Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኢትዮጵያ የምግብ ዘይት የዕውቀትና የሕግ ክፍተት ችግሮችና የመፍትሔ ዕጦት

የኢትዮጵያ የምግብ ዘይት የዕውቀትና የሕግ ክፍተት ችግሮችና የመፍትሔ ዕጦት

ቀን:

በእንየው ታደሰ (ዶ/ር)

  1. መግቢያ

የምግብ ዘይት ነፍስ ወከፍ ፍጆታ መጨመር፣ የሕዝብ ቁጥር ማደግና የቅባት እህል እጥረት በዓለም ላይ የምግብ ዘይት እጥረትን በማባባስ ከሚታወቁት ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከተቀረው ዓለም ጋር የምትጋራቸው በርካታ ተግዳሮቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በኢትዮጵያ ለየት ያሉ ችግሮችም አሉ፡፡ አንደኛውና የችግሩን ምንጭ አጥርቶ ማወቁ ነው፡፡ ሁለተኛው ችግር አገሪቱን በሌላ አገር ላይ ጥገኛ የማያደርግ የመፍትሔ መረጣ ነው፡፡ ለእነዚህ ችግሮቻችን ብዙውን ጊዜ ፅንፍ የረገጡ መፍትሔዎች ሲሰነዘሩ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ዘይት አስመጪዎች ሲደጎሙ (መደጎም የግድም ነበር) የአገር ውስጥ አምራቾች ይጎዳሉ፡፡ የቅባት እህል ኤክስፖርት ሲደረግ (አለማድረግ አይቻልም) የምግብ ዘይት ጥሬ ዕቃ እጥረት ይከሰታል፡፡

ግን ምን ምን አማራጮች ነበሩ? እንዴትስ ይህንን ፅንፍ ዕሳቤ ሚዛናዊ ማድረግ ይቻላል? ብሎ ማየት ይቻል ነበር፡፡ ተገቢው ምክክር ሳይደረግበት የሚወሰኑ ውሳኔዎችን የመቋቋምና አቅጣጫ የማስያዝ አቅም ያላቸው የአምራች ማኅበራት አለመኖርም ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ መንግሥትም መድረክ በመፍጠር አገር ውስጥ ያለውን ዕውቀት ከእነ መፍትሔው አሟጦ መሰነድና መመካከር ላይ ቢያተኩር ጥሩ ነበር፡፡ ዘርፉን የሚመሩ የመንግሥት አካላትም ተረጋግተው ሥልጣናቸው ላይ ስለማይቆዩና በኖሩበትም ወቅት ብዙውን ጊዜ በሌሎች ጉዳዮች የተዋከቡ ስለሚሆኑ፣ ችግሩ ይወሳሰባል፡፡ ስለዚህ ዕቅድን መሠረት አድርጎ ከሚሠራ ሥራ ይልቅ፣ እንደ ድንገተኛ ደራሽ ጉዳይ በዘመቻ በሚደረግ እንቅስቃሴ ብዙ ጉዳት ሲደርስ ይታያል፡፡ በፕሮጀክት መልክ የሚጀመሩ እንቅስቃሴዎችም ጠቃሚ ሆነው ሳለ በፕሮጀክቱ ሒደትም ሆነ፣ ከፕሮጀክቶቹ ማብቃት በኋላ የተጀመሩ ሥራዎችንም ማስቀጠል የተገኙ ውጤቶችን መገምገም ስለሚቻልበት ሁኔታ ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት ትልቅ ችግር ነው፡፡ የምግብ ዘይት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ችግር የሆነው አያያዙ ውጣ ውረድ የበዛበትና የሰከነ ሥልት ያልተቀየሰለት በመሆኑ እንደሆነ ብዙ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡

  1. የምግብ ዘይትአቅርቦት የመጀመርያው ግልጽ ሪፖርት

በ2001 ዓ.ም. የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት አቅርቦት 20 በመቶ ብቻ ሲሆን ቀሪው 80 በመቶ ከውጭ በማስገባት የሚሸፈን መሆኑን ነበር፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በ2007 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በምግብ ዘይት ራሷን ትችላለች የሚል ዕቅድ ነበር፡፡ የምግብ ዘይት ጥራት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ያልተነጠረ/ሪፋይን ያልተደረገ የምግብ ዘይት በኢትዮጵያ እንዲታገድ እንቅስቃሴ ተጀምሮም ነበር፡፡ ይህ በጥራት ማስጠበቅ ስም የተጀመረው እንቅስቃሴ በቂ ግንዛቤ ያልተያዘበት ስለነበር እጥረቱ ይበልጥ ገዘፈ፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ አገራዊ ቡድን እስከ መቋቋም ቢደርስም፣ የድንጋጤውን ያህል ችግሩን ከመሠረቱ አጥንቶ ለመፍታት ትኩረት የተሰጠበት አልነበረም፡፡

  1. የምግብ ዘይት ምርት ዓይነትና ቴክኖሎጂው

የምግብ ዘይት በመካኒካል መጭመቂያ ማሽን ሲጨመቅ እንደ መጭመቂያው ጉልበት መጠን የወጣው ዘይት ሁለት ዕጣ ፈንታ ይኖረዋል፡፡ አነስተኛ ጉልበት ባላቸው ማሽኖች ሲጨመቅ ድንግል ዘይት (ቨርጅን ኦይል) ቀዝቃዛ ጭምቅ ዘይት ሆኖ በማጣሪያ (ፊልትሮ) ሒደት ብቻ በማለፍ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ከፍተኛ ጉልበት ባላቸው ማሽኖች የተጨመቀ ከሆነ በማንጠር (ሪፋይነሪ) ሒደት ውስጥ ማለፍ የግድ ይሆናል፡፡

3.1.   ኢንጥር/ድንግል ዘይት (ቨርጅን ኦይል)

በአነስተኛ ጉልበት ከተጨመቀ ድፍርሱን በማዝቀጥና ወይም በፊልትሮ በማጣራት ቀጥታ ለምግብነት ሊውል ይችላል፡፡ ድንግል ዘይት የነጠራ ሒደት እንደማያስፈልገው ስሙ አመልካች ነው፡፡ ድንግል ዘይት ለጥራቱ የነጠራ ማስተካከያ ስለማይደረግለት፣ የጥሬ ዕቃ ጥራትና የጨመቃ ጥንቃቄው ትኩረት ይፈልጋል፡፡ ይህ ዘይት በሙቀት በቀላሉ የሚጎዳ በመሆኑ ከፍተኛ ሙቀት ለሚጠቀም ምግብ መጥበሻነት አያገለግልም፡፡ በምርት ውጤታማነት ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ለምግብነትና ለጤና ካለው ጥቅም አንፃር ከንጥር ዘይት ሲነፃፀር በተሻለ ዋጋ ይሸጣል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ድንግል ዘይት ላይ የሚሰነዘረው ትችት ብዙው ሳይንሳዊነት የጎደለውና ዓለም አቀፉን ዕውቀት ያላገናዘበ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ድንግል ዘይቶች ካላቸው የጤና ጠቀሜታና ምጣኔ ሀብት የማነቃቃት ጥቅማቸው አንፃር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ እንደ ገና መቃኘት አለበት ተመራጭነታቸውም ከፍ ያለ ነው፡፡

3.2.   ንጥር ዘይትን ከድፍድፍ ዘይት

በከፍተኛ ጫና የተጨመቀውና በምዝመዛ (ሶልቫንት ኤክስትራክሽን) የወጣው ዘይት ከመነጠሩ በፊት (በተናጥልና በቅልቅል) ድፍድፍ ዘይት ይባላል፡፡ በመሠረቱ ድፍድፍ የሚለው ቃል ምርቱ የነጠራ ሒደት እንደሚቀረው አመላካች ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንዶች ድንግል ዘይትን ድፍድፍ ዘይት ብለው መጥራታቸው የተሳሳተና የመሠረተ ሐሳብ ችግር ያለበት ነው፡፡ እንዲሁም ድንግል ዘይት የሚለው የነጠራ ሒደት የማያስፈልገውና በራሱ ያለቀለት ልዩ ምርት እንደሆነም መታወቅ አለበት፡፡ ከፍተኛ ጫና ባለው ማሽን የተጨመቀ ድፍድፍ በመሆኑ፣ ተጨምቆ ከተጣራ በኋላ ወደ ማንጠር ሒደት እንዲገባ ይደረጋል፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት በከፍተኛ ጫና የሚፈጠረው ሙቀት የዘይቱን ተፈጥሮ ስለሚቀይረው አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ሲባል ነው፡፡ ስለዚህ ድፍድፍ የሚለው ቃል ከድንግል ጋር እንደ ተመሳሳይ ወይም ተተካኪ ቃላት መቆጠር የለባቸውም፡፡

3.3.   ከፊል ንጥር ዘይት (ሰሚ ሪፋይንድ ኦይል) አወዛጋቢው ሒደት

ይህ አወዛጋቢ ትርጉም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በማን እንደሆነ በውል ባይታወቅም፣ ከፍተኛ የግንዛቤ ችግር የነበረበት በመሆኑ ትልቅ ጉዳት አድርሷል፡፡ አወዛጋቢውን ሐሳብ ያመጡ ሰዎች የአሲድ ማስወገጃ ሒደት እንዲከናወን ይመክራሉ፡፡ ይህ የኒውትራላይዜሽን ሒደት ከተካሄደ ግን ዘይት ሆኖ ለመውጣት ቀጣዮቹን ሒደቶች በሙሉ ይጋብዛል፡፡ ስለሆነም መሀል ላይ ያለው ከፊል ንጥር ሳይንሳዊነት ይጎድለዋል፡፡

  1. የምግብ ዘይት እሴት ሰንሰለት ማጎልበት ፕሮጄክት

የምግብ ዘይት ዕሴት ሰንሰለት በዋናነት የእርሻ ጥሬ ዕቃ ምርት ሒደትና ይህ ጥሬ ዕቃ ወደምግብ ዘይት አምራቾቹ የሚደርስበትን የግብይት ሒደት፣ እንዲሁም በሌላ የምርት ሒደቱንና የተመረተው ዘይት ከፋብሪካዎች ወደ ተጠቃሚዎች የሚደርስበትን የግብይት ሒደት ያጠቃልላል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ለነበረው ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት ኢትዮጵያ ውስጥ የተቋቋመው የምግብ ዘይት ጥሬ ዕቃና ምርት ሒደት ላይ ይበልጥ ትኩረት የሚሰጥ ፕሮጀክት ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ. ጃኑዋሪ 1 ቀን 2010 ተጀምሮ ዲሰምበር 31 ቀን 2012 የተጠናቀቀ የሦስት ዓመት ፕሮጀክት ነበር፡፡ ፕሮጀክቱን የሚያስተባብሩት አካላት ሥራውን የሚያከናውኑት በጥምረት ሆነው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዩኒዶ፣ ኤፍኤኦና አይኤልኦ ሲሆኑ፣ ከኢትዮጵያ ደግሞ ኢንዱስትሪና ግብርና ሚኒስቴሮች ነበሩ፡፡ ፕሮጀክቱ ከቀጥተኛ ውጤቱ በተጨማሪ፣ ከደካማ ጎኑም ትምህርት ተወስዶበት ለተሻለ ሥራ የሚያዘጋጅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን የምግብ ዘይት ቀውስ ተከትሎ በስፓኝ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ሰጪነት በዩኒዶ፣ በኤፍኤኦና በአይኤልኦ አስተባባሪነት ፕሮጀክቱ ተቋቋመ፡፡ ይህም በወቅቱ ፕሮጀክቱ የምግብ ዘይት እሴት ሰንሰለት ማጎልበት ፕሮጀክትም የእሴት ሰንሰለቱን በማፋጠን፣ የኢትዮጵያን የምግብ ዘይት አቅርቦት በእጅጉ ለማሻሻል ዋና ትኩረቱን የቅባት እህል አቅርቦት (እርሻ) እና አነስተኛ የምግብ ዘይት አምራቾች ላይ ያደረገ ነበር፡፡ አነስተኛ አምራቾች ላይ ትኩረት ያደረገበት ምክንያትም ከላይ የተገለጸው ሪፖርት በቀረበበት ወቅት ካለው የአገር ውስጥ አቅርቦት ስልሳ በመቶውን የሚሸፍኑት፣ አነስተኛ የምግብ ዘይት አምራቾች ስለነበሩና እነሱ ላይ ቢተኮር ፈጣን ለውጥ እንደሚመጣ በመታመኑ ነበር፡፡

በቅባት እህሉ አምራችና በምግብ ዘይት አምራቾቹ መካከል ላይ ያሉት የእሴት ሰንሰለቱ ተዋናዮች ጉዳይ ውስብስብ ቢሆንበትም፣ የእነሱንም (የግብይት ሒደት) ሚና ለማየት ተሞክሮ ነበር፡፡ ይህ ፕሮጀክት ኦሮሚያ ክልልን (አዳማን ማዕከል አድርጎ) እና አማራ ክልልን (ባህር ዳርን ማዕከል አድርጎ) ነበር የተንቀሳቀሰው፡፡ ጥሬ ዕቃን (ቅባት እህልን) በተመለከተም በአማራ ክልል በዋናነት ኑ ግን መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ በዋናነት ተልባን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲንና አዳማ ዩኒቨርሲቲንም እንደ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ማዕከል ታሳቢ በማድረግ ነበር እንቅስቃሴ ያደረገው፡፡ ፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ አድርጎ የተንቀሳቀሰው በገበሬዎች በኩል የቅባት እህል አቅርቦቱ እንዲሻሻልና በተሳለጠ ግብይት ወደ ጨማቂዎች የሚደርስበትንና የዘይት ጨማቂዎችም ንጥር ወይም ከፊል ንጥር ዘይትን በተሻለ ጥራትና ውጤታማነት አምርተው ለተጠቃሚው እንዲያቀርቡ ማድረግ ነበር፡፡

4.1.   የጥራት ደረጃና የፕሮጀክቱ መደናገር

ፕሮጀክቱ ላይ መደናገርን ፈጥሮ የነበረው የምግብ ዘይቱ ደረጃና ደረጃውን ለማሟላት የተያዘው አቋም ነበር፡፡ አነስተኛ አምራቾች ምርታቸውም ድንግል የምግብ ዘይት (ቨርጅን ኦይል) ይባላል፡፡ ይህ ድንግል ዘይት ደግሞ አመራረቱ፣ ጥቅሙ፣ አጠቃቀሙ፣ ተፈጥሮውና የተቀመጠለት ደረጃ የምግብ ዘይት አቀነባባሪዎች (ፕሮሰሰርስ) ከሚያመርቱት ንጥር ዘይት (ሪፋይንድ ኦይል) ለየት ያለ ነው፡፡

ይህ ድንግል ዘይት በኢትዮጵያ በወቅቱ በፕሮጀክቱ ዕውቅና አለማግኘቱ መሠረታዊ ችግር ነበር፡፡ ቨርጅን ኦይል (ድንግል ዘይት) ለወይራ ዘይት ብቻ የተሰጠ የሚመስላቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን እንደ አመራረቱ ሁሉም ዘይት ድንግል እንዲሆን ተደርጎ ሊመረት እንደሚችል መታወቅ አለበት፡፡ በመሆኑም በዚህ ፕሮጀክት ትኩረት የተሰጣቸው አነስተኛ አምራቾች ምርታቸው ድንግል ዘይት ሲሆን፣ በጥራትና በደረጃ ጫና ንጥር ወይም ከፊልን ጥር እንዲያመርቱ አቋም መያዙ ዋና የችግሩ ምንጭ ነበር፡፡ ይህ ችግር መልስ ሳያገኝ ፕሮጀክቱም እንዲቀጥል ተደረገ፣ ዛሬም ድረስ ችግሩ እንደ ቀጠለ ነው፡፡

4.2.   የድንግል ዘይት ዕውቅና ዓውደ ምክክር (ፕሮጀክቱን የማገዝ ጥረት)

ይህ ዓውደ ምክክር በዋናነት የምግብ ዘይት ጥራት ደረጃና ዓይነቶች ላይ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት ያቀደ ነበር፡፡ ይህንን ክፍተት መሙላትም የምግብ ዘይት ዕሴት ሰንሰለት ማፍጠን ፕሮጀክትንም በሳይንሳዊና ዓለም አቀፍ ልምድን መሠረት አድርጎ ለመደገፍ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ለፕሮጀክቱ ተልዕኮ መሳካት እንቅፋት ይሆናል ተብሎ የተዘጋበትን የድንግል ዘይትን ከአገሪቱ የማጥፋት የተሳሳተ ድርብ ተልዕኮ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ድጋፍ ለማድረግ ነበር፡፡ በመሆኑም ንጥርና ኢንጥር ዘይት እኩል ዕውቅና ያላቸው መሆኑን አስገንዝቦ፣ ሁለቱም ወይም ከሁለት አንዱ እንደ አስፈላጊነቱ የፕሮጀክቱ አካል ሆነው ያለአላስፈላጊ መገፋፋት ሥራው እንዲካሄድ መርዳት ነበር፡፡   

በምርምር ችግር (ሐሳብ) ላይ በተደረገ ውይይት ኢትዮጵያ ውስጥ የድንግል የምግብ ዘይት ባህል ቢኖርም፣ አሁን አሁን ሥልጣኔ በመሰለ አካሄድ ለእንደዚህ ዓይነት የምግብ ዘይት ምርት ዕውቅና ያለ መስጠት ችግር መኖሩ ታምኖበት ነበር፡፡ የአገሪቱ ዋና ምርት ድንግል ዘይት በመሆኑና ለጤናም ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ምርቱ ላይ እየደረሰበት ያለው ችግር እንዲፈታ የሚል ውይይት ነበር የዓውደ ጥናቱ መወያያ፡፡ ለዚህም አንደኛ ከተመሳሳይ የጀርመን ፋብሪካዎች ተግባራዊ ልምድ መቅሰም እንዲሁም የጀርመንንና የዓለምን ልምድ የሚያስተዋውቅ ዓውደ ጥናት አንዱና ዋናው መርሐ ግብር ነበር፡፡

የተለያዩ ኢትዮጵያውያንና የጀርመን ባለሙያዎችም የድንግል ዘይትን ጥቅም፣ ዕውቅናና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የምግብ ዘይት አምራቾችና የቅባት እህል ተመራማሪ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ደረጃዎች ድርጅት በተገኙበት ሰፊና ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በድምዳሜውም ድንግል ዘይት ለጤና ጠቃሚና ኤክስፖርትን ጨምሮ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበት፣ ምርቱ ዕውቅና ተሰጥቶት እንዲበረታታ ቀጣይ የማስተካከያና የማበረታቻ ጥረቶች እንዲካሄዱና ይህ የድምዳሜ ለሚመለከታቸው እንዲሠራጭ ተወስኖ ዓውደ ጥናቱ ተጠናቆ ነበር፡፡

  1. የአነስተኛ አምራቾቹ ዋና ዋና ችግሮች

እንደ የትኛውም የኢንዱስትሪው ዘርፍና እንደ አነስተኛ አምራችነታቸው በርካታ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው፣ የምግብ ዘይት አነስተኛ አምራቾች ያለ ቅድመ ሁኔታ ሊፈቱላቸው የሚገቡ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት ችግሩ በአምራቾች፣ በመንግሥትና በኅብረተሰቡ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

5.1.   ከአምራቾች አንፃር

አነስተኛ አምራቾች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ከመንግሥት ከሚጠበቀው ድጋፍ በተጨማሪ፣ ጥያቄዎቻቸው እንዲመለስ መደራጀትና ማኅበራቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ መደራጀት ከመንግሥት፣ ከትልልቆቹ አምራቾች፣ ከተጠቃሚው ኅብረተሰብ ጋር አስፈላጊውን ድርድር፣ ትብብር፣ የማስተዋወቅ ሥራ ማድረግ ይረዳቸዋል፡፡ ለምርታቸው ዕውቅና ማግኘት የተዘረዘሩትን የድንግል ምግብ ዘይት ልዩ ባህሪያትና ዓለም አቀፍ ሕግጋትና ዕውቅና አንፃር ምርታቸው ዕውቅና ማግኘት አለበት፡፡ ድንግል ዘይት ለጤና ያለው ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ ገብቶ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ተገቢውን ድርድር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለድንግል የምግብ ዘይት የተለየ ባህሪና የጤና ጠቀሜታ ለተጠቃሚው ሕዝብ በተለያዩ ሚዲያዎች በማስተማር፣ ዕውቅና ማግኘትና ገበያቸውን ተግተው ማሳደግ አለባቸው፡፡   

5.2.   ከመንግሥት አንፃር

ድንግል ምግብ ዘይት በኢትዮጵያ ውስጥ ረዥም ታሪክ ያለውና የጤና ጠቀሜታውም ከፍተኛ በመሆኑ፣ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ለምርታቸው ሕጋዊ ዕውቅና የሚሰጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም በማድረግ ምርቱ አገር ውስጥ ያለውን እጥረት ለማቃለልም ሆነ ምርቱን እንደ ጤና መላሽ ምርት ለየት ያለ ማበረታቻ ማድረግ፣ ምርቱ ይበልጥ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችልበትን መንገድ መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ በዓለም ላይ የድንግል ምግብ ዘይት ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡

5.3.   ከተጠቃሚው አንፃር

ሕዝቡ ይህንን ለዘመናት ሲጠቀም የቆየውን ድንግል ዘይት ተገቢውን ዕውቅናና ክብር እንዲያገኝ ግፊት ማድረግ አለበት፡፡ ኅብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ መጨበጥ ብቻ ሳይሆን፣ ምርቱ ያለውን ጠቀሜታ ያገናዘበ ዋጋ ለምርቱ ለመክፈልና ለመጠቀም ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም ኅብረተሰቡ ይህ ድንግል ዘይት በተገቢው ሁኔታ ጥራቱን ጠብቆ የሚመረትበትንና ከሐሰተኛ ምርቶች የሚጠበቅበት ሁኔታ እንዲመቻችለት፣ ተገቢውን ክትትልና ግፊት ማድረግ አለበት፡፡ በተለይ በዚህ ረገድ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ፡፡

5.4.   የወቅቱ የምርት ሒደት ሞዴልና አወዛጋቢነቱ

የምግብ ዘይቶች ሁሉ መነጠር እንዳለባቸው ታሳቢ ያደረገ አንድ ሞዴል ቀርቦ ተግባራዊ ሊደረግ ሲል አወዛጋ ቢሆን ነበር፡፡ ሞዴሉ ለአነስተኛ አምራቾች ሦስት አማራጮችን ይሰጣል፡፡ ይህንን ሞዴል ያቀረቡት ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ማንጠር የግድ ነው የሚለውን የእኛኑ ግትርነት መሠረት አድርገው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የሌሎችን አገሮች ልምድ ኢትዮጵያም እንድትጠቀምበት ማሳየት ይችሉ ነበር፡፡ ሞዴሉም ለማንኛውም አነስተኛ የሚከተለውን ይመስላል፣

. አማራጭ አንድ፣ የራሳቸውን ማንጠሪያ እንዲያቋቁሙና እንዲያነጥሩ፣ ለምሳሌ የጋራ ማንጠሪያ በትብብር ማቋቋም፡፡

. አማራጭ ሁለት፣ ማንጠሪያ ካላቸው ጋር መቀናጀት፣ ይህ ዘይታቸውን ለትልልቅ አምራቾች በማቅረብ እንዲነጠርላቸው ማድረግ ነው፡፡

. አማራጭ ሦስት፣ ማንጠር ካልተቻለ የምግብ ዘይት ዘርፉን ለቆ መውጣት፡፡

. አማራጭ አራት፣ አራተኛውን አማራጭ የያዘው ሞዴል ለ አማራጭም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ድንግል (ኢንጥር ዘይት) እንደ ምርት ዓይነት የሚቀበል ነው፡፡

የምግብ ዘይት ዕሴት ሰንሰለት ማፍጠኛ ፕሮጀክቱ ይህንን ባለሦስት ምርጫ ሞዴል (ሀ) እንደያዘ ቢቀጥልም፣ ባለ አራት አማራጭ ሞዴል (ለ) በአማራጭነት ቀርቦ አሳማኝ ሆኖ ቢያገኙትም የመንግሥት ውሳኔ ነው የተባለውን አወዛጋቢ ሐሳባቸውን እንደ ገና ሊቃኙት አልፈለጉም ነበር፡፡

ሥዕል 2፡ አወዛጋቢው ሞዴል (ሞዴል ሀ) (Sertse et al., 2011) እና አማራጭ ሞዴል (ሞዴል ለ ከጸሐፊው)

ከአዘጋጁ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው eneyew.tadesse@aastu.edu.et ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...