራውን ተጠቅሞ ያጠራቀመውን ሀብት ለሰው ልጆች የሚጠቅም ሥራ ለሠሩ ሰዎች በየዓመቱ በሽልማት እንዲሰጥ አዘዘ፡፡
እነሆ ዛሬ በመላው ዓለም ከሚሰጡ ሽልማቶች ሁሉ የኖቤል ሽልማት እጅግ ከፍተኛ ክብር ያለው ለመሆን በቃ። ሽልማቱ በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ፣ በሕክምናና በፊዚእሎጅ፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሰላምና በኢኮኖሚክስ የላቀ አስዋጽኦ ላበረከቱ በየዓመቱ ይሰጣል፡፡ ዛሬ አልፍሬድ ኖቤልን በበጎ ሥራው እንጂ ‹‹በሞት ነግዶ በማትረፍ›› የሚያስታውሰው የለም፡፡
ሁላችንም ሳንሞት በፊት ቀብራችን ላይ የሚነበበውን የሕይወት ታሪካችንን እራሳችን ብንጽፍና ብናነበው አቅጣጫችንን ከወዲሁ ለማስተከክል ሊረዳ ይችላል።
- አማረ ገሠሠ ‹‹ዊዝደም ምርጥ ትምህርታዊ ትረካዎች›› (2007)