Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለቀማ ላይ ነን!

እነሆ ጉዞ ከፒያሳ ወደ ዊንጌት። ቀልደኛው ወያላ በሕይወትና በራሱ ላይ እያሾፈ ተሳፈሩ ይለናል። በአንድም በሌላም ሕይወት በጉዞ ውስጥ ናትና እኛም እንሳፈራለን። ሕይወት የብዙ ጉዞዎችና ተሞክሮዎች ድምር ናት። ታክሲ ውስጥ የሚተዋወቁ ሰዎች ያወራሉ። ‹‹እንዴት ይዞሃል?›› ሲል ከወዲህ ‹‹ሰላም ነው…›› ብሎ ይመልሳል ከወዲያ አጠር አድርጎ። አዎ በዛሬ ጊዜ ሁሉንም ነገር ለማሳጠር መሞከር ሲያዋጣ ታይቷል። ሐሳብን ማሳጠር፣ ምኞትን ማሳጠር፣ ፍላጎትን መከርከም ካልተቻለ መኖር ከባድ ነው። ‘ከጓደኞቿ የረዘመች ማሽላ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ’ እንዲሉ ረዘም ረዘም ያለው ነገራችን ሲያጠፋን እንጂ ሲያድነን ለማየት አልታደልንም። ‹‹ሕይወት እንዴት ይዞሃል ጃል?›› ይላል የመጀመሪያው ጠያቂ። ተጠያቂው በበኩሉ፣ ‹‹ይኼው እንደምታየው እንታገላለን፣ ማን እንደሚጥል ግን ገና አልታወቀም…›› ይለዋል ሽሙጡን ጎላ አድርጎ። ሊጀመር ነው!

‹‹እንደ ዘንድሮ ሰው በነገር ሥጋውና ነፍሱ ድርና ማግ ሆነው ታይቶ የሚታወቅ አይመስልም…›› ይላል ከጐኔ የተቀመጠ ረዘም ያለ ወጣት ተሳፋሪ። መለስ ብዬ ሳየው ከ‘አይፎን’ ሞባይሉ ላይ የ‘ፌስቡክ’ ድስቱን ጥዶ ነገር ያማስላል። ትኩረቱ ‘ኔትወርክ’ አጠር ከሆነው ስልኩ ላይ ቢሆንም ጆሮው ግን ወዲህ ነው። ቀና ስል አንድ ጥቅስ አየሁ። ‘ምን ‘ቪኤት’ ቢነዱ ክራውድድ ነው መንገዱ፣ ምን ‘አይፎን’ ቢይይዙ አይገኝ ኔትወርኩ’ የሚል። ጥቅሱን አስተውዬ ፈገግ አልኩ። ጆሮው ከእኛ ዘንድ የተደቀነው አጠገቤ የተቀመጠ ወጣት ቀና ብሎ አይቶኝ፣ ‹‹ምን ተገኘ እባክህ? ሳቅም እኮ ተወዷል እስኪ አካፍለኝና ልሳቅ…›› አለኝ። ጥቁሱን ጠቆምኩት። ሊስቅ ግን አልቻለም። ‹‹አይ እኛ በቃ ራቅ ያለን ነገር ከሆነ እንደ ምንም ሰበብ ፈጥረን ራሳችንን ማፅናናት አያቅተንም አይደል?›› ብሎኝ ፌስቡኩ ላይ ‘ሼር’ ለማድረግ ጥቅሱን ፎቶ አነሳው። እውነትም ራሳችንን በማፅናናት የተካንን ነን። ምን ይደረግ ታዲያ!

‹‹አንተ ግባ በቃ እንሂድ…›› ይላል ሾፌሩ አሮጌዋ ሚኒባስ ታክሲ አልነሳ ብላ እየደጋገመ ቁልፉን እየሞከረ። ወያላው፣ ‹‹እሺ! እሺ!›› እያለ እያጠጋጋ ይጭናል። ‹‹ተጠጋጉ ግድ የለም፣ ሳይጠጋጉ ትዳር የለም። ከየት ይመጣል?›› ይላል እንዳንቆጣው ለዘብ ሲያደርገን። ‹‹ማን መጠጋጋቱን ጠላ ብለህ ነው ኑሮ አልሆን ብሎን እንጂ…›› ትለዋለች አንዲት ወፈር ያለች ወጣት ተሳፋሪ። ‹‹እውነት ነው እሙ፣ እስኪ አሁን ጠጋ በይና ወንድምሽን አስቀምጠሽ አጫውችው…›› ሲላት ከጣራ በላይ ትስቃለች። ሳቋ ሊጋባብን ያንገራግረናል። ወያላው ሳቅ እያለ፣ ‹‹ታክሲና ኑሮ መቼ ሞልቶ ያውቃል?›› እያለ ሲያግባባን ሾፌሩ፣ ‹‹አንተ ልጅ ተው ግባ፣ በቃህ አልኩህ እኮ ከዚህ በላይ ልታሳስረኝ ነው እንዴ?›› ይለዋል ቁርጥ አድርጎ ትርፍ አትጫን ብሎ መንገር ከብዶት። ‹‹አይዞን አትታሰርም ለጊዜው እስር ቤቱ ሙሉ ነው…›› ብሎ መልሶለት በሩን ይዘጋ ጀመር። ‘ህም!’ ይላል ተሳፋሪው ቅኔውን ሲፈታው። ‹‹ለመሆኑ ብታሰር ትጠይቀኛለህ?›› ሾፌሩ ይጠይቀዋል። ወያላው፣ ‹‹እሱ እንደታሰርክበት ምክንያት ነው የሚወሰነው…›› አለው። ‹‹እንዴት?›› ሲለው፣ ‹‹ሕዝብ በዝብዘህና ጨቁነህ ከሆነ እንዴት ልጠይቅህ እችላለሁ?›› ብሎ መልሶ ሲጠይቀው፣ ‹‹አንተ ትርፍ በጫንከው እኔ ብታሰርም?›› አለ ሾፌሩ ዞር ብሎ። ‘ወይ የዘንድሮ ሰው!’ የሚል ይመስላል። ወያላው፣ ‹‹አዎ እኔ በጫንኩት ብትታሰርም። እንዲህ ያለውን ነው አየህ ጥሩ ስም ያወጡለት…›› አለው፡፡ ‹‹ምን አሉት?›› ብሎ ሾፌሩ ሲጠይቀው፣ ‹‹ፖለቲካ!›› ሲል መለሰለት። ‹‹ነገረኛ!›› እያለ ሾፌሩ ይስቃል። ከሳቁና ከወያላው መልስ ጀርባም አንዳች ‘ፖለቲካ’ ያለ ይመስላል! ልብ ያለው ብቻ ልብ ይለዋል!

‹‹አግብተሻል?›› ይጠይቃል ወፈር ያለ ሰውነት ያላት ወጣት ተሳፋሪ ላይ ተደርቦ የተቀመጠ ወጣት። ‹‹ለምን ጠየቅከኝ?›› ትለዋለች ድንገት መጠየቋ ገርሟት። ታክሲዋ ከጅማሮዋ መንገዱን ለማጋመስ ቸኩላለች። አጭሩ መንገድ የሚረዝምበት ረዥሙ የሚያጥርበት ሆነ ዘመኑ። ‹‹አይ ጣትሽ ላይ ቀለበት አይቼ ነው…›› ይላል ወጣቱ። ‹‹እሱ እንኳን ለጌጥ የተደረገ ‘ፌክ’ ቀለበት ነው…›› ትለዋለች። ‹‹ለነገሩ እኮ ዘንድሮ ‘ፌክ’ ቀለበት ብቻ ሳይሆን ‘ፌክ’ ትዳርም በዝቷል። አይደለም እንዴ?›› እያለ ብዙ ሊያስወራት ይጥራል። ‹‹ነው ብለህ ነው ምን ይደረግ? ዘንድሮ ወንዶችን ማመን ቀብሮ ነው…›› አለችው ሰረቅ አድርጋ አይታው። ‹‹እኛም ሴቶች እንላለን እናንተም ወንዶች ትላላችሁ፣ ማንኛችን ነን ትክክል?›› እያላት እየመለሰችለት በደንብ እየተላመዱ ሲቀጥሉ ከኋላ ቀልድ አዘል ምልልሶች ትዳርን ታከው ይደመጡ ጀመር። ነገርን ነገር ያነሳዋል ማለት ነው!

‹‹የዘንድሮ የሀብታም ትዳር አልጋ ለይቶ ነው ሲባል አልሰማችሁም?››  ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹እኔምለው ለምን ይሆን ሀብት ከሰው በልጦ መከራ እያሳየ ያለበት ምክንያት?›› ሲል ምፀቱን ያጋግላል። ወዲያው ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠች ቆንጅዬ ወጣት፣ ‹‹የዓለም ፍፃሜ ምልክቱ ከፍቅር በላይ ገንዘብ ሰውን በመብለጡ ነዋ…›› ስትል ትመልሳለች። ጭውውቱ ቀልድና ምፀት አዘልነቱ ተጠብቆ ሳያመርና ሳያከር እያሳሳቀ ይቀጥላል። ‹‹ለመሆኑ ሀብታሞቹ ባለትዳሮች አልጋ ቢለዩም አንዳንዴ ለማስመሰል ሲሉ አንድ ላይ ነን የሚሉትን እንዴት ታይዋለሽ?›› ብሎ አንደኛው ሲጠይቃት፣ ‹‹ወንድሜ ሀብት ሲካፈሉ ይዞት የሚመጣው መዘዝ ስለሚፈራ ማስመሰሉን ተክነውበታል፡፡ የሚያሳዝነው ግን እየቀለዱ ያሉት በራሳቸው ሕይወት መሆኑን አለመረዳታቸው ነው›› ስትለው የከተማው ዋና አስተናባሪ ትመስል ነበር፡፡ ይገርማል ይደንቃል!

‹‹‘ፌስቡክ’ ላይ ‘ቫት’ ሊጀመር ነው አሉ…›› ብሎ አንዱ ሌላ ጨዋታ አስጀምሯል። ታክሲዋ በድንጋጤ ጎርፍ ተጥለቅልቃለች። ‹‹አይደረግም ይህ የሙሰኞች ወሬ ነው…›› ትላለች የቀይ ዳማ ወጣት ከወደፊት መስመር ጆሮዋን ደፍናበት የነበረውን ‘ኢርፎን’ እየነቀለች። አንድ ተሳፋሪ ታዝቧት፣ ‘እንዴ ‘ኢርፎኑ ማስክ’ ነበር እንዴ?’ እያለ ያማታል። ‹‹እውነትህን ነው? እንዴት ሆኖ?›› አብዛኛው ተሳፋሪ የሚጠይቀው በጭንቀት ነበር። ልጁ ‘ፌስቡክ’ ማለት ከሦስቱ መሠረታዊ ፍላጎቶች መካከል ሊመደብ ምንም እንዳልቀረው ታዝቦ ሲያበቃ፣ ‹‹ኧረ እኔስ ለጨዋታ ነው…›› ብሎ ተሳፋሪውን አረጋጋው። የዕፎይታው ንፋስ ብርድ እንዳያሳምመን እስክንሠጋ ድረስ። ‹‹እኔ ደግሞ ሰሞኑን የምንጠየቀው የዕርዳታ መዋጮ ስለሌለ በዚህ በዚያም ብለው ‘ሊፈልጡን’ ነው ብዬ አስቤ ክው አልኩ…›› አንደኛው ወጣት ሥጋቱ ከምን መንጭቶ እንደደነገጠ ያብራራል፡፡ መተንተንም አያቅተው!

ዊንጌት ለመድረስ የቀሩን ጥቂት ደቂቃዎች ናቸው። ከልክ በላይ አሮጌዋን ሚኒባስ የሚያስጋልባት ሾፌራችን ከምድር ለመጥፋት እንጂ፣ ከፒያሳ ተነስቶ ዊንጌት ለመድረስ ብቻ እንዲያ የሚነዳ አይመስልም። ‹‹ቀስ በል እንዳንል እንደ ዘንድሮ ሰው አስተያየት፣ ምክርና ተግሳጽ የጠላ የለም…›› ይለኛል አጠገቤ ያለው ወጣት። ከኋላችን የተቀመጡት ጎልማሳና ቆንጅዬዋ ወጣት እንዲህ ይጫወታሉ። ‹‹እኔምለው መንግሥት የዶላር መስመሩን ለመዝጋት ቁርጠኛ ሆኖ መነሳቱ እርግጠኛ ነው የሚባለው እውነት ነው?›› ብላ ጎልማሳውን ስትጠይቀው፣ ‹‹ምን አውቃለሁ ብለሽ ነው። ግን እንዲያ ሲባል መቼም እዚህ አገር የማይባል ነገር የለም እያልኩ ነው እንጂ መስማቱን ሰምቻለሁ። ምናልባት ያለ ልማዱ ትልልቅ የጥቁር ገበያ ተዋንያንን ሸብ ያደረገው ሊሆን ይችላል…›› ይላታል። የእኛ ሰው እኮ ምንም አያመልጠውም!

ትንሽ እንደሄድን ‘ኢርፎን’ ጆሮዋ ላይ ሰክታ አልሰማም አላይም ብላ ከተቀመጠችው ወጣት ሦስተኛ ተደርበው የሚጓዙ አዛውንት፣ ‹‹እውነት አገር የሚያደሙት ላይ እንዲህ ከበድ ያለ ዘመቻ ከተጀመረ ማን ሊቀር ነው?›› ብለው ድምፃቸውን አጉልተው ጠየቁ። ‹‹እንዴት?›› ስትላቸው ወይዘሮዋ፣ ‹‹ከተራ ጥበቃ እስከ ዋና ሥራ አስኪያጅ ያለ ምንም እጅ መንሻ መግባት፣ መውጣት፣ ጉዳይ ማስጨረስና መከታተል የማይታሰብባት በሆነች አገር ማን ሊማር? ዘረፋ ሥር ሰዶ ያልተዘፈቀበት የለም። የንግዱ ዓለም ውስጥ ሲገባ ደግሞ እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ጥቂቶች በስተቀር፣ የተቀሩት ራሱን ፈጣሪን ቢያገኙት ከመዝረፍ የማይመለሱ ጉዶች እኮ ናቸው…›› ሲሉን ‘ህም’ ብለን ‘ዝም’። አዛውንቱ እጃቸውን ጨብጨብ ሲያደርጉ ሁላችንም አንገታችንን አዙረን አየናቸው፡፡ ‹‹ለማንኛውም በሌቦች ላይ ዘመቻ ሲጀመር የድጋፍ ድምፃችንን ማሰማት አለብን…›› ሲሉ አንዱ ጥልቅ ብሎ ‹‹ምን ብለን?›› ሲላቸው፣ ‹‹በደንብ ለቃቅመህ አስገባልን እያልን ነዋ…›› እያሉን ወያላው በሩን ከፍቶ ‘መጨረሻ’ ብሎ ውረዱልኝ እያለ ነበር። ወይ ለቀማ! መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት